ዋዜማ ራዲዮ- የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ካበደረገው ብድር በአጠቃላይ የተበላሸው ብድር ምጣኔ 40 በመቶ ደረሰ ።
ልማት ባንኩ አሁን ላይ የሰጠው ብድር ወይንም (outstanding loan) ከ33 ቢሊዮን ብር የሚያልፍ ሲሆን ፤ ከዚህ ውስጥ የተበላሸው ብድር ማለትም (non performing loan) 14 ቢሊዮን ብር መጠጋቱን የባንኩ ምንጮቻችን ነግረውናል ። ይህም ባንኩ የተጋረጠበትን ትልቅ ፈተናና ሀገሪቱ ያለችበትን ኢኮኖሚያዊ ዉጥንቅጥ እንዳባባሰው የዘርፉ ሙያተኞች ያስረዳሉ።
በኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ ህግ መሰረት የልማት ባንክ የተበላሸ ብድር ምጣኔ ካበደረው ገንዘብ ከ15 በመቶ መብለጥ የለበትም ።
ልማት ባንክ የሚያበድረው ገንዘብ በቀጥታ ከቆጣቢዎች ጋር የተገናኘ ሳይሆን መንግስት በተለያዩ መንገዶች አግኝቶ እንዲያበድር የሚሰጠው ገንዘብ ነው ። ልማት ባንኩ ከተቀመጠለት ገደብ ከእጥፍም በላይ ሆኖ የተበላሸ የብድር ምጣኔው የባንኩን ህልውና አደጋ ውስጥ የጣለበት ደረጃ ላይ ደርሷል ።
የጨርቃጨርቅ ዘርፉና ቱርኮች
ባንኩ 14 ቢሊዮን ብር የደረሰ ብድሩ እንዲበላሽ ትልቁን ሚና የተጫወቱት ያለ ምንም የባለሀብቶች ማጣራት ስራ በተለይም ለጨርቃ ጨርቅና ለሰፋፊ እርሻዎች የሰጠው ብድር መሆኑ የልማት ባንኩ ምንጮቻችን ነግረውናል ።
በጨርቃ ጨርቁ ዘርፍ በተለይም የቱርክ ባለሀብቶች በልማት ስም ያለ ጀርባ ታሪክ ጥናት የተሰጣቸው ብድር ባንኩ አሁን ለደረሰበት የአፈጻጸም ወድቀት ምክንያት መሆኑ ይነሳል ። ከነዚህ መካከል ወደ ኢትዮጵያ ሲገባ በተለይም በቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ብዙ ተብሎለት የነበረው የቱርኩ አይካ አዲስ ጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካ ተጠቃሽ ነው ።
ይህ ፋብሪካ ለሀገሪቱ የአምራች ኢንዱስትሪ ሽግግር ብዙ አስተዋጽኦ ያበረክታል ተብሎ ሲጠበቅ አሁን ላይ ብቻውን ከሁለት ቢሊዮን ብር በላይ የተበደረው ገንዘብን ሳይከፍል የመመለሻ ጊዜው አልፎበታል ። ከጨርቃ ጨርቅ ኩባንያዎችም ለልማት ባንኩ ያልተመለሰ ብደር ምጣኔ ከፍ ማለት ትልቁን አስተዋጽኦ ያበረከተው ይሄው አይካ አዲስ ነው ።
የባንኩ ሰራተኞች አስደንጋጭ ያሉት ክስተት- ይህ ኩባንያ በዚህ የአፈጻጸም ዝቅተኝነት ውስጥ እያለ ተጨማሪ ብድር ሊፈቀድለት እንደሆነ መሰማቱ ነበር ።
በአዳማ ጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካውን ከፍቶ የነበረው ሌላኛው የቱርክ ኩባንያ ኤልሲ አዲስም ከ800 ሚሊዮን ብር በላይ ተበድሮ ከሀገር መሰወሩ የሚታወስ ነው ። ይህ ኩባንያ ጥሎት የሄደው ፋብሪካን ለጨረታ በማውጣት ልማት ባንኩ ብድሩን ሊያስመልስ ቢጥርም ኤልሲ አዲስ የተበደረው ገንዘብና ጥሎት የኮበለለው ፋብሪካ ያላቸው የገበያ ዋጋ በፍጹም የሚጣጣም ሆኖ አልተገኘም ።
ኤንጅል የሚባለው የቱርክ ኩባንያ አዳማ ፋብሪካ ለመስራት ተበድሮ በዛው የጠፋ ነው። ኢ-ቱር ደግሞ ለገጣፎ ላይ የነበረና እንዲሁ የደረሰበት ያልታወቀ ተበዳሪ ሲሆን የሁለቱ ኩባ ንያዎች አጠቃላይ ብድር ከቢሊየን ብር ይልቃል።
ኢትዮጵያ የአምራች ኢንዱስትሪን እቀላቀልባቸዋለሁ ያለችው የጨርቃጨርቅ ዘርፍም የልማት ባንኳ የተበላሸ ብድር ዋነኛ ምንጭ ሆነዋል ።
ኩባንያዎቹ ገና ለገና ከውጭ ሀገራት ስለመጡ ማንነታቸው ሳይጣራ የተሰጣቸው ብድር አንዱ ለዚህ ምክንያት ሲሆን በሌላ በኩል የፋብሪካዎቹ ባለቤቶች የሚያስገቡት ማሽን ብዙ የሰራ እና በብድር የወሰዱትን ገንዘብ የማይመጥን ሆኖ በተደጋጋሚ ተገኝቷል ።
ለምሳሌ አይካ አዲስ ያረጀ ማሽንን በውድ ዋጋ አስገብቶ ከዚህ ቀደም መገኘቱ ይታወሳል ።
ስፋፊ እርሻና ውንብድና
በሰፋፊ እርሻ ላይ ተሰማርተው ለልማት ባንኩ ብድርን ያልመለሱ ባለሀብቶች ለዚህ የተበላሸ ብድር ወይንም ለnon performing loan ያላቸው ከፍተኛ አስተዋጽኦ አሁንም ተጠናክሮ ቀጥሏል ።በዚህ ረገድ በጉልህ ስማቸው የሚነሳው በጋምቤላ ክልል የበደሩት ባለሀብቶች መሆናቸው ይታወቃል ።
በዚህ ክልል የነበረው የብድር አሰጣጥ ከፍተኛ ችግር የነበረበት መሆኑ ሲነሳ ቆይቷል ፤ ብድር አሰጣጡ ማንነት ላይ የተመሰረተ ፤ ብድር የሚሰጠው በዝናብ ላይ ለተመሰረተ እርሻ መሆኑ ፤ በሌላ በኩል አንድ መሬት ላይ ሁለት ካርታየተሰጣቸው ሁለት ባለሀብቶች ለአንድ መሬት ለሁለት ባለሀብቶች ብድር የተሰጠበት ሁኔታ እንዳለ ባንኩ ደርሶበታል ።
በጋምቤላ ክልል 45 ሺህ ሄክታር ወይንም የአዲስ አበባ ከተማን ስፋት የሚቀራረብ መሬት ለተለያዩ ባለሀብቶች ተደራርቦ ካርታ መሰጠቱ ሀይለማርያም ደሳለኝ ጠቅላይ ሚኒስትር በነበሩበት ወቅት በጥናት መለየቱ ይታወሳል ።
ከዚህና ሌሎች ችግሮች ጋር ተያይዞ ዘርፉ ብዙም መንቀሳቀስ ሳይችል ቀርቷል ።
ልማት ባንኩ ከጥቂት ወራት በፊት ባወጣው መረጃ መሰረት ለሰፋፊ እርሻዎች ከሰጠው ብድር 5 ነጥብ 6 ቢሊየን ብር ብድር ውስጥ 3 ነጥብ 6 ቢሊየን ብር ብድሩ መበላሸቱን ገልጾ ነበር ።ከዚህ ጋር ተያይዞ ለዚህ ዘርፍ ብድር መስጠት እስከማቆም የደረሰ እርምጃም ተወስዶ ነበር ።
በተለያዩ ጊዜያት የተለያዩ መፍትሄዎች ይወሰዳሉ ቢባልም የባንኩን የተበላሸ ብድር ምጣኔ መቀነስ አልተቻለም ። ከወራት በፊት ባንኩ ራሱ የተበላሸ ብድር ምጣኔዬ ካበደርኩት 25 በመቶ ነው ብሎ የነበረ ሲሆን ፤ በወራት ልዩነት ውስጥ ምጣኔው 40 በመቶ መድረሱ ተሰምቷል ።
የኢትዮጵያ ልማት ባንክ እዚህ ችግር ውስጥ መውደቁ ለተደጋጋሚ ጊዜ የባንኩ አመራረ እንዲቀያየር አስገድዶታል ።
እስከ 2009 አ.ም የመጀመርያ ወራት ድረስ ባንኩን በፕሬዚዳነትነት ያገለገሉት አቶ አሳያስ ባህረ ለባንኩ ውድቀት ተጠያቂ ናቸው በሚል እንዲሱ ተደርጎ በምትካቸው በኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ የፋይናንስ ተቋማት ሱፐርቪዥን ምክትል ገዥ የነበሩት ጌታሁን ናና ፕሬዚዳንት መሆናቸው የሚታወስ ነው ።
አቶ ጌታሁን ባላቸው አቋም የባንኩን አፈጻጸም ያስተካክሉታል ቢባልም በደረሰባቸው ግምገማ ከጡረታቸው በፊት ራሳቸው መልቀቂያ አስገብተው ምክትል የነበሩት አቶ ሃይለኢየሱስ በቀለ አሁን ላይ ፕሬዚዳንት ሆነዋል ።
ከዚህም ሲያልፍ በልማት ባንኩ ውስጥ የተሰሩ ስህተቶች የወንጀል ተጠያቂነት ያመጣሉ ተብሎ አቶ ኢሳያስ ባህረና የቀድሞው የብድር አገልግሎት ዘርፍ ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ታደሰ ሀጢያ ላይ በፌዴራል ፖሊስ ምርመራ ተጀምሮ እንደነበር ተሰምቷል ።
ችግሩ ከልማት ባንክ ያልፋል
ይህ ባንክ የትርፍ ገንዘብ የሚያመጣበት ሁኔታ ከባንኮች የተለመደ ስራም በተለያ መልኩ መሆኑ አስገራሚ ሆኗል ። ለወትሮው ባንክ ትርፍ ማግኘት ያለበት ካበደረው ከሚያገኘው ወለድ ቢሆንም ልማት ባንኩ ግን በካዝናው ባለው ገንዘብ የግምጃ ቤት ሰነድን ከብሄራዊ ባንክ በመግዛት ከሚገኝ ወለድ ነው ትርፍ የሚያገኘው ።
ይህ ባንክ የሚያበድረውን ገንዘብ የሚያገኘው የኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ የግል ባንኮች ብድር ሲሰጡ ከሰጡት ብድር 27 በመቶውን ከማእከላዊ ባንኩ ቦንድ እንዲገዙ በማድረግ ነው ፤ ይህም በአንድም ሆነ በሌላ መልኩ የልማት ባንኩ ብደር የህዝብ ገንዘብ ተደርጎ ይቆጠራል።
ብሄራዊ ባንክ በዚህ መልኩ ከግል ባንኮች በቦንድ የሰበሰበው ገንዘብ ከ60 ቢሊዮን ብር ማለፉን ተናግሯል ።
ይህ ገንዘብ ልማት ባንክ እንዲያበድረው እየተሰጠው ልማት ባንኩም እየከሰረ ነው ። የኪሳራው ሰንሰለትም ብዙዎችን ነው የሚጎዳው ።
የዶክተር አብይ አህመድ አስተዳደር የፋይናንስ አካሄድ የሚፈትነው የልማት ባንክ ጉዳይ ይመስላል ።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ የተሾሙ ሰሞን በሸራተን ሆቴል ከባለሀብቶች ጋር በነበራቸው ቆይታ የልማት ባንካችንን የብድር አሰጣጥ ሁኔታ እናየዋለን ጠብቁን ማለታቸው የሚታወስ ነው ። [ዋዜማ ራዲዮ]
Average Rating