- ሀ/ስብከቱ፣እንደየሥራ ዘርፋቸው በሚያወጣው ድልድል መሠረት በየአጥቢያው ይመደባሉ፤
- በዛሬው ዕለት፣ አለቆችንና ም/ል ሊቃነ መናብርትን ጠርቶ ውሳኔውን አስታውቋል፤ ኾኖም…
- ከተመላሾቹ ውስጥ የእምነትም የሥነ ምግባርም ችግር ያለባቸው መኖራቸው እያነጋገረ ነው፤
- እንደ‘አባ’ ነአኵቶ ለአብ፣ ጌታቸው ዶኒ፣ ጸዳሉ መለሰ ያሉት በማጣራት የተወሰነባቸው ነበሩ፤
†††
- ቀኖናው ቀርቶ ይቅርታ እንዲጠይቁ እንኳ ሳይደረግ ከተበዳዮች እኩል እንዲመለሱ ተወሰነ፤
- ጎይትኦምም ሳይጠየቅ፣ ከሥራ አስኪያጅነቱ በፊት ወደነበረበት ይመለስ ለሚሉ በር ከፈተ፤
- “ቋሚ ሲኖዶሱ፣የገዛ ውሳኔውን ሳያስከብር፣ራሱን እየተቃረነ ቤተ ክርስቲያንን አስደፈረ፤”
- በቀንደኞቹ ሓላፊዎችና ንኡሳን ተባባሪዎች ላይ የወሰነውም ገና በአፈጻጸሙ ይፈተናል፤
†††
- የተፈናቀሉት ቦታ ሳያገኙ፣ የቅጥርና ዝውውር ጉዳይ እንደማይታይ ሀ/ስብከቱ አስታወቀ፤
- ቅጥሩና ዝውውሩም የሚፈጸመው፣ በሰበካ ጉባኤና በክ/ከተማ አግባብነቱ ከተረጋገጠ ነው፤
- የዕድገትና ዝውውር ፈላጊዎች ጥያቄ፣ በቅጽ እየተሞላና በየደረጃው እየተፈተሸ ይቀርባል፤
- “ድለላንና ደጅ ጥናትን በማስወገድ፣ ሞያዊነትንና ተወዳዳሪነትን የሚያበረታታ ነው፤”
†††
ሥልጣናቸውን ተገን አድርገው በዘረጉት የድለላ መረብ ከፍተኛ ምዝበራ ሲፈጽሙ መቆየታቸው በማጣራት የተረጋገጠባቸው የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት 14 የዋና ክፍል ሓላፊዎች በሙሉ እንዲወገዱ ቋሚ ሲኖዶስ የወሰነ ሲኾን፤ አላግባብ ከሥራ በማሰናበትና በማገድ ለእንግልትና ረኀብ የዳረጓቸው 270 ያህል ሓላፊዎች፣ ካህናትና ልዩ ልዩ ሠራተኞች ደግሞ ተመልሰው እንዲመደቡ አዘዘ፡፡
የሀገረ ስብከቱን የሙስና ተግባራትና የአሠራር ጥሰት እንዲያጣራ በፓትርያርኩ የተሠየመው ኮሚቴ በምርመራ አጣርቶ ያዘጋጀውን ሪፖርት፣ ዛሬ ዓርብ፣ ሐምሌ 13 ቀን 2010 ዓ.ም. ሳምንታዊ መደበኛ ስብሰባው ቀርቦለት ካዳመጠ በኋላ፣ የሀገረ ስብከቱ 14 የዋና ክፍሎች ሓላፊዎች በሙሉ ከቦታቸው እንዲወገዱ፣ ሌሎች የክፍል ሓላፊዎችም በሀገረ ስብከቱ እየታዩ አስፈላጊው ማስተካከያ እንዲደረግ ወስኗል፡፡
በሌብነት ከተሳሰሯቸው የአጥቢያ አብያተ ክርስቲያን የጽ/ቤት ሓላፊዎች ጋራ በመመሳጠር ለመስማት የሚዘገንን የጉቦ ተመን አውጥተው የከፈሏቸውን በመቅጠርና በማዛወር፣ አቅም የሌላቸውን ያለበቂ ምክንያት በማገድና ደረጃቸው ሳይጠበቅ በማዛወር ከዚያም አልፎ በማባረር ቦታቸውን እየሸጡ የግልና የተደራጀ የቡድን ዝርፊያ ሲፈጽሙ እንደቆዩ፣ በተበዳዮቹ አቤቱታና ደጋፊ ማስረጃዎች እንደተረጋገጠ በሪፖርቱ ተገልጿል፡፡ በዚህ ረገድ፣ ከቀድሞው ሥራ አስኪያጅ ጀምሮ አብዛኞቹ የአስተዳደር ጉባኤ አባላት የኾኑ የዋና ክፍል ሓላፊዎች ከፍተኛ ተጠቃሚዎች እንደኾኑ ሪፖርቱ አጋልጧል፡፡
አጥቢያ አብያተ ክርስቲያን የሚጠይቁትን የደመወዝና የአበል ጭማሬዎች ለማጸደቅ በሚል የወር ደመወዛቸውን እንዲለቁ የሚገደዱበት ጉቦኝነት ሌላው ሕገ ወጥ አሠራር ሲኾን፤ በዚህ ረገድ በተለይ የሒሳብና በጀት ዋና ክፍሉ ሓላፊዎች ከፍተኛ ሀብት ሲያካብቱ ቆይተዋል፡፡ ሕገ ወጥ የኪራይ ውሎችን ማጸደቅ፣ በማጣራት ወቅት ለአማሳኞች የሚያደሉ ሐሰተኛ ሪፖርቶችን ማዘጋጀት፣ በዓመታዊ ኦዲትና የክብረ በዓላት ቁጥጥር ምዝበራዎችን(ወጪዎችን) ሕጋዊ ማስመሰልም…ወዘተ ይጠቀሳሉ፡፡
ሀገረ ስብከቱ ቀደም ሲል በተካሔዱ ጥናቶች መሠረት ዳግም እንዲደራጅ ቋሚ ሲኖዶሱ ባለፈው ሳምንት ስብሰባው የወሰነ ሲኾን፣ በዛሬው ዕለት የ14ቱም የዋና ክፍል ሓላፊዎች ከቦታቸው እንዲወገዱ መወሰኑም፣ የአስተዳደር ጉባኤው በቂ የትምህርት ዝግጅት፣ አግባብነት ያለው የሥራ ልምድና ሥነ ምግባር ባላቸው ሊቃውንትና ምሁራን ለማዋቀር ምቹ ኹኔታ እንደሚፈጥር ታምኖበታል፡፡ መረጣው፣ በአዲሶቹ ዋና እና ምክትል ሥራ አስኪያጆች በኩል እየተከናወነ እንዳለና ሳይጠናቀቅም እንዳልቀረ ተጠቁሟል፡፡
ቋሚ ሲኖዶሱ፣ ከሥራቸው የታገዱ ሠራተኞች፣ ከሃይማኖት ሕጸጽና ከሙስና ነጻ መኾናቸው እየተገመገመና ጥፋታቸው እየታየ እንዲመለሱ እንዲደረግ አስቀድሞ ወስኖ የነበረ ቢኾንም፣ በዛሬው ስብሰባው ግን፣ የገዛ ውሳኔውን የተፃረረበት ኹኔታ መኖሩ ታውቋል፡፡
አላግባብ የታገዱና የተሰናበቱ 270 ያህል ሠራተኞች፣ የሥራ ሓላፊዎቹ ደረጃቸው እንደተጠበቀ፣ ሌሎቹም በየአጥቢያው በተገኘው ቦታ እንዲደለደሉ ማዘዙ መልካም ኾኖ ሳለ፣ ከእነርሱ መካከል ቀደም ሲል ራሱ ቋሚ ሲኖዶሱ፣ ቀኖና ቤተ ክርስቲያንን ስለ መተላለፋቸው፣ ሕግንና አሠራርን ስለመጣሳቸው ገልጾ ያገዳቸውና ጉዳያቸው በሊቃውንት ጉባኤ እንዲታይ የወሰነባቸው እንደ ‘አባ’ ነአኵቶ ለአብ አያሌው፣ ከቤተ ክህነት ሠራተኝነት ጨርሶ እንዲባረሩ የተወሰነባቸው እንደ ጸዳሉ መለሰ(edit) ያሉ መኖራቸው እያነጋገረ ይገኛል፡፡
ጥፋታቸው አምነው በይቅርታ ከጠየቁ ጉዳያቸው ዳግም ሊታይ እንደሚችል ያስቀመጠው አማራጭ እንኳ ሳይፈተሽ ከተበዳዮች እኩል ወደ ሥራ እንዲመለሱ መወሰኑም ከፍተኛ ቅሬታ አስነሥቷል፡፡ ከሥራ አስኪያጅነቱ ታግዶ በኋላም የተባረረው ጎይትኦም ያይኑ፣ በርካታ ሕገ ወጥ ቅጥሮችንና ዝውውሮችን በመፈጸም ተጠያቂ የሚኾንበትን አካሔድ እንዳዳከመው ተመልክቷል፡፡ከሥራ አስኪያጅነቱ በፊት ወደነበረበት የመንፈሳዊ ኮሌጅ ሓላፊነት እንዲመለስ ላቀረበው ጥያቄና ደጋፊዎቹ በር መክፈቱም ተጠቁሟል፡፡
Wondering where the comments are? We encourage you to use the share buttons below and start the conversation on your own!
- Click to email a link to a friend (Opens in new window)
- Click to share on Facebook (Opens in new window)
- Click to share on Twitter (Opens in new window)
- Click to share on LinkedIn (Opens in new window)
- Click to share on Pinterest (Opens in new window)
- Click to share on Tumblr (Opens in new window)
- Click to print (Opens in new window)
በምዝበራ የበሰበሱ የአ/አበባ ሀ/ስብከት የዋና ክፍል ሓላፊዎች በሙሉ እንዲወገዱ፣በግፍ ያፈናቀሏቸው 270 ሠራተኞች እንዲመለሱ ቋሚ ሲኖዶስ ወሰነ