- ሁለቱ ክልሎች በሟቾች ብዛት የማይጣጣም መግለጫ ሰጥተዋል
- ከ20 ሺሕ በላይ ዜጎች ተፈናቅለዋል
በኦሮሚያና በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልሎች በተቀሰቀሰው ግጭት የበርካታ ዜጎች ሕይወት መጥፋቱን፣ የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት አስታወቀ፡፡
የጽሕፈት ቤቱ ኃላፊ ሚኒስትር ነገሪ ሌንጮ (ዶ/ር) ዓርብ መስከረም 5 ቀን 2010 ዓ.ም. ጋዜጣዊ መግለጫ ሲሰጡ እንደተናገሩት፣ በሁለቱ ክልሎች መሀል በተቀሰቀሰቀው ግጭት የበርካታ ዜጎች ሕይወት ከመጥፋቱ በተጨማሪ፣ ከሃያ ሺሕ በላይ ዜጎች ከመኖሪያ ቀያቸው ተፈናቅለዋል፡፡ የሞቱት ዜጎች ቁጥር በውል እንደማይታወቅ ሚኒስትሩ ቢገልጹም፣ ሁለቱ ክልሎች ግን የሟቾችን ቁጥር ይፋ አድርገዋል፡፡ የኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል በግጭቱ ምክንያት የሞቱ ሰዎችን ቁጥር ከሃምሳ በላይ ሲያደርሰው፣ የኦሮሚያ ክልል በበኩሉ 18 ብቻ ናቸው ብሏል፡፡
በሁለቱ ክልሎች መካከል ሰሞኑን የተቀሰቀሰው ግጭት ዋነኛ መንስዔ ከወሰን ጋር የተገናኘ ተብሎ አንድም ቀን መግለጫ እንዳልተሰጠ የተናገሩት ሚኒስትሩ፣ ጳጉሜን 3 ቀን 2009 ዓ.ም. በቦረና በኩል በሞያሌና በሌሎች ወረዳዎች የነበረውን ግጭት ለማስቆም የሁለቱ ክልሎች መሪዎች ከፌዴራልና አርብቶ አደር ልማት ጉዳዮች ሚኒስቴር ጋር በመሆን ሲሠሩ እንደነበር ገልጸዋል፡፡ ግጭቱ ከወሰን ጋር የተያያዘ እንዳልነበርም አስረድተዋል፡፡
ባለፈው ሳምንት ማክሰኞ መስከረም 2 ቀን 2010 ዓ.ም. በጭናክሰን አካባቢ በሁለት አመራሮች ላይ የተደረገው ግድያ፣ በአወዳይ ከተማ ሕዝባዊ ግጭት እንዲፈጠር መንስዔ መሆኑን ሚኒስትሩ ገልጸዋል፡፡ በሁለቱ ክልሎች መካከል የተከሰተው ግጭት በወሰን ምክንያት እንዳልሆነ የተናገሩት ሚኒስትሩ፣ ከወሰን ጋር የተያያዘ ቢሆን ኖሮ ግጭቱ በወሰን አካባቢ ብቻ ይሆን እንደነበር ጠቁመዋል፡፡
‹‹በሕዝብ ላይ ጥቃት የሚያደርሱ አካላትን በተመለከተ በኦሮሚያ ክልል በኩል ጥቃት አድራሽ አንደኛ የሶማሌ ክልል ልዩ ፖሊስ፣ ሚሊሻና የሶማሊያ ሪፐብሊክ ወታደሮች ያሉበት እንደሆነ ሲገለጽ ሰምተናል፡፡ እነሱ የገለጹት ትክክል ነው ብለን የገለጽነበት ጊዜ የለም፤›› ብለዋል፡፡ ትክክለኛ መረጃ የያዘው አካል በሕጉ መሠረት ታይቶ ወደፊት የሚገለጽ እንደሚሆን ጠቁመዋል፡፡
‹‹በሁለቱ ክልሎች መካከል በተለያዩ ሚዲያዎች ሲገለጽ እንደነበረው ዜጎቻችን ያለውን ችግር በትክክል እንዲረዱ የማድረግ እንቅስቃሴው እንዳለ ሆኖ፣ አቅጣጫ እንዲስትና ሁከቱ እንዲባባስ የማድረግ ድርጊት ግን ኃላፊነት የጎደለው ተግባር ነው፤›› ብለዋል፡፡
ጠቅላይ ማኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ የሁለቱን ክልሎች ኃላፊዎች በስልክ እንዳነጋገሯቸውና ይኼ ችግር በአስቸኳይ መቆም እንዳለበት እንዳሳሰቧቸው አክለዋል፡፡
በሁለቱ ክልሎች መሀል የተቀሰቀሰውን ግጭት እንዲባባስ የሚያደርጉ ማኅበራዊ ሚዲያዎችም ሆኑ ሌሎች ሚዲያዎች ካሉ፣ መንግሥት እየተከታተለ ዕርምጃ እንደሚወስድ ሚኒስትሩ አስጠንቅቀዋል፡፡
ባለፉት 26 ዓመታት ከወሰን ጋር በተያያዘ ጥያቄ ሲነሳ እንደነበር የጠቆሙት ሚኒስትሩ፣ ይኼንን ችግር ለመፍታት መንግሥት ሲሠራ መቆየቱም ተናግረዋል፡፡
ግጭቱን ለማስቆምም በሁለቱ ክልሎች መካከል የመከላከያ ሠራዊትና የፌዴራል ፖሊስ አባላት የተሰማሩ ቢሆንም፣ እስካለፈው ዓርብ በሁለቱ ክልሎች መሀል ግጭት ነበር ብለዋል፡፡
‹‹የልማታዊ አስተሳሰብ የበላይነቱን ባልያዘበት ነባራዊ ሁኔታ ኪራይ ሰብሳቢነትና ወኪሎቹ የሆኑት ትምክህትና ጠባብነት ሰፊ የመንሸራሸሪያ ምኅዳር ማግኘታቸው የማይቀር በመሆኑ፣ በብሔሮች መካከል ቅራኔ በመፍጥር አንድነታችንን ለማላላት ሁሉንም አቅማቸውን አስተባብረው ሲረባረቡ ማየት የተለመደ ሆኗል፤›› ብለዋል፡፡
በኦሮሚያና በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልሎች መሀል የተቀሰቀሰው ግጭት ከዚህ በላይ ጉዳት እንዳያደርስ ሲባልም፣ የመከላከያ ሠራዊትና የፌዴራል ፖሊስ አባላት በአካባቢው እንዲሰማሩ መደረጉንም አክለው ገልጸዋል፡፡ ይኼንን ችግር ለማስቆም የፌዴራል ፖሊስ አባላት ከክልሎች አመራርና ፀጥታ አካላት ጋር በመሆን ኃላፊነት እንደተሰጠው ተናግረዋል፡፡
በሚወስደው ዕርምጃ የዜጎች ሰብዓዊ መብት እንዳይጣስም የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን አባላት አብረው ሄደው ሥራቸውን እያከናወኑ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
ማንኛቸውም አካላት እርስ በርስ ከመወነጃጀል በመታቀብ ችግሩን በሕጋዊ መንገድ ብቻ ለመፍታት እንዲንቀሳቀሱ ሚኒስትሩ ጥሪ ያቀረቡ ሲሆን፣ በዚህ በኩል ችግር የሚፈጥሩ አካላት ከሕግ ተጠያቂነት እንደማያመልጡ አስጠንቅቀዋል፡፡
ከዚህ ቀደም በወሰን ምክንያት በሁለቱ ክልሎች ግጭት በመቀስቀሱ በርካታ ዜጎች መሞታቸው ይታወሳል፡፡ በሚያዝያ ወር 2009 ዓ.ም. በፌዴራልና አርብቶ አደሮች ጉዳይ ሚኒስቴር አደራዳሪነት ግጭቱን ለማስቆም በሁለቱ ክልሎች ርዕሳነ መስተዳድሮች ስምምነት መፈረሙ አይዘነጋም፡፡ አሁን ደግሞ በተቀሰቀሰ ግጭት በርካታ ዜጎች በመሞታቸው በክልሎቹ ብቻ ሳይሆን፣ በመላ አገሪቱ ሥጋት መፍጠሯ ብዙዎችን እያሳሰበ ነው፡፡
ሚኒስትሩ የቅማንት ሕዝብ የማንነት ጥያቄ ተነስቶባቸው በነበሩ 12 ቀበሌዎች እሑድ መስከረም 7 ቀን 2009 ዓ.ም. ሊካሄድ የነበረው ሕዝበ ውሳኔ፣ በስምንቱ ቀበሌዎች ብቻ እንደሚካሄድም ገልጸዋል፡፡
ሚኒስትሩ በሰጡት መግለጫ ላይ እንደተናገሩት፣ አራቱ ቀበሌዎች ተጨማሪ ውይይት እንደሚያስፈልጋቸው በመግለጻቸውና ጥያቄያቸውም ተቀባይነት በማግኘቱ በቀጣይ እንዲታዩ ተደርጓል፡፡ በአሁኑ ጊዜ በስምንት ቀበሌዎች ብቻ ሕዝበ ውሳኔ ለመስጠት እየተሠራ መሆኑንና በዚህም ከ21 ሺሕ በላይ ዜጎች መመዝገባቸውን ሚኒስትሩ አስረድተዋል፡፡
Average Rating