መንግስት ትኩረት ሰጥቸዋለሁ ለሚለው “የትምህርት ጥራት” በተለይም “የከፍተኛ ትምህርት ጥራት” የመምህራን ልማት ዋና የትኩረት አቅጣጫ እንደሆነ በተለያዩ ጊዚያት ሲለፍፍ ቆይቷል። ይህን ለማሳካት የከፍተኛ ት/ት ተቋማት መምህራን የትምህርት ደረጃ፤ 0% የመጀመሪያ ዲግሪ፣ 75% የሁለተኛ ዲግሪ እና 25% የሶስተኛ ዲግሪ እንዲሆን እየሰራ መሆኑን በተደጋጋሚ መግለፁ ይታወሳል፡፡ የትምህርት ሚኒስቴር አመታዊ እቅድና ሪፖርቶች ይህን ያመለክታሉ። በዚህ መሠረት፣ የት/ት ሚኒስቴር የመምህራን ልማት እቅዱን ለማሳካት በሃገር ውስጥና በውጭ ሀገራት መምህራንን ልኮ በማስተማር ላይ ይገኛል፡፡
የትምህርት ሚኒስቴር መምህራኑን ለውጪ የትምህርት ዕድል ከሚልክባቸው ውስጥ ህንድ (India) በግንባር ቀደምትነት ትጠቀሳለች፡፡ በአሁን ሰዓት ወደ 1000 የሚጠጉ የኢትዮጲያ መምህራን የሁለተኛና ሶስተኛ ድግሪ ትምህርታቸውን በህንድ ሀገር በመከታተል ላይ ይገኛሉ፡፡ ከቅርብ ግዜ ወዲህ ግን እነዚህ መምህራን በከፍተኛ ችግር ውስጥ ይገኛሉ፡፡ መምህራኑ በየወሩ ይከፈላቸው የነበረው 350 የአሜሪካ ዶላር በመቋረጡ (በመዘግየቱ) ምክንያት በሰው ሀገር የሚበሉት አጥተው፣ የመኖሪያ ቤት ኪራይ መክፈል ተስኗቸዋል፡፡
በህንድ ሀገር ትምህታቸውን በመከታተል ላይ የሚገኙ መምህራን የመኖሪያ አበል ክፍያቸውን በየሶስት ወሩ ሲከፈላቸው ነበር፡፡ በኢትዮጵያ ኢምባሲ በተዘጋጀ የትምህርትና ስልጠና አገልግሎት አሰጣጥ መመሪያ ነሐሴ 2008 ዓ.ም 1.2.3 (መ) መሰረት ተማሪዎቹ የመኖሪያ አበል ክፍያቸውን ማግኘት የነበረባቸው ወሩ በገባ እስከ 10ኛው ቀን እንደሆነ ይደነግጋል። ይህም አቆጣጠር በፈረንጆች አቆጣጠር እንደመሆኑ በጥቅምት 2017 መጀመሪያ ላይ መከፈል የነበረበት ክፍያ እስካሁን ድረስ አልተከፈላቸውም፡፡
መምህራኑ በህንድ የሚገኘውን የኢትዮጵያ ኢምባሲ በስልክ፣ በኢሜልና በተለያዩ ዘዴዎች ከትምህርት አታሼው እስከ አምባሳደሩ ድረስ ለማናጋገር ሞክረዋል፡፡ ሆኖም ግን፣ የኢትዮጵያ ኢምባሲው ሃላፊዎች “ትምህርት ሚንስቴርን ጠይቁ እኛ ስንጠይቅ ዶላር የለም ትብለናል” የሚል ምላሽ እንደተሰጣቸው ይናገራሉ፡፡ ከዚህ በተጨማሪ፣ “ካልፈለጋችሁ ትምህርታችሁን አቋርጣችሁ ወደ ሀገራችሁ መመለስ ትችላላችሁ” የሚል ሃላፊነት የጎደለው ምላሽ መሰጠቱን አማርረዋል።
“ትምህርት ሚንስቴርን ጠይቁ እኛ ስንጠይቅ ዶላር የለም ትብለናል” በህንድ ትምህርታቸውን በመከታተል ላይ የሚገኙ የኢትዮጲያ መምህራን
በዚህ ምክንያት መምህራኑ ለአንድ ወር ያህል በከፍተኛ ችግር ውስጥ አልፈዋል፡፡ ችግራቸው በአስችኳይ መፍትሄ ካልተሰጠው ከአንድ እስከ አራት አመት የደከሙበትን ትምህርት ለማቋርጥ እንደሚገደዱ ገልፀውልኛል። በመሆኑም በዶላር እጥረት ምክንያት የመምህራኖቻችን የትምህርት እድልና የብዙ አመት ጥረት ከንቱ ሊሆን ነው፡
Average Rating