www.maledatimes.com ስርዓተ አልበኝነት የነገሰበት የግብይት ስርዓት ና የኑሮ ውድነት - MALEDA TIMES
Loading...
You are here:  Home  >  Ethiopia  >  Current Article

ስርዓተ አልበኝነት የነገሰበት የግብይት ስርዓት ና የኑሮ ውድነት

By   /   October 27, 2012  /   1 Comment

    Print       Email
0 0
Read Time:36 Minute, 20 Second
የኑሮ ውድነት፣ የመግዛት አቅም መዳከም፣ የአቅርቦት መመናመን፣ የጥራት መጓደል፣ ስርዓተ አልበኝነት የነገሰበት የግብይይት ስርዓት አጅበውት የመጡት ኢኮኖሚያዊ ችግሮች የኑሮአችን አካል ከሆኑ ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ እነዚህ ኢኮኖሚያዊ ችግሮች ከስጋትነት አልፈው የእለት ተእለት መወያያ ርእሳችን ከሆኑም ሰነባብተዋል፡፡ መሽቶ በነጋ ቁጥር ኑሮአችንን መሸከም አቃተን፣ ቤተሰብ በቅጡ መምራት አዳገትን የሚሉት መሰረተ ሰፊ የሕዝብ ጥያቄዎችና ሮሮዎች መፍትሄ አጥተው በስፋት መሰማታቸውን ቀጥለዋል፡፡ መንግስትም ኢኮኖሚያዊ ቀውሱን በማመን መንስኤው በመካሄድ ላይ የሚገኘው ሰፋፊ የመሰረተ ልማት ግንባታ በመሆኑና ስርዓቱም የሚገለፀው በዚሁ ፍልስፋና በመሆኑ መፍትሄው አሁንም ልማቱን ማስቀጠል ብቻ እንደሆነ ተደጋግሞ እየተነገረን ይገኛል፡፡ መሰረታዊው ጥያቄ ግን የችግሩን መንስኤ በተዛባ መልኩም ቢሆን መቅረቡ ብቻ ሳይሆን መልስ አሰጣጡ ሸክሙን እስከመቼ መሸከም እንደሚገባና ሸክሙ ቀለል የሚልበት መዳረሻ የት ጋ እንደሆነ የሚጠቁም የመንግስት ባለሙያ ወይም ሹመኛ አለመኖሩ ጭምር ነው፡፡ ብቻ ነጋ ጠባ በትእግስት ጠብቅ ከሚል ፕሮፓጋንዳ ውጭ ጠብ የሚል መፍትሔ ማምጣት አልተቻለም፡፡

ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ቀውስ የቱንም ያህል የገዘፈ ቢሆንም ቅሉ እንደመፍታሄ የሚቸረን ቀውሱን ያለጥያቄና ያለማንገራገር ተቀብልን፣ ከመሰረተ ልማት ግንባታው ጋር መትመም ብቻ ነው፡፡ ገቢያችን እንደ ግመል ሽንት ወደኋላ ይገሰግሳል፡፡ የኑሮ ውድነትና ኢኮኖሚያዊ ምስቅልቅሉ ከመሰረተ ልማት ግንባታው እኩል በፍጥነት ሽቅብ ይተማል፡፡ መንግስት ስር ነቀል ለውጥ የሚያመጣ መፍትሄ ከመሻት ይልቅ፣ ከአስር ዓመት እልህ አስጨራሽ ኢኮኖሚያዊ ትንቅንቅ በኋላ ዛሬም ግድ የለም፣ እመኑኝ በሚል የማይቆረጠም መፈክር ስር ማብቂያ በሌለው የኑሮ ውድነትና ግሽበት ውስጥ ኑሮአችንን እንድንገፋ በማበረታታት ላይ ይገኛል፡፡
እስከአሁን ድረስ እንዴት እንደሆነ ማስረዳት ባይችሉም፣ ልማቱ ኢኮኖሚያዊ ቀውሱን አንድ ቀን ይፈታዋል በሚል ማስተማመኛ ቃል ኑሮን እየገፋን እንገኛለን፡፡ በምን መንገድ ልማቱ የኑሮ ውድነቱና ግሽበቱን መቼና እንዴት? በከፊል ወይም በሙሉ ሊፈታው እንደሚችል ፍንጭ ማግኘት ግን አልተቻለም፡፡ መኖር እያዳገተን ችግርን እንድናውልና እንድናሳድር ከመምከርና ቃል ከመግባት ገፋ ሲልም አፈጻጸምን ከመራገም በስተቀር አዙሮ ሊደፋን በተቃረበው የኑሮ ውድነት ላይ መንግስትም ሆነ አስፈጻሚዎቹ በግልም ሆነ በጋራ ኃላፊነት በመውስድ ከስህተታቸው ተምረው፣ አዲስ ስልት ሲቀይሱ ማየት አልተቻለም፡፡ ዛሬም ዜማው “ተው ቻለው ሆዴ!” ነው፡፡
ኢህአዴግ የኑሮ ውድነትና ግሽበትን ተቆጣጥሮ ልማትን ማስፈን የሚያስችል ኢኮኖሚያዊ ፖሊሲ መቀየስ አለመቻሉን ተቀብሎ እውነታውን በመጋፈጥ፣ የተሻለ ፖሊሲ ከመቀየስ ውጭ አቋራጭ መንገድ እንደሌለው ለመረዳት እጅግ ዘግይቷል፡፡ ከሃያ አንድ ዓመት አስተዳደር በኋላ ዛሬም በድህነት ስለመማቀቃችንና ኑሮአችን የተመሰቃቀለበት ምክንያቱ የቀድሞው ስርዓት ያስረከበን ባዶ ካዝና ነው ከሚል ስንኩል ያረጀና ያፈጀ ምክንያት መላቀቅ አልቻለም፡፡ ለኢኮኖሚያዊ ቀውስ መነሻ የነበረውና ከሩብ ምዕተ ዓመት በፊት የፈረሰው ስርዓት አስተዋፅኦ ከጊዜና ከሂደት ጋር ሞቶ እየተቀበረ ነው፡፡ ዛሬ ለምንገኝበት ኢኮኖሚያዊ ቀውስ ሃገርን በማስተዳድር ላይ ከሚገኘው መንግስት በላይ ሌላ ተጠያቂ ከየትም ሊፈበረክ አይችልም፡፡ ደርግ ለኢኮኖሚያችን ውድቀት የቆሰቆሰው ጦርነት ለኢኮኖሚያዊ ውድቀቱ ምክንያት የሆነውን ያህል ለኑሮአችን መመሳቀልና ለግሽበት ኢህአዴግ የሚከተለው የኢኮኖሚ ፖሊሲ ብቸኛ ተጠያቂ ነው፡፡ ኢህአዴግም ይህንን መቀበል አለበት፡፡ አራት ነጥብ፡፡
የአቅርቦት ችግር፣ የምርት እጥረት፣ ግሽበት፣ የኑሮ ውድነትና መሰል ኢኮኖሚያዊ ችግሮች መንስኤያቸው የመንግስት ፖሊሲና እቅዶች ድክመት ከመሆን ውጭ ሌላ መጠርያ ሊኖራቸው አይችልም፡፡ ግሽበትና የኑሮ ውድነት እንደ መንፈስ በድንገት የሚከሰቱና በትእግስት ስለጠበቅናቸው የሚሰወሩ አይደሉም፡፡ ለኑሮ ውድነት መንስኤ የሆነውን መሰረታዊ ችግር ከመፍታት ይልቅ የማያጠግቡ ፖሊሲዎችንና እቅዶችንም በመጣፍ ዘለቄታ ያለው መፍትሄ ማምጣት አይቻልም፡፡ ሰሞኑን የተከበሩ ጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማርያም ደሳለኝ ለተከበረው ምክር ቤት በሰጡት ኢኮኖሚያዊ ትንታኔ ላይ፣ ከዚህ ቀደም ያልታዩ ትንታኔዎች ሰምተናል፡፡ አካፋን አካፋ ለማለት የሄዱት ርቀት የሚያስደስት ነው፡፡ ዘይትና ስንዴ ለዓመታት በድጎማ እያስመጡ መቀጠልን የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ እንዴት ሊሸከመው እንደሚችልና የውጭ ምንዛሪው ከሌላ አስፈላጊ አቅርቦት ላይ እየተቀነሰ እንደሆነ ሊያስረዱን አልደፈሩም፡፡ በከፍተኛ ወጭ የሚሸመተውና የሚረጨው ስንዴም በኢህአዴግ ፖሊሲ ልዩ ጥበቃ የሚደረግለት አርሶ አደር ያመረታትንም ያህል ወደ ገበያ አላመጣ በማለቱ፣ የተከሰተውን የአቅርቦት መመናመንና የዋጋ ንረት ለማውረድና አርሶ አደሩ ምርቱን እንዲያወጣ ለማስገደድ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ የኛም ጥያቄ ለአቅርቦት መመናመን ቀጥተኛው ምክንያቱ አርሶ አደሩ ቢመስልም ይህንን ስልጣን እንዲቀዳጅ የተደረገው የሃገሪቱ የምርት አቅርቦት ስርዓቱ አርሶ አደሩን ለመከላከል በሚል መፈክር ስር በገበያ ስርዓት እንዳይመራ በመደረጉ እንደሆነ ግልጽ ነው፡፡ መለስተኛና መካከለኛ ሜካናይዝድ እርሻዎች በሃገር በቀል አራሾች አማካኝነት እንዳይስፋፉ ኢህአዴግ መፈለጉና የተፈቀደ ግን የማይተገበር እንዲሆን የተለያዩ ቀጥተኛና ቀጥተኛ ያልሆኑ መሰናክሎች በአስፈሚዎች መቀፍቀፋቸው ለዚህ ችግር መንስኤ ተጠቃሽ ምክንያት ነው፡፡
ጠቅላይ ሚኒስቴር ሃይለማርያ ደሳለኝ፤ ግሽበት ወደ 18 ፐርሰንት መውረዱንና እድገታችን በ11 ፐርሰንት እንደሚያድግ ተንብየዋል፡፡ እሰየው!! ትንቢታቸው እንዲሰምር ምኞቴ ነው፡፡ የሚያነጋግረን ቁም ነገር ግን ይህ ብቻ አይደለም፡፡ 18 ፐርሰንት ወርሃዊ ግሽበት ቋሚ ገቢ ባለውና ደሞዙ በማያድግ ሕዝብ ውስጥ መሆኑን በነካ እጃቸው ባስረዱን ደግ ነበር፡፡ የዛሬ አመት ከ800 እስከ 1000 ይጠራ ነበረው የጤፍ ዋጋ ዛሬ 1600 ብር ነው፡፡ ዛሬም የሰራተኛው ደሞዝና የአርሶአደሩ ገቢ እዛው የዛሬ አመት በነበረበት ላይ ነው፡፡ በአንድ አመት ውስጥ የጤፍ ዋጋ በአማካይ 60 ፐርሰንት ሲያድግ የማህበረሰቡ ገቢ ባለበት ይገኛል፡፡ ወይም በዚሁ ምርት ላይ የማህበረሰቡ የመግዛት አቅም በ60 ፐርሰንት አሽቆልቁሏል፡፡ እሳቸው እንዳሉት ካለፈው ወር ወደዚህ ወር ስንሸጋገር፣ አብዛኛው ምርት ላይ ከፍተኛ ጭማሪ አልታየም ይሆናል፡፡ ጤፍም ምስርም ሽሮም በርበሬም ከዛሬ ወር በፊት በነበሩበት ዋጋ ላይ ተገኝተው ይሆናል፡፡
አንድም ከፍተኛ የዋጋ ንረት ቋሚ ገቢ ያለውንና የመግዛት አቅሙ ወትሮውንም የተመታው ከገበያ እያወጣው በመሆኑና ግብይይት በመቀነሱ ዋጋ ባለበት ቆሟል አሊያም በሁለቱ ወራት መካከል የተከሰተው የዋጋ ንረት እዚህ ግባ የሚባል ስላልሆነ ወርሃዊ ግሽበቱ እንዲቀንስ አንዱ ምክንያት ሆኖ ሊታሰብ ይችላል፡፡ ጥሬ እውነታው ያለው ግን ወዲህ ነው፡፡ አይኑ እያየ በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ የሸቀጣ ሸቀጥ ዋጋ ከ45 እስከ 100 ፐርሰንት ለጨመረበት በስልትና በተጠና አቀራረብ የተነረገው የግሽበት ቅንስናሽ ሊቆረጠምለት አይችልም፡፡ ቋሚ ገቢው እዛው እየዳከረ፣ የአቅርቦቱ ዋጋ ሰማይ እንደወጣ ተሰቅሎ በቀረበት ሁኔታ ውስጥ ሆኖ በሰቀቀን ዋጋዉን አንጋጦ እየተመለከተ ሳለ፣ በተቀመረ ስሌት ስለ ግሽበት መቀነሰ መናገር ቢቻልም ውጤቱ ከማሸማቀቅ አያልፍም፡፡
የማህበረሰቡን ችግር ለዘለቄታው ከመፍታት አኳያ እዚህ ግባ የሚባል ሚና ባይኖራቸውም ከሊቢያ ጀምሮ በርካታ የአፍሪካ መንግስታት የዓለም አቀፍ ማህበረሰብን ያስደመሙ ፖሊሲዎች፣ እቅዶችና ፕላኖችን ሲቀረጹ ማስተዋል ተችሏል፡፡ ኢኮኖሚያዊ ቀውሶች ውስብስብ ከሆኑ ፖሊሲ፣ እቅዶችና ጥናቶች በተጨማሪ ቅድመ ዝግጅት፣ ትኩረት፣ የእለተ ተእለት ክትትል፣ የማስፈጸም ብቃት፣ ቁርጠኝነት በተለይ ደግሞ በሕዝብ ሃብት እራሳቸውን ከሚያደልቡ አስፈጻሚዎች የጸዳ ንፁህ እጅ ይሻል የሚል ጽኑ እምነት አለኝ ፡፡
በዚህ ጽሁፌ የኢህአዴግን የልማታዊ መንግስት ኢኮኖሚ ፖሊሲዎችና ችግሮቻቸውን ለመፈተሽ አልሞክርም፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ በቂ ጊዜ ተወስዶ ውይይት ሲካሄድበት ኖሮአል፡፡ ካስፈለገም ወደፊት ልመለስበት እችላለሁ፡፡ ግሽበቱ ወደ ችግር እያዳፋ እየወሰደን እንደሆነ ለመረዳት ከተፈለገ ከኢኮኖሚ ፍልስፍና ትንተናዎች በላይ ያለንበት ኢኮኖሚያዊ ምስቅልቅል ፍንትው አድርገው የሚሳዩን እውነታዎች የእለት ተእለት ኑሮአችንን የምንገፋበትን ሁኔታን ነው፡፡
ከላይ ለማንሳት እንደሞከርኩት በልማትና (Economic Development) በእድገት (Economic growth) እንዲሁም በግሽበት (Unadjusted inflation) ዙርያ የሚጠቀሱ ቁጥሮችና ፐርሰንቶች አንዳንዴም ፈገግ የሚያስደርጉ፣ አንዳንዴም የሚያስደምሙ በመሆናቸው በቁጥሮቹ ላይ ክርክር ማካሄዱ የመፍትሄው አካል ለመሆን የሚያግዝ አይደሉም፡፡ ኢህአዴግ ከፍ ከፍ ያሉ አመላካች ቁጥሮችንና ፐርሰንቶችን አይ.ኤምኤፍና ወርልድ ባንክ ሲዘግቧቸው፤ ኢኮኖሚያዊ ትንታኔውና ምንጩ የኒዮሊበራሎች አስተሳሰብና የትንተና ውጤት ቢሆንም ስሌቱንም ሆነ ስልቱን እንደ መረጃና የዘገባ ማጠናከርያነት ከመጠቀም ወደ ኋላ አይልም፡፡ ውጤቱ ኢህአዴግ ከሚፈልገው አመላካች ቁጥርና ፐርሰንታይል ወጣ ካለ ግን አምና ምስክር የነበሩት ዓለም አቀፍ ተቋማትና ድርጅቶች ዘንድሮ በልማት ምቀኝነት መፈረጃቸው የተለመደ ነው፡፡
ይህ ሁሉ በቁጥር፣ በስሌትና በሰንጠረዥ የማሳመንና የሌለ ዳቦ የማጉረስ አባዜ እንደተጠበቀ ሆኖ፣ በእኔ እምነት ዛሬም የሕዝቡ ጥያቄ በማያወላዳ መልኩ እየቀረበ ነው፡፡ ጥያቄውም ፈረንጆቹ እንደሚሉት (where is the beef?) ወይም “ስጋው ወይም ዳቦው የታለ?” የሚል ነው፡፡
ኢህአዴግ የተለየ መረጃ የሚጠቅሱትን ማሸማቀቁ የተለመደ እንደሆነ አውቃለሁ፡፡ ዛሬ ኢትየጵያ ያለችበት ኢኮኖሚያዊ እውነታን በቁጥር ማስቀመጥ ይቻላል፡፡ በተለይ አይ.ኤምኤፍ በተለያዩ ሃገራት ላይ ኢኮኖሚያዊ ትንታኔ የሚያደርጉ ድርጅቶች እ.ኤ.አ በሰኔ ወር 2012 ላይ ባወጡት ዘገባ መሰረት፤ የኢትየጵያ አጠቃላይ ሃገራዊ ምርት እድገት ወደ ስድስት ፐርሰንት እንደሚያሽቆለቁል ተንብየዋል፡፡ የሚያስደስት ዜና ባይሆንም በኢኮኖሚያዊ ትንታኔ ላይ የተመሰረተ ዜና ነው፡፡ የተከበሩ ጠቅላይ ሚኒስቴር ሃይለማርያም ደሳለኝ ደግሞ የ11 ፐርሰንት እድገትን ተንብየዋል፡፡ በወቅቱ በወጣው ዘገባ ላይ፣ ለሃገሪቱ እድገት ማሽቆልቆል በምክንያትነት ከተነሱት ነጥቦች መካከል በዋነኛነት የተወሳው ደግሞ ግሽበትና ከፍተኛ የሆነ መንግስት ከብሄራዊ ባንክ የሚወስደው የሃገር ውስጥ የገንዘብ ብድር ነው፡፡ አዙሪቱ ግልጽ ነው፡፡ የግሽበቱ አይነተኛ መንስኤ ዝቅተኛ የምርት እድገትና የምርት አቅርቦት፣ ከፍተኛ የገንዘብ ስርጭት፣ ዝውውርና ሕትመት ሲደመር ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታቸው ያልተረጋገጠ፣ ከፍተኛ የገንዘብ ወጭን የሚጠይቁ፣ ለሙስናና ለብክነት የተጋለጡ የመሰረተ ልማት ግንባታዎችንና የስራ እድል ፈጠራ በሚል ስም የሚተገበሩ ለእድገት አስተዋጽኦ የሌላቸው ስራዎችን ፋይናንስ ማድረግ ነው፡፡
አለም አቀፍ የገንዘብ ድርጅት ዘገባውን ሲያቀርብ፣ ግሽበቱ 40 ፐርሰንት ደርሶ ነበር፡፡ በርካታ ዓለም አቀፍ የመረጃ አደራጅ ተቋማት፤ ኢትዮጵያ የምትገኝበት የድህነት ደረጃ ከታች ወደ ላይ ሲለካ ከአንድ እስከ አምስት በሚገኙ ሃገራት ተርታ የሚያስቀምጧት ሲሆን ግሽበቱን ደግሞ ከላይ ወደ ታች ሲለካ 52.4 ፐርሰንት ካስመዘገበችው ቤላሩስ ቀጥሎ በ33.2 ፐርሰንት በሁለተኛ ደረጃ ያስቀምጧታል፡፡ ይህንን ሪፖርት ተክትሎ በመንግስት በኩል የተሰጠው ማብራሪያ፤ ከኢኮኖሚያዊ መለኪያዎች አኳያ አፈጻጸሙ እንዴት እንደሆነ ማወቅ ባይቻልም የተባለውን አመታዊ እድገቱ ሳይታጠፍ ግሽበቱን በጥቂት ወራት ምናልባትም በሶስት ወራት ውስጥ ወደ አንድ ዲጂት እንደሚያወርደው ተገልጾ ነበር፡፡ ይህ እንግዲህ ከሆነ ዓመታት አልፎታል፡፡ ግሽበቱም አለ፤ የኑሮ ውድነቱም ቀጥሏል፡፡ ከላይ የቀረበውን ትንታኔ ላጤነውና እንደ ኢህአዴግ ፍላጎት ከሆነ በወቅቱ የታቀደው ግሽበቱን ወደ አንድ ዲጂት አውርዶ የመሰረተ ልማት ግንባታውን አሁን ባለበት መጠን ማስቀጠል መቻል ነበር፡፡ ይህ ማለት ደግሞ ኬኩን በልቶ ኬኩን ለማቆየት ከመመኘት ያለፈ ትርጉም እንዳልነበረው ዛሬም ከግሽበቱ መቀጠል ጋር በማነጻጸር መተንተን ይቻላል፡፡
ስር ነቀል ኢኮኖሚያዊ ልማትን ብቻ ሳይሆን ስር ነቀል ኢኮኖሚያዊ እድገትን፣ በኑሮ መሻሻልን ለማረጋገጥ ስንጠብቅ ዓመታት አልፈውናል፡፡ ዛሬ ልማቱ እየተጓዘ ያለበት መንገድ በሌላ ወቅት የምመለስበት ይሆናል፡፡ አጠቃላይ የተስተካከለ ግሽበቱን (Adjusted inflation) ግን እንደተባለው ወደ አንድ ዲጂት መወረዱ ቢቀር እንኳን ባለበት ለማቆምም አልተቻለም፡፡ በስታትስቲክስ ቢሮ ዘገባ መሰረት፤ እ.ኤ.አ በሰኔ ወር 30 ፐርሰንት አካባቢ የነበረው ግሽበት በሀምሌ ወር ወደ 40 ፐርሰንት ገደማ አድጓል፡፡ የሰኔ ወር ግሽበት ከሐምሌ ወር ጋር ሲነጻጸር በከፍተኛ ሁኔታ ጨምሯል፡፡ በተቃራኒው ደግሞ የመስከረሙ ወር ደግሞ ወደ 18 ፐርሰንት አሽቆልቁሏል፡፡ ለግሽበቱ ማሽቆልቆል ምክንያት የለኝም፡፡ የጥናቱም ባለቤት በቂ ትንታኔ አላቀረበም፡፡ መንስኤው እንቆቅልሽ ቢሆንም ከግሽበቱ መቀነስ በኋላም ቢሆን የምግብና የጤፍ አቅርቦቶች ዋጋ ንረት እንደቀጠለ ነው፡፡ የከብት ስጋ ዋጋ አልቀመስ ካለና የሽቅብ ጉዞውን ከተያያዘው ከርሟል፡፡
ሰሞኑን ደግሞ ተራው የጥራጥሬና የበግና ፍየል ሆኗል፡፡ ይህ የሚያሳየው ግሽበቱ አቅማችንን ከመፈታተን አልፎ የማርያም መንገድና መሸሸጊያ እያሳጠን መሆኑን ነው፡፡ አኗኗራችንን ማስተካከልም ሆነ ከስጋ ወደ ሽሮ፣ ከከብት ወደ በግ ማፈግፈግ አልተቻለም፡፡ ይህ ለምን ሊሆን እንደቻለና ይህንኑ ውጣ ውረድ እስከመቼ መታገስ እንዳለብን መልስ ሰጭ የለም፡፡ የስታትስቲክስ ቢሮም ቢሆን ስለፐርሰንቱ መጨመርና መቀነስ፣ አልፎ አልፎም የትኞቹ ምርቶች እንደጨመሩ ከመግለጽ ውጭ የጭማሪው መንስኤ ምን እንደሆነና እንዴት እንደሚቀለበስ መልስ የለውም፡፡
ሃገራችን ውስጥ ያለው የተዛባ የመረጃ አቅርቦትና እጥረት እንደተጠበቀ ሆኖ በእርግጠኝነት መናገር የሚቻለው ነገር ቢኖር፣ ከሰኔ ወር ወደ ሀምሌ ወር ስንሸጋገር የገዢውና የተጠቃሚው ቁጥር በግሽበቱ ልክ አለመጨመሩንና ምርትም አለማሽቆልቆሉን ብቻ ነው፡፡ ታድያ ግሽበቱና ኑሮ ውድነቱ እለት ከእለት የሚያሻቅበው ለምን ይሆን? ይህ የሕዝብ ጥያቄ አግባብነት ያለውና በቅጡ በኢህአዴግ በኩል መመለስ ያለበት ይመስለኛል፡፡
ኢኮኖሚውን ለማሳደግ ሲባል በርካታ ጊዜያዊ መፍትሄዎች፣ ነገር ግን በረጅም ጊዜ ውስጥ የሃገሪቱን ኢኮኖሚ ለውጥረት የሚዳርጉ በችግር ፈችነት ተግባር ላይ ውለዋል፡፡ እነዚህ መፍትሄዎች የትም አላደረሱንምና ምናልባትም ከታች ከዘረዘርኳቸው መካከል አንዱ በተናጠል ብቻውን ወይም አብዛኞቹ በድምር አሊያም ሁሉም በጥቅል ለአጠቃላይ ችግሮቻችን ምክንያት ሊሆኑ ይችላሉና መፍትሔ ሊሰጣቸው ይገባል የሚል እምነት አለኝ፡፡
ከመጀመርያ ረድፍ ውስጥ ከሚጠቀሱት መካከል፣ መንግስት የበጀት ጉድለቱን የሚደጎምበትን መንገድ ለማረም ቃል በገባው መሰረት፣ ከብሄራዊ ባንክ ገንዘብ መበደርን አለማቆሙ፤ በሙስናና በዘረፋ ኢኮኖሚው ውስጥ የሚፈሰው የገንዘብ መጠን የግብይይት ስርዓቱን እያዛባው መሆኑ፤ የሃገሪቱ የውጭ ብድር ኢኮኖሚው ሊሸከመው ከሚችለው በላይ ስለተለጠጠ፤ የውጭ ብድሮች ወለድ ከፍተኛና የክፍያ ዘመናቸው አጭር መሆናቸው ሊጠቀሱ ይችላሉ፡፡ የግብይይት ስርዓታችን ኋላ ቀር በመሆኑና “ስግብግብ ነጋዴዎች” መብዛታቸው፤ የአምራቾች ህብረት ስራ ማህበራት የአርሶ አደሩን የምርት አቅርቦት በብቸኝነት በመቆጣጠራቸውና ብቸኛ ዋጋ ተማኝ በመሆናቸው፤ በስራ እድል ፈጠራ ስም ለምርታማነትም ሆነ ለምርት እድገት ቀጥተኛ ጠቀሜታ የሌላቸው የስራ እድሎችን መንግስት በስፋት ፋይናንስ እያደረገ የመግዛት ፍላጎትንና አቅምን ብቻ ከሚገባው በላይ ማዳበሩ፤ ኢኮኖሚያዊና አትራፊ ባልሆነ መንገድ ምርታማነትን ለማሳደግ የሚደረጉት ጥረቶች የምርት ዋጋ ላይ ከባድ ተጽእኖ እያሳደሩ መሆኑ፤ በሁለተኛነት ሊጠቀሱ የሚችሉ ናቸው፡፡ በመጨረሻም አብዛኛዎቹ የመሰረተ ልማት ግንባታዎች ኢኮኖሚያዊ አቅምን፣ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታን ከግምት ከማስገባት ይልቅ ቅድሚያ የሚሰጠው አጣዳፊነታቸው መሆኑና በዚህ ላይ ፖለቲካዊ ዝንባሌ መጨመሩ ሌላው ኢኮኖሚያዊ ወጥመድ ነው፡፡
በአጠቃላይ መፍትሔ ከመንግስት ሊገኝ ይችላል የሚል ትምኔታዊ ግለሰብ አይደለሁም፣ ነገር ግን መንግስት በቅድሚ የድርሻውን ማንሳትና ከሕዝብ ጋር ተቀራርቦ ለመስራት ዝግጁነቱን ማረጋገጥ አለበት፡፡ እንደሚታወቀው መንግስታት የገቡትን ቃል ማስፈጸም ሲያዳግታቸው ማየት አዲስ ነገር አይደለም፡፡ መንግስታት ቃላቸውን መጠበቅ ያልቻሉበትን መሰረታዊ ምክንያት መግለጽ አለመቻላቸው ግን ዴሞክራሲያዊ ነን ከሚሉ መንግስታት የሚጠበቅ ተግባር አይደለም፡፡ የስልጣን ባለቤትና የችግሩ ተጠቂ የሆነውን ሕዝብ ማክበርም ሆነ መፍራት የዴሞክራሲያዊ መንግስታት አይነተኛ መግለጫ መሆኑ በኢህአዴግም በኩል ተደጋግሞ መረጋገጥ አለበት፡፡ መንግስት የዜጎችን ኑሮ እያመሰቃቀለ የሚገኘውን ችግር ወቅታዊና ቀልጣፋ መፍትሄ በመስጠት መፍታት ባይችል እንኳ መፍትሔ መስጠት ያልተቻለበትን ምክንያትና በቀጣይ ለመስራት ያቀደውን ያለማሳወቅ እንዲሁም ሕዝቡ ለሚከፋውም ሆነ ለሚበጀው መዘጋጀት እንዲችል አለማድረግ በምርጫ ስልጣንን አግኝቶ ለሚያስተዳድር መንግስት ሊያሳስብው ይገባል፡፡

Happy
Happy
0 %
Sad
Sad
0 %
Excited
Excited
0 %
Sleepy
Sleepy
0 %
Angry
Angry
0 %
Surprise
Surprise
0 %
    Print       Email
  • Published: 12 years ago on October 27, 2012
  • By:
  • Last Modified: October 27, 2012 @ 11:01 am
  • Filed Under: Ethiopia
  • Tagged With:

Average Rating

5 Star
0%
4 Star
0%
3 Star
0%
2 Star
0%
1 Star
0%

One thought on “ስርዓተ አልበኝነት የነገሰበት የግብይት ስርዓት ና የኑሮ ውድነት

  1. እጅግ በጣም ጥሩ ትንታኔና ግንዛቤ ነው፡ መንግስት’ተሞክሮ’እያለ ኢኮኖሚን በካድሬ ከሚያሰራ በውጭው ዓለም እውቀት እና ልምድ ያላቸውን በኢኮኖሚው ዘርፍ ካላሳተፈ ችግር ይገጥመናል። ስለአንዲት ኢትዮጵያችን ዕድገት እና ብልፅግና ስለሕዝባችን የተሻለ ኑሮ ከፐርሰንት ወይም ከአሀዝ ድርደራ ባለፈ በተግባር ሰምቶት ብቻ ሳይሆን ኖሮበት እንዲያልፍ መልካሙን ሁሉ እንመኛለን።አይ ኤም ኤፍ ወይንም የዓለም ባንክ ሲያሞግስ፤ሲያበድር፣ ወይንም ብድር ሲሰርዝ እያደነቁ የተሳሳተ መረጃ በመስጠት ማጭበርበር ስለዕድገት በቂ መረጃ ሲጠየቅ የጠላት ወሬ,ሟርት,ዕድገታችን የማይዋጥላቸው ተላላኪዎች,እያሉ መቀሳፈት እራስን ከማሰገመት ሀገርን ከማሳፈር ህዝብን ከመናቅ ሌላ የወንበዴ ባህሪ ተብሎ ያስፈርጃል!! “ኢትዮጵያ አፍሪካ ፓወር ሀውስ ሆናለች” የሚሉትን ቧልት እናንተም ሰምታችሗል á‹°/ር ዘለዓም ተክሉ

Comments are closed.

<"Without the support of our readers, the Maleda Times website would not exist in its present form">

You might also like...

በሰሜን ሸዋ ዞን ኤፍራታ እና ግድም ወረዳ መከላከያ ከአማራው ማህበረሰብ እና ከፋኖ ጋር ጦርነት ገጥሟል

Read More →

This site is protected by wp-copyrightpro.com

Skip to toolbar