www.maledatimes.com አንዳርጋቸው ሳይሆን ኢ.ኤን.ኤን ኦሮማይ ሆነ (በግርማ ደገፈ ገዳ) - MALEDA TIMES
Loading...
You are here:  Home  >  Addis Admas  >  Current Article

አንዳርጋቸው ሳይሆን ኢ.ኤን.ኤን ኦሮማይ ሆነ (በግርማ ደገፈ ገዳ)

By   /   July 30, 2018  /   Comments Off on አንዳርጋቸው ሳይሆን ኢ.ኤን.ኤን ኦሮማይ ሆነ (በግርማ ደገፈ ገዳ)

    Print       Email
0 0
Read Time:16 Minute, 25 Second

አንዳርጋቸው ሳይሆን ኢ.ኤን.ኤን ኦሮማይ ሆነ

(በግርማ ደገፈ ገዳ)

እ.ኤ.አ. በ2014፣ አንዳርጋቸው ጽጌ በህወሓት መንግሥት ከየመን ታፍኖ ወደ ኢትዮጵያ መወሰዱ በጣም ካስደሰታቸው አንዱ የኢ.ኤን.ኤኑ ብንያም ነበር። የበዓሉ ግርማን ኦሮማይ መጽሐፍ ርእስ ወስዶ “ኦሮማይ! ፀሓፊ፦ አዘነጋሽ ቦጋለ – ከሽሮሜዳ” የሚባል ትረካ ተረከበት።ከግንቦት ሰባት ፖለቲካዊ አቋም በተቃራኒ የተሰለፉ ፖለቲከኞች፣ አብዛኛው ኢትዮጵያውያንና የውጭ ሀገር ዜጎች ጭምር፤ የህወሓት መንግሥትን የማፍያ ዓይነት ርካሽ ጠለፋ ሌት ተቀን ሲያወግዙ፤ ብንያም ጠላፊ አለቆቹን ለማስደሰት “እኔም ማረፍ አማረኝ” እና “በቃሉ የጸናው አንዳርጋቸው ጽጌ” እያለ በሌሎች ተከታታይ ትረካዎች ቀለደበት። በኋላም፣ የህወሓት መንግሥትን ማጅራት ጨምድደው ከግራ ቀኝ የሚያላትሙትን ጠንካራ የፖለቲካ ድርጅቶች ዱካ እየተከተለ መሳደብን የሙሉ ጊዜ ሥራው አደረገው። ሻእብያን ለማጣጣል፣ ትግራይ ውስጥ የስደት ካምፕ ተከፍቶላቸው የህወሓት ባለሥልጣናት ባንክና ለልጆቻቸው ቪዛ የሆኑትን ኤርትራውያንን፣ ሱዳን ጠረፍ ድረስ ሄዶ ከትህዴን የከዱ የተባሉ አባላትንና የግንቦት ሰባት ምርኮኞች ናቸው የተባሉ ታጋዮችን ታሪክ ህወሓትና ዶላሩ በፈለገው መንገድ እየጻፈ በየቦታው ሲለጣጥፍ ጊዜው በረረ። እንደ ሸማኔ መወርወሪያ ከወዲያ ወዲህ የሚያንከራትቱትን የህወሓት አለቆቹን ለማስደሰት ብሎ፣ የውሸት ድርሰቶቹን እየሞነጫጨረ፣ ለሚያልፍ ቀን ሕይወቱን በከንቱ ሲያረክሳት ከረመ። ካናዳን የመሰለች የህግና የሰላም ሀገር ትቶ፣ የህወሓት ቡድን የክፉ ሰዎች ክፉ ሥራ አከናዋኝ ወይም ሲ.ኢ.ኦ ሆኖ አረፈው። በስተመጨረሻም፣ ድካሙን ያዩለት የአንዳርጋቸው ጽጌ ጠላፊ አለቆቹ፣ ኢ.ኤን.ኤን የሚባል የክፋት ቴሌቪዥን ጣቢያ “ከፈትንልህ” አሉት። ሚስተር አዘነጋሽ ቦጋለ ጎል እንዳገባ የማንቸስተር አጥቂ በደስታ ተገለባበጠ። ሙሉ የክፋት ጊዜውንም ኢ.ኤን.ኤን ላይ ማባከን ጀመረ። ኢትዮጵያ ውስጥ የተቀረጹ ክፋቶቹን ወደ ናይልሳት102 7ድግሪ ዌስት እየላከ፣ ኢትዮጵያ ውስጥ እንዲበተኑ ማድረጉን ተያያዘው። ከሰው ጋር ሲተዋወቅም “ብንያም እባላለሁ” ማለት ትቶ “the founding father of the modern Ethiopian television station. The first African CNN in Ethiopia, ENN” ማለት ጀመረ። ከቤኒያም ወደ ብንያም፣ ከዚያም ወደ ቤንጃሚን፣ከዚያም ወደ አዘነጋሽ ቦጋለ፣ በመቀጠልም ወደ the founding father of ENN ቁልቁል አደገ።

በኢ.ኤን.ኤን ቴሌቪዥን ቃለመጠይቅ የሚደረግላቸው አብዛዎቹ፣ የቶሎሳ ኢብሳን አገላለጽ ልዋስና የህወሓት ሚሊሽያ ጄነራሎች ነበሩ። ከዜሮ በአንድ ሌሊት ሚሊየነር የሆኑ ታሪኬ ዜሮዎችም ዕድሉን እንደጉድ አግኝተዋል። የቀይ ባህርን ፖለቲካ አስመልክቶ በሚሰናዱ ውይይቶች ላይ የሚሳተፉ ትንታኔ ሰጪዎች፣ የቀይ ባህርን ያለ የሌለ ችግር በሙሉ ኤርትራ ላይ የሚደፈድፉ ነበሩ። ደፍረው ሳውዲ አረቢያን፣ ሱዳንን፣ ኢትዮጵያን፣ የመንን ወይም ግብጽን ሲተቹ አይታዩም። የፈረንሳይ፣ የአሜሪካና የቻይና ከባድ መሳሪያዎች አልቤርጎ የሆነችውን ጅቡቲን እንኳከትችታቸው ይዘሏታል። ጠንካራ የፖለቲካ ፓርቲን እያፈራረሱ፣ አዳዲስ የደህንነት ድርጅት ተላላኪ የሆነ ፓርቲ የሚያቋቋሙ ተመሳሳይ ግለሰቦች ፈንጭተውብታል። በየክልሉ የሚኖሩ የራሳቸው ዜጎች ግንባር ላይ ጥይት የሚያርከፈክፉ ገዳዮች ተስተናግደውበታል። በየቀኑ፣ ከትውልድ ቀያቸው የሚፈናቀሉ ህጻናት ስቃይን እንደ ሙዚቃ ቆጥረው የሚደንሱ አሽቃባጮች ጮቤ ረግጠውበታል።  ኢትዮጵያውያን በያቅጣጫው የነፃነትን ችቦ ይዘው አንድ እርምጃ ለመራመድ በጀመሩ ቁጥር “በኢሕአዴግና የዴሞክራሲ ባሕሉ የጥቃቅንና አነስተኛ ኢንዱስትሪ ከየት ወዴት? … የፖለቲካ ምህዳሩ ጥበትና ቁምጣዊ ስቃይ በአቶ አየለ ጫሚሶ ላይ ያሳደረው እንግልት” የሚባሉ ለዘመኑ የአንደኛ ክፍል ተማሪዎች እንኳ የማይመጥኑ የውይይት መድረኮችን እያዘጋጀ፣ የተለመደ ፀረ-ዴሞክራሲ ፕሮፓጋንዳውን በተለመዱ ፀረ- ዴሞክራሲ ግለሰቦች ይነዛ ነበር።

ዛሬ፣ እ.ኤ.አ2018 ነው። ከአራት ዓመት በኋላ ሁሉም ነገር ተገለባበጠ። ኢትዮጵያ ለውጥ በለውጥ ሆነች። ነገሮች ሁሉ ሕልም ነው የሚመስሉት። መሽቶ በነጋ ቁጥር አንድ ደስ የሚል ነገር ይታያል። ይህ ደስ የሚል ነገር ለብንያም ደስ የማይል ነገር ነው። መሸሽ አለበት። የአምባገነኖች አሽከርነቱ በነፃይቱ ኢትዮጵያ ውስጥ የሚያስኖረው አልመሰለውም። የሰራውንና ያሰራውን ያውቃል። ለደህንነቱ መስሪያ ቤት ተውኔት ከሚጽፉት አንዱ ነበር። እናም ያ መከረኛ አውሮፕላን ቦሌ ዓለምአቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ እየጠበቀው ነው። በቀይ ኮከብ ጊዜም ይኸው ነበር። በአዘነጋሽ ቦጋለ ጊዜም ይኸው ነው። በጥድፊያና በብዙ ገንዘብ የተገዛ ቲኬት ነው የያዘው። ሻንጣውን በችኮላ ሞልቶቷል። ምን እንዳጎረበት እንኳ እስኪያቅተው ድረስ። ከዚያም ከዚህም ዓይኑ ያረፈበትንና እጁ የደረሰበትን ነው የሞጀረበት። ነፍስ ግቢ ነፍስ ውጪ ነው የሆነበት። ከቤቱ ጣሪያ ላይ ድምጽ በሰማ ቁጥር፣ ግንቦት ሰባት ወይም ቄሮ በኮርኒሱ በኩል የመጣ እየመሰለውና ተወርውሮ አልጋ ሥር መግባት እያማረው ነበር ሻንጣውን በአንድ እግሩ የሚጠቀጥቀው። “ወይ ጉድ!” አለ በግድግዳው ላይ ከሰቀለው የስማርቱ ለገሰ ፎቶግራፍ ላይ ዓይኑን ተክሎ። “ከአራት ዓመት በኋላ ሁሉም ነገር ተገለባበጠ” አለ ደገመና። “አንተስ እ.ኤ.አ. በ2012 መሬት ውስጥ ገባህ። እኔ አሁን የት ልግባ? … ካናዳ? … ዱባይ? … ወይስ ከነምጽላል አልጋ ሥር?” … ሌሊት፣ ሌሊት ባቃዠው ቁጥር ከዚህ ትልቅ ፎቶግራፍ ሥር ነበር ተንበርክኮ የሚጸልየው። “ስማርቱ አባቴ ለገሰ ሆይ … በነሜቴክ በኩል ዶላሬን በግሬደር ስላሳፈስከኝ አመሰግናለሁ …” ቀን ከሆነና ጊዜ ካለውም ወደ ሥላሴወረድ ብሎ ከሁለቱ ወታደሮች መሃል ሆኖ ያለቅሳል። ለምስክርነትም እልቅሻውን በዩቱብ ያሰራጫል።

ወደ ቦሌ ለመሄድ አንድ ነገር ነው የቀረው። የኢ.ኤን.ኢን ቴሌቪዥን ጋዜጠኞችን ማሰናበትና መሰናበት። ለሁለት ዓመት “ነፃ ጋዜጠኞች ናችሁ። …. ነፃ ቴሌቪዥን ላይ የምትሰሩ ነፃ ጋዜጠኞች” እያለ ሲያታልላቸውና ራሱንም ሲያታልል ከራርሟል። ዛሬ ግን ምን ብሎ ይሰናበታቸው? “ለማ መገርሳ ከኦሮሚያ አባረረኝ? … ድሪባ ኩማ የአዲስ አበባን አስፋልት እንዳትረግጥ አለኝ? … ገዱ አንዳርጋቸው የሜቴክን ጣጣ ይዘህ አባይን እንዳትሻገር? … ወይስ አብይ አህመድ ከፌደራል መሥሪያ ቤቶች ድርሽ እንዳትል ብሎኛል?” ማለት። እነዚህ ምክንያቶች’ማ የምክንያት ጠረጴዛው ላይ ተደርድረው ነበር። እንደማያዋጡየተረዳው ከሳምንት በፊት ነበር።  ‘ማን ወንድ ይነካኛል?’ ያለ ኮንትሮባንዲስት ጄኔራል ሁሉ “በየሱስ ስም! አንተ ሚሊሽያ ጄኔራል … ጡረታ እንድትወጣ አዝዤሃለሁ። አለበለዚያ አሥር አለቃነት በጉጉት ይጠብቅሃል” ሲባል፣ አሥር አለቃ ላለመሆን እየተሽቀዳደመ “ጀረነል ሰዓረ፣ ቃቡሽ!” እያለ ሽጉጡን ለጄነራል ሰዓረ በአየር ላይ እየወረወረ ወደ ጡረታ ሚኒስቴር መብረሩን ሲያይ ተስፋ ቆረጠ። ኤታማዦር ሹሙ፣ የምሥራቅ ዕዝ አዛዡ፣ የምእራብ ዕዝ አዛዡ፣ የሰሜን ዕዝ አዛዡ፣ ካሱ ኢላላ፣ አባይ ፀሓዬ፣ ስብሃት ነጋ፣ ህላዊ ዮሴፍ፣ አባዱላ ገመዳና ግርማ ብሩ የጡረታ ደብተራቸውን ከጡረታ ሚኒስቴር ደጃፍ ላይ ቆመው የደረት ኪሳቸው ውስጥ ለመሸጎጥ ሲታገሉ ካየ በኋላ የምክንያት መቆለያ ጠረጴዛውን አፀዳው። … ብቻ ለማንኛውም ሻንጣውን ተሸክሞ ከውጭ ይጠብቀው ከነበረው መኪና ውስጥ ገባ። ሚሊሺያ ጄኔራሎች፣ ተለማማጅ ሚንስትሮች፣ አኮላሽ ደህንነቶችና የህወሓት አሽከሮች ከጎኑ በነበሩ ጊዜ ሁሉንም ነገር በእርጋታና በኩራት ነበር የሚያደርገው። ሌሊቱን ቆቅ ሆኖ ማሳለፉ፣ ደጋግሞ “ወይ ጉድ!” ማለቱ እየገረመውና ከጋቢና ተቀምጦ “እዩኝ … እዩኝ” ማለቱ ቀርቶ የኋላ ወንበር ላይ ተደብቆ ጋዜጠኞቹ እንዲጠብቁት ከነገራቸው ቦታ ደረሰ። መጥፎነቱ፣ የወሬ ወሬ የሰሙ ወይም ለመምጣት የፈለጉ ጥቂት ጋዜጠኞችን ብቻ ለማየት ቻለ።

“በሉ እንግዲህ ከሰኞ ጀምሮ የቴሌቪዥን ሥርጭታችንን አቁመናል” አላቸው።

ብዙዎቹ ተደሰቱ። እሱ ግን፣ ይከፋቸዋል፣ ያዝናሉ፣ ከንፈር ይመጣሉ፣ ‘ወይኔ ቢኒዬ!’ እያሉ ትከሻው ላይ ተጠምጥመው እንባቸውን የሚረጩ ነበር የመሰለው። ግን አንድም አዛኝ ባለማግኘቱና ‘ወይኔ ቢኒዬ!’ የሚለው በመጥፋቱ ልቡን ከፋው። “ሁለት ዓመት ሁሉ እዚህ ቴሌቪዥን ላይ ለፍቼ” አለ በልቡ።

“በቃ እንዲህ ነው?” አላቸው የዛሬው ብንያም የትላንቱ አዘነጋሽ ቦጋለ – ከሽሮሜዳ።

አንዱ ጋዜጠኛ “አዎ፣ እንዲህ ነው። ጭማሪ ምን ፈለግህ? … ግንቦት …” አለው።

ፈጥኖ “እሺ ተዉት” አላቸው ‘ግንቦት’ ብሎ የጀመረው ጋዜጠኛ ‘’ባት’ን ሳይጨምርበት።

ሌላ ጋዜጠኛም “አንተን ተማምኜ የመንግሥት ሥራ መልቀቄ” አለውና ትከሻው ላይ ያንጠለጠለውን ሻንጣ ያዘበት። “ሚሊሽያ ጄኔራል ሳሞራ ምንህ ነው? የመንደር ጂኦሜትራ ክንፈ ዳኘውን የት አወቅኸው? ደብረጽዮንስ? … ለመሆኑ ሜዳ ላይ በትነኸን የት ልትጠፋ ነው?” አከለበት።

“ጎበዝ!” አለ ብንያም አዘነጋሽ ቦጋለ። “ከእጄ በልታችሁ …”

“ከሜቴክ ነው የበላነው … ካንተ አይደለም” አለው ይኸው የተበሳጨ ጋዜጠኛ ሻንጣውን እንደያዘበት። “የኩራዝ፣ የበለስና የወልቃይት ስኳር ፋብሪካዎችን ባጀት ነው በማንኪያ ያስነጨኸን።”

“ወንድም ልቀቅ ሻንጣዬን። … አውሮፕላኑ ቆሟል። … ልሂድበት።”

“ድርሻዬን ስጠኝ! የትም አትሄዳትም! የኩራዝን ስጠኝ! … የደቡብ ሰው ስለሆንኩኝ የኩራዝን ስጠኝ! የበለስና የወልቃይት ይበቀሃል …”

ዓይኑ ሲቁለጨለጭ፣ ሌሎች ሁለት ጋዜጠኞች፣ ድርሻውን የሚጠይቀውን ጓደኛቸውን ለምነው ብንያምን አስለቀቁት። አቶ ብንያም አዘነጋሽ ቦጋለ እየሮጠ ወደ መኪናው አመራ።

“አንጠልጥሎ ለአብይ ነበር መስጠት” የሚል ድምጽ ከወደኋላው ስለሰማ የሩጫ ፍጥነቱን ጨመረው። “ቄሮ መጣልህ! … ቄሮ! … ቄሮ! … ግንቦት ሰባት! …”

ድርሻውን ጠያቂ ጋዜጠኛም “ኃይለማሪያም ሰፌድ ተጫወተብን” ብሎ መሬቱን በእርግጫ መታ።

የ“እኔም ማረፍ አማረኝ” ደራሲ ብንያም፣ ኢትዮጵያ ውስጥ የዴሞክራሲ ለውጥ ሽታ መንፈስ ከመጀምሩ በፊት፣ ሰተት ብሎ የማይገባበት የመንግሥት መሥሪያ ቤት አልነበረም። ቤተ-መንግሥት፣ ኢሕአዴግ ጽሕፈት ቤት፣ ኦሕዴድ ጽሕፈት ቤት፣ ብአዴን ጽሕፈት ቤት፣ ደኢሕዴን ጽሕፈት ቤት፣ ሶሕዴፓ ጽሕፈት ቤት፣ መከላከያ ሚኒስቴር፣ ደኅንነት ሚኒስቴር፣ ገቢ ሚኒስቴር፣ ብሮድካስት ኤጀንሲ፣ ብሔራዊ ባንክ፣ ባለስትራ ባንክ፣ ንግድ ባንክ፣ ዝርፊያ ባንክ፣ ልማት ባንክ፣ ጥፋት ባንክ፣ እንዳጋጣሚ 70 ፐርሰንት ባንክ፣ ወጋገን ባንክ፣ ጨለምለም ባንክ፣ ንብ ባንክ፣ ዝንብ ባንክ፣ ሸረሪት ባንክ፣ አየር ባየር ባንክ፣ አየር መንገድ፣ መንገድ ትራንስፖርት፣ ቤቶች ኤጀንሲና ሜቴክ በእጁ ነበሩ። በሚዲያ፣ የኢትዮጵያ ጦር ኃይሎች ኢታማዦር ሹም፤ ዶክተር – ፕሮፌሰር – ሪሰርቸር – የሱዳን የላቀ ሜዳሊስት – የብሔራዊ ሙዚየም ጋርድ – ባለ አራት ኮከብ – የዓለም ሎሬት ሚሊሺያ ጄኔራል ሳሞራ ይባላል እንጂ፣ አዛዡ ብንያም ነበር ሲባልም ነበር። ከወያኔ ወገን ያልሆኑ ጄነራሎች፣ ብንያምን መከላከያ ሚኒስቴር ግቢ ውስጥ ሲያዩት “በሉ ቻዎ! ማእከላዊ ዕዝ አሽቸኳይ ስብሰባ አለብኝ” እያሉ በጓሮ በር ሽው ነበር የሚሉት።

የኢ.ኤን.ኤኑ አዘነጋሽ ቦጋለ፣ የፈለገውን መረጃ ከፈለገው መሥሪያ ቤት ለማግኘት አንድ ነገር ብቻ ነው የሚያደርገው – ስልክ ደውሎ ማስፈራራት። የቀድሞው የኦሮሚያው ፕሬዝዳንት ሙክታር መጫወቻው ነበር። ብንያም የጠየቀውን ብቻ ሳይሆን ያልጠየቀውንም ይመርቅለታል። የጌታቸውን ስም ከጠራበት “ያ አላህ! … ማል ወያ በረና?”እያለ ጠረጴዛው ላይ ይንፈራፈራል ይባላል። በኢትዮጵያ የጦር ኃይሎች ታሪክ እንደአፈታሪክ ተወርቶ በማይታወቅ ሁኔታ፣ የኢትዮጵያን አየር ኃይል ሄሊኮፕተርን ተጠቅሞ ከሶማሊያ ስለውሸት ጦርነት የውሸት ሪፖርት ዘግቧል። በኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ናይሮቢ በነጻ ተጉዞ፣ ኢትዮጵያውያንን የሚያስፈራራ የሽብር ሪፖርት ከናይሮቢ አሰራጭቷል። ይህን ሁሉ ያደርግ በነበረበት ወቅት፣ የመንግሥት ሠራተኛ አልነበረም። የጋዜጠኝነት ፍቃድ የለውም። በኢትዮጵያ ውስጥ የተመዘገበ የሚዲያ ድርጅት አልነበረውም። በመከላከያ ውስጥ ባለ ሶስት መስመርአፍሪካ ሎሬት ሚሊሽያ ሃምሳ አለቃነት አይታወቅም። የካናዳ ዜግነት ያለው ሌባ ፊት፣ ሥልጣንና ሀብት ካላቸው ሰዎች ጀርባ ላይ ተጣብቆ የሚኖር ትውልደ ኢትዮጵያዊ ብቻ ነው። ሌባ ፊቱ ላይ የተተከለችውን ምላሱን ያፍታታው “ከኢሉባቦር ወገን ነኝ። ኩማ ደመቅሳ ከመጣበት። ዘመዴ ነው” በማለት ነበር። ኦቦ ኩማ ይህን ይወቅ አይወቅ እግዜር ነው የሚያውቀው። “አያቴ አዲስ አበባ ስትመጣ አማርኛ ስለማትችል በኦሮምኛ ስትናገር ይሳቅባት ነበር” መነገጃው ነበረች። ዛሬ በሽሽት ላይ ነው። መደበቅን መርጧል። አማርኛ የማይችሉም የሚችሉም በግፍ የተገደሉ ወጣቶች ደም እየጮኸበት ነው። እንደ ሳዳም ጉድጓድ ውስጥ ቢገባም ሳይከተለው አይቀርም። “አንተ ካሳ ሰብሳቢ!” ተብሎ የተሰደበበት ወቅትም ነበር። ገንዘብ እየተሰጠው በህወሓት የተገደሉትን ዜጎች አልተገደሉም ብሎ ስለሚያሰራጭ። የሱም መልስ የሚገርም ነበር። “እኔን ብቻ ለምን ካሳ ሰብሳቢ ትሉኛላችሁ? አውራምባ ታይምስና ሆርን አፌርስ ያው እንደኔው አይደሉም ወይ?”

ቦሌ ሲደርስ የኢሚግሬሽንና የፍተሻ ሠራተኞች እንደከዚህ ቀደሙ ፈርተውና እየሳቁ ያለፍተሻ አላሳለፉትም። ሻንጣውን በኤክስሬይ ማሽን ሶስት ጊዜ ጠብሰው የሻንጣ ቋንጣ ነው ያደረጉለት። የሻንጣው ጥብሰት ስለሸተታቸው እንጂ አምስት ጊዜም ኤክስሬዩን ቢያስጎበኙት ደስ ባላቸው ነበር። የሱሪና የጃኬት ኪሶቹን ጎትተው እያወጡና እየገለበጡ ነው የበረበሩት። “የተዘረፈ የሚሊሽያ ጄነራል ሳሞራና የሜቴክ ዶላር አመላላሽ ኤንትሬ” እያሉ ሲሳለቁበት “ለጌታቸው ስልክ ደውዬ አሳፍስሻለሁ” አላላቸውም። “የውሸት ጊዜ በእውነት ተለወጠ። ታሪክን መገለባበጥ የሚችል አምላክ ሁሉንም ገለባበጠው” ሲሉት መልስ ሳይሰጣቸው እንዴት ተወርውሮ አውሮፕላኑ ውስጥ መግባት እንዳለበት ብቻ ነበር የሚያስበው። የኤክስሬይ ማሽኑ የተፋትን የኪስ ቦርሳውን ከፈት አድርጎ ተመለከታት። “ኩማ ደመቅሳኮ ዘመዴ ነው! … ተመልከት! … ኢጆሌ ኢሉባቦር!” እያለ ለማስረጃነት የሚመዛት ፎቶግራፍ አርጅታለች። ለውጥ ሳይጎዳት አልቀረም።

አውሮፕላኑ ውስጥ ሲገባ ላብ በላብ ነበር። የፍርሃት ላብ ከያቅጣጫው እየመጣ መላ አካሉን አርሶታል። “እነዚያ ቁጥር ሥፍር የሌላቸው መሬቶቼስ? እነግራውንድ ፕላስ ኮካ ቪላዎቼስ? ለማ መገርሳ ይወስዳቸው ይሆን? ለቄሮ ያድልብኝ ይሆን? እትዬ ምጽላል ፍራሽ ሥር የደበኳቸው ዶላሮቼስ? ያ ዳንኤል በርሄ መቸስ አይታመን። በእንግሊዝኛ ‘Thank you very much, BenjaminFranklin. In God We Trust’ እያለ እንደ አወዳይ ጫት መቶ መቶዎቼን ይቆረጥማቸዋል … ለወሬ ነጋሪ እንኳ አንድ ዶላር አያስቀርም … እንደው ድሬዳዋ እሱን ታፍራ? … ለነገሩ በፍርድ ቤት ህግ ተመርቆ የፌስቡክ ሸርሙጣ ሆኖ ከቀረ idiot ምን ይጠበቃል!?” በሚሉ ሃሳቦች ብቻ አይደለም የተሞላው። ኦሕዴድ፣ ብአዴን፣ ኦነግ፣ ግንቦት ሰባት፣ ታንድ፣ የኦጋዴን ነጻ አውጪ፣ የአዲስ አበባ ወጣቶች፣ የኦሮሚያ ቄሮዎች፣ የጉራጌ ዘርማዎችና የአማራ ፋኖዎች ቢይዙት የመልካዋከና ኤሌክትሪክ ማስተላለፊያ ረጅሙ ምሰሶ ላይ የሚያንጠለጥሉት ነገር ነው የሚመስለው። በተለይ ኦሕዴድ፣ ኢሳያስ አፈወርቂ፣ ሙክታር ከድር፣ ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ፣ ግንቦት ሰባትና ትሕዴን የሱ ትረካና መጣጥፍ መለማመጂያ ነበሩ። ስለነሱ ሳያነሳ ውሎ ማደር አይችልም ነበር።

 የኦሮሞ ወጣቶች ለመብታቸው ብለው ግንባራቸውን ለመትረየስ ሲያስረክቡ፣ አቶ ብንያም አዘነጋሽ ቦጋለ ከተደበቀበት ሼራተን ሆቴል ብቅ ይልና “ኦህዴድ የቤት ሥራውን አልሠራም!” ብሎ የኦሕዴድ ሰዎች ላይ ይደነፋል። መቸም ያ ሙክታር ፈርዶበታል። ስልክ ደውሎ ከአዳማ ጨፌ ኦሮሚያ “ያ አላህ! … ማል ወያ በረና?”ን ያዘፍነዋል። ኢሳያስ አፈወርቂ “የወያኔን መሪዎች እናውቃቸዋለን። በቃላቸው የማይገኙ ውሸታምና ሌቦች ናቸው” ሲል፣ አቶ ብንያም አዘነጋሽ ቦጋለ ከመሸገበት ኩሪፍቱ ሪዞርት ብቅ ይልና “ኤርትራ ደሃ ከመሆኗ የተነሳ ኢሳያስ አፈወርቂ ዛሬም ሸበጥ ነው የሚያደርገው። እንደ ጂንስ ያለቀ አሮጌ ማርቸዲስ ነው ያለው” ይላል። “እምቢ ለባርነት!” ያሉ የጎንደር እና የባህርዳር አፍላ ወጣቶች በአጋዚ ጥይቶች ሲቀነጠሱ፣ አቶ ብንያም አዘነጋሽ ቦጋለ ብዙ ሺህ ዶላር እየመዠረጠ የሚለጋውን አረቄ በንዴት ይደፋውና “ብአዴን የድሮ ሥርዓት ናፋቂ ሆኗል። ራሱን ማጥራት አለበት። በረከትና አዲሱ የብአዴን ዋና እና ምክትል ሊቀመንበር መሆን አለባቸው። በአስቸኳይ!” በማለት የአቶ ገዱ አንዳርጋቸውን አስተዳደር ተጠያቂ ያደርጋል። ግንቦት ሰባትን ለማጣጣል የሚጓዘው የክፋት ርቀት የሚገርም ነው። ግን አውሮፕላኑ ውስጥ የገጠመው ልዩ ነው። የእግዚአብሄር ድንቅ ሥራ ሳይሆን አይቀርም።

አውሮፕላኑ የኢትዮጵያን አየር ክልል ከመጨረሱ በፊት ወደ መጸዳጃ ቤት የምትሄድ አንዲት ሴት አየችው። የአዲግራት ልጅ ናት። “አንተ ሌባ!” ስትለው የደነገጠው ድንጋጤ በቃላት አይገለጽም። ሌባ ፊቱ ፏ አለች። አንዲት የትግራይ ቆንጆ “ሌባ!” ትለኛለች ብሎ አልጠበቀም። እንደበፊቱ “መዓረይ … ሹካሬይ … ክቡር ወጣቱ ኢንቨስተር … የተከበረው ተተኪው ባለርዓይ … የአፍሪካው ሲ.ኤን.ኤን ባለቤት … የኢሉባቦሩ መለስ ዜናዊ … የመቱው አሊኮ ዳንጎቴ … የታዋቂው የኦሮሞ ሕዝብ መብት ታጋይ የኩማ ደመቅሳ ዘመድ … ያላሙዲ አማካሪ … የሚኖረው’ኮ ሼራተን ነው … ቺርስ!” ነበር ያለመው።

ነገሩን ለማለሳለስ ፈለገና “ለምለም … ጽቡቅቲ … የት ነው የምትሄጂው?” አላት በፈገግታ።

 “የአዲስ አበባ ሕዝቦች ስላንተ የሚያወሩትን ሰምተሃል?” ብላ ጠየቀችው በንቀት።

“የአዲስ አበባ ሕዝቦች ስለ’ኔ ምን ያወራሉ? ቢያወሩም the founding father of the modern Ethiopian television station ነው የሚሉት:: The first African CNN in Ethiopia, ENN” አላት።

“እዋይ! አንተ … ዛሬም እሱን አልተውክም … ጌታቸው’ኮ የለም። የኩራዝ፣ የበለስና የወልቃይት ስኳር ፋብሪካዎችን መገንቢያ ገንዘብ ሙልጭ አድርገው ከሰረቁት መካከል አንተም አንዱ ነህ እየተባለ ነው።”

“እንዴ! እኔ የመንግሥት ሠራተኛ አይደለሁም። ገንዘቡን ማን ይሰጠኛል?”

“ዋ! መንግሥት ምን አገባው አንተ? … የአድዋ ሚሊሽያ ጄኔራሎች እያሉ … ሄሊኮፕተር እንዴት ሰጡህ? …  the founding father of the modern Ethiopian ሰራቒstation ቢሉህ ነበር ጥሩ። TNN, Thieves News Network … የናንተው ሌቦች ወይም Yours Thieves!”

“አንቺ የትግራይ ልጅ አይደለሽም እንዴ! … እንዴት እንደዚህ ትያለሽ? … እኔ’ኮ ኦሮሞ ሆኜ ለናንተ ነው የማግዘው።ሙክታርን ‘ያ አላህ! … ማል ወያ በረና?’ የማዘፍነው ለናንተ ብዬ ነበር።”

“የትግራይ ልጅ ብሆንስ! … እኛ ሌብነት አግዙን መች አልን? ሌባ መች አጣን። ህንፃ፣ ግድብ፣ መንገድ፣ ተራራ፣ ባንክና ወረዳ የሚሰርቁ ሞልተውን የለም እንዴ!”

“ከአዲግራት ነሽ እንዴ?”

“አዎ ከአዲግራት ነኝ። ሁሉም አዲግራት! አዲግራት! ይላል። አዲግራት ላይ ምን ተደረገልን? የጦር አውድማ ሆነን ስጋትና አቧራን ስንተነፍስ ነው የከረምነው። ይልቅ በኢንተርፖል ተቀፍድደህ ከዱባይ እንዳትጠረዝ። ያንን አስብ” አለችው።

“ወይ መዓልቲ … ለፍተን ለፍተን መጨረሻችን …” ብሎ ሲጀምር

“ትግርኛውን ተውና ኢሉባቦር ላይ ያደረከውን አስታውስ። … ምኑን ነው የለፋኸው? ሌብነቱን?” ብላው ወደ መጸዳጃው አቅጣጫ ሄደች።

….. ኢሉባቡር የሆነው ይህ ነበር። በኦሮሚያና በአማራ ክልሎች የመብት ትግሉ እየተጧጧፈ በሄደ ጊዜ፣ የህወሓት መንግሥት በጣም ደነገጠ። የመደንገጡ ዋናው ሰበብ፣ ከኦሮሚያ ምድር ላይ የሙክታር ‘ያ አላህ! … ማል ወያ በረና?’ ከሥሩ ተነቅሎ፤ በለማ መገርሳ “ኢትዮጵያዊነት ሱስ ነው!” መተካቱ ነበር። ይሁንና ወያኔ የለማ መገርሳን “ቀድጄው ነው የምጥለው”ን ድፍረት በመፈታተን፣ ይህንን የመብት ትግል ወደ አልተፈለገ አቅጣጫ በመውሰድ ማክሸፍ እንዳለበት ወሰነ። ወኪሎቻቸውንና በገንዘብ የገዟቸውን ተላላኪዎቻቸውን ሰብስበው አንድ ግዳጅ ሰጧቸው። ግዳጁን ለመፈጸምም ወደ ኢሉባቦር ላኳቸው። የኦነግ ባንዲራዎች፣ በራሪ ወረቀቶች፣ በርከት ያሉ ሽጉጦች፣ በብዙ መቶዎች የሚቆጠሩ ጥይቶች፣ ስለታም ጩቤዎችና ዩኒፎርሞችን ከደህንነት መሥሪያ ቤት አውጥተው፤ በተዘጋጀው ሌላ መኪና ወደ ኢሉባቦር ላኩት። ኢሉባቦር የተመረጠበት ምክንያት አቶ ብንያም አካባቢውን ስለሚያውቀው ነበር። የአባቱ አገር ነው። ከልጅነቱ ጀምሮ አያቱን ለመጠየቅ ብዙ ጊዜ ተመላልሶበታል። ሁለተኛውና ዋናው ምክንያት ግጭቱን ወደ ኦሮሞና አማራ ጉዳይ በመውሰድ ለህወሓት ፋታ ለማስገኘት ነበር። ከዚያ ፈትለወርቅ የበግ ቁርበት ለብሳና እንደ በግ ‘በእእእእ’ እያለች አስታራቂ ሆኖ ብቅ እንድትል። ሶስተኛው ምክንያት፣ ይህንን ትንቅንቅ በመጠቀም የኢ.ኤን.ኤን ቴሌቪዥን ተመልካቾችን ቁጥር ከፍ ለማድረግ ነበር። ልክ እንደኳስ ጨዋታ “ጦርነቱ ተጀመረ!” ሲባል “ሰበር ዜና! … አሁን የደረሰን! … በጣም ትኩስ! …” ለማለት።

….. እንዳቀዱትም የአካባቢውን ሰላማዊ ነዋሪ እርስ በርሱ ማጋጨት ጀመሩ። የኢ.ኤን.ኤን ጋዜጠኞችም ከህወሓት ተጽፎ የተሰጣቸውን ሰበር ዜና አስተላለፉ። በሽመልና በድንጋይ የሚፈነካከቱ ሰዎች እንጂ በጦርነት እሳት የሚንቦገበጉ ቤቶች ስላጡም ከሰው ሀገር ቃጠሎ ላይ በሰበር ዜናው መሃል “ጨምሩ” የተባሉትን ምስል ጨመሩበት። ይህ በዚህ ሁኔታ ላይ እንዳለ፣ ወኪሎቻቸውንና በገንዘብ የገዟቸው ተላላኪዎቻቸው ካረፉበት ሆቴል በቀላሉ ተይዘው በኦሮሚያ ፖሊስ ቁጥጥር ሥር ዋሉ። የለማ መገርሳ “ቀድጄው ነው የምጥለው … ኦሮሚያን የማስተዳደሩ ኃላፊነት እስከተሰጠኝ ድረስ የምወስነው እኔና እኔ ብቻ ነኝ። በግልባጭ አልወስንም!” በተግባር ፍሬ ማፍራት ጀመረ። በኦሮሚያ ውስጥ ያለው የመንግሥት መዋቅርና ሕዝቡ፣ የንጹሃን ዜጎችን ሬሳ ከየቦታው መልቀም ስለሰለቻቸው ከስግብግ ህወሓቶችና ተላላኪዎቻቸው ጋር በሁሉም ዘርፍ የሚያደርጉትን ትንቅንቅ ቀጠሉ። … የአዲግራቷ ልጅ “ኢሉባቦር ላይ ያደረከውን አስታውስ” ያለችው ያንን ነው።

የአራት ሠዓት በረራ አራት ቀን ሆኖበት ዱባይ ዓለምአቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ በስቃይ ደረሰ። ሊቀበለው የመጣው ያው የተለመደው ተባባሪው ነው።

 “ኡኡኡ ጭሷ ዱባይ!” አላለም ብንያም። በፊት ገና ተቀባዩ ሲደርስ ነበር ዶላር ያጨቀበትን ሻንጣውን መኪናው ውስጥ ወርውሮ፣ የዱባይን ሰማይ አንጋጦ እያየና ሁለት እጆቹን ወደ ሰማይ ዘርግቶ “ኡኡኡ ጭሷ ዱባይ! … ገባንላት!” እያለ ይጮኽ የነበረው። ከጋቢናው ተቀምጦና ሁለት እግሮቹን ዳሽ ቦርዱ ላይ ጥሎት “ዱባይ ነፍሴ! … የዱባይ ገዥ ሼህ መሃመድ ቢን ራሺድ አልማክቱም ለዘላለም ይኑር” ዘፈኑ ነበረች። “ቤት ሳንደርስ ቀጥታ ወደ ክትፎ ቤት! ገብቶሃል? የዱባይ ክትፎ አምሮኛል። እነዚያን ሁለት ቆነጃጅት ከግራና ቀኝ ታፋዬ ላይ አስቀምጬ ክትፎዬን መዋጥ ፈልጋለሁ” ማለት ለሱ አዲስ አልነበረም። በዱባይ ዳንስ ቤቶች እየዞረ፣ ከኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ የተዘረፈ ዶላር በየሴቱ ዳሌ ላይ “ቿ!” እያደረገ ይለጥፍ ነበር። የመቶ ኖቶችን እንደ ወረቀት እየወረወረ ነበር ደረታቸው ላይ የነሰነሱትን ሽቶ ለሰኮንድ የሚያሸተው። ትንሽ ሞቅ ባለው ቁጥር የላይኛው ከንፈሩን እንደ በግ ወደ ላይ ገልብጦና አፍንጫውን አሹሎ ያገኘው ላይ ሁሉ ዘሎ በመውጣት ይታወቃል።

ተባባሪው ለወቅታዊ መረጃ በጣም የዘገየ ይመስላል። “አንቺ’ኮ ስማርት ነሽ። ስማርት ጋዜጠኛ። ያለምንም ገንዘብ ከካናዳ ተነስተሽ ቤተ-መንግሥትና ሼራተን የገባሽ። አዲሱን ጠቅላይ ሚኒስትራችንን ኢንተርቪው የምታደርጊው መች ነው? ከመለስና ከኃይለማሪያም ጋር ያደረግሽው ተአምር ነበር” ብሎ ጠየቀው።

“ቤት ውሰደኝ። እኔም ማረፍ ፈልጋለሁ። ቤት ብቻ ውሰደኝ” ብቻ ነው ያለው።

አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ከአራት ዓመት የሰቆቃ እስር በኋላ ነፃ ወጣ። እውነት አሸነፈ። ከእስር ቤት ወጥቶ ቤተ-መንግሥት በክብር ተጠራ። ከአዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ጋር ተወያይቶ ወደ እንግሊዝ ሄደ። ከትንሽ ጊዜ የእንግሊዝ ሀገር እረፍት በኋላ ወደ ኤርትራ በረኻ አቅንቶ የትግል ጓዶቹን ጎበኛቸው። የግንቦት ሰባትን የበረኻ ትግል ሀ ብሎ ያስጀመረው ሳይሆን የጀመረው እሱ ነው። እንደ ኢ.ኤን.ኤኑ ብንያም “ኦሮማይ” ቢሆን ኖሮ፣ አንዳርጋቸው እንደታፈነ ይቀር ነበር። ኢ.ኤን.ኤንም ውሸቱን ይቀጥል ነበር።

የኦሮሚያ ክልል የህወሓት ክፋት በእጅ አዙር ካልሆነ በስተቀር በቀጥታ የማይደርስበት መሬት ሆነ። የክልሉ መንግሥት ልዩ ልዩ አዋጆችን አወጣ። የብንያምና ስግብግብ ጓዶቹ መሬት ተቀማ። በውሸት ኢንቨስተር ስም የሚመዘበረው የኦሮሚያ ሀብት እረፍት አገኘ። የኦሮሞ ወጣቶች ከዳር እስከዳር በፖለቲከኞች ተደነቁ። የነፃነት ፈረስ መጋለብ፣ ዘፈኖች መዝፈን፣ ሥራ መሥራት … ቀጠሉ። “ለኦሮሞ ሕዝብ ነፃነት እንታገላለን” ያሉ በደርዘን የሚቆጠሩ ፖለቲከኞች ከያሉበት ወደ ሀገር ቤት መመለስ ጀመሩ። በውጭ ሀገር ሳሉ “ቶኩማ” እያሉ ከመዘመር በቀር አንድ ለመሆን የሚቸገሩ ነበሩ። የባሌ፣ የአርሲ፣ የሸዋ፣ የወለጋ፣ የሐረርጌ፣ የኢሊባቦር፣ የጉጂ፣ የቦረና እና ኦሮሚኛ መናገር የማይችል ኦሮሞ ቡድን አቋቁመው ሲኮራኮሙ የከረሙ ናቸው። በኦሮሚያ ሰማይ ላይ የትግል ባንዲራቸውን ለማውለብለብ ከልካይ አጡ። ነገ “ይህንን ባንዲራ ለመጀመሪያ ጊዜ ለኦሮሞ ሕዝብ ያስተዋወኩት እኔ ነኝና መጠቀም ያለበት የኔ ድርጅት ነው” ተብሎ መገዳደል እንዳይመጣ ዋስትናው ምንድ ነው? ምርጫ ቦርድም አንድ ባንዲራ ወይም ዓርማ ለአሥር ድርጅት አይፈቅድም። ወይስ ሊወሃዱ ነው? መልሱ በነሱ እጅ ነው።

የአማራ ክልል ነዋሪዎች ባለ 500 ሜትር ኮከብ አልባ የኢትዮጵያን የቀድሞ ባንዲራ በባህርዳር ላይ አሳዩና ጉድ ተባለ። “የአሮጌው ዘመን ቁማርተኞች” በአቶ ገዱ አንዳርጋቸው ተነገረ። በየአቅጣጫው “ኢትዮጵያ! ኢትዮጵያ!” ሆነ። ኢትዮጵያዊ በሙሉ የልቡን መናገር ጀመረ። የፍራቻ አጥር ተሰባበረ። ማን ከብአዴን መባረርና ማን መታሰር እንዳለበት የሚገልጹ ምልክቶች በግልጽ ይታያሉ። አንዱም በአሜሪካ የኢትዮጵያ አምባሳደር የሆነው ካሳ ተክለብርሃን ነው። እሱም ይህን ስላወቀ ሥልጣኑን ላለማጣት ይፈራገጣል። በጣም የተጠላ አምሳደር ሆኖ ሳለ በጣም የተወደደ ለመምሰል መከራውን ያያል። በፖለቲካው ጉዳይ ተስፋ ቆርጦ ለቤተሰቦቹ ሲል የሚሟሟት ይመስላል። መኪናው፣ ሞተሩ፣ ባጃጁ፣ ብስክሌቱ፣ ጀልባውና የቆነጃጂት ፊቶች በባንዲራ ተዋቡ። ሳቅ። ደስታ። ዘፈን። መዝሙር። ያልተደሰተና ሃሳቡን በነፃ የማይገልጽ ማግኘት አስቸጋሪ የሆነበት ጊዜ ሆነ። ወጣቶችም የአማራ ብሄራዊ ንቅናቄ የሚባል የፖለቲካ ድርጅት መስርተዋል። ኃይለኛ ድርጅት ይመስላል። ከሚቀጥለው ምርጫ በኋላ የአማራን ክልል የማስተዳደር ሥልጣን ሳይረከብ አይቀርም። መቶ በመቶ እንዳይሆን ያሰጋል። በጭቆና የተንገበገቡ እሳት የነከሱ ወጣቶች ናቸው። ህወሓት ከ547 የተጭበረበረ ወንበር፣ ሃቋ የሆነውን 38ቷን በፀጋ የምትቀበልበት ዘመን በግልጽ የሚታወጀው በነዚህ ወጣቶች እንዳይሆን።

“ከአሥመራ ጀምሮ እስከ ሞቃድሾ ድረስ የተዘረጋውን የሽብር መረብ ይመራሉ። አዲስ አበባን በማተረማመስ ባግዳድ ለማድረግ ታጥቀው ተነስተዋል. …” እየተባሉ በህወሓት መንግሥት ሲወነጀሉ የነበሩት የሀገረ ኤርትራ ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ፣ የህወሓት ባለሥልጣናት እያዩዋቸው አዲስ አበባ በክብር መጡ። አንድም የህወሓት ባለሥልጣን ሊይዛቸውና እስር ቤት ሊጨምራቸው አልሞከረም። የፈሯቸውም በስብሰባ ስም መቐሌ ተደበቁ። “ድንበር እንጋራለን፣ አንድ ቋንቋ እንናገራለን፣ ቤተሰባሞች ነን፣ አንድ ደም ነው ያለን፣ እህታማቾችና ወንድማማቾች ነን፣ ኤርትራውያን ከሌላው ኢትዮጵያውያን ይልቅ ከኛ ጋር የሚያመሳስላቸው መአት ነገር አለ” እንዳላሉ ሁሉ፤ “ህወሓት ውሸታምና ሌባ ነው” የሚላቸው በደም አንድ የሆነ ወንድማቸው አዲስ አበባ ሲመጣ ደብዛቸው ጠፋ። ለምን? … ይልቅ ለፕሬዚዳንቱ የክብር መድፍ ተተኮሰላቸው። ባንዲራቸው የኢትዮጵያን አየር ደነሰበት። ብሔራዊ መዝሙራቸው ናኘበት። ሕዝቡ በጋለ ወንድማዊና ናፍቆታዊ ስሜት እየዘፈነ ተቀበላቸው። ያለቀሱም ሞልተዋል። ከወደ ሀዋሳም ወረድ ብለው ከሲዳማ ባሕላዊ የእርቅና የምርቃት ሥነ-ሥርዓት ላይ ተሳታፊ ሲሆኑ ታዩ። የአርሲ ኦሮሞን ባሕላዊ ምግብ ቀምሰውና እርጎ ተጎንጭተው፣ በሚሊኒየም አዳራሽ “አሸባሪ” ሳይሆን “ኢሱ … ኢሳያስ” ተብለው ተወደሱ። በጣም የተደሰቱት ኢሱ እንባቸውን እንደምንም ታግለው ሲይዙት ከፊታቸው ይነበብ ነበር። አማርኛ አሰምተው፣ ከሁለት ቀን የኢትዮጵያ የዝነጣ ቆይታ በኋላ ወደ አሥመራ በክብር ተሸኙ። የዓመታት የህወሓት ክስና የኢ.ኤን.ኤኑ ብንያም ድንፋታ አፈር ድሜ በላ። ኢጋድ፣ አፍሪካ ህብረትና ዩኤን ትዝብት ላይ ወደቁ። ያ ሁሉ ፕሮፓጋንዳ ለዚሁ ነው? … ባግዳድ ለማድረግ … ሸበጥ ነው የሚያደርገው …ቱልቱላ! ግን ሰላማዊ ግንኙነቱ ይቀጥል ይሆን? አንድ መቶ ሺህ ሕዝብ ማጣትና የሃያ ዓመት ቅጣት ቀላል አይደለም።

አቶ ብንያም አዘነጋሽ ቦጋለ ካናዳ ገባ ይባላል። ከዱባይ በኋላ ማንም አላገኘውም። ከኢትዮጵያ በተዘረፈ ገንዘብ ሩዋንዳንና ታንዛኒያን በሪል ስቴት የሚያሳድጉ ጓደኞቹም ሊያስጠጉት አልፈለጉም። “ጣጣ አታምጣብን። እኛ ድምጻችንን አጥፍተን ሀገር እየገነባን ነው” ብለውታል። እንግዲህ ምን ይደረጋል … ኑሮውን ከዜሮ መጀመር ነው። ያውም ኢንተርፖል የተደበቀበትን ቤት በር ካላንኳኳ! ቻዎ ቻዎ ኢ.ኤን.ኤን። ምስኪኑ የህወሓት ተላላኪ ብንያም። አሁን አንተ ኦሮማይ ላይ ስለሆንክ ሌላ ኦሮማይ እንዳትተርክ። እባክህ። ከቤኒያም ወደ ብንያም፣ ከዚያም ወደ ቤንጃሚን፣ ከዚያም ወደ አዘነጋሽ ቦጋለ፣ በመቀጠልም ወደ the founding father of ENN ቁልቁል አድገህ ነበር። አሁን ግን አንዳርጋቸው ሳይሆን ራስህ ኦሮማይ ሆንክ። የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ፣ የኢትዮጵያ መድህን ድርጅት፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ የኢትዮጵያ መከላከያ ሚኒስቴርና የደህንነት መሥሪያ ቤት ፊታቸውን አዞሩብህ። አንተ ኢትዮጵያን ከለቀክህ በኋላ የኢትዮጵያ መንግሥት መኪናዎች ነፃ ወጡ። ቦምብ ለማፈንዳት የምታስቆርጡት የስልክ ኔትወርክም ደህና ነው። ሰላም ብሎሃል። “የሶማሌ ልጃገረዶች ያለአግባብ በአብዲ ኢሌ ታጣቂዎች ተሰቃዩ” ብሎ አምነስቲ ኢንተርናሽናል መግለጫ ሲያወጣ፣ የአዘነጋሽ ቦጋለ ካሳ ሰብሳቢ ኮፖሬሽን አባላት ደገሃቡር ወርደው፣ የተሰቃይ ወላጆችን ያስጨንቃሉ። “ሪፖርቱ ውሸት ነው። እከሌ የምትባል የቤተሰብ አባል የለንም በሉ” ብለው ቪዲዮ ያነሱና ያሰራጩታል። አርባምንጭ አድርገውታል። ኦሮሚያ ላይ ደጋግመውታል። አሁን የለም። ኢትዮጵያ አንተን የመሰሉ ሌቦች መጫወቻ የማትሆንበት ዘመን ተጀምሯል።  ከፈለግህ የተረፈ ዶላር ካለህ እሱን አስረክብና ተደመር። ምን ቸግሮህ ለጌታቸው ባሪያ እንደሆንክም ተናዘዝ። የኢትዮጵያውያን ሞት ለምን ያስደስትህ እንደነበር አስረዳ። በኩማ ደመቅሳ ስም ንግድ እንደከፈትከው ሁሉ “አብይ አጎቴ ነው” ብለህ ማታለል እንዳትጀምር። እሱ ገና ነው። በአንዴ’ማ አይሆንም።

__._,_.___
Happy
Happy
0 %
Sad
Sad
0 %
Excited
Excited
0 %
Sleepy
Sleepy
0 %
Angry
Angry
0 %
Surprise
Surprise
0 %
    Print       Email

Average Rating

5 Star
0%
4 Star
0%
3 Star
0%
2 Star
0%
1 Star
0%
<"Without the support of our readers, the Maleda Times website would not exist in its present form">

You might also like...

Ethiopia’s Media Under Siege Amid Escalating Conflict in Amhara

Read More →

This site is protected by wp-copyrightpro.com

Skip to toolbar