“ሥርዓቱ ይሆናል እንጂ አገር አትበታተንም”
በኦሮሚያ እና በሶማሌ ክልሎች በተቀሰቀሱ ግጭቶች ምክንያት የብዙ ሰዎች ህይወት ጠፍቷል፤ ከ75 ሺህ በላይ የሚሆኑ የኦሮሚያ ተወላጆች አካባቢያቸውን ጥለው መፈናቀል እንዲሁም ለሺህዎች ንብረት መውደምም ምክንያት ሆኗል።
የክልሎቹ መንግሥታት ግን እርስ በርስ መወነጃጀልን መርጠዋል። ምንም እንኳን ይሄ እሰጥ እገባ እየቀለለ የመጣ ቢመስልም ግጭቶቹ እንዳልበረዱም፤ የሚፈናቀልም ሰው ቁጥር እየጨመረ እንደሆነ የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ፅህፈት ቤት ኃላፊ ሚኒስትር ነገሪ ሌንጮ በቅርቡ አሳውቀዋል።
የኢህአዴግ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባልና የድርጅቱ ፅህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሽፈራው ሽጉጤ ለቢቢሲ እንደተናገሩት፤ ማዕከላዊው መንግሥት ችግሩ በተከሰሰበት አካባቢ በፌዴራል አካላት፣ በመከላከያና በፖሊስ ኃይል አማካኝነት ዋና ዋና መንገዶችን በመቆጣጠር ችግሩን አብርዷል። እርሳቸው ይሄንን ቢሉም በክልሎቹ መካከል እስካሁን ግጭቱ ያልተፈታ መሆኑ ለብዙዎች እንቆቅልሽ ነው።
ባስ ሲል በቅርቡ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ አባ ዱላ ገመዳ ከስልጣን ለመልቀቅ ጥያቄ ማቅረባቸውም ግርምት ፈጥሯል። አቶ ሽፈራው ኢህአዴግ ከያዘው የመተካካት ስርዓት ጋር የተያያዘ ነው የሚል ምላሽ ሰጥተዋል። ከመንግሥት የስልጣን ጊዜያቸውን ሳይጨርሱ ልልቀቅ ማለታቸው ያልተለመደ መሆኑንም አቶ ሽፈራው አልደበቁም።
ምንም እንኳን አባ ዱላ ለመልቀቅ የጠየቁበትን ምክንያት ለወደፊቱ እገልፃለሁ ቢሉም፤ በኦሮሚያና በሶማሌ ክልል በተነሳው ግጭትና መፈናቀል ማዕከላዊው መንግሥት የሰጠው አዝጋሚ ምላሽም ቅር እንዳሰኛቸው የቅርብ ሰዎች እየተናገሩ ነው።
አገራዊ ተቃውሞዎች
በተለያዩ የኦሮሚያ አካባቢዎች አገሪቷን ያናወጠ ከፍተኛ ተቃውሞ ተነስቷል። ከዓመት በላይ የዘለቀው ይህ ተቃውሞ የተነሳው ጊንጨ አካባቢ ሲሆን፤ ይሄም የጪልሞ ጫካ ወደ ግል ይዞታ በመዛወሩ የተነሳ ነበር። ይሄም በአገሪቱ ላይ አከራካሪ የሆነውንና ለዘመናት መመለስ ያልተቻለውን ‘መሬት የማን ነው?’ የሚለውን ጥያቄ ከኋላ አንግቦ የተነሳ ነው። በርካታ ገበሬዎች በልማት መነሳት ያመጣቸውንም ቀውሶች ያጋለጠ ነበር።
የአዲስ አበባና የኦሮሚያ ወረዳዎች የተቀናጀ ማስተር ፕላን ሊያመጣቸው የሚችሉ ከፍተኛ መፈናቀሎችን በመቃወምም ብዙዎች ህይወታቸውን አጥተዋል።
ይህ ከመሬት ጋር ተያይዞ የተነሳው ጥያቄ የፖለቲካ ተንታኞች እንደሚሉት ብሄርን መሰረት ያደረገው ፌደራላዊ ሥርዓት ያልመለሳቸው ጥያቄዎች ናቸው።
በተመሳሳይ በአማራ ክልልም ከወልቃይት የማንነት ጥያቄ ጋር ተያይዞ በተቀሰቀሰ ተቃውሞ በርካታ ሰዎች ህይወታቸውን አጥተዋል። ችግሩም እሳካሁን መፍትሄ አልተገኘም የሚሉ ሰዎች ጥያቄውን በማንሳት ላይ ናቸው።
ሥርዓቱ የክልል መንግሥታት ራሳቸውን የሚያስተዳድሩበት፣ የራሳቸውን ተወካዮች የሚመርጡበት፣ የራሳቸውን ቋንቋ የሚናገሩበትን ሥርዓት መመስረት፣ ቀድሞ የነበረውን የዜግነት እሳቤን መቀየር የሚል ቢሆንም የተለያዩ የፖለቲካ ተንታኞች በትክክል ተግባራዊ እንዳልተደረገ ይተቻሉ።
ታዋቂው የፖለቲካ ሳይንስ ምሁርና ተንታኝ ጆን ማርካኪስ “ይሄ ሁሉ ግን የተደረገው ህዝቡን ፀጥ ለማስባል እንጂ ስልጣንን ለማጋራት አልነበረም፤ ፌደራሊዝሙ በኢህአዴግ የተሰላ ጥረት ነው” ይላሉ።
“ስልጣን አሁንም በማዕከላዊው መንግሥት ቁጥጥር ስር ነው፤ ፌደራል መንግሥቱ ስልጣንንም ሆነ ሀብትን በቁጥጥር ስር አድርጎ ለማከፋፈልም ሆነ በጋራ ለመጠቀም ዝግጁ አይደለም። ይኼ አካሄድ ደግሞ ለሥርዓቱ ትልቅ ጠንቅ ነው፡፡ የአንድን አገር ህልውና ለመጠበቅ ኃይል ብቻውን በቂ አይደለም፡፡” በማለት ይጨምራሉ።
ሕዝቦች ራሳቸውን የሚያስተዳድሩበት፤ ስልጣንና ሀብትን የሚጋሩበትን ሥርዓትን ይህ መንግሥት መፍጠር አልቻለም የሚሉት የመድረክ ምክትል ሊቀ-መንበርና የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ሙላቱ ገመቹ ናቸው። “ራስን በራስ የማስተዳደር መብት አልተሰጠም፤ አሁንም ለይምሰል ነው እንጂ ለሥርዓቱ ታማኝ የሆኑ ሰዎች ከላይ በማስቀመጥ በተዘዋዋሪ አሃዳዊ በሆነ መልኩ በጠመንጃ የሚተዳደሩበት ሥርዓት ነው።” ይላሉ።
የዲሞክራሲ እጥረት
የተለያዩ ምሁራን እና የፖለቲካ ተንታኞች የችግሩን ምንጭም ሆነ መፍትሄውን በተለያየ መነፅር ይመለከቱታል።
የቀድሞ የአየር ኃይል ዋና አዛዥ ጀነራል አበበ ተክለሃይማኖት (ጆቤ) “ፈተና የሌለበት ሥርዓት የለም” በማለት በአገሪቷ የተከሰተውን አመፅና ግጭት በአሉታዊነቱ ብቻ አይመለከቱትም። በአገሪቷ የተተገበረው የፌደራሊዝም ሥርዓት ፍሬ ነው ብለው ያምናሉ። ጆን ማርካኪስ ራስን የማስተዳደር ጥያቄና ነፃነትን ከመፈለግ የሚመነጭ እንደሆነ ከሚያነሱት ሃሳብ ጋር ይዛመዳል።
“ኢህአዴግ ‘ትምክህተኞችና ጠባቦች’ እያለ በጠላትነት የሚፈርጃቸው ወገኖች ጊዜና ፋታ እየጠበቁ ጥያቄ ማንሳታቸውን አያቆሙም” ይላሉ። “ችግሩም ያለው ከጠያቂዎቹ አይደለም፤ ከመላሹ እንጂ” በማለት ጨምረው ይናገራሉ።
አቶ ሙላቱም ሆነ ጀኔራል አበበ እንደ መፍትሄ የሚጠቁሙትም ትልቅ ህዝባዊ ውይይትና መነጋገርን ነው።
“ኢህአዴግ የተከሰተው የፖለቲካ ቀውስ መሆኑን አምኖ ካልተቀበለ አገሪቷን ትልቅ ዕድል ያስመልጣታልም” ይላሉ።
እሳቸው እንደሚሉት ጥያቄ እየተነሳ ያለው ኢህኣዴግ በጠላትነት ከሚፈርጃቸው ወገኖች አይደለም። በተቃራኒው ከህዝብ እንጂ። እንደ ምሳሌም የሚያነሱት በአማራ ክልል ሲውለበለብ የተሰተዋለውን አርማ የሌለበት ሰንደቅ ዓላማ “ህዝቡ ነው ያውለበለበው” ይላሉ። በቅርቡም የኦነግን ሰንደቅ አላማ የሚያውለበልቡ የኢሬቻ በአል ታዳሚዎች በኦሮሚያ ክልል ተስተውለዋል።
“እነዚህ ሰንደቅ ዓላማዎች ምን ማለት ናቸው?” ሲሉ ጀኔራሉ ይጠይቃሉ።
“እኩልነትን ያመጣል ተብሎ የታመነበት አዲሱ ሰንደቅ ዓላማ ከ25 ዓመታት በኋላ ይሄን ያህል ተቃውሞ የሚገጥመው ከሆነ፤ አንድም ህዝቡ አልተቀበለውም ወይም የማስረዳት ችግር አለ ማለት ነው” ይላሉ።
ጥያቄው መነሳቱ ተገቢ መሆኑን አምነው።
“የኢህኣዴግ አመራር ጥያቄዎቹን ማፈን እንጂ መመለስ አልቻለም በተቃራኒው አስተዳደራዊና የኃይል እርምጃ መውሰድን መርጧል” ይላሉ።
ቀይ መብራት
የቀድሞው የኢዴፓ ሊቀመንበር አቶ ልደቱ አያሌው በበኩላቸው ቀውሱን ከዚህ በተለየ መንገድ ይረዱታል። አገሪቷ በአንድ ፓርቲ ቁጥጥር ሥር ባለችበት ሁኔታ እንዲህ ዓይነት ቀውስ ተከስቶ የጋራ ነገር እየጠፋ መሄዱ አደገኛነቱ ያመዝናል ይላሉ። “በዚህ ሥርዓት ስር የተለያዩ ፖሊሲ ያላቸው ፓርቲዎች በምርጫ አሸንፈው የተለያዩ ክልሎችን ቢያስተዳድሩ፤ ምን ይውጠን ነበር?” በማለት ስጋታቸውን ይገልፃሉ።
በፖለቲካ ቀውሱ ምክንያት ተቃውሞና አመፅ እየተቀጣጠለ አገሪቷ ወደባሰ ደረጃ እየሄደችም እነደሆነ አቶ ልደቱ ይጠቅሳሉ። ይሄንን ሃሳብ አቶ ሙላቱም የሚጋሩት ሲሆን ሥርዓቱ መውደቅ ብቻ ሳይሆን አገሪቷ ወደበለጠ ማጥ ውስጥ እየገባችም ነው ብለው ያምናሉ።
“ኢትዮጵያዊ ነኝ በሚል የሚታወቀው አማራ፤ ታይቶና ተሰምቶ በማይታወቅ ደረጃ ብሄርተኝነቱ እየጎለበተ መምጣቱ፤ ሁሉም የጋራ አገርን እየዘነጋ ወደ እየራሱ ማየት መጀመሩ ትልቅ ምልክት ነው” ይላሉ አቶ ልደቱ።
አቶ ልደቱ ብሔርን መሰረት ያደረገው ፌደራሊዝም ችግሮቹን አባብሷቸዋል ብለው የሚያምኑ ሲሆን የመገንጠልም ጥያቄዎችም ተጧጡፈዋል ይላሉ።
የዚህ ሥርዓት ሌላኛው ፈተና የተለያዩ ብሔር ተወላጆች በተለያዩ ክልሎች ተንቀሳቅሰው የመስራት እክሎች እያጋጠማቸው እንዲሁም “ከክልላችን ውጡ” በሚሉ መፈክሮች ብዙዎች መፈናቀላቸው አገሪቷ የመበታተን ጥላ እንዳጠላባት ተንታኞች ይናገራሉ።
በተቃራኒው ጀኔራል አበበ ከዚህ በፊት በ1966 እና በ1983 መንግሥት ባልነበረበት ታሪካዊ ቅፅበቶች እንኳን አገሪቷ አለመበተኗንና አሁንም ህዝቡ ውስጥ ኢትዮጵያዊነት እንዳለ ይናገራሉ።
“ሥርዓቱ ይሆናል እንጂ አገር አትበታተንም” ብለዋል።
መፍትሔው ምን ይሆን?
ለተነሱት ከፍተኛ ተቃውሞዎች መንግሥት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በማወጅ እንዲሁም ብዙዎችን በማሰር መልስ የሰጠ ቢሆንም፤ ይህ የኃይል እርምጃ ቀውሱን ከማብረድ ውጭ እንዳልፈታው ቢቢሲ ያነጋገራቸው እነዚህ ተንታኞች ይናገራሉ።
“እንደ ቀድሞዎቹ መንግሥታት ኢሕአዴግም ተመሳሳይ ቀውስ ገጥሞታል፡፡ እነዚህን ጥያቄዎች ከመመለስ ይልቅ እንደ ቀደሙት መንግሥታት ችግሮቹን ለመፍታት ሠራዊቱን ማሳተፍን መርጧል” በማለት ጆን ማርካኪስ ይናገራሉ።
አቶ ሙላቱ እንደ መፍትሄ የሚጠቁሙትም እውነተኛ ፌደራሊዝምን መፍጠር፣ ህዝቡ የፈለገውን እንዲመርጥ መፍቀድ፣ የመናገርና የመፃፍ ነፃነትን ማክበር፣ የፖለቲካ እስረኞችን መፍታት እንዲሁም የአንድ ፓርቲ የበላይነት የሚያበቃበትን ሥርዓት መዘርጋት ያስፈልጋል ብለዋል።
አቶ ልደቱ በበኩላቸው ስርዓቱ ራሱን መፈተሽ እንዳለበትና አሁንም አገራዊ ውይይት እንደሚያስፈልግ አፅንኦት ሰጥተዋል።
“መንግሥት ወዶና ፈቅዶ መዋቅራዊ ለውጥ ካላመጣ፤ በኃይል ተገዶ ለውጥ መምጣቱ አይቀርም” ብለዋል።
Average Rating