www.maledatimes.com እሳትን ከውሃ፡ የታፈነው የአማራጭ ሃይል ታሪክ - MALEDA TIMES
Loading...
You are here:  Home  >  Ethiopia  >  Current Article

እሳትን ከውሃ፡ የታፈነው የአማራጭ ሃይል ታሪክ

By   /   October 28, 2012  /   Comments Off on እሳትን ከውሃ፡ የታፈነው የአማራጭ ሃይል ታሪክ

    Print       Email
0 0
Read Time:59 Minute, 32 Second
በግደይ ገብኪዳን
“ብዙ ሰዎች በጋዝ ነዳጅነት ተጠቅመው መኪናቸውን ሲያሽከረክሩ በሃይድሮጅን እያሽከረከሩት እንዳለ ልብ አይሉትም፡፡ እኛ [በውሃ የምትሰራ መኪና የሰራነው] ደሞ እያደረግን ያለነው ሃይድሮጅኑን ከውሃ ነው እየተጠቀምን ያለነው፡፡ የብሄራዊ ልኬት (ስታንዳርድ) ቢሮ መረጃ እንደሚያሳየው ደግሞ ውሃ ስትጠቀም የሚለቀቀው ሃይል ጋዝ ተጠቅሞ ከሚገኘው በማጠጋጋት ሁለት ከግማሽ በእጥፍ ይበልጣል፡፡ እናም ውሃ እጅግ ሃያል ነዳጅ ነው፡፡ ስታን መየር (እ.ኤ.አ. 1992)
እንዲህ የገዘፈ ትራጀዲ የሰው ልጅን አልገጠመውም፡፡ ይህ በሰው ልጅ ላይ የደረሰው ከፍተኛው በደል ነው፡፡ ይህ ውድቀት በአራተኛው ክፍለ ዘመን ላይ በአለክሳንደርያ ቤተ መፃህፍት በእሳት ቃጠሎ መውደሙ በሰዎች ስልጣኔን ወደኋላ በመጎተት ከደረሰው ኪሳራ የከፋ ነው፡፡ ይህ ሳይንሳዊ ግኝት ከቤንጃሚን ፍራንክሊን የኤሌክትሪሲቲ ግኝት የበለጠ፣ ከቶማስ ኤዲሰን አለማችንን ለመጨረሻ ግዜ የቀየረው የፐርል ጎዳና ኤሌትክ ማከፋፈያ ስርአት ምስረታ እጅግ የበለጠ ነው፡፡ ሁለተኛውን ኢንዱስትሪያዊ አብዮት በር የከፈተው የኒኮላ ቴስላ ኤሌትሪክ ሃይል በገመድ አርቆ እንዲጓዝ ያስቻለው የአልተርኔቲንግ ከረንት ግኝቱ በላይ የሆነ ፈጠራ ነው፡፡ በነገራችን ላይ ሌሎች ይፋ ያልሆኑ የኒኮላ ቴስላ ፈጠራዎች ይበልጣል ማለቴ አይደለም፡፡
ይህ ፈጠራ ውሃን በመሰንጠቅ ማለትም ሃይድሮጅኑንና ኦክስጅኑን በመለያየት ሃይል መፍጠር ማለት ነው፡፡ ይህ ፈጠራ ጥቅም ላይ ቢውል የካርበን ልቀትን ሙሉ ለሙሉ ያስወግዳል፡፡ የሰው ዘር በማለቅ ላይ ባለው ነዳጅ ላይ ካለው ጥገኝነቱ ያላቅቀዋል፣ በዚህም ሰበብ የሚከሰቱት ጦርነቶች እና የሰው ህይወት ህልፈቶች ማስወገድ ይቻላል፡፡ ከቆሻሻው፣ አስቂኙ እና አደገኛው የኒኩሌር ሃይልን አገልግሎት አላስፈላጊ ያደርገዋል፡፡ አስቂኝ የተባለበት ምክንያት የኒኩሌር ነዳጅ ዘንጎችን (ፍዩል ሮድስ) ለማምረት የሚፈጀው ሃይል ኒኩሌር ጣብያ ገብተው ከሚሰጡት ሃይል በላይ ስለሆነ ነው፡፡ ይህ የታፈነው ቴክኖሎጂ ከሚጠቀምበት ሃይል እጅግ የበለጠ ሓይል ይሰጣል ምክንያቱም ነዳጁ ውሃ ስለሆነ ነው፡፡
በውሃ እንዲሰራ የተደረገ መኪና ከእድሳት ወጪ በተጨማሪ እያሻቀበ በሚሄድ በንፁሃን ደም ፈሶበት የተገኘ ነዳጅ ወጪ አትጠይቅም፡፡
ይህ ግን በሚያሳዝን እና ቅስም በሚሰብር ሁኔታ እውን እንዲሆን አልተፈቀደም፡፡ የኣለም ጥቂት ገዢ ቁንጮዎች ለጥቅም እና ለስልጣን ካላጨው ጥማት የተነሳ በቴክኖሎጂ ወይም በሃይል ዘርፍ የሰው ዘርን ነፃ እንዲወጣ የሚያደርግ ተግባር እውን እንዲሆን አልፈቀዱም፡፡ ቁንጮዎቹ ስቃያችንን እንደ አሳዛኝ እጣ ፈንታችን ተቀብለን እንድንፋላቸው ነው ምኞታቸው፡፡ ለነሱ ምድሪቷን እየሞላ ያለው የሰው ዘር ሰውነት ላይ እየተንሰራፋ እንዳለ ካንሰር ወይም ጥገኛ ተዋህስያን ነው የሚጣያቸው፣ ለዚህ ህዝብ ነፃ ሃይል ሳይሆን ያዘጋጁለት ሰው ሰራሽ ረሃብ፣ ሰው ሰራሽ የተፈጥሮ አደጋ፣ ሰው ሰራሽ ወረርሽኝ፣ ሰው ሰራሽ ጦርነት ወይም ባጭሩ ድንቁርናና ህልቂት ነው፡፡
ስታን መየርን ይተዋወቁት
ስታን መየር የፈጠራ ብልህ (ጂንየስ) ነው፡፡ It Runs on Water በሚል ርእስ ለተዘጋጀ ዘጋቢ ፊልም በሰጠው ቃለ መጠይቅ እንደሚለው ከሆነ በውሃ የሚሰራውን መኪና ቴክኖሎጂ የፈጠረው በሰባዎቹ አንድ ትንሽዬ ዓረብ ሃገር አሜሪካ ላይ የነዳጅ ማእቀብ በማድረግ ግዙፉን ሃገር መንቀጥቀት የምትችል መሆኗን ከነዳጅ ቀውሱ በኋላ ሲታሰብ ለመፍጠር ተነሳሳሁ ይላል፡፡ የተለመደው የትምህርት ዘይቤን አልተከተለም፡፡ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን እንኳን አላገባደደም፡፡ አቋርጦ የምርምር ተቋም ተቀላቀለ፡፡
የፈጠራ ብቃቱን በጥቅም አሳልፎ መስጠት አልፈለገም፡፡ ፈጠራውን እንዲደብቅ ከዓረብ አገር የመጡ ከበርቴዎች እስከ ቢሊዮን ዶላር (እስከ ሃያ ቢሊዮን ብር) ድረስ ማታለያ አቅርበውለት ነበር፡፡ ለአሜሪካ መንግስት እና ቁንዎች የሚሰሩ የደህንነት ሰዎች የተለያየ የማስፈራርያ ዛቻ ይደርስበት ነበር፡፡ ይህን ሁሉ ተቋቁሞ ነበር የፈጠራ ስራውን ያከናውን የነበረው፡፡ ከነዳጅ እና ጦርነት ትርፍ ያግበሰብሱ ከነበሩት ጋር ሳይሆን ከተራው ህዝብ ጋር ነበር ልቡ፡፡
የውሃ መኪናው ከኤሌትሪክ መኪና የተሸለች ነች ምክንያቱም የኤሌትክ መኪኖቹ ዞሮ ዞሮ የሚሞሉት የኤሌትሪክ ሃይል ታዳሽ ካልሆነ ምንጭ የተገኘ ሊሆን ስለሚችል ነው፡፡ የስታን የውሃ መኪና ከጀነራል ሞቶርስ የሃድሮጅን መኪና በጅጉ የተሸለ ነነበር ምክንያቱም የጂ ኤም የሃይድሮጅን መኪና የተሸከመችው ሃይድሮጂን ካርቦን አመንጪ ሃይል ተጠቅሞ የተሰራ ነው፡፡
ስታን ግማሽ አምፒር ኤሌክትሪክ ተጠቅሞ ውሃ ውስጥ ያለውን ሃይድሮጅን እና ኦክስጅን መለያየት ችሏል፡፡ ሃይድሮጅኑ በሚፈጠርበት ግዜ ሲቃጠል በጋዝ ከሚፈጠረው ፍንዳታ የላቀ ነው፡፡ የስታን የውሃ ኢንጅን በቀላሉ አውሮፕላኖችን፣ መርከቦችን፣ ባቡሮችን፣ መንኩራኩሮችን ሁሉ ሃይል ምንጭ ሊሆናቸው ይችል ነበር፣ ይህም ሙሉ ለሙሉ የነዳጅ አስፈላጊነትን ያስቀር ነበር፡፡
በተለምዶ በሚሰጠው ትምህርት ውሃን ለመሰንጠቅ የሚጠቀመው ሃይል ከተሰነጠቀ በኋላ ከሚገኘው ሃይል እጅጉኑ የላቀ ነው ስለዚህም ከውሃ ሃይል ማትረፍ አይቻልም ይላል፣ ዘዴውም ኤሌክትሮሊሲስ ይሰኛል፡፡ ስታን ግን እጅግ ዝቅተኛ ኤሌትሪክ ተጠቅሞ ውሃን በመሰንጠቅ እጅግ የላቀ ሃይል ማመንጨት ችሏል፡፡ ለዚህም የአይምሮ ንብረት መብት ምስክር ወረቀት ከስንት ትግል በኋላ ተቀብሎበታል፡፡
ይህን ፈጠራውን ማጣጣል የመረጡ ሳይንቲስቶች የሚያቀርቡት ምክንያት አላቸው፡፡ ምክንያታቸውም እንደ ፈጠራ ሰው ሳይሆን እንደሳይንቲስት ስለሆነ የሚያወሩት ሰምን ልናልፋቸው እንችላለን፡፡ እንደሚሉት ከሆነ ውሃ አይቀጣጠልም፣ በኤሌክትሮሊሲስ ውሃን ሰንጥቀን የምናገኘው ጉልበት ለመሰንጠቅ ከምናወጣው ጉልበት እጅግ ያነሰ ነው፡፡ እናም ውሃን ወደ ሃይድሮጅን ስንቀይረው ሃይል ይጠፋል እንጂ አይፈጠርም ይላሉ፣ እናም ይህ ሃሳባቸውን አለመቀበል ሁለት የሳይንስ ህጎችን የመጀመርያው እና ሁለተኛው የቴርሞዳይናሚክስ ህጎች ጥሰትን መፈፀም ነው ይሉናል፡፡ ይህ ከሳይንቲስቶች የሚጠበቅ ነው ምክንያቱም እነሱ የሚያስቡት ቀድመው በቀረፁት መጫወቻ ሜዳ አጥር ውስጥ ሁነው ነውና፡፡ የፈጠራ ሰዎች ግን ከሳይንሳዊ ህጎች በላይ በተግባራዊ ሙከራ ይሰራል ወይስ አይሰራም የሚለው ይበልጥ ያሳስባቸዋል፡፡ ለዚህም ነው አብዛኞቹ አለምን የቀየሩ ፈጠራዎች ሳይንቲስቶች ከሚውሉበት የኒቨርስቲ ሳይሆን ከፈጠራ ሰዎች ቤት የሚመነጩት፡፡ የስታን ቴክኖሎጂም እንደሚሰራ በተግባር የታየ ነው፡፡
ስታን መየር ከላይ ለጠቀስነው የቢቢሲ ፊልም በሰጠው ቃል መላእክት እንደሚጠብቁት እንደሚያምን ተናግሮ ነበር፡፡ ሆኖም እ.አ.አ. በማርች 1998 ዓ.ም በከተማው ግሮቭ ሲቲ ሬስቶራንት ምግብ በልቶ ከወጣ በኋላ መኪና መቆምያው ጋር ሞተ፡፡ መንታ ወንድሙ ስቲቭ መየር እንደተናገረው ከሆነ ከመሞቱ በፊት መረዙኝ ብሎ ነበር፡፡ ከሞቱ ከሳምንት በኋላም የመንግስት ሰዎች ቤቱ መጥተው መኪናውን በጋሎን መቶ ማይል (በ3.785 ሊትር ውሃ 1,609.344 ሜትር) የምትሄደውን መኪናውን እና የምርምር እቃዎቹን በርብረው ወስደዋል፡፡ መኪናውን ሲያሰራት፣ ሲነዳት እና እንዴት እንደምትሰራ ከነሙሉ ማብራርያው በቪድዮ እና በፅሁፍ ከኢንተርኔት ማግኘት ይቻላል፡፡ ለመጀመር ያህል ድረ-ገፃቸውን መጎብኝት ይቻላል፡www.waterpoweredcar.com
በውሃ የምትሰራው መኪና
ውሃን ወይም ሃይድሮጂን/ኦክስጅን እንደሃይል ምንጭ የሚጠቀሙ መኪኖች መቶ በመቶ ውሃን እንደ ነዳጅ የሚጠቀሙ እውነተኛ ፈጠራ ናቸው፡፡ ውሃን በኤሌክትሮሊሲስ በመክፈል ጋዝን መተካት ይቻላል፡፡ በትምህርት ቤት ይህ እንደማይቻል ትምህርት ይሰጣል፡፡ ከተሰጣቸው አጥር ውጪ የማየት ምናብ የሌላቸው ኢንጂነሮች፣ ሳይንቲስቶች እና ፕሮፌሰሮች በዚህ ዝባዝንኪ ማመን እብደት ነው ይላሉ፡፡ እንደተሳሳታችሁ ለማሳየትም ማስረጃቸውን ሊያቀርቡ ይችላሉ፡፡ የፊዚክስ ህጎቻቸው እ.ኤ.አ በ1825 ዓ.ም በተፈጠረ ንድፈ ሃሳብ ላይ የተንጠለጠለ ነው፡፡ የፋራዳይ ህጎች፡፡ የመጀመርያው ኢንተርናል ኮምባስሽን ኢንጅን ወይም በተለምዶ ሞተር በውሃ የሚሰራ እንደነበር ያውቃሉ? ናፖሊዮን ቦናፓርቴ ነበር የአይምሮ ንብረት መብት ፈቃዱን ለኒፕሲ ወንድማማቾች  (Niepce Brothers) የሰጣቸው፡፡ ትላልቅ የመኪና ድርጅቶች በዚህ ዙርያ እየሰሩ ይገኛሉ፣ የተለያዩ የአይምሮ ንብረት መብቶችን በመግዛት እንቅስቃሴ የታወቁም አሉ፡፡ የማይሸጡ የፈጠራ ሰዎች እንዲወገዱ ይደረጋሉ፡፡ ከላይ በጠቀስነው ዶክመንታሪ አዘጋጁ ለማንኛውም ፈጠራ ሳይንስቶች የሚሰጡትን ምላሽ በአራት ደረጃ ከፋፍሎ ያቀርበዋል፡
አንደኛ፡ “ይህ ወለፈንዴ ሃሳብ ነው፡፡”
ሁለተኛ፡ “ይህ ወሳኝ አይደለም፡፡”
ሶስተኛ፡ “ሁሌም ቢሆን ይህ ጥሩ ሃሳብ ነው እል ነበር፡፡”
አራተኛ፡ “ቀድሜ አስቤው ነበር፡፡” ይላሉ ብሎ ያስረዳል፡፡
ይህ መኪና ጥቅም ላይ ቢውል የሚጎዳው ብቸኛው አካል የነዳጅ ድርጅቶች ብቻ ናቸው፡፡ ኢኮኖሚውን ያናጋዋል የሚል ፍራቻ ከፖለቲከኞች ይሰማል፡፡ ይህ ግን ስህተት ነው፡፡ እነሱ አሁን ህዝቡን እያታለሉ ከዚህ ትርፍ እያገኙበት ነው፡፡ መንግስታት የሃይል እጥረቱን ለመፍታት የሚያቀርቡት ሃሳብ ሃገራትን ከመውረር እና ጦርነት እና እርስ በርስ ግጭት ከማስፋፋት ውጪ አዋጭነት የሌላቸውን ቴክኖሎጂዎችን ነው፡፡ ለምሳሌ ስለ ሃይድሮጅን እንኳ የሚቀርበው ሃሳብ ውሃን አይነካም ስለ ሃድሮካርቦን እና ስለ ሃይድሮጅን ማደያ እና እኚህን ለመተግበር ግዙፍ መኪኖችን ማስለመድ ላይ ተጠምደዋል፡፡ እራሷ ውሃ ሞልታ ሃይድሮጅን እያቃጠለች የምትሄድ ቴክኖሎጂ ለፖለቲካዊ ግባቸው ተስማሚ አይደለችም፡፡
እና በዚህ በ20ኛው ክ/ዘመን ታላቅ ፈጠራ ዙርያ ምን እያደረጉ ነው? በድብቅ ለግላቸው ከመያዝ ውጪ ምንም አላደረጉም፡፡ ለምን? አምርተው ካስፋፉት የዓለም ችግርን ሊቀርፍ ነው፡፡ የዓለም ችግር ከተፈታ ለስልጣን እና አለም አቀፋዊ ግባቸው እንቅፋት ይሆንባቸዋል፡፡
“መደምደምያ፡” ይሉና ዶ/ር ጂን ማሎቭ (Dr. Gene Mallove) ሌላኛው የተገደሉ የፈጠራ ሰው ስለ ስታን መየር በፃፉት አጭር ፅሁፍ “ስታንሊም የለም ጋዝ መግዛታችንን ቀጥለናል፣ የዓለም ሙቀትንም በሚገርም ፍጥነት መጨመር ተያይዘነዋል፣ እናም ማንም ምንም አያደርግም፡፡” ብለው ባጭሩ ይዘጉታል፡፡
ሌሎች የታፈኑ አማራጭ የሃይል ምንጭ ቴክኖሎጂዎች
የላይኛው የስታን ታሪክ በአማራጭ ሃይል ምንጭ ዙርያ እጅግ አዋጭ ኤሌክትሮሊሲስ ዘዴ ተጠቅሞ የሰራውን እና የገጠመውን የዳሰስነው ነው አሁን ከስር አጠር አድርጌ ሌሎች የታፈኑ ቴክኖሎጂዎችን አስነብባችኋለው፡፡ “The Free Energy Secrets of Cold Electricity” የተሰኘው መፅሃፍ ደራሲው ፒተር ሊንደርመን የፃፋት “Where in the World is all the Free Energy?” የተሰኘችው አጭር ፅሁፍ ለዚህ ምንጫችን ትሆናለች፡፡
በ1880ዎቹ መጨረሻ ጆርናሎች በቅርቡ “ነፃ ኤሌክትሪሲቲ” በቅርቡ እንደሚገኝ ሲተነብዩ ነበር፡፡ ስለኤሌክትሪሲቲ የሚደንቁ ግኝቶች በየቀኑ ይፋ ይደረጉ ነበር፡፡ ኒኮላ ቴስላ “ገመድ አልባ መብራት” እና ሌሎች ከከፍተኛ ሞገድ ኤሌክትሪሲቲ ጋር የተያያዙ ተአምራትን ለህዝብ ሲያሳይ ነበር፡፡ መጪው ግዜ ስለያዘው ነገር ከፍተኛ ጉጉት ተፈጥሮ ነበር፡፡
ቀጥሎ ባሉት 20 ዓመታት መኪኖች፣ አውሮፕላኖች፣ ተንቀሳቃሽ ምስል (ፊልሞች)፣ የተቀረፁ ዘፈኖች፣ ስልክ ወይም ቴሌፎን፣ ራድዮ እና ካሜራ ዓለምን ተቀላቀሉ፡፡ ህመም እና ድህነት እጅ እንደሚሰጡ ተስፋ ተደረገ፡፡ ሂወት እየተሻሻለ መጣ፡፡ ሁሉም ከዳቦው እየደረሰው ነበር፡፡
ሌሎች ዘርፎች እንዲህ ሲቀያየሩ ኤሌክትሪሲቲ ግን ባለበት ቀረ፡፡ ምን ተገኘ? ግንቶቹ ሁሉ ስህተት ነበሩ ማለት ነው? የተሻሻለ ነገር አልፈጠረም ማለት ነው? የነዚህ ጥያቄ ምላሹ አሉታዊ ነው፡፡ አዲስ ነገሮች ተገኝተዋል፣ ከዛን ግዜ ጀምሮ በዝቅተኛ ወጪ ግዙፍ ሃይል መፍጠር ተችሏል፡፡ ከነዚህ ዘዴዎች ግን አንዳቸውም ለህዝብ እንዲቀርቡ አልደረገም፡፡ የዚህ ምክንያቱን መጨረሻ እንመለስበታለን፡፡ አሁን ግን ዘዴዎቹን እንመልከታቸው፡፡ እነዚህ የተለያዩ ዘዴዎችን አንድ የሚያደርጋቸው ባህርይ አለ እርሱም ሁሉም የሚስቡት የሃይል ምንጭ በአከባቢው በዙርያችን ከሚገኘው ኢተር ፊልድ ነው፡፡
1.      ራድያንት ኢነርጂ (Radiant Energy)፡ ይህ የኒኮላ ቴስላ አጉዪ ማስተላለፍያ (Magnifying Transmitter)፣ የቲ. ሄነሪ ሞራይ ራድያንት ኢነርጂ ዲቫይስ (Radiant Energy Device)፣ የኤድዊን ግረይ ኢ ኤም ኤ ሞተር (EMA Motor) እና የፖል ባውማን ቴስታቲካ ማሽን (Testatika Machine) ሁሉ የሚከተሉት ዘዴ ነው፡፡ በተፈጥሮ ያለው የሃይል ይዘት (በተለምዶ “ስታቲክ” ወይም “ቋሚ” ኤሌክትሪሲቲ የሚባለው) ቀጥታ ከከባቢ አየሩ ወይም ከተራ ኤሌክትሲቲ “ፍራክሽኔሽን” በተሰኘ ዘዴ መሰብሰብ ይቻላል ፡፡ ራድያንት ኢነርጂ ከተለመደው ኤሌክትሪሲቲ ከሚጠይቀው አንድ መቶኛ ወጪ ብቻ በማውጣት ሃይል ያስገኛል፡፡ ይህ ሃይል ልክ የኤሌክትሪክ ባህርያት ስለሌሉት በሳይንስ ማህበረሰቡ ዘንድ አለመረዳትን ፈጥሯል፡፡  በአሁኑ ግዜ በስዊዘርላንድ የሚገኝ የመተረኒታ ማህበረሰብ (The Methernitha Community) የተሰኙ ኗሪዎች እንዲህ አይነት አምስት ወይም ስድስት ማሽኖች ባለቤቶች ናቸው፡፡
2.     ቋሚ – የማግኔት – ሃይል – ሞተር (Permanent-Magnet-Powered Motors)፡ ዶ/ር ሮበርት አዳምስ (ከኒው ዚላንድ)፣ ዶ/ር ቶም ቢርደን (ከዩ.ኤስ.ኤ.) ሁለቱም የየራሳቸው የሚሰሩ ሞዴሎች አሏቸው፡፡ ቢርደን ማሽኑን ሞሽንለሽ ኤሌክትሮማግኔቲክ ጀነሬቶር ወይም ኤም ኢ ጂ ይለዋል፡፡ ዤን-ሉ ናውዲን በፈረንሳይ የቢርደንን ማሽን ቅጂ መስራት ችሏል፡፡ የዚህ መሳርያ መሰረታዊ መርሆች እ.ኤ.አ በ1978 በፍራንክ ሪቻርድሰን (ከዩ.ኤስ.ኤ) ነበር የተገኘው፡፡ ተሮይ ሪድም (ከዩ.ኤስ.ኤ) መሳርያ አለው፡፡ ሌሎችም ብዙ የፈጠራ ሰዎች ማግኔት ተጠቅመው ሞቶር ቶርክ (motor torque) ሰርተዋል፡፡
3.     መካኒካል ማሞቅያዎች (Mechanical Heaters)፡ መካኒካል (ተንቀሳቃሽ) ጉልበትን ተጠቅመው እጅግ ሰፊ ሙቀት ማምረት የሚችሉ ሁለት ዓይነት ማሽኖች አሉ፡፡ የፍረኔቴ (Frenette) እና ፐርኪንስ (Perkins) (ሁለቱም ከዩ.ኤስ.ኤ) ተሸከርካሪው ሲሊንደር ናቸው፡፡ በነዚህ ማሽኖች አንድ ሲሊንደር ባንድ ሲሊንደር ውስጥ በማህላቸው የአንድ ስምንተኛ ኢንች ልዩነት ኑሮት ይሽከረከራሉ፡፡ በማህል ያለው ክፍተት በውሃ ወይም በዘይት ይሞላል፣ ይህ ፈሳሽ ነው ሲሊንደሩ ሲሾር የሚሞቀው፡፡ ሌላኛው ማግኔት የሚጠቀመው ነው፡፡ ይህ በሙለር (ከካናዳ)፣ በአዳምስ (ከኒው ዚላንድ) እና በሪድ (ከዩ.ኤስ.ኤ) ተሰርተዋል፡፡ እኚህ ማሽኖች ከተለመደው አስር እጥፍ የላቀ ሙቀት ያመነጫሉ፡፡
4.     እጅግ-የላቀ-ኤሌክትሮሊሲስ (Super-Efficient Electrolysis)፡ ይህ ከላይ ያየነው ነው፡፡ ውሃ ወደ ሃይድሮጅን እና ኦክስጅን መክፈል ነው፡፡ የመማርያ የኬሚስትሪ መፃህፍት ይህን ለማድረግ የሚፈጀው ሃይል በኋላ ሁለቱ ሲጣመሩ ከሚገኘው ሃይል ያነሰ ነው ይላል፡፡ ይህ እውነት የሚሆነው በቀሽም ሁኔታ (worst case scenario) ስር ብቻ ነው፡፡ ውሃ ስታን መየር እንደሰራው ወይም Xogen Power, Inc. የተባለ ድርጅት እንዳደረገው ተደርጎ በራሱ ሞገድ (molecular resonant frequency) የተመታ እንደሆነ እጅግ ዝቅተኛ ኤሌክትሪክ በመጠቀም ወደ ሃይድሮጅን እና ኦክስጅን መክፈል ይቻላል፡፡ ኤሌክትሮላትስ ውሃው ውስጥ በመጨመር ደግሞ ይበልጥ የተሸለ ውጠየት ማግኘት ይቻላል፡፡ የዚህ ውጤት ገደብ የሌለው የሃይድሮጅን ምንጭ ተገኘ ማለት ነው፣ በውሃ ወጪ ከመኪና አስከመንኩራኩር ማሽከርከር ይቻላል ማለት ነው፡፡ እጅግ የሚደንቀው ደግሞ ፍሬድማን (Freedman) (ከዩ.ኤስ.ኤ) እ.ኤ.አ በ1957 የራሱ የብረት ቅይጥ ተጠቅሞ ያለምንም ኤሌክትሪክ ጉልበት እና ብረቱ ላይ ምንም ኬሚካላዊ ለውጥ ሳይከተል ውሃ በብረቱ መክፈል የሚያስችለውን የአይምሮ ንብረት ምስክር ወረቀቱን ወስዷል፡፡ ይህ ማለት ይህ የብረት ቅይት ወይም አሎይ ያለ ተጨማሪ ወጪ ዘላለሙን ከውሃ ሃይድሮጅን ያመርትልናል ማለት ነው፡፡
5.     ኢምፕሎዥን/ቮርቴክስ ኢንጅን (Implosion/Vortex Engines)፡ ሁሉም ግዙፍ ኢንዱስትሪ ኢንጅኖች እንደ መኪና ኢንጅን ስራ ለመስራት ሙቀትን ይጠቀማሉ፣ ሙቀቱ መስፋፋት እና ግፊት በመፍጠር ስራን ያስገኝልናል፡፡ ተፈጥሮ ግን በተቃራኒው ነች የምትሰራው፣ በማቀዝቀዝ መመጠጥ እና ባዶ መቅረት በማስከተል ስራን ታስገኛለች፡፡ ልክ እንደ አውሎ ንፋስ ማለት ነው፡፡  በ1930ዎቹ እና 1940ዎቹ ነበር ለመጀመርያ ግዜ ኦስትሪያዊው ቪክር ሻዉበርገር (Viktor Schauberger) የሚሰሩ የኢምፕሎዥን ኢንጅን ሞዴል የሰራው፡፡ ካሉም ኮትስ “Living Energies” በሚለው መፅሃፉ የሰውየውን ስራ ላይ በሰፊው ፅፏል፡፡ ከዛን ግዜ ወዲህ ነዳጅ የማይጠቀሙ ከባዶ (ቫኲም) የሚወሰድ ጉልበት ተጠቅመው ተንቀሳቃሽ ስራ ማስገኘት የቻሉ ኢንጅኖችን የሰሩ ሰዎች ብዙ ናቸው፡፡ ከዚህ የቀለሉ ደሞ የቮርቴክስ እንቅስቃሴን ተጠቅመው ከስበት እና ሴንትሪፉጋል ጉልበት በፈሳሾች ውስጥ ቋሚ እንቅስቃሴን ማስገኘት የቻሉ አሉ፡፡
6.     ኮልድ ፊውዥን ቴክኖሎጂ (Cold Fusion Technology)፡ እ.ኤ.አ ማርች 1989 ዓ.ም ማርቲን ፍሌሽማን እና ስታንሊ ፖንስ የተባሉ ሁለት ኬሚስቶች ከብሪንሃም ያንግ ዩኒቨርስቲ፣ ዩታ (ዩ.ኤስ.ኤ) በቀላል ጠረጴዛ ላይ በሚቀመጥ መሳርያ አቶሚክ ፉውዥን ሪአክሽን ማግኘታቸውን ይፋ አደረጉ፡፡ ይህን ተከትሎ በስድስት ወር ውስጥ ግኝታቸው ውሸት ነው ተብሎ ከህዝብ እንዲሰወር ተደረገ፡፡ የእውን ግን ኮልድ ፊውዥን የሚሰራ እውነታ ነው፡፡ በተደጋጋሚ ተጨማሪ ሙቀት ብቻ ሳይሆን ያስመዘገቡት፣ ዝቅተኛ ጉልበት ያላቸው አቶሚክ ንጥረ ነገር የለውጥ ሂደት ተመዝግቧል፣ እጅግ ብዙ የተለያዩ ሪአክሽኖችን በማካተት! ይህ ቴክኖሎጂ ዝቅተኛ ወጪ ያለው ኢነርጂ ማመንጨት ይችላል፣ ሌላም ተጨማሪ ኢንዱስትሪያዊ ፋይዳ ይኖረዋል፡፡
7.     የፀሃይ ሙቀት መንፊያ መሳርያ (Solar Heat Pump): ከነዚህ ተጠቃሹ በየቤቱ የገባው ማቀዝቀዣ ማሽን (ፍሪጅ) ነው፡፡ ይህ በኤሌክትሪክ የሚሰራ ሙቀት መንፊያ ነው፡፡ አንድ የጉልበት መጠን (ኤሌክትሪክ) ተጠቅሞ ሶስት ጉልበት (ሙቀት) ይሰራል፡፡ ይህ በሶስት እጥፍ መጨመሩ “ኮኦፊሸንት ኦፍ ፐርፎርምንሱን” ሶስት ያደርገዋል፡፡ ፍሪጁ በዚህ መልኩ ሙቀት ከፍሪጁ ያስወግዳል፡፡ ይህ ግን የቴክኖሎጂው እጅ ደካማ አጠቃቀም ዘዴ ነው፡፡ የሙቀት መንፍያው ሙቀትን “ከምንጩ” ወደ “መጥለቂያው” ያስተላልፋል፡፡ ምንጩ ሙቅ ሲሆን መጥለቂያው ደሞ ቀዝቃዛ መሆን ይኖርበታል ይበልጥ ውጤታማ እንዲሆን፡፡ በፍሪጅ ግን የዚህ ተቃራኒ ነው የሚሆነው፡፡ የሙቀቱ ምንጭ ቀዝቃዛ ከሆነው ሳጥን ውስጥ ሲሆን ሙቀቱ የሚወገድበት ደሞ ወደ ቤቱ ሲሆን የቤቱ ሙቀትን ያህል አለው ማለት ነው፡፡ ለዚህ ነው ኮኦፊሸንቱ ዝቅተኛ የሆነው፡፡ ይህ የሁሉም ሙቀት መንፍያ መሳርያዎች እውነታ አይደለም፡፡ ኮኦፊሸንታቸው ከ8 እስከ 10 የሚደርሱ መሳርያዎች አሉ፡፡ ከዚህም የተሻሉ ምሳሌዎች አሉ፡፡ እኚህ የፀሃይን ወይም የውቅያኖስ ሙቀትን የሚጠቀሙ መሳርያዎች ናቸው፡፡ ከሶላር ፓነል ጋር እንዳይጋጭባቹ ይለያያሉ፡፡
አሁን ግሪን ሃውስ ጋዞችን መልቀቁን ማስቆምና የኒኩሌር ሃይል ጣብያዎችን መዝጋት እንችላለን፡፡ አሁን በዝቅተኛ ወጪ የውቅያኖስ ውሃን ማጣራት እንችላለን፣ በዚህም የውሃ እጥረትን ሙሉ ለሙሉ መቅረፍ እንችላለን፡፡ የሁሉም ምርቶች ማምረቻ እና ማጓጓዣ ወጪ እጅግ በጣም ይወርድልናል፡፡ ምግብ በየትኛውም ወቅት በየጥኛውም ቦታ ማብቀል ይቻላል፡፡
እኚህ ሁሉ አስደናቂ ጥቅሞች ሂወት በምድራችን እጅ የተሸለ ሊያደርጉ የሚችልበት አጋጣሚ ለብዙ አስርት አመታት እንዲጓተት ተደርጓል፡፡ ለምን? በመዘግየቱ ማን ነው የሚጠቀመው?
የማይታዩት የአማራጭ ሃይል ጠላቶች
አማራጭ ሃይል በእግሊዘኛ በስፋት ፍሪ ኢነርጂ ማለትም ነፃ ሃይል እየተባለ በተለምዶ ይጠራል ይህ በቀላሉ ሊያስተን አይገባም እንደተመለከትነው ያለን ነገር ማጉላት እንጂ ከምንም ሃይል አልፈጠሩም ሆኖም ጋዜጦች ነገሩን በሚዘግቡበት ወቅት ያወጡለት ስም ስለሆነ ነው የተለመደው፡፡ እናም እኔ ለአማርኛው አማራጭ ሃይል እያልኩኝ ተርጉሜዋለው፡፡
አማራጭ ሃይል የሚገባውን ቦታ እንዳይዝ የሚያደርጉ አራት ግዙፍ ጠላቶች ተደቅነውበታል፡፡ ይህን ለማፈን ሴራ እንዳለ ብቻ አድርጎ ሴረኞችን መውቀሱ ነገሩን አቅልሎ ማየት ነው፡፡ ይህ ተወቃሽነትን ከያንዳንዳችን ውጪ ያደርገዋል፡፡ የሁላችንም ያለመንቃት እና ምንም ሳይንቀሳቀሱ መቀመጥ መምረጥ ጉዳይ ከነዚህ የማይታዩ ጉልበቶች ሁለቶቹ እንደ “በፀጋ መቀበል” አድርገው ይቆጥሩታል፡፡
እነማናቸው ከማይጠይቅ ህዝብ ውጪ ሶስቱ ጠላቶች?
1.    የገንዘብ ባላባቶች
በተለመደው ኢኮኖሚያዊ ንድፈ ሃሳብ ሶስት የኢንዱስት መደቦች አሉ፡ ካፒታል፣ ሸቀጥ እና አገልግሎት ናቸው፡፡ በካፒታል ስር ደሞ፡ ተፈጥሯዊ ካፒታል፣ መገበያያ ገንዘብ እና ብድር ይገኙበታል፡፡ በተፈትሯዊ ካፒታል ስር ጥሬ እቃዎች (እንደ ወርቅ መአድን)፣ የሃይል ምንጭ (እንደ ነዳጅ ጉድጓድ ወይም ውሃ ኤሌትክ ማመንጫ ግድብ) የመሳሰሉት ይጠቀሳሉ፡፡ መገበያያ ገንዘብ ደሞ ወረቀት “ገንዘብ” ማተምንና ሳንቲም መቅረፅን ያካትታል፣ ይህ በብዛት የመንግስት ስራ ነው፡፡ ብድር ደሞ የባንክ ደንበኞች በቁጠባ ሂሳባቸው ያስቀመጡትን በወለድ ክፍያ ኢኮኖሚያዊ እሴትን ለመጨመር ማበደርን ያካተተ ነው፡፡  በዚህ ሁኔታ ስንመለከተው የሃይል ምንጭ በኢኮኖሚው ውስጥ ያለው አስተዋፅኦ ልክ እንደ ወርቅ ወይም ገንዘብ ህትመት ወይም ብድር ነው፡፡
በዓለም ዙርያ ባሁኑ ወቅት የገንዘብ ዘርፉ በጥቂቶች እጅ ገብቷል ወይም የጥቂቶች ሞኖፖል ሁኗል፡፡ የፈለግነውን ያህል ገንዘብ የማካበት መብት አለን የምናካብተው ግን የታተመውን ያህል ብቻ ነው፡፡ በየትኛውም መልኩ በወርቅ ወይም በሌላ ዘዴ እንዲከፈለን ማድረግ መብት የለንም፡፡ በዓለም ደረጃ ዋና መገበያያ የሆኑት እንደ ዶላር፣ ዩሮ ወዘተ. በጥቂቶች የግል ባንክ ቁጥጥር ስር ናቸው፣ ባንኮቹ ደሞ ከዓለማችን እጅግ ጥቂት ሃታም ቤተሰቦች ስር ናቸው፡፡ እቅዳቸው የዓለማችንን ካፒታል ምንጭ 100 እጅ መቆጣጠር ነው፣ በዚህም የሁሉንም ሰው ሂወት በሸቀጦች እና አገልግሎቶች አቅርቦት (ወይም ባለማቅረብ) መቆጣጠር ነው፡፡ ነፃ የሆነ የሃብት ምንጭ (እንደ ነፃ/አማራጭ ሃይል) በዓለማችን በእያንዳንዱ ሰው እጅ መግባቱ ዓለምን በቋሚነት ለሁል ግዜ የመቆጣጠር እቅዳቸውን ያከሽፋል፡፡ የዚህን እውነትነት ማየት እጅግ ቀላል ነው፡፡
አሁን የወለድ መጠንን በመጨመር ወይም በመቀነስ የአንዲት ሃገርን እድገት ፍጥነት መቀነስ ወይም መጨመር ይቻላል፡፡ በኢኮኖሚው ግን ነፃ የካፒታል (ወይም ሃይል) ምንጭ ቢኖር ማንኛውም ግለሰብ ከባክ ሳይበደር የካፒታል መጠኑን ማሳደግ ይችል ነበር፡፡ ወለድን እንደ ሸምቀቆ ለመጠቀም የሚደረግ ሙከራ ውጤት አይኖረውም ነበር፡፡ የነፃ ሃይል ቴክኖሎጂ የገንዘብ ዋጋን መቀየር ይችላል፡፡ የአለማችን ቁንጮ ሃታም ቤተሰቦች እና አበዳሪዎች አዲስ ተፎካካሪ አይፈልጉም፡፡ የዚህን ያህል ነገሩ ቀላል ነው፡፡ ሞኖፖሊያቸውን ማጣት አይፈልጉም፡፡ ነፃ/ አማራጭ ሃይል መታፈን ያለበት ነገር ብቻ አይደለም ለነሱ ሁሌም መታገድ ያለበት ነገር ነው!
እንዲህ የሚያደርጉበት ምክንያታቸው “ከላይ የተሰጣቸው የመምራት ፀጋ” የሚል እምነታቸው፣ ስግብግብነታቸው (ጥማታቸው)፣ እና ከራሳቸው በቀር ሁሉን የመቆጣጠር አመላቸው ነው፡፡ ይህን ለማሳካት የተጠቀሙበት ዘዴ አታላይ “ሙያተኞችን”፣ ቴክኖሎጂዎቹን መብት ገዝቶ በመሸሸግ፣ የፈጠራ ሰዎች ግድያ እና የግድ ሙከራ፣ ስም ወይም ስብእና ማጥፋት፣ ስራዎችን ማቃጠል እና የፈጠራ ሙያተኛውን ሊረዱ ይችላሉ የሚባሉትን በገንዘብ መደለልና ማታለል የመሳሰሉት ናቸው፡፡ በተጨማሪም ነፃ ሃይል ምንጭ ሊሆን አይችልም የሚለውን የቴርሞዳይናሚክስ ህግ የበላይነት እንዳይነካ ስራዎችን ይሰራሉ፡፡
2.   ብሔራዊ መንግስታት
ሁለተኛው ሃይል መንግስታት ናቸው፡፡ እዚህ ያለው ችግር ገንዘብ የማተሙ ሳይሆን ብሄራዊ ደህንነት የሚሉት ነው፡፡ ዓለም አስፈሪ ጫካ ነች ሰዎች ደሞ እጅግ ጨካኝ፣ ከሃዲ እና ተንኮለኛ ተደርገው ሊቆጠሩ ይችላሉ፡፡ የሁሉንም ደህንነት ማስጠበቅ ደሞ የመንግስት ሃላፊነት ነው፡፡ ለዚህም ህግን ለማስከበር የፖሊስ ሃይል ይሰማራል፡፡ አብዛኞቻችን በህግ የምንገዛው ለግላችንም ጥቅም ቢሆን ቀናውን መንገድ እንደሚሻል ስለተቀበልን ነው፡፡ ሆኖም ግን የግል ጥቅማቸው የጋራውን ባለማክበር ይጠበቃል ብለው የሚያምኑ ይኖራሉ፡፡ ህገ ወጦች፣ ወንጀለኞች፣ ሰርጎ ገቦች፣ ከሃዲዎች፣ አብዮታውያን (ለውጥ አቀንቃኞች) እና አሸባሪዎች ሊሆኑ ይችላሉ፡፡  መንግስታት ደሞ ከረዥም ልምድ እነደተማሩት ከሆነ እንዳደረጉላቸው ነው መልሰው የሚያደርጉት፡፡ ሁሌም ጠንካራው የበላይ ይሆናል፡፡ በኢኮኖሚክስ ወርቃማው ህግ ይባላል፡ “ወርቅ ያለው የበላይ ይሆናል፡፡” በፖለቲካም እንዲሁ ነው ጠንካራው ብቻ ያሸንፋል፡፡
በፖለቲካ ግን ጠንካራው ማለት እጅግ ጨምላቃው ማለት ነው፡፡ የበላይነት ለማግኘት ሁሉን ነገር ያደርጋሉ፡፡ ሁሉም ወዳጅም ሆነ ጠላት እንደ ባላንጣ ነው የሚቆጠረው፡፡ ተወደደም ተጠላም የትኛውም የአለም መንግስታት የሚንቀሳቀሱበት ስነ ልቦናዊ ምህዳር ይህ ነው፡፡ የትኛውም መንግስት ባላንጣው የሚሻሻልበትን በር አይከፍትም፡፡ ይህ እራስን ማጥፋት ማለት ነው በሃገር ደረጃ፡፡ ለባላንጣ በር የሚከፍት ነገር ደሞ እንደ ብሄራዊ ደህንነት አደጋ ይታያል፡፡ ሁሌም!
ነፃ የሃይል ምንጭ የብሔራዊ መንግስት የስጋትና ቅዠት ምንጭ ነው፡፡ ይህ ተቀባይነት ቢኖረው ሁሉም የጦር የበላይነትን ለማግኘት ሩጫውን ይጀምራል፡፡ በአሁኑ ሁኔታ ነፃ የሃይል ምንጭ በሁሉ እጅ ቢገባ የሃይል ሚዛኑን የሚከለስበትን ሁኔታ ይፈጥራል፡፡ ይህ ገደብ የሌለው የሃብት እና ስልጣን ምንጭ የሆነውን ቴክኖሎጂ ሌላው እንዳይጠቀምበት ጦርነት ይከፈትበታል፡፡ ሁሉም ለራሱ ይፈልገዋል ሁሉም ደሞ ሌላው እንዳይዘው ይፈልጋል፡፡
በሶስት መንገዶች ማለትም፡ አንድ የውጭ ጠላት እንዳይጠቀምበት፣ ሁለት ግለሰቦች ከመንግስት ቁጥጥርን ውጪ በመውጣት ስርአት አልበኝነት እንዳይፈጥሩና የመንግስትን ስልጣን እንዳይቀናቀኑ እና ሶስት አሁን በጥቅም ላይ ካሉ የሃይል ምንጮች የሚገኘውን ገቢ ለማስጠበቅ ሲሉ መንግስታት ይህን ቴክኖሎጂ ይቃወሙታል፡፡
ለዚህ ዓላማም ሲሉ የአእምሮ ንብረት ማረጋገጫ ሰነድ ባለመስጠት፣ በግብር ጣጣዎች፣ በማስፈራራት፣ በድብቅ ስለላ፣ በማሰር፣ በማንደድ፣ በመዝረፍ ወዘተ ነፃ የሃይል ምንጭ ወደ ገበያው እንዳወጣ ያደርጋሉ፡፡
3.   ስህተት እና ቅጥፈት በአማራጭ ሃይል እንቅስቃሴ ዙርያ
ሶስተኛው ሃይል ያበዱ የፈጠራ ሰዎች፣ አጭበርባሪዎች እና አስመሳዮች ናቸው፡፡ ከላይ የተቀስናቸው ሁለቱ ሃይሎች አማራጭ ሃይልን ለማጣጣል የነዚህ ሰዎችን ስራ በሚድያ በስፋት ያቀርቡታል፡፡  በዚህ ሶስተኛው መደብ ስማቸው ዝነኛ እንዲሆን ከተደረጉት ኪሌ፣ ሁባርድ፣ ኮለር እና ኸንደርሾት የታወቁት ናቸው፡፡ የነዚህ ሰዎች ፈጠራዎች ልክ ሊሆኑ ይችሉ ይሆናል ግን በቂ ቴክኒካል መረጃ የለም፡፡ ዘርፉን ማጣጣል የሚፈልጉም የነዚህን ሰዎች ስም እና የማጭበርበር ስራ ደጋግመው ይጠቅሳሉ፡፡
4.   የማይጠይቅ ሕዝብ
ሌሎቹ ላይ ለማጥፋት ያለውን መነሳሳት ማየት ቀላል ነው፣ በያንዳንዳችን ውስጥ ያለውን ግን ማየት ይሳነናል፡፡ እንደ ቁንጮ ቤተሰቦቹ ሁላ በእኛም ውስጥ ከራሳችን ውጪ ሌሎቹን የመቆጣጠር ሚስጥራዊ ፍላጎት አይመላለስምን? ከፋተኛ ገንዘብ ቢቀርብልን እውነቱን አሳልፈን አንሰጥምን? ወይም እንደ መንግስታት የራሳችንን መኖር ወይም ሕልውና ቅድሚያ ከምንም በላይ ማረጋገጥ አናስቀድምም? በእሳት እየነደደ ያለ አዳራሽ ውስጥ እራሳችንን ብናገኝ ከድንጋጥያችን የተነሳ ደካሞቹን እየገፈተርንና እየጨፈለቅን ለመውጣት አንሞክርም? ወይም ደሞ እንዳበደው የፈጠራ ሰው አንዳንድ ግዜ የሚኮረኩር እውነታን በሚደላ የቁም ህልም ወይም ውሸት አንቀይርም? ሌሎችን የሚገባቸውን ከመስጠት ይልቅ ይበልጡኑ ስለራሳችን ስናጠነጥን አንውልም? ታላቅ ምቾትን ቃል ቢገባም የማይታወቀውን ነገር አንፈራም?
አራቱም ሃይሎች በህብረተሰቡ በተለያየ መዓርግ የሚንቀሳቀስ የአንድ ጉልበት የተለያዩ ገፅታዎች ናቸው፡፡ እናም ነፃ የሃይል ምንጭ የሰው ልጅ እንዳያገኝ ያደረገው ብቸኛው ተጠያቂ መነቃቃት የሌለው የሰው ተፈጥሮ ነው፡፡ ነፃ የሃል ምንጭ ሁሉ የተትረፈረፈበት በመፈቃቀድ እና መቻቻል የተመሰረተ ማህበረሰብ ወይም ምድራዊ ገነት እና የፈጣሪ ፈቃድ መገለጫ ነው፡፡ እርስ በርስ የማይቀናኑ፣ ወደ ጦርነት እና አካላዊ ፀብ መግባት የማያስፈልጋቸው፣ ልዩነቶች የሚቻቻሉበት ህብረተሰብ ሊጠቀምበት የሚችል ነው፡፡
ነፃ የሃይል ምንጭ ቴክኖሎጂን ተጠቅሞ ማንም ትርፍ ሊያከማችበት አይችልም፣ ማንም ሊገዛበት አይችልም፡፡ ባጭሩ የእግዚአብሔር ስጦታ ነው፡፡ ሁላችንንም ለምግባሮቻችን ሃላፊበት እንድንወስድ ያደርገናል፡፡ ዓለም አሁን ባለችበት ሁኔታ ለዚህ የበቃች አትመስልም፡፡
የኢያን ራንድን “Atlas Shrugged” (1957) ልበወለድ ወይም የክለብ ኦፍ ሮም “The Limits To Growth” (1972) ጥናታዊ ሪፖርት ፅሁፎችን ቢያነቡ ቁንጮዎቹ ይህ ጉዳይን እንደተረዱት ይገባችኋል፡፡ የነሱ እቅድ ለራሳቸው በነፃ ሃይል ምንጭ ያለበት ዓለም ውስጥ መኖርና ሌላውን ባለበት መግታት ነው፡፡ አሁን ኢንተርኔት ይህን አፈና ሰብሮታል፡፡ ቀጣ ውሳኔ የግሎ ነው፡፡
ተጨማሪ ንባብ በቴክኖሎጂው ዙርያ፡
Adams, Robert, DSc, Applied Modern 20th Century Aether Science, Aethmogen Technologies, Whakatane, New Zealand, special update 2001, 2nd edition.
Aspden, Harold, Dr, Modern Aether Science, Sabberton, UK, 1972.
Coats, Callum, Living Energies, Gateway Books, UK, 1996.
Lindermen, Peter, DSc, The Free Energy Secrets of Cold Electricity, Clear Tech, Inc., USA, 2001.
Manning, Jeane, The Coming Energy Revolution: The Search for Free Energy, Avery Publishing Group, USA, 1996.
Vassilatos, Gerry, Secrets of Cold War Technology: Project HAARP and Beyond, Adventures Unlimited Press, USA, 1999.
Happy
Happy
0 %
Sad
Sad
0 %
Excited
Excited
0 %
Sleepy
Sleepy
0 %
Angry
Angry
0 %
Surprise
Surprise
0 %
    Print       Email
  • Published: 12 years ago on October 28, 2012
  • By:
  • Last Modified: October 28, 2012 @ 9:24 am
  • Filed Under: Ethiopia

Average Rating

5 Star
0%
4 Star
0%
3 Star
0%
2 Star
0%
1 Star
0%
<"Without the support of our readers, the Maleda Times website would not exist in its present form">

You might also like...

በሰሜን ሸዋ ዞን ኤፍራታ እና ግድም ወረዳ መከላከያ ከአማራው ማህበረሰብ እና ከፋኖ ጋር ጦርነት ገጥሟል

Read More →

This site is protected by wp-copyrightpro.com

Skip to toolbar