የገዱ አንዳርጋቸው መግለጫ ሲተረጎም
ክንፉ አሰፋ
ኦቦ ለማ መገርሳ ህወሃት ያጎራቸውን 2,345 እስረኞች ነጻ አወጡ የሚለውን ዜና በቀኝ እየሰማን፣ የጉዱ አንዳርጋቸው መግላጫ ደግሞ በግራ በኩል ብቅ አለ። ሰበር ጋዜጣዊ መግለጫ። በርግጥም “ወገብ የሚሰብር”። ልዩ መግለጫው ተከባብዶ ሲነገረን “ገዱ ደግሞ ስንት ሺህ አማሮችን ከእስር አስለቀቀ” እያልን በጉጉት ባንጠብቅም “የኢትዮጵያ ሕዝብ እና ሕዝቦች ሆይ በወልድያ እና በቆቦ ለተፈጸመው እልቂት ተጠያቂው እኔ የምመራው ብአዴን ነው” ብሎ አረፈው።
ይህቺ ሃላፊነት የመውሰድ ዲስኩር ደግሞ አዲስዋ ቅኝት መሆነዋ ነው። ለትርጓሜዋ ቱርጁማን የማያሻት ቅኝት። ማራቶን ያሉት የአራቱ ድርጅቶች ስብሰባ እንዳበቃ አይቴ ደብረጽዮን ገብረ-ሚካኤልም ረገት ዓድርጎ ብሏታል። የናቴ ቀሚስ አድናቅፎኝ … ምናምን የምንለው ነገር የለም። ለጠፋው ጥፋት ሁሉ ሃላፊነቱን ወስደናል። ብሎ ተነግሯል። ይህንን የተናገረው በህልም ሳይሆን በውን ነበር። በአለም መገናኛ ስንሰማ ያደግነው፤ ሰላማዊ ዜጋ ላይ እንዲህ አይነት አደጋ ሲደርስ ሃላፊነት የሚወስዱት እነ ሙጃህዲን፣ እነ አልቃይዳ እነ አይሲስን ነበሩ።
ደብረጽዮን በኢቢሲ ቀርቦ ለእልቂቱ እና ለውድመቱ ተጠያቂዎቹ “እኛ ነን” ብሎናል። የጥልቅ ተሃድሶው ጥልቅ ድፍረት! ንቀትም ነው። ታድያ የፍትህ ስርዓቱን እነ ዳኛ ዘርዓይ ባይይዙት ኖሮ፣ ለጥፋቱ ተጠያቂ መሆናቸውን ያመኑት ሁሉ ማእከላዊ (ሙዝየም) ገብተው በሕዝብ ይጎበኙ አልነበር?
ገዱ አንዳርጋቸውስ ይህን ለማለት ምን ያንሰዋል? ቅርቃር እንደገባች አይጥ እየተቁለጨለጨ ሃላፊነቱን እወስዳለሁ ብሎ ሲናገር ሰማነው። በእርግጥ የደብረጽዮን እና የገዱ አገላለጽ የተለያዩ ናቸው። የደብረጽዮን “ገድለናል። ምን አባክ ታመጣለህ” አይነት ቅኝት ያለ የተረገጠ አነጋገር ሲሆን ገዱ ግን እየረገጠ ሳይሆን እየተረገጠ የሚናገር ነው የሚመስለው። ከካሜራ ጀርባ ወይ ላውንቸር፣ አልያም የስኳር ደብተር ያመኖሩንስ ማን አየ?
ቴሌቭዝኑ ላይ ወጥቶ እንዲህ አይነት አስገራሚ መግለጫ የሚሰጠው “ገዱ ነው ወይንስ ደብረጽዮን?” ብሎ ያልተጠራጠረ ቢኖር፣ የፍራንስ ፋነንን “black skin white mask” የሚል መጽሃፍ ያነበበ ብቻ ነው። ሃብትና ንብረቱን፣ አለፍ ሲል ደግሞ አካሉን እና አእምሮውን የተሰለበ ሰው ስነ-ልቦና።
ይህ የመግለጫ ገቢር፣ ገዱ አንዳርጋቸው ከ”በላይ” አካል ተጽፎ የተሰጠውን ይህን መግለጫ ለማንበብ ሲጨናነቅ በግልጽ ያሳየናል። ወረቀቱ ሲዝረከረክበት የሚያሳየውን ቦታ እንኳን ሳያርሙ ነው የለቀቁት። ምንም ያህል ስኳር ቢልስ፣ ምንም ያህል ያልተከፈለ እዳ ቢኖርበት፣ ሰውዬው በዚህ ደረጃ ይጃጃላል ብሎ ማሰብ ግን ይከብዳል። ለእልቂቱ ሃላፊነቱን ይውሰድ፣ ግን ጽላት ላይ በድፍረት የማስተኮስ ሃላፊነትን መውሰድ ከጤነኛ ሰው ይጠበቃል?
የተባበሩት መንግስታት የሰብአዊ መብት ኮሚሽን ለሰራተኞቹ በለቀቀው የውስጥ መልእክት ግድያውን “የትግራይ ወታደሮች” መፈጸማቸውን በግልጽ አስቀምጦታል። የወልድያው እልቂት በተባበሩት መንግስታት ድርጅት መወገዙ ሰዎቹን ብርክ አንዳስያዛቸው ቢታወቅም፣ ይህንን “የኒዮ ሊብራሎች ሴራ” ለማፍረስ፣ ገዱ አንዳርጋቸው ለመስዋእትነ እንደቀረበ ከብት በአደባባይ ወጥቶ ሂሱን ውጧል። ገዱ ያለ ሃጥያቱ የወንጀለኞቹን መስቀል ለመሸከም የመፍቀዱ ምስጢር ግን ግልጽ አይደለም። አንዱ የበላውን ሌላው እንዴት ይውጠዋል?
እኚህ ሰው ልብ ገዝተው ከህወሃት ሰዎች ጋር እኩል መናገር ሲጀምሩ፣ “ወፌ ቆመች…” ብለን ሳንጨርሳት፣ ይኸው ደግሞ ሃሞት እንደሌለው ሰው ሲልፈስፈሱ አየን።
ደብረጽዮን፣ “ሁሉንም ሳይሆን ትምክህተኛውን አማራ፣ ሁሉንም ሳይሆን ጠባቡን ኦሮሞ እየነጠልን መምታት ነው ያለብን!” ብሎ በትግርኛ ትዕዛዝ ካስተላለፈ ወር አልሞላውም።
ከዚህ ቀደምም ስለ በማራው ላይ ጦርነት ሲያውጅ እንዲህ ነበር ያለው “… መከላለያ ሃይላችን እንኳንስ ለ30 ሚሊዮን (የአማራ) ሕዝብ አደለም፤ መላው አፍሪካን ለመደምሰስ አቅም እንዳለው የተለያዩ ዓለም አቀፍ ተቋማት ያረጋገጡት ሃቅ ነው። … የመከላከያ ኃይላችን በሙሉ ትጥቅ በመሆን ብጥብጡ ወደከፋባቸው አካባቢዎች በመሄድ አስፈላጊውን እርምጃ ሁሉ እንዲወስድ በጠቅላይ ሚኒስትራችን ታዟል።”
አካባቢው የተጠራቀሙ ችግሮች አሉ ተብለናል። ችግሩን ለመፍታትም ልማታዊው መንግስት ብዙ ይሰራልም ብለዋል። “ይሰራል” የሚለውን ቃል የተናገሩት ተሳስተው ካልሆነ በቀር ከደብረጽዮኑ ድንፋታ ጋር የሚጋጭ ነው። እናም ድርጅታቸው ብዙ ይሰራል የሚለው ቃል ብዙ “ይገድላል” ነው የሚሆነው። ለችግሮች እና ለጥያቄዎች ሁሉ መፍትሄያቸው አፈሙዝ ስለሆነ!
ገዱ ሃላፊነቱን ወሰደም አልወሰደ፣ በነባራዊው እውነታ ላይ የሚለወጥ ነገር አይኖርም። ያልበላውን ማከኩ ግን ራሱን ምን ያህል ለህወሃት ተገዥ እንዳደረገ ያሳየናል። በወሎ ለፈሰሰው ደም ተጠያቂው ማን እንደሆነ ወንዙ ላይ ስንደርስ እናወራዋለን። የመከላከያ ሚኒስትሩን የሚመራው ሲራጅ ፈርጌሳ እና አዛዥ ነኝ የሚለው ሃይለማርያም ደሳለኝም ቢሆኑ በዚያን ግዜ “ግድያውን እኛ አላስፈጸምንም። በቦታው እንደ አሻንጉሊት ነው የተቀመጥነው… እትት እትት” ቢሉ ማንም አይሰማቸውም። የኑረንበርጉን ችሎት ያስተውሏል!
ግን አንድ ነገር ልብ እንበል። ወያኔ ፊቱን ወደ ወሎ ሲያዞር የተሳሳተ ቁልፍ ነው የነካው። ሰላም ባስ ዛሬ ከአዲስ አበባ በአፋር ዞራ ትግራይ ትገባ ይሆናል። ነገ ደግሞ በሱዳን…
Average Rating