ባሳለፍነው እሁድ የኦሮሚያና የሶማሌ ክልል ፕሬዝዳንቶች ሰላም እንዲሰፍን እንሰራለን ካሉ በኋላ በምሥራቅ ሐረርጌ ጭናክሰን ወረዳ በተፈፀመ ጥቃት በርካታ ሰዎች ሲሞቱ ሌሎች ቀሰሉ።
ባደረግነው ማጣራት በጭናክሰን ወረዳ ባለፉት ሶስት ቀናት ውስጥ 22 ሰዎች መገደላችውን፣ 35 ሰዎች መቁሰላቸውንና 86 የአርብቶ አደር ቤቶች በእሳት መጋየታቸውን ታውቋል።
የጭናክሰን ወረዳ አስተዳዳሪ የሆኑት አቶ ጀማል ሙሳ ጥቃቱ የተፈጸመው ከሶማሌ ክልል ተሻግረው በመጡ ታጣቂዎች ነው ሲሉ ለቢቢሲ የተናግረዋል።
የኦሮሚያ ክልል ቴሌቪዥን የኦሮሚያ ብሮድካስት ኔትዎርክ ያናገራቸው የወረዳው የፀጥታ ሃላፊ ጥቃቱ የተፈፀው በልዩ ሃይል እንደሆነ ገልፀዋል።
አቶ ጀማል ሙሳ ጨምረው እንደተናገሩት ጥቃቱ ከመቆም ይልቅ እየጨመረ የመጣ ሲሆን የጥቃት ፈጻሚዎቹም ቁጥር ከፍ እያለ መሆኑን ነው።
የሁለቱ ክልል ፕሬዝዳንቶች ሰላም እንዲሰፍን ጥረት እናደርጋለን በማለት ቃል ገብተው የነበረ ቢሆንም ያለው ግጭት እንደቀጠለ ነው።
የኦሮሚያ ብሮድካስት ኔትዎርክ ጋዜጠኛ ከጭናክሰን ወረዳ በጥቃቱ እየተቃጠለ የነበረ ቤት የተመለከተ ሲሆን በጥይት ተመተው የቆሰሉ ሰዎችንም አነጋግሯል።
ጋዜጠኛው ያነገራቸው አንድ አዛውንት እንዳሉት ”እየደረሰብን ያለውን ጉዳት የኦሮሚያ ክልል ሊያስቆምልን ካልቻለ ለተቀረው ዓለም አቤቱታችንን ማሰማት እንፈልጋለን” ሲሉ ተናግረዋል።
ጋዜጠኛው ጥቃቱ በተፈፀመበት አካባቢ በነበረበት ወቅት የተኩስ ድምዕ መስማቱን ለቢቢሲ ተናግሯል።
ከዚህ በተጨማሪ የጤና ባለሙያዎች ግጭቱን በመፍራት ከአካባቢ ስለሸሹ ሶስት ጤና ጣቢያዎች ሙሉ በሙሉ ሥራ እንዳቆሙ ማጣራት ችለናል።
ከሶማሌ ክልል በኩል ያለውን ምላሽ ለማወቅ የደረግነው ተደጋጋሚ ጥረት ሊሳካ አልቻለም።
በሁለቱ ክልሎች መካከል በተከሰተው ግጭት ከአካባቢያቸው የተፈናቀሉ ሰዎች ቁጥር ከ55 ሺ በላይ ደርሷል።
Average Rating