በአሁኑ ወቅት በኦሮሚያ እና በሶማሌ ክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎች በተቀሰቀሱ ግጭቶች ምክንያት የሰዎች ህይወት ጠፍቷል፤ ከሃምሳ አምስት ሺ በላይ የሚቆጠሩ ዜጎችም ከመኖሪያቸው እንዲፈናቀሉ ተገደዋል።
የኦሮሚያ ክልል መንግሥት፤ የሶማሌ ልዩ ፖሊስን እንዲሁም ሚሊሻዎች ወደ ኦሮሚያ ዘልቀው በመግባት ጥቃት አድርሰዋል ሲል የሚከስ ሲሆን፤ የሶማሌ ክልል በበኩሉ አጥቂዎቹን በኦሮሚያ ክልል የሚደገፉ ናቸው ሲል በኮሚኒኬሽን ቢሮው በኩል አሳውቋል። መወነጃጀሉና የቃላት ምልልሱ መካረር የክልሎቹ መንግስታት ግንኙነት ያለበትን ደረጃ ከማሳበቁም ባለፈ የግጭቶቹን መረር ማለትም አመላካች ነው። ይሁንና በሁለቱ ክልሎች መካከል ውዝግብ፣ ግጭት፣ ሲያልፍም ደም መፋሰስ ሲያጋጥም የአሁኑ የመጀመሪያው አይደለም።
1.አጨቃጫቂ ወሰን
በቆዳ ስፋቱ ከአገሪቱ ቀዳሚውን ስፍራ የሚይዘው የኦሮሚያ ክልል፤ ከሁለተኛው ሰፊ የሶማሌ ክልል ጋር የሚያዋስነው 1410 ኪሜ ድንበር አለው። ይህ ድንበር ግን ክልሎቹ አሁን ያሉበትን ቅርጽ ይዘው ከተመሰረቱበት ጊዜ አንስቶ ውዝግብ አያጣውም። ውዝግቡን ፈትቶ ወሰኖቹን መልክ ለማስያዝ ታስቦም ሕዝበ ውሳኔ ከ400 በሚበልጡ ቀበሌዎች በጥቅምት ወር 1997 ዓ.ም ተደርጓል።
በሕዝበ ውሳኔው መሰረት ከ80 በመቶ በላይ የሚሆኑ ቀበሌዎች በኦሮሚያ አስተዳደር ሥር እንዲጠቃለሉ የተወሰነ ቢሆንም የወሰን ማካለል ሥራው ተግባራዊ ሳይሆን ቆይቷል። ይህም በየጊዜው ለሚነሱ ግጭቶች አባባሽ ምክንያት መሆኑ አልቀረም።
ባለፈው ሚያዝያ ግን የሁለቱም ክልሎች ፕሬዚዳንቶች ሕዝበ ውሳኔውን ተግባራዊ ለማድረግ ያስችላል የተባለ ስምምነት ተፈራርመዋል። ስምምነቱ በተፈረመበት ወቅት የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት ለማ መገርሳ “ትልቅ ድል” መገኘቱን ሲገልፁ፥ የሶማሌ ክልል አቻቸው አብዲ መሃመድ በበኩላቸው “በሁለቱ ወንድማማች ሕዝቦች መካከል ዳግመኛ ግጭት አይኖርም።” ብለው ነበረ።
የኦሮሚያ ክልል ቃል አቀባይ አቶ አዲሱ አረጋም የችግሩ ምንጭ ”የድንበር ጉዳይ እንዳልሆነ የሚያረጋግጥልን፤ ድንበር በማንጋራባቸው አካባቢዎች ጭምር ጥቃት ሲፈፀም የነበረው። የድንበሩን ጉዳይ በ1997 ሕዝበ-ውሳኔ መሰረት ለመፍታት በተደረሰው ስምምነት መሰረት እየሰራን ነው።ሥራውም ሰባ በመቶ በላይ ተጠናቋል።” ሲሉ ሌላ ምክንያት ሊኖር እንደሚችል ይጠቁማሉ።
2.የተፈጥሮ ሃብት ፉክክር
በኢትዮጵያና ኬንያ ድንበር የሚገኙ የኦሮሞ እና የሶማሌ ክልል አርብቶ አደርና ከፊል አርብቶ አድር ሕዝቦችን ግንኙነት ያጠኑት የማኅበረሰባዊ ሥነ-ሰብ ተመራማሪው ፈቃዱ አዱኛ እንደሚሉት ፉክክርና ግጭት በተለይ የቦረና ኦሮሞዎችና የአካባቢው ሶማሌ ጎሳዎች መገለጫዎች ሆነው ቆይተዋል ይላሉ።
ፉክክርና ግጭቶቹ በብዛት ውሃ እና የግጦሽ መሬትን በመሳሰሉ የተፈጥሮ ሃብቶች ተጠቃሚነት ዙርያ የሚያጠነጥኑ ቢሆንም ከቅርብ ጊዜ አንስቶ የብሔር መልክ እየያዙ መምጣታቸው ይወሳል።
በአገሪቱ ፖለቲካዊ አወቃቀር የብሄር ድንበሮች የፖለቲካ ድንበሮች ጭምርም በመሆናቸው፤ በማኅበረሰቦቹ ዘንድ ያለውን የፉክክር መንፈስ ክልላዊ ገፅታ አላብሶታል ሲሉ ይከራከራሉ አቶ ፈቃዱ። ለዚህም በማሳያነት የሚጠቅሱት ከዚህ ቀደም በአንፃራዊነት ሰላማዊ ግንኙነት የነበራቸው የአርሲ ኦሮሞና አጎራባች የሶማሌ ጎሳዎች ደም ወዳፋሰሰ ግጭት መግባታቸውን ነው።
አካባቢዎቹ ለድርቅ ተጋላጭነታቸው ከፍ ያለ መሆኑ በተፈጥሮ ሃብት ፍላጎቶች ላይ ለሚነሱ ቅራኔዎች ተጨማሪ ነዳጅ የሆኑ ይመስላል።
3.የሕዝበ-ውሳኔ ራስ ምታት
ለተመራማሪው ፈቃዱ አዱኛ፤ መንግሥት ለአካባቢዎቹ ወሰን ተኮር ግጭቶች ፖለቲካዊ መፍትሄ ለመስጠት ባደረገው እንቅስቃሴ ሕዝበ-ውሳኔ ማከናወኑ የአካባቢዎቹን ነባራዊ ሁኔታ ያላገናዘበ ነው። የአካባቢው ኗሪዎች በአብዛኛው አርብቶ አደሮች እንደመሆናቸው ከሥፍራ ሥፍራ ይንቀሳቀሳሉ። ይህም ወሰኑን ቁርጥ ባለ ሁኔታ ማስቀመጥን አዳጋች ያደርገዋል።
የህዝበ-ውሳኔው ውጤት በሁለቱ ክልሎች መካከል የተነሳውን ጥያቄ ምላሽ ሰጥቷል ቢባልም የተካሄደበትን ወቅት መሰረት ያደረገ ሌላ ጉዳይ አሁን እንደተነሳ ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ የፖለቲካ ሳይንስ መምህር “ከሶማሌ ክልል በኩል የሚነሳው ጥያቄ ሕዝበ-ውሳኔው የተካሄደበት ወቅት የሶማሌ ክልል የራሱን ግዛት ሊያስጠብቅ በማይችልበት አቅም ላይ በነበረበት ጊዜ በመሆኑ ብዙ ግዛት ተወስዶብኛል የሚሉ ጥያቄዎች እያነሳ ነው።” ይላሉ።
4.ሞትና መፈናቀል
ባለፈው ነሐሴ የተካረሩ ግጭቶችን ያስተናገደው የሚኤሶ አካባቢ ለወትሮውም ለዚህ መሰል ፍጭቶች ባይታወር አይደለም። ሕዝበ ውሳኔን ባስተናገደው የ1997 ዓ.ም በመኢሶና በቦርደዴ አካባቢዎች በአስር ሺህዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን እንዲፈናቀሉ ያስገደዱ ግጭቶች ተከስተዋል ይላል የአይ ዲ ፒ ፕሮጄክት ሪፖርት።
በ2005 ዓ.ም ደግሞ በሞያሌ አካባቢ በተቀሰቀሰ የሁለቱ ብሔር አባላት ግጭት ከ20ሺህ በላይ የሚሆኑ ዜጎች ሸሽተው ኬንያ መግባታቸውን የኬንያ ቀይ መስቀል ማህበር በዚሁ ወቅት አስታውቆ ነበር። በወቅቱ ለግጭቱ መቀስቀስ ምክንያት ተደርጎ የተጠቀሰው በግጦሽ መሬት ይገባኛል ቢሆንም ግጭቶቹ ብሄር ተኮር ይዘት እንዳላቸውም አብሮ ተዘግቧል።
ባለፈው ዓመት ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባደረጉት ንግግር የሚከሰቱት ግጭቶች መንስዔ የብሄር ይዘት አለው ባይሉም፤ በግጦሽ መሬትና በውሃ የተቀሰቀሰ ነውም አላሉም። ከዚያ ይልቅ ለጉዳዩ ቅርበት አላቸው ያሏቸውን የአካባቢውን አስተዳዳሪዎችን ወቅሰዋል።
5.ማኅበረ-ባህላዊ ልዩነቶችና አንድነቶች
የኦሮሞና ሶማሌ ሕዝቦች ከምስራቅ ኩሽ የቋንቋ የዘር ግንድ የሚመዘዙ ሲሆን በኢትዮጵያ ሶማሌዎችና በተለይም እስልምና በገነነባቸው የኦሮሞ አካባቢዎች መካከል መልካም የሚባል ግንኙነት ተመስርቶ መቆየቱን የሚያነሱት አቶ ፈቃዱ፤ ባሌ ውስጥ የሚገኘው የሼክ ሁሴን መስጊድ በሁለቱም ሕዝቦች እንደ ቅዱስ ቦታ መቆጠሩን ያስታውሳሉ።
የሶማሌና የኦሮሞ ሕዝብ አብሮ ከመኖሩ አንፃር በርካታ አንድ የሚያደርጓቸው ነገሮች እንደሉ የሚጠቅሱት የፖለቲካል ሳይንስ መምህሩ፤ ምንም እንኳን እነዚህ ግዛቶች በወሰን ቢከፋፈሉም አሁንም የሁለቱ ህዝቦች የሚንቀሳቀሱባቸው ከተሞች አሉ፤ በማለት የሁለቱ ሕዝቦች አብሮነት እንደማይቋረጥ ይናገራሉ።
Average Rating