ወርቅነህ ገበየሁ ቀጣዩ ጠቅላይ ሚኒስትር እንዲሆን በህወሃት ተሹሟል። ይህ ከታማኝ ምንጭ የደረሰን መረጃ ነው። መረጃው እንደሚጠቁመው፤ እነ ዶ/ር ደብረጽዮን ሹመቱን ያጸደቁለት፤ አቶ ሃይለማርያም ደሳለኝ ገና በስልጣን ላይ እንዳሉ ነበር። የህወሃት ሰዎች፤ “የኦሮሞ ጠቅላይ ሚኒስትር መሆን ሃገሪቱ አሁን የገባችበትን አስከፊ ችግር ይፈታል” የሚል ቅኝት ይዘው ወደ ምዕራቡ አለም እንዲሰማሩም ተደርጓል። ከሀገሬው ሕዝብ ይልቅ የአሜሪካ እና የአውሮፓን ልብ መግዛት ከቻሉ ለተለመደው የበጀት ድጎማ ዋስትና ያገኛሉ። ሁሉም ወገኖች ሳይስማሙበት በሸፍጥ የተፈጸመው ይህን ሹመት ከአሜሪካ ባለስልጣናት ይሁንታ አግኝቷል ተብሏል። የአሜሪካ መንግስት ይህንን ሹመት ለመቀበል ሁለት ምክንያቶች አሉት። አንደኛው ምክንያት አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ኦሮሞ ስለሆነ የተቀሰቀሰውን የቄሮ አመጽ ሊያስቆም ይችላል በሚል የተሳሳተ መረጃ ሲሆን ሁለተኛው እና ዋነኛው ምክንያት ደግሞ አገዛዙ የኢትዮጵያን ሳይሆን ይልቁንም የአሜሪካን ብሄራዊ ጥቅም ለማስጠበቅ ፍቃደኛ በመሆኑ ነው።
የወያኔ ባለስልጣናት “እኛ ከሌለን ሃገሪቱ ትበታተናለች!” የሚል የማስፈራርያ መፈክር ይዘው ምእራባውያንን ለሶስት አስርተ-ዓመታት ሲደልሉ ቆይተዋል። አሁን ደግሞ ራሳቸው እያጠናከሩ ያሉትን አልሻባብ ማንሰራራት እንደ አጀንዳ ይዘው ብቅ ብለዋል። በያዝነው ሳምንት በውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ የሚመራ አንድ ቡድን በአሜሪካ ስቴት ዲፓርትመንት በመገኘት፤ አገዛዙ ከተወገደ አሜሪካ በአፍሪካ ቀንድ ላይ የሚኖራት ብሄራዊ ጥቅም አደጋ ውስጥ እንደሆነ ገለጻ አድርጓዋል።
የአሜሪካ መንግስት የአስቸኳይ ግዜ አዋጁን መቃወሟ ይታወሳል። ይህ ተቃውሞ ለሁለተኛ ግዜ መሆኑ ነው። የአስቸኳይ ግዜ አዋጆችን ብቻ ሳይሆን አገዛዙ የሚያወጣቸውን አፋኝ ህጎች እና አዋጆጅ ሳይቃወሙ ያለፉበት ግዜ የለም። የመለስ መስተዳደር አልሻባብን ለመምታት ሶማልያን በወረረ ግዜም አሜሪካ በአደባባይ ተቃውሞዋን አሰምታለች። ይሁን እንጂ የወረራ ትእዛዙ ከአሜሪካ በስውር እንደመጣ ወደ ኢትዮጵያ ይገባ የነበረው ወታደራዊ ቁሳቁስ ምስክር ነው። አሜሪካኖች ሕገ-ወጥ ድርጊት ሲፈጸም ለማስመሰል ይቃወማሉ እንጂ በተግባር አንድም እርምጃ ሲወስዱ አይታይም።
አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ የችግሩ ቁልፍ መሆናቸውን በጋዜጣዊ መግለጫ ተናግረው እንዲወርዱ መደረጉ በድንገት የመጣ ዱብ-እዳ እንደ ነበር አሁን ይፋ እየሆነ ነው። ሃገሪቱ ለገባችበት ውስብሰብ ችግር፣ መፍትሄው የእሳቸው ከስልጣን መውረድ መሆኑን በብሄራዊ ቴሌቭዢን ተናግረው እንዲወርዱ ማድረጋቸው አሳማኝ ባይሆንም ፤ አቶ ሃይለማርያም ይህን ከማለት ውጭ ሌላ አማራጭ እንዳልነበራቸው ተገልጿል።
ተተኪው ጠቅላይ ሚኒስትር ወርቅነህ እንዲሆን ህወሃት ወስኗል። ሙሉ ስሙ ወርቅነህ ገበየሁ ወልደኪዳን ሲሆን፣ ለምርጫ ቦርድ ያስመዘገበው ግን ወርቅነህ ገበየሁ ነገዎ ነው። የአያቱን ስም አንዳንዴም “ነገዬ” ይለዋል። “ነገዎ”ም ሆነ “ነገዬ” – ሁለቱም በማጭበርበር ኦሮሞ ለመሆን የወጡ ስሞች ናቸውና ለውጥ አያመጣም። ይህ ሰው ከየት ተነስቶ አሁን ያለበት ስፍራ እንዴት እንደደረሰ ከዚህ ቀደም በስፋት ስለሄድኩበት አሁን አልደግመውም።
በሙስና ታስሮ ከነበረበት የሻሸመኔ እስር ቤት በድንገት ተጠርቶ የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽነርነት ማዕረግ ሲሰጠው፤ ጥቂት እንኳ አልተግደረደረም። ዘሩን እና ሸሚዙን ቀይሮ ወንበሩ ላይ ቁጭ አለ። ከዚያ በስሩ ከነበረው ከሃሰን ሽፋ የሚሰጠውን ትዕዛዝ ማስፈጸም ሙሉ ስራው አደረገ። አፈናው፣ ቶርቸሩ፣ ግድያው ሁሉ በኦህዴድ ስም፣ በኦሮሞ ስም ይፈጸም ነበር። ኮሚሽነር ሆኖ ከፈጸመው እጅግ የከፋ ወንጀል መካከል በምርጫ 97 ወቅት በሕዝብ ላይ የደረሰው ስቃይ እና ግድያ ይጠቀሳል። በዚህ ዙርያ ተሰይሞ የነበረው አጣሪ ኮሚሽን ያሰባሰበው ዘግናኝ ዘገባ ለታሪክ ተቀምጧል።
አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ በሕዝብ ላይ እርምጃ ለመውሰድ ማንገራገራቸው ለስልጣናቸው መልቀቅ ምክንያት እንደሆነ ይነገራል። በዚህም ምክንያት “ለዘብተኛ” የሚል ስም ወጥቶላቸዋል። ህወሃቶች ወርቅነህ ገበየሁ ወልደኪዳን ጠቅላይ ሚኒስትር እንዲሆን የፈለጉበት ምክንያት በአመራር ብቃቱ እንዳልሆነም ግልጽ ነው። “የበሰበሰ ዝናብ አይፈራም” እንዲሉ በእጁ ላይ ቀድሞ የሰራው የሙስና ወንጀል እና ደም ስላለ፣ የሚሰጠውን ትዕዛዝ ከመፈጸም ወደ ኋላ አይልም በሚል እሳቤ እንደሆነ ይነገራል።
ሃገሪቱ አሁን የገባችበትን ችግር ልትላቀቅ የምትችለው ሕዝብ ላይ በደል የፈጸመን ሰው መሪ ማድረግ አይደለም። እንዲህ አይነቱ አካሄድ ሕዝብን የባሰ ያስቆጣዋል እንጂ እነሱ እንዳሰቡት ፍርሃት እንዲያድርበት አያደርግም። ይህንን አድርጎ ስለ ሰላም ማሰብ ፣ ይህንን እያደረጉ በስልጣን መቆየት፣ ፈጽሞ የማይታሰብ እንደሆነ ሕዝብ በተግባር እያሳየ ይገኛል።
ሃገሪቱ ብሄራዊ ችግር ውስጥ ነች። ወያኔ ይህንን ብሄራዊ ቀውስ እንደ እድል ተጠቅሞ ለእውነተኛ ብሄራዊ መግባባት ቢጠቀምበት ለራሱም ይበጀው ነበር። እንደ ለማ መገርሳ ያሉ አስታራቂ ሚና እየተጫወቱ ያሉ፣ ሕዝብ የሚፈልጋቸውን መሪዎች ወደ መድረክ የማምጣቱ እድል አሁንም አለ። ኳሱ በነሱ እጅ ላይ ነው። ሰዓቱ ሳይረፍድ ይህንን እውን ማድረግ ይችላሉ። ይህ ዕድል ካመለጣቸው ግን አወዳደቃቸው የሚያምር አይሆንም።
ምዕራቡ አለምም ቢሆን የሃይል ሚዛን እያየ ነው የሚቀየሰው። ከግብጹ ሆስኒ ሙባረክ እና ከቱኒዥያው ቤን አሊ የበለጠ የአሜሪካ ወዳጅ አልነበረም። በነዚህ አንባገነኖች ላይ ሕዝብ ሲነሳባቸው፣ አሜሪካም ተነሳች!
Average Rating