- የጠቅላይ ሚንስትሩን ቢሮ በመሰለል መረጃው ለሶስተኛ ወገን ይተላለፍ ነበር
ዋዜማ ራዲዮ- የኢትዮ-ቴሌኮም ስራ አስፈፃሚ ዶ/ር አንዱዓለም አድማሴን ጨምሮ የተለያዩ የድርጅቱ ሀላፊዎች ከሀላፊነታቸው መነሳታቸውን ከድርጅቱ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
ወ/ሪት ፍሬሕይወት ታምሩ ዋና ስራ አስፈፃሚ ሆነው ተሹመዋል።
የግዥ፣ የሰው ሀይልና የኦፐሬሽን ሀላፊዎችም ተነስተዋል።
ሀላፊዎቹ ከጠቅላይ ሚንስትሩ ቢሮ በተፃፈ ደብዳቤ እንዲሰናበቱ መደረጉንም ለመረዳት ችለናል።
ዶ/ር አንዱዓለም በሀላፊነት በቆዩበት ወቅት ድርጅቱን ህገ ወጥ ለሆነ ተግባር ክፍት በማድረግና የአንድ አካባቢ ሰዎች የድርጅቱን አገልግሎት ለወንጀል እንዲጠቀሙበት አድርገዋል በሚል ሲወነጀሉ ቆይተዋል።
በድርጅቱ ላይ ምዝበራ ሲፈፀም ማስቆም አለመቻላቸው፣ የደህንነት መስሪያቤቱን እንደ ሽፋን በመጠቀም ግለሰቦች ከድርጅቱ የደንበኞችን ምስጢር እንዲያወጡ መንገድ ማመቻቸታቸው በድክመት ይነሳባቸዋል።
የኦፐሬሽን ሀላፊ የነበሩት አቶ ኢሳይያስ ዳኘው ከሀላፊነታቸው የተነሱት ቀደም ባሉት ቀናት ሲሆን ከሕወሐት ጋር በመመሳጠር የድርጅቱን ሁለንተናዊ እንቅስቃሴ በቁጥጥር ስር አውለው እንደነበር የድርጅቱ ባልደረቦች ይናገራሉ።
አቶ ኢሳያስ የሜቴክ ሀላፊ የነበሩት ክንፈ ዳኘው ወንድም ናቸው።
ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ ስልጣን ላይ ከወጡ በኋላ በኢትዮ ቴሌኮም ትብብር የጠቅላይ ሚንስትሩን ቢሮና የሌሎች ባለስልጣናትን የስልክ ግንኙነቶች በመጥለፍ መረጃውን ለሶስተኛ ወገን የማቀበል ስራ ሲሰራ እንደነበረም በድርጅቱ የቴክኒክ ዘርፍ ውስጥ ያሉ ሰራተኞች ለዋዜማ ተናግረዋል።
የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ (ኢንሳ) ማናቸውንም ስራዎቹን ያከናውን የነበረው በኢትዮ ቴሌኮም ወጪ እንደነበርና ተቋሙን ለከፍተኛ ምዝበራ አጋልጦት መቆየቱን የድርጅቱ ባልደረቦች ለዋዜማ ያስረዳሉ።
በየዘፉ የነበሩና በደህንነት መስሪያ ቤቱ ጭምር ተመድበው ሲሰሩ የነበሩ ባለሙያዎች ባለፉት ሳምንታት ከስራቸው እንዲሰናበቱ መደረጉ ይታወቃል። ” በብሄር ማንነታቸን ብቻ ከስራ እንድንባረር ተደርገናል” ያሉ የትግራይ ብሄር አባላት የሆኑ ሰራተኞች ቅሬታቸውን ወደ ህግ ለመውሰድ እየተዘጋጁ ነበር። ድርጅቱ ግን ብሄርን መሰረት ያደረገ እርምጃ አልተወሰደም ሲል እየተከራከረ ነው።
አዲሷ ተሿሚ ወ/ሪት ፍሬሕይወት በድርጅቱ ውስጥ በቦርድ አባልነት፣ በምክትል ስራ አስፈፃሚነት፣ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ዘርፍ ሀላፊ በመሆን ለ8 ዓመታት ያገለገሉ ሲሆን በአሁኑ ወቅት የዶክሳ አይቲ ቴክኖሎጂ መስራችና ዳይሬክተር ናቸው።
የድርጅቱ የቦርድ ሰብሳቢ አቶ ተፈራ ደርበውም ድርጅቱን በተገቢው መምራት ባለመቻላቸው በቅርቡ ከሀላፊነት ለማንሳት ዝግጅት እየተደረገ እንደነበርም ስምተናል።
ከኢትዮ ቴሌኮም ኃላፊነት የተነሱት ዶ/ር አንዷለም አድማሴ የከፍተኛ ትምህርት አግባብነትና ጥራት ኤጀንሲ ዳይሬክተር ሆነዋል። ይህ ኤጀንሲ የኢንሳ ምክትል ሀላፊ በነበሩትና በቅርቡ ለእስር ለተዳረጉት ለአቶ ቢንያም ተወልደ ተሰጥቶ የነበረ ነው።
Average Rating