www.maledatimes.com ድምጻዊ ኤፍሬም ታምሩ በኮፒ ራይት ክስ ተቀጣ ! - MALEDA TIMES
Loading...
You are here:  Home  >  Addis Admas  >  Current Article

ድምጻዊ ኤፍሬም ታምሩ በኮፒ ራይት ክስ ተቀጣ !

By   /   July 22, 2018  /   Comments Off on ድምጻዊ ኤፍሬም ታምሩ በኮፒ ራይት ክስ ተቀጣ !

    Print       Email
0 0
Read Time:2 Minute, 24 Second

 


ድምፃዊ ኤፍሬም ታምሩ የቅጅና ተዛማጅ መብቶች ጥበቃ አዋጅ ቁጥር 410/96 እና የተሻሻለውን አዋጀ ቁጥር 872/2007 አንቀጽ (41)ን ተላልፏል ተብሎ፣ የተመሠረተበትን የፍትሐ ብሔር ክስ ማስተባበል ባለመቻሉ ቅጣት ተወሰነበት፡፡

ሪፖርተር ጋዜጣ እንደዘገበው ድምፃዊው የገንዘብ ቅጣት የተወሰነበት በ1977 ዓ.ም. ባሳተመው የካሴት ዘፈን ውስጥ ‹‹የቀይ ዳማ›› ወይም ‹‹የድንገት እንግዳ›› የሚል ርዕስ ያለውን ዘፈን ደራሲ የአቶ ማስረሻ ሽፈራውን ወራሽ ወ/ሮ ቤተልሔም ማስረሻን ሳያስፈቅድ፣ እንደ አዲስ ሙዚቃ በማቀናበር በ2007 ዓ.ም. በድጋሚ አሳትሞ ለሕዝብ አሠራጭቷል የሚለው ክስ በማስረጃ በመረጋገጡ መሆኑን የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ውሳኔ ያስረዳል፡፡

ከሳሽ ወ/ሮ ቤተልሔም ለፍርድ ቤቱ ባቀረቡት ክስ እንዳስረዱት፣ አባታቸው አቶ ማስረሻ የ‹‹ቀይ ዳማ›› ዘፈን ብቸኛ ደራሲ ናቸው፡፡ አባታቸው ጥቅምት 19 ቀን 1994 ዓ.ም. አርፈው በማግሥቱ ጥቅምት 20 ቀን 1994 ዓ.ም. ሥርዓተ ቀብራቸው መፈጸሙን፣ እሳቸውም ወራሽ ስለመሆናቸው የአዲስ አበባ ከተማ የመጀመርያ ደረጃ ፍርድ ቤት በመዝገብ ቁጥር 4239/07 ውሳኔ ማረጋገጡን ለፍርድ ቤቱ አሳውቀዋል፡፡

የአባታቸውን ድርሰት ያለሳቸው ፈቃድ ድምፃዊው በሙዚቃ አቀናብሮና አሳትሞ በልዩ ልዩ ማኅበራዊ ድረ ገጾችና ኤፍኤም ሬዲዮ ጣቢያዎች በማሠራጨት፣ የጥቅምና የሞራል ጉዳት እንዳደረሰባቸው ገልጸዋል፡፡ በመሆኑም ድምፃዊው አዋጆቹን በመተላለፍ ያሳተመው ቅጅ እንዲታገድ፣ ፈቃድ ቢጠይቃቸው ኖሮ ሊያገኙ ይችሉ የነበረውን 30,000 ብር፣ እንዲሁም ለደረሰባቸው የሞራል ጉዳት ካሳ ደግሞ 140,000 ብር እንዲከፍላቸው እንዲወሰንላቸው ፍርድ ቤቱን ጠይቀዋል፡፡

ተከሳሽ ድምፃዊ ኤፍሬም በበኩሉ ባቀረበው መከራከሪያ እንዳስረዳው፣ ሟች አቶ ማስረሻ ዜማውን በ1977 ዓ.ም. ያስተላለፉለት ያለ ጽሑፍ ነው፡፡ የዜማው ደራሲ ራሱ እንጂ ሟች ወይም ወ/ሮ ቤተልሔም አይደሉም፡፡ መብቱም የተላለፉለት የቅጅና ተዛማጅ መብቶች ጥበቃ አዋጅ ቁጥር 410/96 ከመውጣቱ በፊት ነው፡፡ በመሆኑም ተፈጻሚነት ያለው በፍትሐ ብሔር ሕጉ ላይ የሚገኙት የቅጅና ተዛማጅ መብቶችን የሚመለከቱት ድንጋጌዎች እንጂ፣ አዋጁ አለመሆኑን ለፍርድ ቤቱ አስረድቷል፡፡ የዜማው ደራሲ ራሱ ኤፍሬም እንጂ ከሳሽ ካለመሆናቸውም በላይ፣ በአዋጁ አንቀጽ 7(3) ላይም ‹የአንድ ሥራ አመንጪ የሆነ ሰው ሥራውን ለሌላ ሰው ካስተላለፈ በኋላ ከሚደረገው ድጋሚ ሽያጭ ዋጋ ውስጥ የተወሰነው ድርሻ ለሥራ አመንጪው፣ ወይም ለወራሹ የካሳ ጥያቄ ማቅረብ ተቀባይነት የለውም፤›› በማለትም ተከራክሯል፡፡

በድረ ገጾችና በኤፍኤም ሬዲዮኖችም የተሠራጨው በእሱ ሳይሆን በራሳቸው መሆኑንም አክሎ ተከራክሯል፡፡ በወቅቱ አንድ ዜማ የሚሸጥበት ዋጋ ከ3,000 እስከ 7,000 ብር ብቻ ሆኖ ሳለ፣ ከሳሿ 200,000 ብር እንዲከፍላቸው ስለጠየቁት፣ የተጠቀሰውን ዜማ ትቶ ሌሎቹን ዜማዎች ብቻ በማሳተሙ፣ የጣሰው መብትና የጎዳው ሞራል እንደሌለ በመጥቀስ የከሳሽ ክርክር ተቀባይነት እንደሌለው አስረድቷል፡፡

ፍርድ ቤቱም ተከሳሹ፣ ‹‹የቅጅ መብት በዜማው ላይ አለው? ወይስ የለውም? የከሳሽን የቅጅ መብት ጥሷል? ወይስ አልጣሰም? ካሳ መክፈል አለበት? ወይስ የለበትም? ሊከፍል የሚገባው የካሳ መጠን ምን ያህል ነው?›› የሚለውን ጭብጥ ይዞ በመመርመር ፍርድ ሰጥቷል፡፡

ከሳሽ ፈቃድ ቢጠይቁ ኖሮ 30,000 ብር ሊከፈላቸው ይችል እንደነበር ያቀረቡትን መከራከሪያ በአግባቡ አለማስረዳታቸውን ፍርድ ቤቱ ገልጿል፡፡ በወቅቱ ለአንድ ዜማ ደራሲ ይከፈል የነበረው ከ7,500 ብር እንደማይበልጥም የኢትዮጵያ ኦዲቪዥዋል አሳታሚዎች ማኅበር አቶ ሃይላይ ታደሰ መመስከራቸውንም ፍርድ ቤቱ በፍርዱ ገልጿል፡፡ የሌሎች ዘፈኖች ዜማ ደራሲ አቶ ፀጋዬ ደቦጭና ሌሎች ምስክሮችም በዜማ ከ7,000 ብር እስከ 10,000 ብር እንደሚከፈል መመስከራቸውን ፍርድ ቤቱ ገልጾ፣ የያዘውን ጭብጥ ከአዋጁ ዝርዝር አንቀጾችና ከሌሎች ሕጎች ጋር በማዛመድ ትንታኔ ሠርቶ ፍርዱን ሰጥቷል፡፡ በመሆኑም ድምፃዊ ኤፍሬም ሕጉን መተላለፉ ስለተረጋገጠበት ከከሳሽ ፈቃድ ጠይቆ ቢሆን ኖሮ ሊከፈል የሚችለውን 8,000 ብር፣ እንዲሁም የሞራል ጉዳት ካሳ 100,000 ብር እንዲከፍል ፍርድ ሰጥቷል፡፡

Source: Reporter Amharic Newspaper

Happy
Happy
0 %
Sad
Sad
0 %
Excited
Excited
0 %
Sleepy
Sleepy
0 %
Angry
Angry
0 %
Surprise
Surprise
0 %
    Print       Email

Average Rating

5 Star
0%
4 Star
0%
3 Star
0%
2 Star
0%
1 Star
0%
<"Without the support of our readers, the Maleda Times website would not exist in its present form">

You might also like...

Ethiopia’s Media Under Siege Amid Escalating Conflict in Amhara

Read More →

This site is protected by wp-copyrightpro.com

Skip to toolbar