www.maledatimes.com የኤርትራው ዕርቅ ፈተና ይጠብቀዋል - MALEDA TIMES
Loading...
You are here:  Home  >  Ethiopia  >  Current Article

የኤርትራው ዕርቅ ፈተና ይጠብቀዋል

By   /   July 17, 2018  /   Comments Off on የኤርትራው ዕርቅ ፈተና ይጠብቀዋል

    Print       Email
0 0
Read Time:8 Minute, 45 Second

የኤርትራው ዕርቅ ፈተና ይጠብቀዋ

July 16, 2018 0

SHARE!

Afeworkie and Abiyዋዜማ ራዲዮ- ሁለቱ መሪዎች አሥመራ ላይ መግባቢያ ስምምነት መፈራረማቸውን ተከትሎ ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ኢትዮጵያን ጎብኝተዋል፡፡ ከሁሉም በፊት ግን መጀመሪያ ደፋሩን የዕርቀ ሰላም ርምጃ የወሰዱት ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ ቢሆኑም ፕሬዝዳንት ኢሳያስም በጎ ምላሽ ለመስጠት ጊዜ አላጠፉም፡፡ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቱም በኢምባሲዎች ደረጃ ተጀምሯል።፡፡

በርግጥ አስመራ ላይ የተፈረመው ባለ አምስት ነጥቡ የመግባቢያ ስምምነት ገና በዝርዝር ስምምነቶች መብራራት ያለበት ነው፡፡ ፍትሃዊ ንግድ፣ ዜግነት፣ የዜጎች ዝውውር፣ ድንበር እና ብሄራዊ ደኅንነት ዙሪያ የሚያጠነጥኑ ውስብስብ ችግሮች አሉ፡፡ ዘላቂ ዕርቀ ሰላም ለማውረድ ምን ዕድሎች እና መሰናክሎች አሉ? የሚሉትን ጥያቄዎች ከወዲሁ ማንሳት ያስፈልጋል፡፡ ጠቅላይ ሚንስትሩ ገና ስልጣን ከመያዛቸው ከኤርትራ ጋር ዕርቅ የፈጠሩት በሀገሪቱ ብሄራዊ ጥቅም ላይ ያነጣጠረ አደጋ ታይቷቸው ነው? ወይንስ ከፖለቲካ ሃይለ አሰላለፍ እና ስልጣን ጋር የተያያዘ ስልታዊ እና ስትራቴጂካዊ ጥቅም ስላላቸው ነው? መግባቢያ ስምምነቱን ለመተግበር ምን ዕድሎች እና መሰናክሎች ይኖሩ ይሆን? ኢትዮጵያ አሰብ ወደብን መጠቀሟስ ምን ትሩፋት እና ተግዳሮት ይኖረዋል? የሚሉትን ጉዳዮች ማየት ያስፈልጋል፡፡ [በዚህ ጉዳይ ላይ ዝርዝር የድምፅ ዘገባ ከታች ይመልከቱ፣ አልያም ንባብዎን ይቀጥሉ]

ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አሕመድ እና ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ አሥመራ ላይ ባለ አምስት ነጥብ የጋራ መግባቢያ ስምምነት ከተፈራረሙ ወዲህ የሁለቱ ሀገሮች ዕርቀ ሰላም እና ቀጣይ ግንኙነት ትልቅ ተስፋ ተጥሎበታል፡፡ ፕሬዝዳንት ኢሳያስ ከድርድር በፊት የኢትዮጵያ መንግሥት መጀመሪያ ወታደሮቹን በዐለም ዐቀፍ ፍርድ ቤት ከተፈረዱልን አካባቢዎች ያስወጣ የሚለውን አቋማቸውን ትተው ሰላም ስምምነት መስማማታቸው ሳይበቃ ኢትዮጵያን በአካል መገብኘታቸው ደሞ መተማመኑን ወደላቀ ደረጃ ያደረሰው ይመስላል፡፡ ሁለቱም መሪዎች በየሀገራቱ የተቸራቸው አቀባበልም የዕርቀ ሰላሙ ጥንስስ በመሪዎች ብቻ የተንጠለጠለ ሳይሆን ሰፊ ሕዝባዊ መሠረት ያለው መሆኑን አሳይቷል፡፡

ፕሬዝዳንት ኢሳያስ ኢትዮጵያን መጎብኘታቸው በርግጥም በድንበር ስምምነቱ አፈጻጸም ላይ እንደ ድሮው ግትር እንደማይሆኑ ሊጠቁም ይችላል፡፡ በጉብኝታቸውም “ሁለቱ ሕዝቦች አንድ ናቸው፤ ከእንግዲህ ወደኋላ አንመለከትም” ሲሉ ተደምጠዋል፡፡ በርግጥም ዕርቀ ሰላሙ ለሁለቱም ሀገሮች በርካታ ትሩፋቶች እንደሚያስገኝ አያጠያይቅም፡፡ ተግባራዊ የመሆን ዕድሎች ያለትን ያህል ተግዳሮቶችም ሊገጥሙት ይችላሉ፡፡ ዕድሎችንም ሆነ ተግዳሮቶችን ለመገመት ግን በቅድሚያ ሁለቱን መሪዎች ለዕርቀ ሰላም ያነሳሷቸው ምክንያቶች ምንድን ናቸው? የሚለውን ጥያቄ መመርመር ያሻል፡፡ በርግጥም ሁለቱም መሪዎች ዕርቀ ሰላሙን ለየራሳቸው ስልታዊ እና ስትራቴጀካዊ ግቦች እንደፈለጉት መናገር ይቻላል፡፡

ሕወሐትን ማስጎብደድ

በጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ ጎላ ብለው የሚታዩት ውስጣዊ ፖለቲካዊ ምክንያቶች ናቸው፡፡ አንዱ ምክንያታቸው ከሕወሃት እና ትግራይ ክልላዊ መንግስት ጋር የተያያዘ ነው፡፡ በጠቅላላው የትግራይ ልሂቃን በዕርቀ ሰላሙ ላይ ውልውል ውስጥ እንደገቡ መታዘብ ይቻላል፡፡ ባንድ በኩል ግዛትን አሳልፎ መስጠት ሕዝባዊ ተቀባይነትን እንዳያሳጣቸው ይሰጋሉ፡፡ የትግራይን ሕዝብ ሙሉ ድጋፍ ከመቼውም ጊዜ በላይ የሚፈልገት ደሞ አሁን ነው፡፡ በሌላ በኩል በውጭ ግንኙነት ጉዳይ ላይ ከፌደራል መንግስቱ እና ኢሕአዴግ የተለየ አቋም መያዝ ፖለቲካዊ ዋጋ እንደሚያስከፍላቸው አውቀውታል፡፡ በሁለቱም ወገን ሕዝቡ ለዕርቀ ሰላሙ ያሳየው ድጋፍም ማንቂያ ደወል ሆኖላቸዋል፡፡ የኢሳያስ መንገሥት ከኦሮሞ እና አማራ ለውጥ አቀንቃኝ ልሂቃን ጋር ከተባበረ ትግራይ ክልል እና ሕወሃት በመልካ ምድርም ሆነ በፖለቲካ ሃይል አሰላለፍ አጣብቂኝ ውስጥ እንደሚገቡም ያወቁት ይመስላል፡፡ እናም ላሁኑ የሕወሃት እና የክልሉ መንግስት መሪዎች ፈራ ተባ እያሉም ቢሆን ድጋፋቸውን ማሰማት ነው የመረጠት፡፡

ችግሩ የሕወሃት አንጋፋዎችን የያዘ አድፋጭ አክራሪ ሃይል መኖሩ ነው፡፡ ይሄ አኩራፊ ሃይል በዕርቀ ሰላም ሂደቱም ቁልፍ ሚና መጫወት አልቻለም ወይም አልፈለገም፡፡ እንዲያውም ከጊዜ ወደ ጊዜ ከሂደቱ እየተነጠለ በመምጣቱ የጦርነት ነጋሪት ጎሳሚ እየሆነ ነው፡፡ ጠቅላይ ሚንስትሩ ሐዋሳ ላይ በፕሬዝዳንት ኢሳያስ ፊት “በገንዘብ የምትገዙ” ላሏቸው ግጭት እና እንቅፋት ፈጣሪ ሃይሎች የመጨረሻ ማስጠንቀቂያ ሲሰጡም ይህንኑ ሃይል ማለታቸው እንደሆነ ይታመናል፡፡

በርግጥ አኩራፊው ሃይል ራሱ የድንበር ውዝግቡ በሰላም መፈታቱን የሚጠላ አይደለም፡፡ እንዲያውም ድንበር ውዝግቡን ለመፍታት ቅስቀሳ የጀመሩት ከሕወሃት ጋር ግንኙነት ያላቸው ግለሰቦች እና ሲቪል ማኅበራት እንደነበም አይዘነጋም፡፡ ችግሩ ዕርቁ ከፕሬዝዳንት ኢሳያስ አገዛዝ ጋር መሆኑ ላይ ከበረሃ ጀምሮ የነበረውን የድርጅታዊ መናናቅ ቀስል የሚያመረቅዝ መሆኑ ነው፡፡ ውዝግቡ ይፈታ ከተባለም “ከእኛ በላይ ችግሩን የሚያውቅ ወይም ለውዝግቡ መንስዔዎች የሚቀርብ ማንም የለም፤ ባለቤቶቹ እኛ ነን” የሚል መታበይም ያለው ይመስላል፡፡ በሌላ በኩል በሀገር ውስጡ ፖለቲካዊ ለውጥ ያጣውን ተሰሚነት መልሶ ለመያዝ ሲልም ሂደቱን ማጓተትን እንደ መሳሪያ ሊጠቀምበት የሚችልበት ዕድል አይጠፋም፡፡ ለዚህም ታሪካዊ እና መልክዓ ምድራዊ ሁኔታዎች ምቹ ሁኔታ ሊፈጥሩለት ይችላሉ፡፡

ጠቅላይ ሚንስትሩ ዕርቀ ሰላሙን ያፋጠኑትም እንግዲሀ ይሄን ሃይል ለማሽመድመድ እንደሆነ ብዙ ታዛቢዎች ይስማሙበታል፡፡ የዚሁን ሃይል ድጋፍ ቀድመው ለማግኘት ምን ያህል እንደጣሩ ግን አሁን ግልጽ አይደለም፡፡

ወደ ጥንቱ የጥርጣሬና ዘረፋ አዙሪት ብንመለስስ?

ባጠቃላይ አሁን ያለው ሁኔታ በቅድመ-ወረራ የነበረውን ፖሊሲ የሚደግም ነው የሚመስለው፡፡ ተጻራሪ አቋሞችን የያዙ የትግራይ ልሂቃን ማለት ነው፡፡ ከኤርትራ ጋር ክፍት ድንበር እና ልቅ ግንኙነት የሚፈልጉ ልሂቃን ባንድ በኩል፣ መርህን እና ብሄራዊ ጥቅምን ብቻ ታሳቢ ያደረገ የሁለት ሉዓላዊ ሀገሮች ግንኙነትን የሚፈልጉ ደሞ በሌላ በኩል… መንግስት የትግራይን ልሂቃን ሙሉ ድጋፍ ካላገኘ ደሞ የድንበር ውዝግቡን መፍታት ወይም ዘላቂ ዕርቀ ሰላም ማውረድ ይቅርና የድንበር ንግድ ልውውጥ፣ የሰዎች ዝውውር እና ሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነትን ማቀላጠፍ አስቸጋሪ ነው የሚሆንበት፡፡

ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ መንግስታቸው እና የለውጥ አጀንዳቸው ገና ሳይረጋ ወደዚሀ ጉዳይ የገቡት እንዲህ ያለውን ውስጣዊ ፖለቲካዊ ዐላማ ለማሳካት ሲሉ ከሆነ በርግጥም የሀገራቸውን ዘላቂ ብሄራዊ ጥቅም ለማስጠበቅ ሊቸገሩ እንደሚችሉ መናገር የሚቻለው፡፡ የውጭ ግንኙነትን ለውስጣዊ ፖለቲካዊ ውጥረት ማስተንፈሻ መጠቀም ደሞ መዘዘኛ ይሆናል፡፡

ሌላው ተግዳሮት ሁለቱም መንግስታት በውስጣዊ ፖለቲካዊ ችግሮች የተወጠሩ መሆናቸው ነው፡፡ የዐቢይ መንግስት ደሞ ስላልረጋ በሄራዊ ጥቅምን የሚያስጠብቅ ፖሊሲ ለመቅረጽ እና ስምምነት ለመድረስ ይቸገር ይሆናል፡፡ መንግስት “ለኤርትራ አዲስ የውጭ ፖሊሲ እየነደፍኩት ነው” ብሎ የነበረ ቢሆንም ፖሊሲው አልቆ ሳይጸድቅ ነው ጠቅላይ ሚንስትሩ ባቋራጭ ስምምነት እየደረሱ ያሉት፡፡ አዲስ ሁለገብ ፖሊሲ ሳይኖር ደሞ ኢትዮጵያ ከሁለትዮሽ ግንኙነቱ የምታገኛቸውን ታሳቢ ብሄራዊ ጥቅሞች ባግባቡ አንጥሮ ማውጣት አይቻልም፡፡

ጠቅላይ ሚንስትሩ በደፈናው “የጋራ ድንበሩ ፈርሷል” ማለታቸውም ጊዜውን ያልጠበቀ ዱብዳ ነው ማለት ይቻላል፡፡ ያለ በቂ ዝግጅት ከተተገበረ ለሁለቱ ሀገሮች ሕዝቦችም የራሱን ትሩፋት እና መርገምት ይዞ ሊመጣ ይችላል፡፡ ሁለገብ የዲፕሎማሲ፣ ጸጥታ እና ኢኮኖሚ ፖሊሲ ሳይቀረጽ እንዲህ ያለ መግለጫ መስጠት ውሎ ሳያድር ነባሮቹ ኢኮኖሚያዊ ልዩነቶችን ከማጎንቆል አያስቀራቸውም፡፡ የኤርትራ መንግስት እንደ ድሮው ጉልበትን መጠቀም ባይችል እንኳ ልቅ የሆነውን ግንኙነት ፍትሃዊ ላልሆነ ንግድ እና አንጡራ ሃብት ምዝበራ ላለመጠቀሙ ምንም ዋስትና የለም፡፡ ሁለገብ ፖሊሲው ሁለቱንም ሀገሮች ተጠቃሚ ካላደረገ የኤርትራ ምጣኔ ሃብት ችግር ዞሮ ዞሮ ዳፋው ከኢትዮጵያ ጫንቃ አይቀርድም፡፡

በወረራው ማግስት የተባረሩ ኤርትራዊያን ጉዳይም መረሳት የበትም፡፡ በ10 ሺዎች የሚቆጠሩ ትውልደ-ኤርትራዊያን በግፍ ሲባረሩ የባከነው እና የተዘረፈው ንብረታቸው ባብዛኛው ከትግራይ ተወላጆች ጋር የተያያዘ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ ንብረታቸውን ቢጠይቁ መንግስት ምን ሊያደርግ እንዳሰበ ግልጽ አይደለም፡፡ በሌላ በኩል ሃብት መፍጠር የሚችሉ ኤርትራዊያን ነጋዴዎች ወደ መኻል ሀገር መምጣታቸውን የትግራይ ተወላጅ የሆኑ ባለሃብቶች በበጎ ዐይን ያዩታል ተብሎ አይታሰብም፡፡

የኤርትራዊያን በገፍ መምጣት ለኢትዮጵያ ብሄራዊ ጸጥታ ስጋት ቢፈጥርስ? የሚለውም መታሰብ ያለበት ነው፡፡ አሁን ደሞ ፖለቲካዊ ሁኔታው ለዚህ አመቺ ነው፡፡ለዚህም ነው እንግዲህ የድንበር ውዝግብ አፈታቱንም ሆነ አጠቃላይ ቀጣይ ግንኙነቱን መጀመሪያ ተቋማዊ እና መንግሥታዊ ፈር ማስያዝ አስፈላጊ የሚሆነው፡፡

ሕዝቡ ለድንበሩ ውዝግብ አፈታት እና ዕርቀ ሰላሙ እንዲህ ያለ አወንታዊ ስሜት ማሳየቱም በኤርትራ መንግስት በኩል እንደምን እንደሚተረጎም አፍን ሞልቶ መናገር አይቻልም፡፡ የሀገር ውስጡ ግጭት እና ድርጅታዊ ቅራኔም አንደ ድክመት ሊታይ ይችላል፡፡ ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ ቅን ሃሳብ ቢይዙም በፖለቲካ አረዳድ ግን ብቻቸውን ተነጥለው የቆሙ መስለው ሊታዩ ይችላሉ፡፡

ወዳጅነቱ ለኤርትራ ጥሩ ዕድሎችን ይዟል

በኤርትራ በኩል አምባገነናዊ አገዛዙ አሁንም ሆነ በቅርብ ሊቀየር ስለመቻሉ ከውስጥም ከውጭም የረባ እንቅስቃሴ የለም፡፡ የዕርቀ ሰላም ሃሳቡ የኤርትራን መንግስት ሳይዘጋጅበት ነው በድንገት የዋጠው፡፡ ቢሆንም ስምምነቱ ድንበሩን ለማስመር፣ ዐለማቀፋዊ ገጽታን ለማሻሻል እና ወደ ዐለም ዐቀፉ ኅብረተሰብ ለመቀላቀል እንዲሁም በጦርነት እና በመገለል የደቀቀውን ኢኮኖሚ እንዲያገግም ለማድረግ በር ይከፍትለታል፡፡ የተመድ ማዕቀብ በኢትዮጵያ ጎትጓችነት ከተነሳላት ደሞ ዐለም ዐቀፍ ፋይናንስ እና ኢንቨስትመንት ያስገኝለታል፡፡

በሌላ በኩል የጦርነት ምዕራፉ መዘጋት የኤርትራ መንግስት ግዳጅ ወታደራዊ አገልግሎትን ለማስቀጠል አመክንዮ ያሳጣዋል፡፡ ይሄም ደሞ የሥራ ዕድል መፍጠርን ጉዳይ ቀዳሚ አጀንዳ ያደርጋል፡፡ ለፖለቲካዊ ማሻሻያም ከውስጥም ከውጭም ግፊት ሊፈጥርም ይችላል፡፡ በርግጥም በተለይ የኢትዮጵያው ጅምር ለውጥ ወደ ዲሞክራሲ ካመራ ፕሬዝዳንት ኢሳያስ ሁለት ምርጫ ነው የሚኖራቸው፤ አንድም ሀገራቸውን ወደ ሕገ መንግስታዊ ሥርዓት መውሰድ፤ አሊያም ከኢትዮጵያ ጋር ያላቸውን ፖለቲካዊ ግንኙነት መቀነስ፡፡ በፕሬዝዳንት ኢሳያስ አመራር ስር ኤርትራ ወደ ሕገ መንግስታዊ አስተዳደር ልታመራ ትችላለች ወይ? የሚለው ጥያቄ ግን ሙሉ በሙሉ ዝግ ባይሆንም በእጅጉ አጣራጣሪ ይመስላል፡፡ ምናልባት በቅርቡ ደንበሩ ከተከፈተ ዜጎቹ እንደፈለጉ ወደ ኢትዮጵያ እንዲገቡ እና እንዲወጡ መፍቀድ አለመፍቀዱ ፍንጭ ይሰጥ ይሆናል፡፡

እናም ፕሬዝዳንት ኢሳያስ ነገ ከነገ ወዲያ የጠቅላይ ሚንስትሩን ቅን ሃሳብ ገፍተው አምባገነናዊ አገዛዛቸውን ለማስቀጠል ቢጠቀሙበትስ? የሚለውን ታሳቢ ማድረግ ተገቢ ይሆናል፡፡ ምክንያቱም ይሄ ዕድል ዝግ መሆኑን የሚያሳይ ሁነኛ ፍንጭ የለም፡፡ ድንበሩን ከፍርድ ቤቱ ካርታ ይልቅ በድርድር እና ውይይት ለመጨረስም ዕምነት ብቻ ተጣለባቸው እንጅ ቃል አልገቡም፡፡ አስመራ ላይ የተፈረመው መግባቢያ ስምምነትም ይኸው ፍቃደኝነት ስለመኖሩ አንዳች ፍንጭ አይሰጥም፡፡ ጠቅላይ ሚንስትሩ ይሄን ያህል ቀና መንገድ ተጉዘው ድንበሩ እንደወረደ ከተሰመረ ደሞ ትርፋቸውን በጣም ያሳንሰዋል፡፡ ፖለቲካዊ ዋጋም ሊያስከፍላቸው ይችላል፡፡

ከዚሁ ጋር ተያይዞ መነሳት ያለበት ተግዳሮት ድንበሩ እንደወረደ ቢሰመር እና ኢትዮጵያ ወታደራዊ ገዥ መሬቶችን ብታጣ ጦር ሠራዊቱ ቦታዎቹን ለመልቀቅ ፍቃደኛ ይሆናል ወይ? የሚለው ነው፡፡ ከፍተኛ ወታደራዊ አዛዦች ደሞ ለሕወሃት ወይም ትግራይ ክልላዊ መንግሥት ወገንተኞች ናቸው፡፡ አሁንም ለጠቅላይ ሚንስትሩ የለውጥ እና ዕርቀ ሰላም አጀንዳ ምን አተያይ እንዳላቸው አይታወቅም፡፡ ድምጻቸው የጠፋው ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከፖለቲካ ገለልተኛ ስለሆኑ ነው ለማለት ግን ፈጽሞ የሚቻል አይሆንም፡፡

ተቃዋሚ ድርጅቶችን ስለመደገፍና ማስጠለል

መግባቢያ ስምምነቱ ታጣቂ ተቃዋሚዎችን ወደፊት በግዛቶቻቸው የማስጠለሉን ነገር አላካተተም፡፡ እናም በተለይ አዲሳባ የከተሙት የኤርትራ ሰላማዊ ተቃዋሚዎችም ሆኑ በድንበር አካባቢ የሚንቀሳቀሰው የቀይ ባሕር አፋሮች ታጣቂ ሃይል ዕጣ ፋንታ ምን እንደሚሆን ግልጽ አልሆነም፡፡ ይሄ ሽምቅ ተዋጊ ደሞ ከኢትዮጵያ መንግሥት ድጋፍ እንደሚያገኝ ነው ሲነገር የኖረው፡፡ ባጠቃላይ ተቃዋሚዎች ኤርትራ መሽገው እንደነበሩት ኢትዮጵያዊያን ሽምቅ ተዋጊዎች ወደ ሀገራቸው ይመለሳሉ እንዳይባል የኤርትራ መንግስት አወንታዊ ፖለቲካዊ ማሻሻያ አልወሰደም፡፡ የመግባቢያ ስምምነቱ ሲፈረም ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ በዚህ ጉዳይ ላይ ለፕሬዝዳንት ኢሳያስ የገቡላቸው ቃል ካለ ወደፊት ይታያል፡፡

የአሰብ ወደብ

ከኢትዮጵያ መንግስት በኩል ጎላ ብሎ ባይሰማም አሰብ ወደብን የመጠቀም ጉዳይ አንዱ የመግባቢያ ስምምነተ አካል ሆኗል፡፡ ኤርትራ አሰብን ለኢትዮጵያ መጠቀሚያ ብትፈቅድ ከኪራይ የውጭ ምንዛሬ ታገኝበታለች፡፡ በዚህ በኩል ችግር ያለ አይመስልም፡፡

ከኢትዮጵያ አንጻር ስናየው ግን ወደቡን መጠቀም ምን ትሩፋት እና ተግዳሮት ይኖረው ይሆን? የሚለው ካሁኑ መፈተሸ ያለበት ነው፡፡

አንዱ የአሰብ ትሩፋት ወደቡ በመልካ ምድራዊ ቅርበቱ እና በሚጠይቀው ወጭ ከየትኛውም ወደብ በላይ ለኢትዮጵያ ጠቀሜታ ያለው መሆኑ ነው፡፡ በርግጥ ኢትዮጵያ በመንገድ እና ባቡር መስመር ዝርጋታ ብዙ መዋዕለ ነዋይ ያፈሰሰችበትን የጅቡቲን ወደብ እና ሽርክና የገባችበትን በርበራ ወደብ ርግፍ አድርጋ ልትተው አትችልም፡፡ በመካከለኛ እና ረጅም ጊዜ ግን ከፊሉን ገቢ እና ወጭ ንግዷን ወደ አሰብ ማዞሯ ስለማይቀር ጅቡቲ እና በርበራ ጥቅማቸውን ያጣሉ፡፡ የኢትዮጵያ መንግሥት በተለይ ከጅቡቲ የወደብ ኪራይ ቅነሳ ለማግኘትም አሰብ ተጨማሪ መደራደሪያ ልትሆነው ትችላለች፡፡

አሰብ ወደብ ከብሄራዊ ደኅንነት ጋር የተያያዘ ትሩፋትም አለው፡፡ እንደሚታወቀው አሰብ ወደብ ከጅቡቲ በተቃራኒ የዐለም ሃያላን ሀገራት ወታደራዊ ቀጠና አይደለም፡፡ ከባሕረ ሰላጤው ሀገሮችም የተባበሩት ዐረብ ኢምሬትስ ብቻ ናት ወታደራዊ ጦር ሠፈር ያላት፡፡ ኢምሬትስ ደሞ በርበራ ወደብን ከኢትዮጵያ ጋር በሸርክና ቀድማ የያዘች እና የኢትዮጵያን መንግሥት ከፕሬዝዳንት ኢሳያስ ጋር በማሸማገልም ቁልፍ ሚና እንደተጫወተች ስለሚታመን የሁለቱም መንግሥታት ወዳጅ ናት፡፡ ይሄ ሁኔታም አሰብ ወደብን መጠቀም ለኢትዮጵያ ብሄራዊ ደኅንነት እምብዛም ስጋት እንደሌለው ያሳያል፡፡ ይህ የሚቻለው ግን ቢያንስ ዐለም ዐቀፍ ሕግን መሰረት ያደረገ የወደብ አጠቃቀም ስምምነት ሲኖር ብቻ ነው፡፡

ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ ከሌሎቹ ሀገሮች ጋር እንደተስማሙት የወደብ ሽርክና ያስገኛሉ? ወይንስ ሙሉ የባሕር በር ባለቤትነት ይጠይቃሉ? ብለን ብንጠይቅ ከጅበቲ ወይም በርበራ የተለየ ፍላጎት ያለ አይመስልም፡፡ መንግስት የባህር በር መውጫ መብት እንዲጠይቅ ግን ምሁራን እየገፋፉ ነው የሚገኙት፡፡ ይሄን ከባድ ጅኦፖለቲካዊ ጉዳይ ለውጥ ሂደት ላይ ያለው የጠቅላይ ሚንስትሩ መንግስት ገፍቶ ይሄድበታል ወይ? የሚለው ግን አጠራጣሪ ነው፡፡ ለዚህም ይሆናል ከመንግስት አንደበትም ጉዳዩ የማይሰማው፡፡

በርግጥ አሰብ ወደብን መጠቀም ተግዳሮቶችም ይኖሩታል፡፡ በተለይ ድንበር ማስመሩ በቶሎ ባይሳካ ኤርትራ አሰብ ወደብን ለኢትዮጵያ ክፍት ታደርግ ይሆን? ክፍት ቢሆንስ ከደኅንነት አንጻር ለኢትዮጵያ አስተማማኝ ሊሆንላት ይችላልን? የሚሉት ጉዳዮች ተግዳሮት መሆናቸው አይቀርም፡፡ የኤርትራ መንግስት በወረራው ማግስት አሰብ ወደብ ላይ የተከማቸውን የኢትዮጵያን ወጭ አና ገቢ ዕቃዎች በማናለብኝነት መዝረፉ ሊዘነጋ አይገባም፡፡ የተዘረፈው ንብረት ጉዳይ ወደፊት በምን ይካካሳል የሚለውም ሌላ በእንጥልጥል ያለ ጉዳይ ነው፡፡

ባጠቃላይ ኢትዮጵያ ትልቅ ሀገር እንደመሆኗ ዘላቂ ብሄራዊ ጥቅሞቿን ለማስጠበቅ ዐይነተኛ ዕድል ያላት አሁን ነው፡፡ ዛሬ ያመለጡ ዕድሎች ደሞ ተመልሰው ላይገኙ ይችላሉ፡፡ ሁለቱ ሀገሮች ዲሞከራሲያዊ ሥርዓትን ካልገነቡ ግን ዘለቄታዊ የጋራ ሰላም፣ ኢኮኖሚያዊ ዕድገት፣ ጠበቅ ያለ ዲፕሎማሲያዊ እና የጸጥታ ትስስር ማድረግ የመቻላቸው ዕድል ውስን ሆኖ መቀጠሉ የሚቀር አይመስልም፡፡ [በዚህ ጉዳይ ላይ ዝርዝር የድምፅ ዘገባ ከታች ይመልከቱ]

https://youtu.be/kCPibGbzRiQ

Happy
Happy
0 %
Sad
Sad
0 %
Excited
Excited
0 %
Sleepy
Sleepy
0 %
Angry
Angry
0 %
Surprise
Surprise
0 %
    Print       Email

Average Rating

5 Star
0%
4 Star
0%
3 Star
0%
2 Star
0%
1 Star
0%
<"Without the support of our readers, the Maleda Times website would not exist in its present form">

You might also like...

በሰሜን ሸዋ ዞን ኤፍራታ እና ግድም ወረዳ መከላከያ ከአማራው ማህበረሰብ እና ከፋኖ ጋር ጦርነት ገጥሟል

Read More →

This site is protected by wp-copyrightpro.com

Skip to toolbar