www.maledatimes.com “የሰንደቅ ዓላማና አርማ ጉዳይ ለህዝብ ውይይት አልቀረበም” ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ (አዲስ አድማስ) - MALEDA TIMES
Loading...
You are here:  Home  >  Ethiopia  >  Current Article

“የሰንደቅ ዓላማና አርማ ጉዳይ ለህዝብ ውይይት አልቀረበም” ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ (አዲስ አድማስ)

By   /   October 15, 2017  /   Comments Off on “የሰንደቅ ዓላማና አርማ ጉዳይ ለህዝብ ውይይት አልቀረበም” ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ (አዲስ አድማስ)

    Print       Email
0 0
Read Time:8 Minute, 10 Second

ከአዲስ አድማስ የተወሰደ

ህገ መንግስቱን ከማርቀቅ አንስቶ እስከ ማፅደቅ በነበረው ሂደት ወሳኝ ሚና የነበራቸው የቀድሞ የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ፤ የሰነድ ማስረጃዎችን በመንተራስ ስለ ህገ መንግስቱና የጸደቀበትን ሂደት መቼም ቢሆን ከማስረዳት ሰልችተውና ቦዝነው አያውቁም፡፡ የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ በሰንደቅ ዓላማ ዙሪያ አሁን ለነገሰው አለመግባባት መንስኤው ምን እንደሆነና መፍትሄውን እንዲሁም ተያያዥ ርዕሰ ጉዳዮችን አንስቶ አነጋግሯቸዋል፡፡ ከዶ/ር ነጋሶ ገዳዳ ጋር የተደረገውን ቃለ ምልልስ እንዲህ አጠናቅረነዋል፡-

የቀድሞ የኢትዮጲያ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ (ምንጭ፦ አዲስ አድማስ)
***አሁን በሥራ ላይ ያለው ብሔራዊ ሰንደቅ ዓላማ እንዴት ነበር በህገ መንግስቱ የተካተተው ?

በመጀመሪያ በህገ መንግስቱ መካተት ያለባቸው ጉዳዮች ብለን፣ ረቂቅ ሃሳቦችንና ጉዳዮችን ሰብስበን በዝርዝር አሰፈርን፡፡ በጥያቄ መልክ 73 ጉዳዮችን ነው በዝርዝር ያስቀመጥነው፡፡ እነዚህን 73 ጥያቄዎች ደግሞ ቅርፅ ያስያዙልን ኤክስፐርቶች (ባለሙያዎች) ነበሩ፡፡ ጥያቄዎቹ ተዘርዝረው የነበረው በመጠይቅ መልክ ሲሆን “ድጋፍ”፣ “ተቃውሞ” በሚል ተለይተው ነው፣ የህዝብ አስተያየት የተሰበሰበባቸው፡፡ የተቃውሞና ድጋፍ ውጤቱ የተሰላውም በመቶኛ ነበር፡፡

እስቲ ለምሳሌ ያህል ይጥቀሱልን— ?

ለምሳሌ አጨቃጫቂው የህገ መንግስቱ አንቀፅ 39 ማለትም፣ የብሔር ብሔረሰቦች መብት እስከ መገንጠልን የሚፈቅደው በመጠይቅ ዝርዝሩ ተካትቶ ነበር፡፡ በዝርዝር ጉዳዮች ላይ ደግሞ በተመረጡ 23 ሺህ ቀበሌዎች ላይ ነው የህዝብ ውይይት የተደረገው፡፡ እኔ ለምሳሌ ደምቢዶሎ ላይ አወያይቻለሁ፡፡ ደምቢዶሎ ትልቅ ከተማ ነው። ህዝቡ ከ50 ሺህ አያንስም ግን እኔ ያወያየኋቸው ከ200 አይበልጡም፡፡ በዚህ አይነት ነው ውይይቶች የተካሄዱት፡፡

በዚህ መሰረት ለምሳሌ አንቀፅ 39 (የብሔር ብሔረሰቦች መብት እስከ መገንጠል) ላይ በክልል አንድ (ትግራይ) መቶ በመቶ ድጋፍ አግኝቷል። በክልል ሁለት (አፋር) ደግሞ ይህ አንቀፅ 98 በመቶ ድጋፍ አግኝቷል፡፡ በክልል 3 (አማራ ክልል) 89 በመቶ ድጋፍ አግኝቷል፡፡ ክልል 4 (ኦሮሚያ ላይ) 97 በመቶ ድጋፍ አኝቷል፡፡ ክልል 5 (ሶማሌ) 72 በመቶ ድጋፍ አግኝቷል፡፡ ክልል 6 (ቤኒሻንጉል ጉሙዝ) 88 በመቶ ነበር ድጋፍ ያገኘው፡፡ ክልል 12 (ጋምቤላ) ደግሞ 59 በመቶ ድጋፍ አግኝቷል፡፡

በዚህ መንገድ ነው በጉዳዮቹ ላይ ከህዝብ ሃሳብ የተሰበሰበውና ህገ መንግስቱ ውስጥ የሚካተቱ አንቀፆችን በባለሙያዎች እንዲቀረፁ ያስደረግነው። እኔ እስከማስታውሰው ድረስ፣ ይሄ ሁሉ የረቂቅ ሂደት ሲከናወን የሰንደቅ አላማ ጉዳይ አልተነሳም ነበር፡፡ ትልቁ ጥያቄ የነበረው ሀገሪቱ ፌደራሊዝም ያስፈልጋታል አያስፈልጋትም የሚለው ነበር እንጂ የሰንደቅ አላማ ጉዳይ እንደ ሌሎቹ አንቀፆች የድጋፍና የተቃውሞ ድምፅ ከህዝብ አልተሰበሰበበትም፤ ለህዝብ ውይይትም አልቀረበም ነበር፡፡ ኮሚሽኑ የሰንደቅ አላማን ጉዳይ ለህዝብ ውይይት አላቀረበም።

ለምንድን ነው የሰንደቅ ዓላማ ጉዳይ ለህዝብ ውይይት ያልቀረበው?

በወቅቱ ዋናው ትኩረት፣ የሀገሪቱ ስርአት ፌደራል ይሁን አይሁን የሚለውና የብሔር ብሔረሰቦች መብት ጉዳይ ነበር፡፡ ለዚህ ይመስለኛል የሰንደቅ ዓላማ ጉዳይ ያን ያህል ትኩረት ያላገኘው። አስቀድሜ እንዳልኩት፣ ትኩረቱ የፌደራሊዝም ጉዳይ ላይ ነበር፡፡ ፌደራል ይሁን አይሁን በሚለው ላይ ከክልሎች (ከህዝብ) የተሰበሰቡ አስተያየቶች የመቶኛ ስሌትን ስንመለከት ደግሞ፤ ክልል አንድ (ትግራይ) 99 በመቶ ፌደራሊዝም ይሁን የሚለውን ሲደግፍ፣ ክልል 2 (አፋር) 97 በመቶ፣ ክልል 3 (አማራ) 92 በመቶ፣ ክልል 4 (ኦሮሚያ) 95 በመቶ፣ ክልል 5 (ሶማሌ) 65 በመቶ፣ ክልል 6 (ቤኒሻንጉል ጉሙዝ) 60 በመቶ ደግፎታል፡፡ ክልል 12 (ጋምቤላ) 84 በመቶ፣ ክልል 13 (በወቅቱ ሃረሪ ይመስለኛል) 97 በመቶ፣ ክልል 14 (አዲስ አበባ) 93 በመቶ ፌደራሊዝሙን ሲመርጡ፣ ድሬደዋ ላይ 11 በመቶ የሚሆነው ብቻ ነበር የመረጠው፡፡ ትንሹ ቁጥር የድሬደዋ ነው፡፡ ከዚያ ውጪ እኔ ዘንድ ያሉ ሰነዶች፣ በወቅቱ አንዳንድ ያልተወያዩ ክልሎች እንዳሉም ያመላክታል፡፡

የሰንደቅ ዓላማው ጉዳይ እንዴት በህገ መንግስቱ ላይ ተደነገገ ታዲያ?

አርቃቂ ኮሚሽኑ የሰንደቅ ዓላማ ጉዳይ መግባት አለበት ብሎ በራሱ አስገብቶት ነው፡፡ ኮሚሽኑ በእንዲህ መልኩ የሰንደቅ አላማውን ጉዳይ በአንቀፅ 3 አስቀምጦ፣ ከየክልሉ ለተውጣጡትና የህገ መንግስት ጉባኤ አባላት አቅርቦ ነበር፡፡ በዚህ አንቀፅ ስር ሶስት ንኡስ አንቀፆች አሉ፡፡ የአርማ ጉዳይን፣ የክልሎች ሰንደቅ አላማን የተመለከቱ ናቸው፡፡ በጉባኤው በዚህ ጉዳይ ላይ ብዙም ክርክር አልተካሄደም ነበር፡፡ በጉዳዩ ላይ ውይይት የተደረገው፣ ለሁለት ቀናት ማለትም፣ ጥቅምት 29 እና 30፣ 1987 ዓ.ም የነበረ ሲሆን በሰንደቅ ዓላማው ጉዳይ ሃሳባቸውን የሰጡ ሰዎች 37 ብቻ ነበሩ፡፡ ሰንደቅ ዓላማውን በተመለከተ የቀረበውን ረቂቅ ድንጋጌ፣ 513 የጉባኤው አባላት ድጋፍ ሲሰጡበት፣ በ4 ተቃውሞና በ5 ድምፀ ተአቅቦ ነው ፀድቆ፣ የህገ መንግስቱ አንቀፅ 3 በመሆን የተደነገገው፡፡

በወቅቱ የአርማው መቀመጥ ጉዳይ ላይ የቀረበ ጠንካራ ተቃውሞ አልነበረም?

ብዙም አልነበረም፡፡ አቶ ግርማ ብሩ (አሁን አምባሳደር) ብቻ ነበር “የአርማና የባንዲራ ልዩነት ምንድን ነው?” የሚል ጥያቄ ያቀረበው እንጂ ብዙም ጠንካራ ክርክርና ጥያቄ አልተነሳም፡፡ ሻለቃ አድማሴም እንዲሁ ተቃውሞ አቅርበው ነበር፡፡ ከክልል 5 (ሶማሌ) የተወከሉት አቶ አሊ አብዱ፤ ሶስቱ ቀለማትና አርማው እንዳለ ሆኖ፣ “ነጭ” ቀለም ይጨመርበት የሚል ሃሳብ አቅርበው ነበር፡፡ ከአፋርም እንዲሁ ነጭ ቀለም ይጨመርበት የሚል ሀሳብ ተሰንዝሮ ነበር፡፡ በዚህ የአርማ መጨመር ጉዳይ ላይ በተሰጠው የጉባኤው አባላት ድምፅ መሰረት፤ 517 ሰዎች አርማ መጨመር አለበት ሲሉ፣ 4 ተቃውሞ እንዲሁም 4 ድምፀ ተአቅቦ አድርገው ነበር፡፡

የክልሎች ሰንደቅ አላማን በተመለከተስ — የተነሱ ሃሳቦችና ክርክሮች ነበሩ?

አሁን በህገ መንግስቱ አንቀፅ 3 ንኡስ አንቀፅ 3 ስር ተደንግጎ የሚገኘውና “የፌደራሉ አባሎች የየራሳቸው ሰንደቅ አላማና አርማ ሊኖራቸው ይችላል” የሚለውን በተመለከተ፣ ብዙም የተቃወመ አልነበረም፡፡ ነገር ግን “ብቻውን የሚውለበለብ ሳይሆን ከፌደራሉ ጋር ጎን ለጎን ነው የሚውለው” በሚለው ላይ የተወሰኑ ሃሳቦች ተሰንዝረው ነበር፡፡ በዚህ ጎን ለጎን መውለብለብ አለባቸው በሚለው ጉዳይ ላይ በተሰጠ ድምፅ፡- ድጋፍ 5፣ ተቃውሞ (ጎን ለጎን መሰቀል አያስፈልግም ያሉ) ደግሞ 517 ነበሩ፡፡ ድምፀ ተአቅቦ ያደረጉ 8 ነበሩ፡፡

አሁን ግን ከፌደራሉ ጎን ለጎን መሆን አለበት የሚል መመሪያ ወጥቷል …. ይሄ እንግዲህ በህገ መንግስቱ ያልተወሰነ፣ ነገር ግን በመመሪያ የወጣ ይመስለኛል፡፡

በፌደራሉ ሰንደቅ ዓላማ ላይ የቀረቡ ሌሎች ሃሳቦችስ ነበሩ?

እንግዲህ ይሄ አረንጓዴ፣ ቢጫ፣ ቀይ ቀለማት በዓለም ላይ የታወቅንበት፣ የነፃነት አርማም ስለሆነ መቀየር አያስፈልግም፤ ነገር ግን በመሃሉ የሃይማኖት፣ የብሔር ብሔረሰቦች እኩልነትን የሚወክል አርማ የግድ መኖር አለበት—የሚል ሃሳብ ነው በስፋት የተሰነዘረው፡፡

በተለይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በሠንደቅ ዓላማ ጉዳይ ከፍተኛ አለመግባባትና ልዩነት እየተፈጠረ ነው፡፡ ለዚህ ምክንያቱ ምንድን ነው ብለው ይገምታሉ?

ቀደም ብሎ እኔ እንደማውቀው፣ የኢህአዴግ ስብሰባዎች ካልሆኑ በስተቀር ብዙ ጊዜ ህዝቡ ይዞ የሚወጣው ሌጣውን ነበር፡፡ በተለይ በሰሜኑ የሃገሪቱ ክፍል አካባቢ በተለይ ኮከቡ ያለበትን ሠንደቅ ዓላማ ተቃውሞ እንደሚቀርብበት በሚገባ የተመለከትኩት፣ በእነዚህ ሁለት ዓመታት (2008 እና 2009) ጊዜ ውስጥ በተፈጠሩ ህዝባዊ ተቃውሞዎች ላይ ነው፡፡ በተቃውሞዎቹ በግልፅ በባለኮከቡ ሠንደቅ ዓላማ ያለው ተቃውሞ በአብዛኛው ታይቷል፡፡ ተቃዋሚ ፓርቲዎችም ይሄን ሰንደቅ ዓላማ ይቃወማሉ፡፡ በኦሮሚያ በኩል የሚታየው ተቃውሞ ደግሞ ከማንነትና ከማንነት መለያ ጋርም የተያያዘ ነው የሚመስለው፡፡ ለምሳሌ በኢሬቻ በዓል ላይ ሁለት አይነት ነው የሚታይ የነበረው፡፡ የኦነግ ደጋፊዎች የኦነግን መለያ ባንዲራ ሲያውለበልቡ ነበር፣ በሌላ በኩል የአባገዳዎች ባንዲራም ታይቷል፡፡ የክልሉ ባንዲራም ራሱን ችሎ ነበር፡፡
ስለዚህ አሁን በኦሮሚያ ያለው ሶስት አይነት ባንዲራ ነው ማለት ነው …

እኔ የአባገዳዎች ባንዲራ ማለትም ጥቁር፣ ቀይ እና ነጭ ቀለማት በተከታታይ ያሉበት ባንዲራ እንዴት መጣ ብዬ ሽማግሌዎችን ለመጠየቅ ሞክሬ ያገኘሁት መረዳት አለ፡፡ ይህ ባንዲራ በሁለት ጎሳዎች (አካላት) ጦርነት መካከል በሠላም ለማለፍ የሚያሣዩት ምልክት ነበር፡፡ ከላይ ጥቁር ቀለም የሆነው በገዳ ስርአት ሽማግሌዎችን ይወክላል፤ ከአባገዳ ጀምሮ ያሉትን ይወክላል፡፡ ቀዩ ደግሞ እድሜያቸው ከ18-40 የሆኑ ወጣቶችን ይወክላል። ወጣትነት ትኩስ ሃይል መሆኑን ለማሳየት ነው፤ የወጣትነት እድሜ ስራ የሚሰራበት፣ ጦርነት የሚሳተፉበት እድሜ ነው፡፡ ነጩ ቀለም ደግሞ ህፃናትን ይወክላል፡፡ ህፃናት ገና ከፈጣሪ ስለመጡ ንጹሐን ናቸው የሚል ትርጉም አለው፡፡ በኦሮሞ ባህል ህፃናት እስከ 8 ዓመት እድሜያቸው በፆታ አይለዩም፡፡ ወንዱም ሴቱም ተመሣሣይ ፀጉር፣ ተመሣሣይ አለባበስ ነው የሚኖራቸው፡፡

የብዙ ሰዎችን ፍላጎት ስናይ፣ በክልሉ ካሉ ሶስት አይነት ባንዲራዎች የሚቀበሉት፣ የአባ ገዳዎቹን ይመስላል፤ ግን የህዝቡን ስሜት ህዝበ ውሣኔ ባልተካሄደበት ሁኔታ ማወቅ አይቻልም። የፌደራሉን ባንዲራ ያለመቀበል ስሜት የሚታየውም ከዚህ አንፃር ይመስለኛል፡፡ የፌዴራል ስርአት የኛን ጥያቄ ስላልመለሰ፣ የፌደራል ሠንደቅ አላማ አይወክለንም የሚል ስሜት ያለ ይመስላል፡፡

ታዲያ እንዴት ነው በአንድ አገራዊ ሠንደቅ ዓላማ መስማማትና መግባባት የሚቻለው?

አስቀድሜ እንዳልኩት፣ ይህ አሁን መመሪያ ወጥቶለት በግድ ሊተገበር በታሠበው ሠንደቅ ዓላማና አርማ ላይ ህዝቡ ውይይት አላደረገበትም። በሌላ በኩል ሁሉም የፖለቲካ ሃይሎች በእኩል በሂደቱ አልተሣተፉም፡፡ ኢህአፓ፣ መኢሶን፣ ኦነግ፣ ኢሠፓ ሌሎችም በዚህ ሂደት አልተሣተፉም። እነዚህ ኢትዮጵያውን ናቸው፣ ደጋፊዎች አሏቸው፤ ነገር ግን በሠንደቅ ዓላማው ጉዳይ ውይይት አላደረጉም፡፡ በህገ መንግስቱ ላይም እንዲሁ። በሌላ በኩል፤ በረቂቅ ህገ መንግስቱ ላይም ሆነ በፀደቀው ህገ መንግስት ላይ ህዝቡ የራሱ ፍላጎት ስለመካተቱ የሚያንፀባርቅበት ህዝበ ውሣኔ አልተካሄደም፡፡ እንዳለ ወደ ህዝቡ ነው ፀድቆ የወረደው፡፡ የሠንደቅ ዓላማው ሆነ ሌሎች ችግሮች የሚመነጩት፣ አንደኛው ከዚህ አንፃር ነው፡፡ ህገ መንግስቱ ላይ ህዝበ ውሣኔ ካልተካሄደበት ስርአቱ ወይም ህገ መንግስቱ በህዝቡ ተቀባይነት እንዳለው ማረጋገጫ ማቅረብ አይቻለውም ማለት ነው፡፡

አሁንም የሚሻለው በህገ መንግስቱም ሆነ በሠንደቅ አላማው ጉዳይ ላይ የማሻሻያ ሃሣቦች ካሉ፣ ማሻሻያ ይደረግ የሚሉ አካላት ፊርማ አሠባስበው ቢያቀርቡና፣ ጉባኤ ተደርጎ፣ ለህዝብ ውሳኔ ቢቀርብ ነው፡፡ ሁነኛ መፍትሄ የሚሆነው ህዝበ ውሣኔ ማካሄድ ነው፡፡

በአሁኑ ወቅት በአዋሳኝ ድንበሮች እየተፈጠሩ ያሉ ግጭቶችና አለመግባባቶች መንስኤያቸው ምንድን ነው?

ችግር የተፈጠረው የፌደራል ስርአት መርህን ካለማክበር ነው፡፡ ሁሉም ብሔር ብሔረሰቦች ራሳቸውን በራሳቸው የማስተዳደር መብት በህገ መንግስቱ ተሰጥቷል፡፡ ይሄ ባለበት ሁኔታ ደግሞ በጋራ በሚዋሰኑበት ድንበራቸው ሊከተሉት የሚገባ መርህ አለ፡፡ የጋራ አስተዳደርና የግል አስተዳደር የሚባል መርህም በህገ መንግስቱ ተቀምጧል፡፡ ይሄን መርህ ተግባራዊ ማድረግ አለመቻል ነው አንዱ ችግር፡፡

የዲሞክራሲ ጥያቄም አለ፡፡ ህገ መንግስቱን የሚቀበሉ የፖለቲካ ድርጅቶች እስካሉ ድረስ የእነዚህ ድርጅቶች በማናቸውም መልኩ በምርጫ ተፎካክረው አስተዳደር መሆን የሚችሉበት ሁኔታ ካልተፈጠረ በስተቀር የፌዴራል ስርአቱ ችግር ላይ ይወድቃል። አጋር ድርጅቶች የሚያስተዳድሩት ክልልም ሆነ ኢህአዴግ በሚያስተዳድሯቸው ክልሎች፣ በነፃ ምርጫ ተወዳድሮ፣ የክልል አስተዳዳሪነት ስልጣን የሚያዝበት ሁኔታ እስካልተፈጠረና የገዥው ፓርቲ፤ ”የእኔ ፕሮግራም ብቻ ነው ተግባራዊ መደረግ ያለበት” የሚል አመለካከት ካልቀረ በስተቀር ችግሩ ሊፈታ አይችልም፡፡

በስፋት የሚታየው ድንበርን አስታኮ የሚፈጠር ችግር በህዝበ ውሳኔ እንዲፈታ ነው በመርህ ደረጃ የተቀመጠው፡፡ በዚህ መሠረት በሁሉም ቦታዎች እልባት የተሰጠ አይመስለኝም፡፡ ህዝበ ውሣኔ ቢደረግም ተግባራዊ ማካለል አለማድረግ ሌላው የግጭት መንስኤ ነው፡፡

አሁን መፍትሄው ምንድነው?

መፍትሄው ዲሞክራሲን ማስፋት፣ በህገ መንግስቱ የተቀመጡ መርሆችን መተግበር ነው። ህዝበ ውሣኔ የተደረገባቸውን ጉዳዮችም በጊዜ መደምደም ያስፈልጋል፡፡ እነዚህ በጊዜ ካልተመለሱ የፌደራል ስርአቱ ጥያቄ ውስጥ ይገባል፡፡

ምናልባት ከእርስዎ በኋላ በይፋ ለህዝብ አሳውቆ ሥልጣንን በመልቀቅ ረገድ አፈ ጉባኤ አባ ዱላ ገመዳ ሁለተኛው የመንግስት ከፍተኛ ኃላፊ ሳይሆኑ አይቀሩም፡፡ የእሳቸው በዚህ ወቅት ከሥልጣን መልቀቅ አንደምታው ምን ሊሆን ይችላል ?

በዝርዝር ለመናገር ይከብዳል፡፡ ምክንያቱም እሳቸው ማብራሪያ አልሰጡበትም፡፡ በውስጥ ያሉ ሁኔታዎችንም ማወቅ ባልተቻለበት ሁኔታ ብዙ መናገር አይቻልም፡፡

የእሳቸው ከስልጣን መልቀቅ ለኢህአዴግ ወይም ለመንግሥት ብዙ የሚያጎድሉበት ይመስልዎታል?

ኦህዴድን ከመሠረቱት መካከል ዋናው ሰው ናቸው፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ኢህአዴግ 1993 ላይ በተንገዳገደ ጊዜ ከታደጉት ሰዎች አንዱ ናቸው። ጦርነቱንም ከመሩት አንዱ ቁልፍ ሰው ናቸው፡፡ የኦሮሚያን አስተዳደር ከኦነግ ጋር ሆነው ከወሰኑ የኦህዴድ ሰዎች ዋነኛው ናቸው፡፡ በኋላ ላይም ኦነግ ከኦሮሚያ እንዲወጣ በማድረግ በኩልም ቁልፍ ሰው ናቸው፡፡ በኢህአዴግ ውስጥ በ1993 መከፋፈል በመጣ ጊዜ የእነ አቶ መለስን ቡድን ከታደጉት አንዱ ቀልፍ ሰው ናቸው፡፡ እስከ 1993 ድረስ ወታደር ነበሩ፡፡ ሜጄር ጀነራል ነበሩ፡፡ ወደ ሲቪል የመጡበት አካሄድም ትክክልና ህጋዊ አልነበረም፡፡ ለኔ እስካሁን ጀነራል ናቸው እንጂ ሲቪል አይደሉም፡፡ ምክንያቱም የጀነራልነት ማዕረጉን የሠጠሁት እኔ ነኝ፤ ማዕረጉንም ሊያነሳ የሚችለው ፕሬዚዳንቱ ነው፡፡ ያ ማለት እኔ ነበርኩ ማንሳት የነበረብኝ፡፡

በወቅቱ ጉዳዩ ለእርስዎ አልቀረበም ነበር?

ፈፅሞ አልቀረበም፡፡ በዚያን ጊዜ የኢህአዴግ ማዕከላዊ ኮሚቴና ስራ አስፈፃሚም በጉዳዩ ላይ አልተወያየም፡፡ ይሄ የተደረገው በጠቅላይ ሚኒስትሩና በተወሰኑ ሰዎች ሊሆን ይችላል እንጂ በድርጅቱ ደረጃ በኢህአዴግም ሆነ በኦህዴድ ውስጥ ውይይት አልተደረገበትም፡፡ ነገር ግን ሰውየው የእነ አቶ መለስን ቡድን በመታደግ ጥሩ ሚና ነበራቸው። ከዚህ ባሻገር በፊንፌኔ ዙሪያ ኦሮሚያ ልዩ ዞንን በማቋቋም፣ በአዲስ አበባ የኦሮሞ ባህል ማዕከልን በማቋቋምም ወሳኝ ሚና ነበራቸው፡፡ የኦሮሚያ ዋና ከተማን ወደ አዲስ አበባ በማምጣትም ይታወቃሉ።

ከስልጣን ለመልቀቃቸው ምክንያቱ ምን ሊሆን ይችላል?

እኔ እንደሚመስለኝ የሶማሊያና ኦሮሚያ ግጭት ጉዳይ ብቻ አይደለም፡፡ እንደሰማሁት ከሆነ በአጠቃላይ በአካሄዶች አለመደሰታቸውና የህዝቡ ቅሬታ በአግባቡና በታሰበው መንገድ እየተፈታ አይደለም የሚል ቅሬታም እንዳላቸው ነው፡፡ ስለዚህ የግጭቱ ጉዳይ ብቻ አይመስለኝም፡፡ በኢህአዴግ ውስጥ ችግር እንዳለ በሚገባ የሚያመላክት ነው፡፡

*****

ምንጭ፦ አዲስ አድማስ

Happy
Happy
0 %
Sad
Sad
0 %
Excited
Excited
0 %
Sleepy
Sleepy
0 %
Angry
Angry
0 %
Surprise
Surprise
0 %
    Print       Email
  • Published: 7 years ago on October 15, 2017
  • By:
  • Last Modified: October 15, 2017 @ 10:49 am
  • Filed Under: Ethiopia

Average Rating

5 Star
0%
4 Star
0%
3 Star
0%
2 Star
0%
1 Star
0%
<"Without the support of our readers, the Maleda Times website would not exist in its present form">

You might also like...

በሰሜን ሸዋ ዞን ኤፍራታ እና ግድም ወረዳ መከላከያ ከአማራው ማህበረሰብ እና ከፋኖ ጋር ጦርነት ገጥሟል

Read More →

This site is protected by wp-copyrightpro.com

Skip to toolbar