- ረቡዕ ማለዳ 12:00፣ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋራ ቦሌ አየር ማረፊያ ይደርሳሉ፤
- በቦሌ አየር ማረፊያና በቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ደማቅ አቀባበል ይደረጋል፤
- “የሁላችሁ በዓል ነው፤በቅዱስነታቸው እንድትባረኩ በነቂስ ውጡና ተቀበሉ፤”
†††
- በሁለቱም የተላለፈው ቃለ ውግዘት እንዲፈታ የተወሰነው እየተፈጸመ ነው፤
- ከአሜሪካ የተላለፈው፣በተገኙት አባቶች ውሳኔ ባለፈው ዓርብ ተነሥቷል፤
- ከአ/አበባ የተላለፈውን ለማንሣት፣ ለነገ ሰኞ አስቸኳይ ስብሰባ ተጠርቷል፤
†††
በአባቶች ዕርቀ ሰላም ፍጻሜ የቤተ ክርስቲያናችን ሲኖዶሳዊ አንድነት በዋሽንግተን ዲሲ መበሠሩን ተከትሎ፣ የፊታችን ረቡዕ ማለዳ፣ ወደ ኢትዮጵያ ለሚመለሱት 4ኛው ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ፥ ሊቃውንት፣ ካህናትና ምእመናን በነቂስ በመውጣት በድምቀት እንዲቀበሏቸው የጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት ጥሪ አቀረበ፡፡
የአቀባበል ዐቢይ ኮሚቴው ሰብሳቢ ብፁዕ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቡነ ዲዮስቆሮስ፣ ዛሬ እሑድ፣ ሐምሌ 22 ቀን 2010 ዓ.ም. ማምሻውን ለብዙኃን መገናኛ በሰጡት መግለጫ፣ ለ26 ዓመታት የዘለቀው መለያየት በዕርቀ ሰላም ተቋጭቶ ቅዱስነታቸው አቡነ መርቆሬዎስና በውጭ ያሉት ብፁዓን አባቶች ወደ ሀገራቸው መመለሳቸው፣ ለቤተ ክርስቲያናችንና ለሀገራችን ታላቅ ደስታ፣ ታላቅ ልደት በመኾኑ፣ ካህናትና ምእመናን በነቂስ ወጥተው በድምቀት እንዲቀበሏቸው ጥሪ አቅርበዋል፡፡
በፓትርያርክ ክብርና ደረጃ ወደ ሀገራቸው የሚመለሱትን ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስንና የሰላም ልኡካኑን ለመቀበል፣ በተለያየ ዘርፍ ኮሚቴ ተቋቁሞ ዝግጅቱ መጠናቀቁን የገለጹት ብፁዕ ዋና ሥራ አስኪያጁ፣ የአቀባበል ሥነ ሥርዐቱ፣በቦሌ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያና ከዚያም በመቀጠል በመንበረ ጸባኦት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል በተለያዩ መርሐ ግብሮች እንደሚከናወን አስታውቀዋል፡፡
በዚህም መሠረት፣ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስና የሰላም ልኡካን ከክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋራ ከሚደርሱበት የፊታችን ረቡዕ፣ ሐምሌ 25 ቀን ማለዳ 12:00 ጀምሮ፣በቦሌ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ፣ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስና ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት፣ የመንግሥት ባለሥልጣናት፣የገዳማትና አድባራት አስተዳዳሪዎች፣ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን፣ ካህናት፣ የሰንበት ት/ቤት ወጣቶችና ምእመናን በተገኙበት ደማቅ አቀባበል ይደረጋል፤ በጋራ የምስጋና ጸሎት ይደርሳል፡፡
ከዚያም በመቀጠል፣ ወደ መንበረ ጸባኦት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ጉዞ ተደርጎ፣ በሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያንና በሰንበት ት/ቤት ወጣቶች ስብሐተ እግዚአብሔር ቀርቦ ፍጹም የቤተ ክርስቲያናችን አንድነት መመለሱን የሚያበሥርና የሚያውጅ የደስታ መግለጫ መልእክት ከተላለፈ በኋላ የመርሐ ግብሩ ፍጻሜ ኾኖ ቅዱስነታቸውና የሰላም ልኡካኑ በመንበረ ፓትርያርኩ ወደተዘጋጀላቸው ማረፊያ እንደሚያመሩ ብፁዕ ዋና ሥራ አስኪያጁ ገልጸዋል፡፡ ሥላሴ ካቴድራል ጉዞ ተደርጎ፣ በሊቃውንተ ቤተ ክ
“ሊቃውንት፣ ካህናትና ዲያቆናት፥ለአቀባበሉ ዝግጅት እንድታደርጉና እንድትወጡ ጥሪ እናቀርባለን፤” ያሉት ብፁዕ አቡነ ዲዮስቆሮስ፣ “በዓላችሁ ስለኾነ ሁላችሁንም ይመለከታችኋል፤ የበረከቱ ተሳታፊ እንድትኾኑ፣ በቅዱስነታቸውም እንድትባረኩ ረቡዕ ከማለዳው 12:00 ጀምሮ እንድትወጡ እናስታውቃለን፤”በማለት የቤተ ክርስቲያንን ጥሪ አስተላልፈዋል፡፡
በተያያዘ ዜና፣ ልኡካን አባቶች በደረሱበት የዕርቀ ሰላም ስምምነት መሠረት፣ የቤተ ክርስቲያንን መብት ባለማስጠበቅና ጊዜውን በመምሰል በአዲስ አበባም ይኹን በአሜሪካ በነበረው ሲኖዶስ ቀኖናዊ ጥሰት እንደተፈጸመ በመታመኑ በኹለቱም በኩል የተላለፈው ቃለ ውግዘት እንዲፈታ በተወሰነው መሠረት እየተፈጸመ መኾኑ ታውቋል፡፡
በአሜሪካ በስደት በነበረው ሲኖዶስ የተላለፈው ቃለ ውግዘት፣ ከትላንት በስቲያ ዓርብ፣ ሐምሌ 20 ቀን 2010 ዓ.ም.፣ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ በተገኙበት መነሣቱ ታውቋል፡፡ በሌላ በኩል፣ ነገ ሰኞ፣ ሐምሌ 23 ቀን በአዲስ አበባ በተጠራው አስቸኳይ የቅዱስ ሲኖዶስ ስብሰባ፣ በ1984 ዓ.ም.፣ በ1985 ዓ.ም. እና በ1999 ዓ.ም. ከአዲስ አበባ የተላለፉት የውግዘት ውሳኔዎች እንደሚፈቱ ተጠቁሟል፡፡
ጥፋቱና የዓመታት ልዩነቱ የምእመናኑን ልብ በሐዘን የሰበረ በመኾኑ፣ ያለፉትንም ኾነ በሕይወት ያሉትን ልጆቿን በጋራ ይቅርታ ለመጠየቅልኡካኑ በጋራ ወስነዋል፡፡ ከሁለቱ ሲኖዶስ መዋሐድ በኋላ ቤተ ክርስቲያንን ከዳግም መከፋፈል ለመጠበቅና ሉዓላዊነቷን ለማስከበር፣ ሕጉንና ሥርዐቱን ያገናዘበ ደንብ በቅዱስ ሲኖዶሱ እንዲወጣ ልኡካኑ ተስማምተዋል፡፡
ከዚህም በኋላ፣ ቤተ ክርስቲያን፣ ከአንድ ቅዱስ ሲኖዶስ መመሪያ እየተቀበለች የምትመራ ሲኾን፣ ኹለቱንም ቅዱሳን ፓትርያርኮች በእኩል የአባትነት ክብር ትቀበላለች፡፡ አገልግሎቷን በምታከናውንባቸው የዓለም ክፍሎች ሁሉ፣ የሁለቱንም ስም በቅደም ተከተል ትጠራለች፡፡
ሁለቱም ቅዱሳን ፓትርያርኮች የሥራ ድርሻ እንደሚኖራቸው በስምምነቱ ተጠቅሷል፡፡ 4ኛው ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ፣ በጸሎትና በቡራኬ መንፈሳዊ አገልግሎት ይሰጣሉ፤ 6ኛው ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱ አቡነ ማትያስ ደግሞ፣ የአስተዳደሩን(የቢሮውን) ሥራእያከናወኑ አጠቃላይ አመራር ይሰጣሉ፡፡
ከልዩነቱ በፊት የተሾሙ ነባር ሊቃነ ጳጳሳት፣ ስማቸውና ክብራቸው ተጠብቆ በውጭ ሀገርም ኾነ በሀገር ቤት እንዲመደቡና እንዲያገለግሉ፤ ከልዩነቱ በኋላ የተሾሙት ኤጲስ ቆጶሳት፣ ጳጳሳትና ሊቃነ ጳጳሳት ደግሞ፣ ስማቸውን እንደያዙ ቅዱስ ሲኖዶስ እንዲቀበላቸው፣ በውጭም ኾነ በሀገር ቤት አህጉረ ስብከት ተመድበው እንዲያገለግሉ ልኡካኑ ተስማምተዋል፡፡ የስም ተመሳስሎ ያላቸው አባቶች፣ እንደ ሢመት ቅደም ተከተላቸው ቀዳማይ፣ ካልዓይ፣ ሣልሳይ…ወዘተ በሚል እንዲለዩ ተወስኗል፡፡
Average Rating