ዋዜማ ራዲዮ፡ የሶማሊያ መንግስት በቅርቡ ለኢትዮጵያ ተላልፎ የተሰጠው የኦጋዴን ብሄራዊ ነፃነት ግንባር (ኦብነግ) አመራር አብዱከሪም ሼክ ሙሴ የአሸባሪ ድርጅት አባል ነው ሲል ወነጀለ።
የሶማሊያ መንግስት ካቢኔ በጉዳዩ ላይ ከህዝብ የደረሰበትን ተቃውሞ ተከትሎ ባደረገው አስቸኳይ ውይይት አብዱልከሪም የሚመራው ድርጅት ኦብነግ ከአልሸባብ ጋር ግንኙነት አለው፣ በቅርቡም ወታደራዊ ጥቃት ለማድረስ ሲዘጋጅ ነበረ ሲል በአሽባሪነት ፈርጆታል።
በተከታታይ ስልጣን ላይ የነበሩ የሀገሪቱ መንግስታት ኦብነግን በመደገፍና መጠለያ በመስጠት ይታወቃሉ። አብዱልከሪም የሶማልያ ዜግነት ያለው መሆኑና ያለፍርድ ለኢትዮጵያ ተላልፎ መሰጠቱ ከፍተኛ ቁጣ ቀስቅሷል።
ኦብነግ የኢትዮጵያን መንግስት በሀይል የሚፋለምና ከ40 አመታት በላይ ዕድሜ ያለው ድርጅት ሲሆን ከ2 ዓመት በፊት አልሸባብ ኦብነግ እስልምናን ያልተቀበለ ድርጅት ነው በሚል ሁለት አመራሮቹን በአደባባይ ረሽኗል።
አሁን የሶማሊያ መንግስት ኦብነግ ከአልሸባብ ጋር ግንኙነት አለው ሲል መክሰሱ ለበርካታ ሶማሊያውያን አልተዋጠላቸውም።
የሶማሊያ ዜግነት ያለውን ግለሰብ አሳልፎ ስለመስጠታቸው የተጠየቁት ባለስልጣናቱ በኢትዮጵያና በሶማሊያ መካከል አሸባሪን አሳልፎ ለመስጠት የሚያስገድድ ስምምነት መኖሩን ጠቅሰዋል።
የቀድሞ የሶማሊያ ባለስልጣናት ግን ከኢትዮጵያ ጋር ይህ አይነቱ ስምምነት ስለመደረጉ እንደማያውቁ ተናግረዋል።
የኦጋዴን ነፃነት ግንባር እንዳስታወቀው የድርጅቱ ማዕከላዊ ኮሚቴ አባልና የወታደራዊ ጉዳዮች ሀላፊ አብዲ ከሪን ሼክ ሙሴን ጋልካዮ ከተማ ቤተሰብ ለመጎብኘት በሄደበት ወቅት በሶማሊያ የፀጥታ ሀይሎች ተይዞ ለኢትዮጵያ መንግስት ተላልፎ መሰጠቱን ገልጿል።
የሞቃዲሾ ነዋሪ የሆነው አብዲከሪን በጦር አውሮፕላን ተጓጉዞ ደብረ ዘይት አየር ማረፊያ መድረሱንም የዋዜማ ምንጮች ያመለክታሉ።
አብዲ ከሪን የተወሰኑ አመታትን በኤርትራ ማሳለፉንና የኢትዮጵያ መንግስት ላለፉት አምስት አመታት በጥብቅ ሲፈልገው የነበረ ነው።
አብዲከሪን ለኦጋዴን ነፃነት ግንባር ቁልፍ የሚባል ሰው ሲሆን በቅርብ አመታት የተደረጉ ወታደራዊ ዘመቻዎችን መምራቱን የድርጅቱ ምንጮች ይናገራሉ።
Average Rating