www.maledatimes.com ደርግ አዘጋጅቶለት የሄደውን ያማረ ሕዝባዊ የፍርሀት ቅብቅብ ወያኔ ምንም ሳይለፋ አሰማምሮና አሻሻሎ ቀጠለበት፡፡ - MALEDA TIMES
Loading...
You are here:  Home  >  Ethiopia  >  Current Article

ደርግ አዘጋጅቶለት የሄደውን ያማረ ሕዝባዊ የፍርሀት ቅብቅብ ወያኔ ምንም ሳይለፋ አሰማምሮና አሻሻሎ ቀጠለበት፡፡

By   /   October 27, 2012  /   Comments Off on ደርግ አዘጋጅቶለት የሄደውን ያማረ ሕዝባዊ የፍርሀት ቅብቅብ ወያኔ ምንም ሳይለፋ አሰማምሮና አሻሻሎ ቀጠለበት፡፡

    Print       Email
0 0
Read Time:75 Minute, 7 Second

እግዚአብሔር ሆይ!

የልቤን ሐሳብ ወደ አንተ አቀርባለሁ፤
አምላኬ ሆይ! በአንተ እታመናለሁ፤
ከመሸነፍና ከመዋረድ አድነኝ፤
ጠላቶቼም በእኔ መዋረድ አይደሰቱ፡፡
በአንተ የሚታመኑት ሐፍረት አይደርስባቸውም፤
ሐፍረት የሚደርስባቸው፣ በአንተ ላይ ለማመፅ የሚጣደፉት ናቸው፡፡
መጽሐፈ መዝሙር ፤ ምዕራፍ 25 ከቁ. 1 – 3

እንተዋቸው፡፡ ግዴለም፡፡ አንናደድ፡፡ በበቀደሙ ደብዳቤየ ጭንቅላቴ ሊፈነዳ መድረሱን የነገርኳችሁንም ለጊዜው እርሱት፡፡ እንደምንም ለመጽናናት ሞክሬ አሁን ተበራትቻለሁ፤ ያጽናናኝ ሰው ባለመኖሩ ግን ትንሽ ቅር ብሎኛል – ይቺ ትዝብት ቢጤ መሆኗ ነው፡፡ እንደዚህ መጨካከናችንም በመጠኑ ሳያሳስበኝ እንዳልቀረ በዚህ አጋጣሚ ብጠቁም ደስ ይለኛል፡፡ እንዲህ የምላችሁ ያን የበቀደም ለታውን ወረቀቴን ላነበባችሁ ነው፡፡ ዋናው የዚያ ጽሑፌ መልእክት ወያኔ/ኢህአዴግ የአቶ መለስን ለኢትዮጵያ ቀርቶ ለቀሪው ዓለም እንግዳ በሆነ ሁኔታ ለሣምንታት የዘለቀ ሙሾ አስመልክቶ እያካሄደው ያለው ሕዝቡን በግድ የማስለቅስና ጥቁር የማልበስ አሳፋሪ ድርጊት መጠቆም ነበር፡፡ በራሴው መንገድ እንዳረጋገጥሁትም ጥቂት የማይባሉ ዜጎች በራሳቸው ተነሳሽነት የሚያሳዩት ቅብጠትና እወደድ ባይነት አበሳጭቶኝ የምሬን ተናድጄ ነበር ቢያንስ ጽፌው ይውጣልኝ በሚል ሞነጫጭሬ የላክሁትና በተወሰኑ ድረ ገጾች ለንባብ የበቃው፡፡ ያወጣችሁልኝ እግዜር ይስጥልኝ፤ ያላወጣችሁልኝንካላወጣችሁልኝ አዳብዬ ማመስገኑ በባህላችን አልተለመደምና ሽሙጥ ይመስልብኛል፡፡ ቢሆንም ቢያንስ እናንተው ካነበባችሁት በቂየ ስለሆነ ለዚሁ በጎ ምግባራችሁ እግዜር ይስጥልኝ፡፡ ይህ ዓይነቱ ልፋትና ጥረታችን በዋናነት ‹ትናንት እንዲህ ብለን ነበር› ከማለት ውጪ ብዙም የሚረዳን ነገር እንደሌለ በበኩሌ እረዳለሁ፡፡ ይበልጥ ተጠቃሚ የምንሆነው ሁሉም ወደየልቦናው ተመልሶ ቆሞም ሆነ ተኝቶ ከሚሮጥበት የሩጫ ዓለም ሲወጣና እርስ በርስ መተያየትና መደማመጥ ሲጀምር ነው፡፡ ያ የአስተዋይነት ዘመን እየመጣ መሆኑ ይሰማኛል፤ ያኔም ሳንነጋገር እንኳን እንግባባለን፡፡ የፈጣሪ ፍቅር በመካከላችን ይነግሣልና! እስከዚያው ግን የምንጫጭር እንጫር፤ ወኔው ያለንም እናንብ – እናስነብብም፡፡

በነገራችን ላይ በዘሐበሻ ድረገፅ ላይ ‹ቤቲ› በሚል ስም በተሰጠኝ አስተያየት አንድ ጥያቄ በተደጋጋሚ ተጠይቄ ነበር፡፡ መልስ መስጠት ያልቻልኩት ኢትዮጵያ ውስጥ የኢንተርኔት ነገር እነዚያን ባለ ጮንጯና ዐይኖች የቻይና ዐይጦችን እግዜር ይይላቸውና መስመሩ እየወጣና እየገባ እንዲሁም በወያኔው ከማይፈቀዱ የተቃውሞ ድረገፆች ጋር እንዳንገናኝ እየተዘጋብኝ ነው እንጂ ሞክሬ ነበር፡፡ ባለአስተያየቷንም አንባቢያንንም ይቅርታ እጠይቃለሁ – የመጀመሪያው የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ መክብብ 3፡ 9-12 ሣይሆን፣ መክብብ 8፡ 9 – 12 መሆኑን ላስታውስ እወዳለሁ፡፡ ባለአስተያየቷ ትክክል ነበረች – የተሳሳትኩት እኔ ነኝ፡፡ የማይሳሳት የሞተ ብቻ ነው – እኔ ደግሞ ከሞተ ሰው በጥቂቱም ቢሆን እሻላለሁ ብዬ ስለማስብ ከይቅርታ ጋር ማስተካከያውን አሁን ሰጥቻለሁ፡፡
በዚህ አጋጣሚ ማስታወስ የሚገባኝ አንድ ቁም ነገር አለ፡፡ ይሄውም ሁላችን መከባበር የሚገባን ስለመሆናችን ነው፡፡ አንዳችን ሌላኛችንን በግለሰብ ደረጃ ማክበር ካልቻልን ሚሊዮኖችንም አናከብርም፡፡ መብትን ማክበር፣ ሰውን ማክበር ከግለሰብ – አጠገባችን ካለ የሚጨበጥና የሚዳሰስ ኅላዌ ካልጀመረ ነቢባዊነት እንጂ እውናዊነት የለውም – እንዲያ ከሆነ ደግሞ የይስሙላ ነው፡፡ የሰው ልጅ በእንስሳነቱ የሚገባው ክብር አለ፤ የሰው ልጅ በሰው ልጅነቱ የሚገባው ፍቅርና አክብሮት አለ፤ የሰው ልጅ በአንድ ሀገራዊ ዜግነቱ የሚገባው የተለዬ ውዴታና ፍቅር አለ፡፡ የዛሬን አያድርገውና ካናዳ ላይ አንድ አፍሪካዊ ሲታይ የትነቱ እንኳን ሳያሳስበን በክፍለ አህጉራዊ መሳሳብ ብቻ ተቃቅፈን እንሳሳም የነበረበት ጊዜ ሩቅ አይደለም፡፡ ዛሬ ዛሬ ሀበሻነቱን በገጽታው እያወቅህ እንደባዕድ ዜጋ ‹የትኛው ብሔር ነህ?› ከሚል ዘመን አመጣሽ ጥያቄ በኋላ ነው የሞቀ ሰላምታህን የምትዘረጋው፡፡ ውርደት ነው፡፡ የዚህን መሰል ማኅበረሰብ አባል ሆኖ መገኘትም ሊያሣፍን ይገባል፡፡ አንድ ሰው ተማረ አልተማረ፣ ደኸዬ ከበረ፣ አበደ ሰከረ፣ጠቆረ ቀላ፣ ባዳ ሆነ ተዛመደ… በሰውነቱና በዜግነቱ ተገቢው ፍቅር ካለአንዳች ማስመሰልና ታይታ ወይም ግብር ይውጣ ሊሰጠው ይገባዋል – ይህን ማግኘትም የዚያ ሰው ሰብኣዊ መብት ነው፡፡ ያኔ ነው በሁሉም ዘንድ መከባበርና መፈቃቀድ ሊመጣ የሚችለው፡፡ በየትኛውም መነሻ ምክንያት ሰዎች ቢናናቁና ለእግዜር ሰላምታ እንኳን ሳይቀር የፕሮቶኮል ደረጃ እያወጡ አንዳቸውን አንዳቸው የሻጉራ ቢመለከቱ ውጤቱ የዜሮ ብዜት ነው፡፡ ይህን ማለት የወደድኩት ለዚያች ቤቲ የተባለች አስተያየተኛ መልስ ልሰጣት ፈልጌ በኢንተርኔት መታፈን ምክንያት በወቅቱ ባለመቻሌና በቀጣይ መጣጥፍ እስከማገኛት የተሰማኝን የቅሬታ ስሜት በማሰብ ነው፡፡ የዚህች አንቀጽ መልእክት በራሷ ብዙ መጣጥፍ የምታጽፍ ናትና ሌሎች መጣጥፈኞች ግፉባት እባካችሁን፡፡ ፍቅርና መተሳሰብ እጅጉን ይጎድለናል፤ የፍቅር ጥማት ሊጨርሰን ቆርጦ ተነስቷል፡፡ ‹ምናባቱ! ምን ያመጣል? የት ይደርሳሉ? ትድ… ኤዲያልኝ ምናባታቸውን ሊያመጡ?…› የምንላቸው የትዕቢትና የትምክህት መገለጫዎች የትም አላደረሱንም፤ አያደርሱንምም፤ እጅጉን አፍራሽና ለበጎ ግንኙነት መፈጠርና ለመተሳሰብ መዳበር ፀሮች ናቸው፡፡ የምለው ከእውነት እንጂ ትህትና ሞልቶ ተርፎኝ ለችርቻሮ እንዳላወጣሁት በአክብሮት ላሳውቅ እፈልጋለሁ፡፡ እርግጥ ነው – መናገር የማድረግን ያህል አይከብድም፡፡ እነሱም በፈሊጣቸው ይላሉ፤ Better said than done. እንሞክረው ይሆንልናል፡፡ ለመፈቃቀር ደግሞ ከማንም ሕዝብ ይልቅ ኢትዮጵያውያን ቅርብ ነን፡፡ በሀዘኔታ ከንፈር መምጠጥ የተጀመረው በኛ ሀገር ሳይሆን ይቀራል? ለመሆኑስ በሌላ ሀገርስ አለ? ክሩ ተበጣጥሶ አላለቀም፤ ግን ሳያልቅ እንድረስለት ነው እያል ያለሁት፡፡

=አሁንም ልድገመውና ወያኔን እንተወው፡፡ የልባቸው ይሙላ – ያልቅሱም ሕዝብንና ምድረ ታዋቂ ተብዬንም በግዳጅም ሆነ በውዴታ ወይም በሁለቱም ያስለቅሱ፤ ለቂም በቀልም አንዘጋጅ፡፡ ክፉን በክፉ ለመቃወም ጊዜ አንስጥ – ለምን ቢባል ልብና ኩላሊትን የሚመረምር አምላክ ክፋትን በክፋት ሊመልሱ የሚያደቡ ሰዎችን ዕቅድ ያከሽፋልና፤ ተንኮልን ሰንቆ ደግ ትልምን ማሣካት ደግሞ የሚቻል አይደለም – ቢቻልም በዞረ ድምሩ ሲጠፋፉ መኖር ነው፡፡ መጽሐፉም ‹መጎናጸፊህን ለሚፈልግ እጀ ጠባብህንም ተውለት› ይላልና ይህን ከንቱ ሥራቸውን እንደመጨረሻ ስንቃቸው ቆጥረን ንቀን እንተወው፡፡ ያዋረዱን ሊመስለን ቢችልም ኃጢያን እነሱው ይሸከሙታልና አክብደን አንየው የሚል ስሜት ነው ለጊዜው እየተሰማኝ ያለ፡፡

አቶ መለስ መሞቱ ከተገለጸ ወዲህ ብዙ ነገሮችን እየታዘብን ነው፡፡ በአንድ በኩል ሳስበው አጠቃላይ አካሄዳቸው “በቅሎ ገመዷን በጠሰች” ቢሉ “ማሠሪያዋን አሳጠረች” እንደሚባለው ትውፊታዊ ብሂል ይመስለኛል፡፡ ምን ለማለት ነው – በሀገራችን ይትበሃል አንድ ሰው ወይም አንድ ቤተሰብ በደረሰበት የሞት አደጋ ልቅሶና ሀዘን ካበዛ ያ ቤተሰብ ሞትን በድጋሚ እየጠራ እንደሆነ በባህሉ ይታመናል፡፡ ልቅሶ የሚያበዛ ሰው ልቅሶን ይጠራል ይባላል – ዐይንን ከማሞጭሞጭና ለበሽታም ከመዳረግ ጎን ለጎን፡፡

በሌላም በኩል የአንድ ሰው ልቅሶ ቅልጥ ያለ ከሆነም ማለትም ቆላ ደጋውን የሚያገናኝ ድብልቅል ያለና የገነነ ከሆነ እንደዚሁ ‹ይሄ ነገር ሌላ ሰው ሊጠራ ነው!› ይባላል፡፡ ይህም ብቻ አይደለም – ንፍሮውና እህል ውኃው ከወትሮው ለየት ባለ ሁኔታ የሚጣፍጥ ወይም የሚጥም ከሆነም ሌላ ሰው ሊያስከትል እንደሆነ በባህሉ መሠረት ይታመናል፡፡ ስለዚህም እነወያኔ፣ ዳኛቸው ቢያድግልኝ በሰሞኑ ግሩም መጣጥፉ እንደጠቀሰው ህዝቡን ለማዋረድና ታዛዥነቱን ለማረጋገጥ በግዳጅ ልቅሶ ቢያስቀምጡትና እያደረጉ ያሉትን ቢያስደርጉትም ዶር. ፍስሐ እሸቱ ባስነበበን ማለፊያ ትንቢት መሠረት እንደተረዳሁት እያደረጉት ያለው ነገር ከጠቀሳቸው አራቱ ሥነ ልቦናዊ ደረጃዎች የመጨረሻውን ማለትም የመበስበሻቸውን አቅጣጫ ስለሚጠቁም በድርጊታቸው ብዙም መከፋት እንዳይገባን ብንሞክር ጥሩ ነው፡፡ ይልቁንም እንደመጽሐፉ “የሚያደርጉትን አያውቁም” በሚለው ነባር አባባል ተረድተናቸው፣ ከነርሱ ጋር የሚያጨበጭበውንም የሕዝብ ወገን ካለማወቅና ክፉ ወቅትን በዘዴ ለማለፍ ከሚደረግ ብልሃት አንጻርም ሊሆን እንደሚችል ተገንዝበን በዶር. ፍስሐ እሸቱ የምክር አስተያየት መሠረት የኛን የቤት ሥራ መሥራቱ የሚያዋጣን ይመስለኛል፡፡ ለመረጃ ትንተናና ለነገር ስንጠቃ የምንሰጠው ጊዜ ባይኖር ወይም አነስ ቢል መልካም ነው፡፡

አንድ ነገር ሰንቀር ላድርግ፡፡ አንድ ጓደኛ ነበረኝ፤ አሁንም በጓደኝነት አብረን አለን፡፡ ይህ ጓደኛየ እንደኔው ብዙም የተማረ አይደለም – የዱሮው 12ኛ ጨራሽ ነው፡፡ በ97 የምርጫ ወቅት የቅንጅት ቀንደኛ አባልና ግምባሩን ለጥይት ከመስጠት ወደኋላ የማይል ፊተኛ ተሠላፊ ነበር፡፡ የቅንጅት ነገር እንዳይሆን ሆኖ ሲቀርና ጊዜም ሲያልፍ ግን ያ ጓደኛየ የወያኔ/ኢሕአዴግ አባል ሆኖ ዐረፈው፡፡ ለምን እንደገባና የት እንደሚሠራ መናገሩ ምሥጢር ማውጣትና ስሙን የመናገር ያህል ይሆንብኛልና ልተወው፡፡ ነገር ግን ከልቡ እንዳልሆነ አሁንም ድረስ ለብቻችን ስንገናኝ እንነጋገራለን፡፡ የአመራር አባል ነው – ልቦለድ እንዳይመስላችሁ፤ ለመኖር ምርጫ ከማጣት የተነሣ የወያኔ አባል ይሁን እንጂ አሁንም በወያኔ አሠራር – በአድልዖው፣ በምዝበራውና በሙስናው፣ በዘረኝነቱ… ክፉኛ ይበሳጫል፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ ሰሞኑን በተከሰተው የመለስ ሞት ከእግር ጥፍሩ እስከራስ ጠጉሩ ድረስ ጥቁር ልብስ ለብሶ አየሁት፡፡ ካልሲው ሳይቀር ጥቁር ነው፤ ክፉኛ ‹አዝኗል› – ፊቱን በባና መንጨት ነው የቀረው፤ የሚሠራበትን መሥሪያ ቤት ሠራተኞች ሳይወዱ በግዳቸው ጥቁር አስለብሶና በተርታ አሰልፎ ወደማልቀሻው ድንኳንና ወደቤተ መንግሥት የሚወስድ እርሱ ነው – ብቻችንን ስንሆን እንደኔና እንደሱ የሚተማመን የለም፡፡ የወያኔን ጉድ በዚህች በነገርኳችሁ ጠባብ የግል ገጠመኜ ሳይቀር በደንብ መረዳት ይቻላል፡፡

ዱሮ የምናውቀው የዐዋጅ ፆም እንጂ የዐዋጅ ልቅሶ የሚባል ነገር በጭራሽ ሰምተን አናውቅም ነበር፡፡ ነገር ግን ዕድሜ ለወያኔ ይሄውና ከገጠር እስከ ከተማ ሕዝቡን እያስገደደ – እስረኛና የሆስፒታል ታማሚ ሳይቀር በቃሬዛ እያወጣ በመለስ የሙሾ ዜማ ደረት ያሰደልቅ ይዟል፡፡ ይህ ላወቀውና ልቦና ላለው የግፍ ግፍ ነው፡፡ወያኔ እርግጥ ነው ቋሚ ሕጉ ሕግ – አልባነት በመሆኑ ከሁሉም ማኅበራዊ ወግና ሥርዓቶች ባፈነገጠ መልክ የተሣፈረባት መርከብ ከአንዱ አለት ጋር ተጋጭታ እስክትቆም ያሻውን እያደረገ ነው፤ በካፈርኩ አይመልሰኝ በከፍተኛ የጣር ሥቃይ ውስጥ ገብታ እያንቋረረች የምትገኝ ነፍሱ እስክትወጣ ድረስም በዚሁ እንደሚቀጥል ከመቶ በሚያልፍ ፐርሰንታይል እርግጠኝነት መናገር ይቻላል፡፡ እንዲህ እያደረገም ነው አሁን ድረስ የዘለቀው – ለኛ አዲስ አይደለም፡፡ ምናልባት አዲስ የሚሆንባቸው ለውጪዎቹ ይሆናል፡፡ በዚህ የሽፍታ አገዛዙ እስካሁን ያን ያህል የሚያሰጋ ተቃውሞ አልደረሰበትም፡፡ አይካድም – በ1997ዓ.ም ችግር ገጥሞት ነበር – ያንንም እንደምንም ለአሩሲዋ እመቤትም ይሁን ለሕንዱ አበጋር ወይም ለሱዳኑ ወልይ የሚገብረውን ገብሮ በሕዝብ ላይ የሚያዞሩለትን በማዞር አፍዝዞን እስካሁን ቆይቷል – የአሁኑ ግን በምንም ዓይነት የንዋይም ይሁን የደም ግብር የሚመለስ አይደለም፤ ጠና ያለ ነው፡፡ ከቁንጮ የሚጀምር ነገር ደግሞ ብዙውን ጊዜ እግርጌ ሳይደርስ በጅምርም ሆነ ዒላማውን ሳይመታ አይቀርም፡፡

ከአሁን በኋላ እንደዱሮው መዘባነን የለም፡፡ ልቅሶውም ጠሪ ነው፡፡ ከእነሱ አንድም ለወሬ ነጋሪ እንኳን የሚቀር እንደማይኖር እየሰማን ነው፤ ካልተረጋገጠ የወሬ ምንጭ በሰማሁት መሠረት እንደመለስ በመጨረሻ ሰዓት ሳይሆን ራሳቸውም ሆኑ ብዙ ሕዝብ ሳያልቅ በጊዜ ንስሐ ከገቡና ከጥፋት መንገዳቸው ባፋጣኝ ከወጡ የምሕረት አምላክ የሚሳነው ነገር ስለሌለ ሊምራቸው ይችላል – ቢማሩ እሰዬው ነው እንጂ ልንመቀኝም አይገባንም፤ ምነው በተማሩልን! ቀደም ሲል ለመጠቆም እንደሞከርኩት ይህ ትዕዛዝ ከሰው አይደለም፡፡ ፍስሐ እንዳለው ይህ መለኮታዊ ቅዱስ በረከት ነው፤ የአንድ ሥርዓት መነሻ እንዳለው ሁሉ መጨረሻም እንዳለው የሚያመለክት ተፈጥሯዊና በድራቦሹም መለኮታዊ አካሄድን የሚጠቁም ነው፡፡ ማማር እንዳለ የውበት መርገፍም አለ፡፡ መወለድ እንዳለ መሞትም አለ፡፡ በዚያ ላይ የሀገራችንን ሁኔታ ለየት የሚያደርገው ብዙ ነገር አለ፡፡ ትልቁ ጅማሮ ግን ሲያቀብጣቸው ሊነኩት የማይገባቸውን ቀፎ ነክተው ዙሪያውን ይጠብቅ የነበረው መርዘኛ ተርብና መለኮታዊ ኮብራ እየተወረወረ ወደመላ ጅስማቸው ይሰጠሰጥባቸው ይዟል፡፡ የተጣለው መቋሚያም በግማሽ ድል እንደማይመለስ ከሁነኛ ሰዎች እየሰማን ነው፡፡ መጽሐፉ ‹ትዕቢትሰ ፀሩ ለክርስቶስ› ይላል አሉ፡፡ ክርስቶስ ትዕቢትን አይወድም እንደማለት ነው፡፡ የእነዚህ ሰዎች ትዕቢት ግን ወጥ ረገጠ፤ ምድርንም አልፎ የጽርሐ አርያምን ደጅ በጠብ ያለሽ በዳቦ በጦር ይወጉ ጀመር፤ ፈጣን ጦርነት ውለድልን ብለው ሙጥናን አሉት፤ እናም ይችሉት አይችሉት እንደሆነ ወደፊት በስፋት የምናየው ሆኖ ጦርነቱ ተጀመረና ግን ገና ከአሁኑ የንጉሡንና የእጨጌውን አናት በመቅላተ ግዳይ ማስቆጠሩን ጀምሯል፡፡ በተኩስ እሩምታ በሚራወጥ የቀብር ቦታ ያለፈ ሼካ የተኩሱን ምንነት እንዲያስረዳው ለጠየቀው መንገደኛ “አላህና ሰው ጦርነት ገጥመው ነው” ሲለው መንገደኛው “ለመሆኑ ስንት ሰው ተጎዳ?” ብሎ ላስከተለው ጥያቄ “ተሰው ወገን አንድ ወድቋል፤ ታላህ ወገን ግን ገና አልታወቀም” ሲል እንደመለሰው በአሁኑ የወያኔና የእግዚአብሔር ጦርነት ሁለት ያህል ፊታውራሪዎች ተከታትሎ ከላይ በተተኮሰ ጥይት እስከወዲያኛው አሸልበዋል፤ ያሳዝናል – ሊቀር ይችል የነበረ ጦርነት ከ21 ዓመታት በላይ በዘለቀ ጥጋብ ተቀሰቀሰና ጉዳቱ እንደልማዱ ከፊት ተሰላፊ ተራ የውጊያ ወታደርና ከመስመር መኮንን ሳይሆን ከኋለኛው የቤተ መንግሥት ቁንጮ ተጀምሮ አዲስ የጦርነት ሥልት/ስትራቴጂ ለማየት በቃን – ጦርነቱ እየተፋፋመ ሲሄድ ገና ብዙ ጉድ እናያለንና አግራሞታችንን በሰሞነኛ የጦርነት ውሎዎች ብቻ እንዳንጨርሰው ጠንቀቅ ብንል አይከፋም፡፡ ጦሳቸው ግን ለሕዝብና ለሀገር ተርፎ ይሄውና አብዛኛው የመንግሥትና የተወሰነው የግል ሥራ ሁሉ ተዘግቶ ሀገር ኪሣራ በኪሣራ እየሆነች ነው – ተሠርቶም አልሆነ እንኳን በልቅሶ ድባብ አርባና ተዝካር እስኪወጣ ተዘፍዝፎ ተቀምጦ – ሁለት ቀን ሦስት ቀን ቢታዘን የወግ ነው፤ ለዚህ ሁሉ ጊዜ ‹ማዘን› ግን የጤንነት አይደለም፡፡

“የናቁት ወንድ ያስረግዛል” ይባላል፡፡ ከአዲስ አበባ እስከ ጎንደር ባለው የ700 እና የ800 ኪሎ ሜትር የተዘረጋ ሥፍራ ለስኳር አገዳ ማብቀያና ማምረቻ ቀርቶ አምስትና ስድስት የሚደርሱ ጅቡቲዎችንና አርሲዎችን ሊያስቀምጥ የሚችል የተንጣለለ መልክዓ ምድር እያለላቸው እዚያ ዋልድባ የሚባል ቦታ ውስጥ እትብታቸውን የቀበሩ ይመስል በተለመደ ድንቁርናቸው፤ እኛ ላይ በለመዱት መደዴነታቸው የተቀደሰውን የመለኮት ሥፍራ ሲደፍሩ ሃቲማቸው ተቋጨ፤ እዚያ ላይ ተገኙ፤ እዚያ ላይ ቋቱ ሞላ፤ በዚያም ምክንያት እንዲህና ገና ከዚህም በላይ እንዲያብዱ፣ አብደውም ሕዝቡን እንዲያሳብዱና ግራ እንዲያጋቡ፣ ቀሪውን ዓለምም እንዲያስደምሙ እየሠሩት ባሉት የጅሎች ሥራም ዓለሙ ሁሉ እንዲገረም፣ ወዳጅ ጠላታቸውም እውነተኛ ማንነታቸውን እንዲያውቅ የፈጣሪ ምርጫ ሆነ – የኛ ምርጫ በ97 ሲከሽፍ የርሱ ቀጠለ፤ እዚያ ላይ ልበ አምላክ ቅዱስ ዳዊት ‹ቀጥቅጥ መዝራዕቶ ለኃጥዕ› እንዳለ እኒህ ከሆዳቸው በስተቀር፣ እኒህ ጃዝ ብሎ ከላካቸው የአጋንንት መሪ ሣጥናኤል በስተቀር እግዚአብሔርንና ሕዝብን የማያውቁና ቢያውቁም የናቁ ኅሊናቢሶች ባልጠረጠሩበት ወቅት ተመቱ፤ አበቅቴው ደረሰ፡፡ የዐዋጁን በጆሮ ካልተባልኩ ከላይ የታዘዘን ጦር ደግሞ የሣሞራ የኑስ በታፈነ የውስጥ ቅራኔ ሊፈነዳ የደረሰ የ“ሀገር መከላከያ ጦር” ቀርቶ የፔንታጎን የኒኩሌር ሚሣኤልና የአቶሚክ ቦምብም ሊመክቱት አቅምና ችሎታ የላቸውም፡፡ የ’CIA/FBI’ም ሆነ የMI5/6 የ’Mossad’ ወይም የ’KGB’ና በ’espionage/intelligence technology’ የላይኛው የሥልጣኔ ደረጃ ላይ የደረሱ መሰል የስለላና ደኅንነት ተቋማት አስቀድመው ሊደርሱበት፣ ደርሰውም መሻሪያ ሊያበጁለት አይቻላቸውም፡፡ እግዚአብሔር ኃያል ነው!

በዘመነ ክርስቶስ የተመዘገበውን የ”ስቅሎ፣ስቅሎ” ታሪክ የማያውቅ መቼም የለም፡፡ ሕዝብ የምንለውን ነገር አንዳንዴ ከጽንሰ ሐሳብ ደረጃ ብዙም ባናሳልፈው የተገባ ነው፡፡ በመሠረቱ ሕዝብ ኃይል ነው፡፡ ሕዝብ ሀብት ነው፡፡ ይህ የሚሆነው ግን እርሾ ሲኖር ነው፡፡ ሕዝብ ብቻውን ግን ምንም ማለት አይደለም – የምንነጋገረው እውነትንና እውነትን ብቻ ነው፡፡ በደረቅ ሌሊት እንቅልፍ እምቢ እንዲለኝና (አሁን ከሌሊቱ 9 ሰዓት ከ53 ነው!) ይህችን ደብዳቤ እንድጭር ያደረገኝ ነገር ይህ ዋና ነጥብ ነው፡፡ እናም ሕዝብ 100 ሚሊዮንም ይሁን 100 ቢሊዮን ለአንድ የተፈለገ ዓላማ ‹ሆ› ብሎ እንዲሰለፍ እርሾ ያስፈልገዋል፡፡ በቁናም ይሁን በበርሜል የተቦካ ሊጥ እርሾ ከሌለው ዋጋ የለውም፤ ይበላሻል፤ ይደፋል፡፡ ብዛት አይደለም ነገሩ – አነሳሽ ኃይል – መሪ ኃይል – ዐዋቂና ፈር ቀዳጅ ሰው(-ኦች) ያስፈልጋል(-ኡ)፡፡ (እነንዋይ መለስን “ሙሤ” ብለው የዘፈኑለት ዘፈን አሁን ምን ሲል ትዝ አለኝ ጃል!) እርግጥ ነው መለስ እርሾ ነበር – ምን ዓይነት እርሾ? ማንን ያነሳሳ እርሾ? ማንን አነሳስቶ፣ ማንን ጠቅሞ፣ ማንንና ምንን የጎዳ እርሾ? ስንቶችን ለስንት ዓመት ያፍለቀለቀ እርሾ? መልሱን ሁሉም ያውቀዋል፡፡ በዚህ ጊዜ ማባከን ጉንጭን ማልፋት ነው፡፡ ዋናው ጉዳይ ግን በመልካም እርሾ የተነሳሳ ሕዝብ ድንቅ ነገር ሊሠራ እንደሚችል ሁሉ በግም እርሾ የተነሳሳ ሕዝብም በተመሳሳይ ሁኔታ ብዙ ጥፋት ሊያደርስ እንደሚችል መረዳት ተገቢ ነው፤ እናም ዋናው መስቀያው ነው ማት ነው፡፡ ምሳሌ በመጥቀስ ዳክሬ አላዳክራችሁም – እዚሁ አጠገቤ ወያኔ ተጎልቶልኝ!

ማህተመ ጋንዲ ጥሩ እርሾ ነበር፤ ኔልሰን ማንዴላ ጥሩ እርሾ ነው፤ እማሆይ ተሬዛ ጥሩ እርሾ ነበሩ፤ እነአብርሃም ሊንከንና ጆርጅ ዋሽንግተን ለአሜሪካ ጥሩ እርሾዎች ነበሩ፤ አፄ ምንሊክ የሀገራችን ሞዴል እርሾ ነበሩ(ሕዝባቸው በሰይጣን ፈረስ አይሄዱብንም ብሎ ሲቆጣቸው እውነቱን ልቦናቸው እያወቀው ከመኪናቸው ወርደው በእግራቸው የሄዱ የመጀመሪያው ሕዝብን አክባሪ ንጉሠ ነገሥት ናቸው፤ ዛሬ ዕድሜ ለሞታቸው ሬሣቸውን እንኳን ልናይ የቻልነው በበረከትና ለበረከትም ነው – እንደቀልድ ቅኔ መወድስ ዘረፍኩለት አይደል?)፡፡ እነመንግሥቱ ኃ/ማርያምና መለስ የሾመጠሩና ሊጡን ወደገደል የከተቱ መጥፎ እርሾዎች ናቸው/ነበሩ፡፡ ሒትለር፣ሙሶሎኒ፣ስታሊን፣ኢዲያሚን፣ሞቡቱ፣ቻውቼስኮ፣ ጋዳፊ ፣አሣድ ፣… የመጥፎ እርሾ ዋነኛ አብነቶች ናቸው፡፡ስለዚህ ሕዝብ ካለእርሾ(ካለሁነኛ መሪ)፣ መኪና ካለሞተር፣ ሰውነት ካለልብ፣ … ዋጋ የላቸውም፡፡ ነገሩ የመማር ያለመማር ብቻም አይደለም – መማርም ትልቅ ዋጋ ያለው መሆኑ ሳይዘነጋ፡፡ ማኅበረሰቡ የተማረና የሠለጠነ ከሆነ እርሾዎችን በቀላሉ ለማውጣትና ወደተፈለገው ግብ ለማምራት አይቸገርም፡፡ አብዛኛው ሕዝብ በማይምነት ድቅድቅ ጨለማ የሚንከላወስ ከሆነ ግን ጥሩ እርሾ የመገኘቱ ዕድል የሰለሰለ ከመሆኑም ባሻገር ያልዘሩት አይበቅልምና ከእርሱ የሚወጣውና ወደሥልጣን የሚመጣው መጥፎ እርሾ ሁሉ ‹ሲጠራው አቤት፣ ሲልከው ወዴት› የሚል ቅን ታዛዥና ከመአረዌ ገዳም የሚቆጠር ተናጋሪ እንስሳ ይሆናል፡፡ እያየነው እንዳለነው ሁኔታ፡፡ ጥሩ እርሾ ያለው ሕዝብ ወደሥልጣኔና ዕድገት ሠገነት ይወጣል፤ መጥፎ እርሾ ያለው ሕዝብ ለመተላለቅ ይፈጥናል፤ በሰበቡም ኑሮው ትርጉም አልባ እየሆነ ይሄድና ለሠለጠኑ ሕዝቦች የቡና ማጣጫ ሆኖ መሳቂያና መሣለቂያ ይሆናል፤ ለነፍስ ይማር ምፅዋትም የተዳረገ ምንዱብ ወምሥኪን ዜጋ ይሆናል – ልክ እንደማን ብዬ ልጠይቅ አልፈልግም፡፡ በዚች ዓለም እኩል ተፈጥረን ስናበቃ በመልካም እረኞች ዕጦት የተነሣ ግን አንዳችን ከአንዳችን የሰማይና የምድርን ያህል እንራራቃለን፡፡

የሀገራችን ሕዝብ ይህን ለመሰለ ተዋራጅነት የበቃው በደርግና በወያኔ ተደጋጋሚ መብረቃዊ መቅሰፍት ነው፡፡ የደርግ መንግሥት ለተገደልንበት የገዛ ራሳችን ጥይት ዋጋ እንድንከፍልና በቀይ ሽብር ስም በተገደሉ ልጆቻችን ሬሣ ዙሪያ እየዘፈንን እንድንጨፍር አደረገን፤ ከዚያም ቀጠለና በሃይማኖታችን ገብቶ ከ‹እንኳን አደረሳችሁ› ወደ ‹እንኳን ደረሳችሁ› ከለወጠን በኋላ ከፈጣሪ ጋር አጣላን – ባንዲት ፊደል ጦስ፤ ማመር መጠጣትንና ክርስትና መነሳትን ነውር አድርጎ በእልህ በሚመስል ሁኔታ ረቡዕና ዐርብን ጨምሮ ዋና ዋና አፅዋማትን ሆን ብለው ጠብቀው በሚዘጋጁ ስብሰባዎችና እዚያ ላ በሚቀርቡ የፍሥግ ምግቦች ማተባችንን ለሆዳችን አውልቀን መጣላችንን እንድናረጋግጥለት አደረገን፣ ከሩቅ በመጣ የአለባበስ ዘይቤ አንገታችን እስኪታነቅ ድረስ ደረጃን በሚለዩ ቀለማት የተሰፉ ዩኒፎርሞችን በግዳችን አለበሰን፤ በከተራና በጥምቀት ዕለታት ሕዝባዊ ስብሰባዎችን በመጥራት የአድባራት ታቦቶች በጥቂት ካህናትና ቀሳውስት ብቻ ወደየማደሪያቸውና ከዚያም ወደየአጥቢያቸው እንዲሄዱ በዚያውም “እግዚአብሔር እንዲዋረድ” አደረገ፡፡ ያ ሁሉ ውርጅብኝ ሕዝቡን በፍርሀት አሸማቅቆ ወደተናጋሪ እንስሳነት ለወጠው፡፡ በዚህ ሁሉ የዞረ ድምር ግን ሕዝብም ደርግም አልተጠቀሙም፡፡ የሆነው ሁሉ ሆነ፡፡ ችግሩ ግን ከዚያ ዘመን ማንም ሊማር አለመቻሉ ነው፡፡

ደርግ አዘጋጅቶለት የሄደውን ያማረ ሕዝባዊ የፍርሀት ቅብቅብ ወያኔ ምንም ሳይለፋ አሰማምሮና አሻሻሎ ቀጠለበት፡፡ በደርግ ከሆንነው በላይም ሆንን፡፡ የተገደልንበትን የኛኑ ጥይት እንድንከፍል ብቻም ሣይሆን የልጃችንን ሬሣ ከነቫቱ እንድንከፍል ተደረገ፤ …. ይሄውና አሁን ደግሞ በገዳያችን ሬሣ ዙሪያ በግድ እንድናለቅስና ማቅ እንድንለብስ የመገደዳችን ምሥጢር ሲፈታ በግፍ በተገደሉ ልጆቻችን ደምና አጥንት፣ በኑሮ ውድነት ሳቢያ የምንልሰውና የምንቀምሰው አጥተን በተራቆተው ገላችን፣ ውሉ በጠፋት አጠቃላዩ ሕይወታችን ዙሪያ ተሰልፈን እንደመጨፈርና ገዳያችንንና አጥፊያችንን “ለምን ትነካብናለህ? ለምንስ እስከወዲያኛው እየገደለንና እየጨፈጨፈን አይኖርም?” ብለን በፈጣሪ ላይ ሁለት ጊዜ እንደማልቀስ ነው፤ የመጀመሪያው በጊዜው ይህን ሰው እንዲያነሣልን የለመንነው፤ ሁለተኛው አሁን ጸሎታችንን ለምን ሰማህ ብለን ለእግዜሩ ቀርቶ ለሰሚ ግራ በሆነ ሁኔታ መማጠናችን፡፡ ለሰው ቀርቶ ለእግዚአብሔር ክፉኛ የሚያስቸግር ሕዝብ ቢኖር የኢትዮጵያ ሕዝብ መሆን አለበት፡፡ መቼም ሲጣሉ ከልብ ሲታረቁም ከአንጀት ነው መሆን ያለበትና ይቅርታችሁን፡፡ ቢሆንም ግን የያዝ ቢይዘን እንጂ በጤናችን እንዳልሆ ያስታውቃል፡፡

እርግጥ ነው ለዚህ ባሕርያችን እኛ ሕዝቡ ብቻ ሳንሆን ከደርግና ወያኔ ባልተናነሰ የተቃውሞውም ጎራ የአንበሣውን ድርሻ ይወስዳል፡፡ አንዳንዱ የሕዝብ ወገን እረጭታን የመረጠው ከዚያም ባለፈ በአላስፈላጊ ሁኔታ ሳይቀር ከወያኔዎች ጋር መሞዳሞድን የፈለገው “አገባሻለሁ ያለ ላያገባሽ ከባልሽ ሆድ አትባባሽ” ከሚልም ይመስላል፡፡ ደግሞም እንዲህም እንደሚባል አንርሳ፡- “የወደዱትን ሲያጡ የጠሉትን ይቀላውጡ፡፡” በዚያ ላይ በደምባራ በቅሎ ፈረስ ተጨምሮ እንዲሉ የኑሮ ዋስትናው ከእጅ ወደ አፍም ሊሆን ያልቻለው የማኅበረሰብ ክፍል አቋሙን የሚያስተካክለው በወስፋቱ እንጂ በኅሊናው ሊሆን እንደማይችል መረዳት ተገቢ ነው፡፡ አምባገነኖች ደግሞ በተፈጥሯቸው ኅሊናን እያጫጩ ለሆድ ማደርን እንደባህል የሚያስፋፉ የሀገር ነቀርሳዎች ናቸው፡፡ በመሠረቱ አምባገነኖች ራሳቸውም በባሕርያቸው ይለያያሉ፤ እያበላ የሚገዛ አለ፡፡ እያስራበ የሚገዛ አለ፡፡ የኛው ግን አንድ ቃልም ሆነ ቲዮሪ የሚገኝለት አይመስለኝም፡፡ ማኅበረሰባችን የደረሰበትን ውጥንቅጥ ገጽታ መመልከት በቂ ነው ይህን እሳቤ ለማጠየቅ፡፡

ከቀደምት ትውልዶች በአንጻራዊ ሁኔታ ለሀገርና ለወገን ተቆርቋሪ የነበረው የስልሣዎቹና የሰባዎቹ ትውልድ ዛሬ ያለው ለዘር ያህል ቢሆን ነው፡፡ ቀሪው አልቋል፡፡ ብዙው በቀለማት ባሸበረቁ የነጭና ቀይ ሽብሮች አለቀ፤ ቀሪው በወያኔ ዘመን ኤድስን ጨምሮ በልዩ ልዩ በሽታዎች ተመተረ፤ በጦርነት፣ በስደት፣ በፀረ ወያኔ ትግል፣ በተስፋ መቁረጥ፣ ለጥቅም በመታለል፣ ራስን በማጥፋት፣ ብርጭቆና አደንዛዥ ዕፅ ውስጥ ገብቶ በመወሸቅ፣ እርጅናን በመሳሰሉት ሰው ሠራሽና የተፈጥሮ ምክንያቶች ከሀገር አለኝታነት ማዕቀፍ እየተስፈነጠረ ወጥቶ አሁን ያለው ብዙም የሚያወላዳና ተስፋ የሚጣልበት አይደለም፡፡ አሁን ያለው ትውልድ ባብዛኛው ወያኔ ሲገባ አንቀልባ ውስጥ የነበረና ከመለስ ሌላ መሪ የማያውቅ፣ የአሁኑን በ100 ብር ገደማ የምትሸጥ አንድ ጉርሻ የማትሞላ ክትፎ ዱሮ ያኔ በደጉ ዘመን እስኪጠገብና ተርፎም እስኪመለስ በሃምሣ ሣንቲም ይበላ እንደነበር ሲነገረው ተረት ተረት እየመሰለው ‹አትቀልዱብኝ› የሚል ዜጋ ነው፡፡ ለዚህ ልዩ ትውልድ ልዩ እርሾ ያስፈልጋል፡፡ ይህ ልዩ እርሾ መሠራት ያለበትም ከዚሁ ትውልድ እንጂ የስብስቴው ሰዎች በዱሮ በሬ እያረሱ የአሁኑንና በብዙ መንገድ ከዱሮው የተለየውን ትውልድ በማይመጥነው ቀምበር ጠምደው እያረሱ ያልዘራውን እንዲያጭድ እያስገደዱት አይደለም፤ አይገባምም፡፡ ይህ የአሁኑ ትውልድ በደርግና በወያኔ የዋግ ምች ሰደድ የተመታ ነው – የአባቱን ጠንካራ ሀገራዊ ሠነ ልቦናና ሀገራዊ የመኖር ተስፋ በደርግ የተነጠቀ፣ ራሱን በወያኔ አፍዝ አደንግዝ የመከራና የሥቃይ አገዛዝ ያነሆለለ በቀቢፀ ተስፋም የሚኖር ትውልድ፡፡ የሁለቱም መንግሥታት ጨካኝ የአገዛዝ መዶሻዎች ሕዝቡን ባልተወለደ አንጀት ቀጥቅጠው አዲስ የማኅበረሰብ ግኝትም አስገኝተው ወደማይቀሩበት የመጨረሻ ግብኣተ መሬታቸው ሄደዋል፤ እርግጥ ነው የወያኔው ገና በጣር ላይ ነው፤ የአሁኑ ሁኔታውም የነፍስ ውጪ ነፍስ ግቢ የመንፈራገጫ ቅጽበት እንጂ ከእንግዲህ ወያኔ እስትንፋስ አግኝቶ አፈር ልሶ ይነሳል ማለት ዘበት ነው – እባቡ ወያኔ ብቻ ሣይሆን መርዛቀባዮቹም ከዱላው አይተርፉም፡፡ የወያኔን ሞት ያቃረበው ደግሞ ተቃዋሚም ሆነ ሌላ ምድርዊ አካል አይደለም፡፡ ይህ የፈጣሪ ቁጣና የመጨረሻ ፍርድ ነው፡፡ በዚህ ዙሪያ ብዙ ጊዜ ተነግሯል፤ ተጽፏልም፡፡ ዘወር ብሎ መቃኘት ነው፡፡

ይህን የእግዚአብሔር በረከት መልክ የሚያሲዝ እርሾ ታዲያ ያስፈልጋል፡፡ እውነት ነው – እግዚአብሔር ሲፈልግና ሲፈቅድ በክፉዎች ላይ መቅሰፍት መላክ ብቻ ሳይሆን ምትክ የሚሆን መልካም እረኛም (ኖላዌ ኄር) እንደሚሰጥ የታመነ ነው፡፡ እናም በአሁኑ ወቅት በተቃውሞው ጎራ እንደጥንት እንደጧቱ ዐመፀንና ክፍፍልን የሚዘራ፣ የሰለቸንን ዘረኝነትንና ጎጠኝነትን የሚሰብክ፣ ሕዝቡን በነበረው ወያኔያዊ የአገዛዝ ሥልት መልሶ ለመንከር የሚሞክር ካለ በወያኔ መንደር የተነሣው ቋያ በዚያም መንደር አይነሳም ብሎ ማሰብ ድንቁርና ነው፤ አለቃ ገ/ሃና ‹እዚያም ቤት እሳት አለ› ያሉትን ያስቧል፡፡ ብቸኛው መፍትሔ ከዚህ ከወያኔ የመጨረሻ ግርፋት በበጎ መልኩ ተምሮ ጠማማ አስተሳሰብንና በክፋት የተሞላ አእምሮን ሳይመሽ በጊዜ ማስተካከል ነው፡፡ ሲረጋገሙና ሲጠፋፉ መኖር ሊያከትም ይገባል፡፡ ቂም በቀል እያረገዙ ዐመፅ መዝራትና ዕልቂትን ማምረት ከእንግዲህ ልንጠየፈው ይገባል፡፡ … ማንም አይጠቀምም፡፡

አሁን አውነትን እየተነጋገርን እንደሆነ ይሰማኛል፡፡ ጥሩ ብሂል አለን፡፡ “ሆድን በጎመን ቢደልሉት፣ ጉልበት በዳገት ይለግማል፡፡” የምናገረው መርዶ አለኝ፡፡ ዕድሜ ለደርግና ለወያኔ የጥፋት ድርጊት በሀገራችን ኢትዮጵያ ውስጥ ለጊዜው በአውሮፓና አሜሪካ ደረጃ ይቅርና በብዙዎች አፍሪካና ካሪቢያን ሀገሮች ሕዝቦች ጋር እንኳን የሚወዳደር ሕዝብ የለንም፡፡ ሁለቱ የወሮበሎች መንግሥታት ቅንጥ ቅንጣችንን ብለው ከሰውነት ተራ አውጥተውናል፤ ችግርን ማመን ለመፍትሔው በግመሰሽ መንገድ እንደመቅረብ ነው የሚባለው ትክክል ነው፡፡ በከንቱ መኮፈስ ይብቃ – የትም አላደረሰንም፤ ኩርማን እንጀራ ሆኖም የልጆቻችንን ወስፋት አልሸነገለልንም – ከሚሊዮን በላይ እንደሚገመት የተነገረውን የአዲስ አበባ ጎዳና ተዳዳሪና በረንዳ አዳሪ፣ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ጮርቃ ሕጻናት ሴተኛ አዳሪዎቻችንን ችግርና ብሶት፣ በዐረብ ሀገር ከፎቅ እየተጣሉ የሚሰቃዩ ልጆቻችንን መከራና እንግልት … አልቀረፈልንም፡፡ ጎበዝ ባልሆንነው ከምንደሰት ይልቅ በሆንነው እንናደድና የጋራ መፍትሔ እንፈልግ(የሆንነው የት ያመልጠናል?)፡፡

ስለዚህ ሕዝብ እንደገና ሊሠራ ይገባዋል፡፡ ሥነ ልቦናችን የተዋራጅነት ሥነ ልቦና ነው፤ ባህላችን ተበርዞ ተከልሷል፤ ልመና፣ ጥንቆላ፣ ድግምትና ትብታብ፣ የሀሰት ምሥክርነት፣ ስርቆትና ማጭበርበር፣ በሕግ ያለመተዳደር፣ፈጣሪን አለመፍራት፣ ከነባር ወግና ሥርዓት ማፈንገጥና የባዕዳኑን መከተል፣ ሃይማኖትን እንደሸቀጥና እንደሸሚዝ እንደ‹አየሩ ጠባይ› በየጊዜው መለዋወጥ፣… አስነዋሪ ከመሆን ይልቅ ከምን ጊዜውም በላይ አኩሪ ባህል እየሆኑ መጥተዋል(ቀሲስ ብርሃኑ ገ/መስቀል ሃጅ አብደላ በሚል አዲስ ስም ወደዐረብ ሀገር መጓዙን ስንሰማ በሀገራችን ላይ የወረደው መዓት ምን ያህል ግዘፍ እንደነሳና ምን ዓይነት የኑሮ አዘቅት ውስጥ እንደገባን እንረዳለን)፤ ማኅበረሰብኣዊ ንቃታችን ወርዷል፤ የ“እናቴን ያገባ ሁሉ አባቴ ነው” የተሸናፊነት መንፈስ ብዙዎቻችንን አንበርክኮናል፤ በተደጋጋሚ መንግሥታዊ በትር ተቀጥቅጠን የማንነት ጥያቄ ውስጥ የገባን ዜጎች ቁጥር ቀላል አይደለም፤ በተስፋ መቁረጥ ሳቢያ የዛሬን ነፍስ ለነገ ለማድረስ ስንል ከሞራልና ከሃይማኖት ጥያቄዎች ባፈነገጠ መልኩ የማንሠራው ሥራ የሌለን ብዙዎች ነን፤ ትላልቆች ከምንባለውም በብዙ መልኩ የጠፋን በርካቶች ነን(በሰባና በሰማንያ ዓመት ዕድሜ የአምልኮት ቦታዎች አካባቢ ወይንም በቤተ መጻሕፍት ውስጥ መገኘት ሲገባን በስኒከርና ጃፖኒ ቼቺንያንና ካዛንችስን ስናስስ ከእምቦቀቅላዎችም ጋር ስንልከሰከስ የምናድር የእንጨት ሽበቶች ሞልተናል – ልክ ልካችንን ነው የምናገር፤ ጉዳችን ብዙ ነው!)፤ በዚያና በሌሎችም ተያያዥ ምክንያቶች የተነሣ ወጣቶች በአርአያነት የሚመለከቱት ብርቅዬ ዜጋ እስከማጣት ደርሰዋል – አውላላ ሜዳ ላይ የተጣለ አሳዛኝ ትውልድ! “ዛሬ ከምሞት ነገ ልሙት” ከሚል የሆዳሞች ፈሊጥ በመነሳት በልባችን እየሳቅን በገጽታችን የምናለቅስ ወይም በልባችን እያለቀስን በገጽታችን የምንስቅ በርካቶች ሆነናል፡፡

በትምህርቱ ዘርፍ ያየን እንደሆነ በአንጻራዊ ሁኔታ የሦስተኛ ደረጃ ዲግሪ ምናልባት ሻል ይል እንደሆነ እንጂ በመጀመሪያና በሁለተኛ ዲግሪዎች የሚመረቁ ወጣቶች ደርግ ወታደራዊ ማዕረጎችን በለብ ለብ የጥቂት ሣምንታት ሥልጠና ‹ከዚህ መልስ መቶ አለቃ፣ ከዚያ ወዲህ በመለስ ሻምበል፤ ከዚህ እንዲህ ወዲያ ጀምሮ ሻለቃ› እያለ በርዕሰ ብሔሩ በትረ መኮንን እየሰቀሰቀ ያስመርቅ ነበር እንደሚባለው ሁሉ(ቀልድ አዘል እውነት ነው) የወያኔ ዩኒቨርስቲዎችም በተመሳሳይ ሁኔታ ራሳቸውን እንኳን በእንግሊዝኛ በአፍ መፍቻ ቋንቋቸውና በሥራ ቋንቋቸው በአግባቡ መግለጥ የማይችሉ፣ በሥራ ገበታቸው ላይም ያንጀትን የማያደርሱ ምሩቃንን እየፈለፈለ ሀገር ምድሩን ከመሙላት በስተቀር በሀገር ግንባታ ረገድ ወሳኝ ሚና የሚጫወቱ ምሁራን አሉን ማለት የማንደፍርበት ወቅት ላይ ነን፡፡ ኅሊናውን ለሰንካላ ዓላማና ለሆድ የሸጠ ምሁር፣ ሃይማኖቱን ለሥጋዊ ጥቅሙና ፍላጎቱ የለወጠ የሃይማኖት አባትና ካህን በተጥለቀለቀባት ሀገር ውስጥ እያየን ያለነው ማኅበረሰብኣዊ ድራማ የሚዘገንንና የሕዝብ ያለህ የሚያስብል ነው፡፡ ስለዚህ ሕዝብ እንደገና መሠራት አለበት፡፡ ሕዝብን ለመሥራት ወይም ለመፍጠር ግን ሠሪው ወይም ፈጣሪው አስቀድሞ ራሱን መፈተሽ አለበት፡፡ ማን ነው ለዚህ ትልቅ ተግባር የተዘጋጀ?

ሕዝብን ማን ይሥራ? ሕዝብን የመፍጠር ኃላፊነት ያለበት ራሱ ሕብዝና በላዕላይ የዕውቀት ደረጃ የሚገኙ ዜጎች ናቸው፡፡ ሕዝቡ ሲባል በተለይ ወጣቱ ሀገሩን ማወቅ፣ ነባር ማኅበረሰብኣዊ ዕሤቶችን ማጥናትና መረዳት፣ የመልካም ሀገራዊ የሥነ ምግባር ኮዶችን እየመረመሩ ለነሱ በሚጠቅም መልክ እያረቁ መመለስ፣ ትህትናንና ታላቅን የማክበር ዕውቀትን የመሻት ጠባይን ማጠንከር… ይገባዋል፡፡ ከተያዘው የአሥረሽ ምቺው መጤ ባህልና ወረርሽኝ ባፋጣኝ ወጥቶ ወጣቱ ኢትዮጵያዊ ቅርጽና ይዘት እንዲኖረው መሠራት ይኖርበታል፡፡ አለቅጥ እየተወነጨፈ ያለውም የሕዝብ ብዛት በዘመናዊ የሥነ ሕዝብ ፖሊሲ አንዳች መፍትሔ ሊበጅለት ይገባል፡፡ በሁሉ የሙያ መስክ ታፍነው የሚገኙ ዐዋቂና ምሁራን ዜጎች መለቀቅ አለባቸው፤ ከያሉበትም መውጣትና ፖለቲካውን እንዳሻቸው የሚያቦኩትንና የሚጋግሩትን ወገኖች ሃይ ማለት ይጠበቅባቸዋል፡፡ ዕውቀት ያላቸው ዜጎች አሉን – አድማጭ ግን አጡ፡፡ ጠብንጃ መሪ በሆነበት ሁኔታ ንግግር ዋጋ ስለሌለው እንጂ እህ ብለን ብናዳምጣቸው ብዙ ዕውቀትና ችሎታ ያላቸው ዜጎች ከየስርጓጉጡ ይወጣሉ – በውጭ ሀገራትማ ብዙ አሉን፡፡ ሁኔታዎች አመቺ ባለመሆናቸው እንጂ ሀገራችን የወላድ መካን አይደለችም፡፡ አሁን ግን ይፈራሉ፡፡ ለነፍሳቸው ይሳሳሉ፡፡ ቢናገሩ እንደሚያልቁ ይረዳሉና በ‹ከነገሩ ጦም እደሩ› ተሸሽገው ይኖራሉ፡፡ የተመቻቸ ሁኔታ ሲፈጠር ግን ከየተደበቁበት ይወጣሉ፡፡ እነዚያን መጠቀም ይኖርብናል፡፡ እንደገና ይሠሩናል፤ እንደቀራፂ አበጃጅተው የተሟላን ሕዝብ ያደርጉናል፡፡ ዋናው ሊሰመርበት የሚገባን ግን አቅጣጫ የሚያሳየንና እንደሙሤ ከግዞት አውጥቶ ወደእውነተኛዋ ኢትዮጵያ የሚወስደን አዲስ እርሾ የሚያስፈልገን መሆናችንን መረዳት ነው፡፡ ከፍ ሲል ለመጠቆም እንደሞከርኩት ይህ እርሾ በቅድሚያ ራሱን ሊያጸዳ ይገባዋል፤ ባጣናቸው መልካም ነገሮች የተሞላ መሆን አለበት እንጂ በሽብልቅ መልክ እየገባ እንደአዲስ እንዲያመናቅረን አይደለም – ስለሆነም ማወቅን ያስቀደመ ጥምጣም በየጭንቅላታችን እንዲኖር ሁላችንም መጣር ይገባናል፡፡ መነሻችን ታዲያ የተመረጡ የቆዩ መደላድሎች ሊሆኑ ይገባል፤ ከዜሮ መጀመር መቅረት አለበት፡፡ ከጥንቱም ከአሁኑም ደግ ደጎቹ ጎኖች ተመርጠው በአዲስ መነሻነት ይጠቅሙናል፡፡ ምክንያቱም ከእምሃበ አልቦ ምንም ዓይነት አዲስ ነገር መፍጠር ያስቸግራልና፡፡ ጅምላ ጥላቻና ጅምላ ፍረጃ ደግሞ መቅረት አለበት፡፡ ‹የነሱ ከሆንክ የኛ አይደለህም› ወይም ‹የኛ ከሆንክ የሌላ የማንም ልትሆን አትችልም› ዓይነት ደርጋዊና ወያኔያዊ አስተሳሰብና አመለካከት በሁለንተናዊ የአወንታዊ አስተሳሰብ ተቀይሮ ሁሉም የአንዱ አንዱም የሁሉ ሊሆን የሚችልበት መልካም መስተጋብር ሊፈጠር ይገባዋል፡፡ ይህ መፈራረጅ የሚሉት ጣጣ ለብዙ ውጣ ውረድ ዳርጎናልና በፍቅርና በመተሳሰብ ከመሳሳብ ውጪ አንዱ አንዱን ፎሪ ለማስወጣት የሚደረግ የመካን አስተሳሰብ ውጤት አሁኑኑ መቅረት ይኖርበታል፤ በፍጹም ስለማይጠቅም፡፡ እነሱና እኛ እየተባባልን ዘመናት ዘለቅን፡፡ ግን ምን ተጠቀምን? ምንም! ችግራችን ይብስ እየተመነገገ ዓለም ጉድ እስኪለን ድረስ ለትዝብት ተጋለጥን፣ የችግሮቻችን መንስኤዎችም ለጊዜው ተጠቀሙብን እንጂ እኛ ተራ ዜጎች ያገኘነው አንዳችም ነገር የለም፤ መጣላትና መናቆር ሰላምንና ዕድገትን ቢያመጣ ኖሮ ኢትዮጵያችን ዛሬ በነአሜሪካን አናት ላይ ቂብ ብላ የዓለም ንግሥተ ነገሥታት በሆነች ነበር፡፡

ጥሩ ጥሩ ሰዎቻችን ባገኙት መንገድ እየሾለኩ የባዕዳን ሀገሮች አገልጋይ ሆነው ቀሩ፡፡ እቤት ያለውም የመውጫ ዕድሉን በማፈላለግ በሀገሩና በሌላ በማያውቀው ሀገር መካከል ሕይወቱን በምናብ ሰንቅሮ ትርጉም ያለው ሕይወት ሳይመራ በማከያው ሕይወቱ ታልፋለች፡፡ ከዚህ የባሰ የትውልድ ውርደትና መረገም የለም፡፡ ይህ እንዲቀር ፈጣሪ የጀመረውን ሰማያዊ አብዮት ወደ ምድር እናውርደውና በእገዛችን ለእኛ ወደሚጠቅም የጋርዮሽ ማዕድ እንለውጠው፡፡ በዘርም ሆነ በሃይማኖት እየተቧደንን እንደእስከዛሬው ብንቆራቆስ ከሕዝብነት ወደ ኢ-ሕዝብነት የሚያወርደንን መንገድ ተከተልን እንጂ አልተጠቀምንም፡፡ ለማንኛውም እግዚአብሔር ይርዳን፡፡ እኛም ልቦና ይስጠን፡፡ ፍቅርን እንደሸማ ያላብሰን፡፡ በመካከላችን ገብቶ ያናጨን ያጋጨን የነበረውን የአጋንንት መንፈስ ብትንትኑን ማውጣቱን እንደጀመረ ሁሉ በዚያ ምትክ የፍቅርና የመተሳሰብ መንፈስን ይዝራብንና ጓደኞቻችን ወደደረሱበት ታላቅ የሥልጣኔና የዕድገት ደረጃ ለመድረስ ያብቃን፡፡

Yiheyisaemro@gmail.com

Happy
Happy
0 %
Sad
Sad
0 %
Excited
Excited
0 %
Sleepy
Sleepy
0 %
Angry
Angry
0 %
Surprise
Surprise
0 %
    Print       Email
  • Published: 12 years ago on October 27, 2012
  • By:
  • Last Modified: October 27, 2012 @ 10:59 am
  • Filed Under: Ethiopia
  • Tagged With:

Average Rating

5 Star
0%
4 Star
0%
3 Star
0%
2 Star
0%
1 Star
0%
<"Without the support of our readers, the Maleda Times website would not exist in its present form">

You might also like...

በሰሜን ሸዋ ዞን ኤፍራታ እና ግድም ወረዳ መከላከያ ከአማራው ማህበረሰብ እና ከፋኖ ጋር ጦርነት ገጥሟል

Read More →

This site is protected by wp-copyrightpro.com

Skip to toolbar