እንዳይመረትና እንዳይዘዋወር ክልከላ የተጣለበትን አደንዛዥ ዕፅ (ኮኬይን) ይዞ ለማለፍ ሲሞክር ቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ በተደረገ ፍተሻ በቁጥጥር ሥር ውሎ ክስ የተመሠረተበት ናይጄሪያዊ፣ በሰባት ዓመታት ፅኑ እስራትና በ15,000 ብር እንዲቀጣ ውሳኔ ተሰጠ፡፡

የፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ የመሠረተውን ክስ ሲመረምር የከረመው የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ስምንተኛ ወንጀል ችሎት፣ ቅጣት የጣለበት ናይጄሪያዊ ሚስተር አማቺ ስቲቭ ነው፡፡

ሚስተር ስቲቭ ከብራዚል ሳኦፖሎ ከተማ ተነስቶ ወደ አገሩ ናይጄሪያ ሲጓዝ ትራንዚት ያደረገው ቦሌ አውሮፕላን ማረፊያ ነበር፡፡ በአውሮፕላን ማረፊያው እንደ ደረሰ በተደረገ ድንገተኛ ፍተሻ 1.3 ኪሎ ግራም ኮኬይን ይዞ መገኘቱን፣ ዓቃቤ ሕግ በክሱ ማሥፈሩን የፍርድ ቤቱ ውሳኔ ያስረዳል፡፡

በድንገተኛ ፍተሻ የተገኘው መርዛማና አደንዛዥ ዕፅ በኤግዚቢትነት ተይዞ በግለሰቡ ላይ ክስ መመሥረቱንና እሱም ድርጊቱን መፈጸሙን በማመኑ፣ የጥፋተኝነት ውሳኔ መሰጠቱን ውሳኔው ይገልጻል፡፡

ፍርድ ቤቱ ተከሳሹ የቅጣት ማቅለያ፣ ዓቃቤ ሕግ ደግሞ የቅጣት ማክበጃ እንዲያቀርቡ ጠይቋቸው ዓቃቤ ሕግ ምንም ዓይነት የቅጣት ማክበጃ እንደሌለው ገልጿል፡፡

ተከሳሹ ግን የቤተሰብ ኃላፊ መሆኑን፣ በሌላ ጊዜ ምንም ዓይነት ወንጀል ፈጽሞ እንደማያውቅና መንግሥትም ይቅርታ እንዲያደርግለት በቅጣት ማቅለያነት አቅርቧል፡፡

ፍርድ ቤቱ የቀረበውን የቅጣት ማቅለያና ክሱን ሳይክድ አምኖ መቀበሉን ከግምት ውስጥ በማስገባት የቅጣት ውሳኔውን ሰጥቷል፡፡ በመሆኑም ናይጄሪያዊው በሰባት ዓመታት ፅኑ እስራትና በ15,000 ብር እንዲቀጣ ውሳኔ ሰጥቷል፡፡