ያለፈችዋ ሌሊት እስክትነጋልኝ በጣም ቸኮልኩ፡፡ መንጋቷ አልቀረም ይሄው በሌሊቱ ቢሮየ ገብቼ ይህችን ማስታወሻ መጻፍ ጀመርኩ፤ ችኮላየም ለዚሁ ነበርና፡፡
አንዳንድ ከበድ ያሉ ሀገራዊ ጉዳዮች ሲከሰቱ የተለያዩ የሀገር ውስጥና የውጪ ሚዲያዎች ምን እንደሚሉ ለማወቅ የዜና አውታሮችን እየለዋወጥኩ እከታተላለሁ፡፡ በዚህ የተለመደ የራሴ አካሄድ ብዙ ነገሮችን እማራለሁ፤ እታዘባለሁ፡፡ በሀገራችን እንደአማራ ቲቪ፣ ትግራይ ቲቪ፣ ኦቢኤን(ኦሮሞ ብሮድካስቲንግ ኔትወርክ)፣ ኢቲቪና ኢሳትን የመሳሰሉ ጣቢያዎች ስለአንዳንድ የሀገራችን ታላላቅ ክስተቶች ምን እንደሚሉና እንዴትም እንደሚሉት ከቋንቋ አንጻርና ከቋንቋ ውጪም ባሉ አንድምታዊ ነገሮችን የመረጃ መንገዶች ለመገንዘብ እሞክራለሁ፤ ጊዜው የጣለብን ሸክም ነው፡፡
ትናንት በቀኑ ውሎየ ክፉኛ ባዝንም ሀዘኔን ለጊዜው የሚያጽናና ነገር በትግራይ ቲቪ በማግኘቴ ደስታየ ወሰን አልነበረውም፡፡ ኢትዮጵያ የምሥጢራት ሀገር፣ ኢትዮጵያ ልትመረመር የማትችል የትንግርት ሀገር፣ ኢትዮጵያ ሊበጠስ የማይችል የአንድ ኅብረ ብሔር ሕዝብ ተጋምዶ የሚገኝባት ዕፁብ ድንቅ ሀገር… መሆኗን የቅርብ ዓመታት አቋሜን በተፈታተነና አመለካከቴንም እንድፈትሽ ባደረገ መልክ ልገንዘብ ችያለሁ፡፡ ጥቂቶች ትናንትም ሆነ ዛሬ ሊያለያዩንና የግፍና የበደላቸውን መርግ ሊጭኑብን ቢሞክሩም እኛ ሕዝቧ ግን የተያያዝንበት እትብት መቼም ሊበጠስ እንደማይችል ዐይኖቼ ዕንባ እስኪያቀሩ ድረስ ውስጤን ዘልቆ በተሰማኝ ልዩ ስሜት ተረድቻለሁ፡፡ እንደዚህች ሀገር ያለ ተዓምረኛ ሀገር ያለ አይመስለኝም፡፡ አለች ስትባል የለችም፤ የለችም ስትባል አለች፡፡ ሞተች ብለን ተስፋ ስንቀርጥ አፈር ልሳ ትነሳለች፡፡
የኢንጂኔር ስመኘው በቀለን ሞቶ መገኘት በተመለከተ ቲቪዎቻችን እንዴት እየዘገቡት እንደነበር ለማጤን ትግራይ ቲቪን ከፈትኩ፡፡ በግሩም ሁኔታ እየተዘገበ ነበር፡፡ አሉታዊ ስሜት ይዤ ስለነበር ወደዚያ የዞርኩት የምጠብቀውን አገኛለሁ ብዬ አላሰብኩም ነበር፡፡ ምክንያቴ ግልጽ ነው፡፡ የችግራችን አንኳር መንስዔ እዚያች ሀገር የመሸገው ነባርና አዳዲስ የሕወሓት አባላትን በምርኮ የያዘው የአጋንንት ኃይል መሆኑን ማንም አያጣውም፡፡ በዚያ ኃይል የሚታዘዝ ጣቢያ ከዚያ ኃይል ፍላጎትና አመራር ይወጣል ተብሎ ታዲያ ሊታሰብ አይችልም፡፡ የትናንቱ ግን ከወትሮው ለየት ይል ነበር፡፡ ልዩ የሆነው ግና በሕዝባዊው የመረረ እውነተኛ ሀዘን እንጂ በግድ በጣቢያው አዛዦች ግፊት ሊሆን እንደማይችል “የዋህ ነህ” የምትሉኝን ሰዎች አለመዘንጋቴን ማስታወስ እፈልጋለሁ፡፡
ጋዜጠኞች በመGለ ከተማ እየተዘዋወሩ የከተማዋ ነዋሪዎች በዚህ ብርቅዬ የሀገር ባለውለታ ሞት የተሰማቸውን እንዲናገሩ ያደርጉ ነበር፡፡ “ከሰማሁ ጀምሮ የት እንዳለሁ አላውቅም፡፡ አሁን ድረስ ራሴን መቆጣጠር አቅቶኝ ነው ያለሁት፡፡ ኢትዮጵያ የሞተች ነው የመሰለኝ፡፡ ወዴት እየሄድን እንደሆነ ማወቅ ቸግሮኛል፡፡…” እያለ ከቋንቋው ይልቅ ስሜቱ አይሎ ዕንባ እየተናነቀው ግብግብ(እርር) ሲል ያየሁት መልከ መልካም ወጣት የሀገር ወዳድ ተጋሩን ትክክለኛ ገጽታ እንድረዳ አስችሎኛል፡፡ ሌሎቹም ከሞላ ጎደል እንደዚሁ ወጣት ናቸው፡፡ በሌሎች ጣቢያዎች ከታዘብኳቸው የመረረ የሀዘን ስሜቶች ይልቅ የዚህች ውብና ታሪካዊ ከተማ ነዋሪዎች ያሳዩት ሀዘን በልጦ አግኝቼዋለሁ፡፡ በዚህም ብዙ ነገር እንድማር ተገድጃለሁ፡፡ ማለት የፈለግሁት ሌላ ነው – ሀዘንተኞችን እያወዳደርኩ እንዳልሆነ ግልጽ ይሁንልኝ፡፡
ተጋሩ የሆነ ነገር ይዟቸው እንጂ ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያውያንን ከማንም ባላነሰ ምናልባትም በበለጠ እንደሚወዱ ብመሰክር አላጋነንኩም – በእስካሁን ጽሑፌ ከዚህ ተቃራኒ ነገር ብዬ ከሆነ በዚህኛው ይስተካከልልኝ፡፡ ይህ ዘመን ያመጣብን ሕወሓትና ትግራይ የሚባል ነገር ብዙዎቻችንን እያበላሸ ስንጥቃቱን አሰፋብን እንጂ እውነቱ ሌላ መሆኑን መረዳት አለብን፡፡ ኢትዮጵያ ያለ ትግራይ፣ ትግራይም ያለ ኢትዮጵያ ማለት ሰውን ሣምባውንና ልቡን አውጥቶ በቀሪ ሰውነቱ እንዲኖር የመልቀቅ ያህል እንደሆነ ይሰማኛል፡፡ ይህን አስተያየቴን ለመቀበል ያን እኔ የተመለከትኩትን ዝግጅት በድጋሚ ማየት ይገባል፡፡ በበኩሌ ከገመትኩትና ከጠበቅሁትም በላይ በሆነብኝ በዚያ የሀዘን መግለጫ አስተሳሰቤን እንዳርቅና እንዳስተካክል ወደኅሊናየ ተመልሻለሁ፡፡ አሁን የሚያስፈልጉን የሰውን አስተሳሰብ ወደጤናማ መንገድ የሚመልሱ (ማኅበረሰብኣዊ) የሥነ አእምሮና የሥነ ልቦና መሃንዲሶች ናቸው፡፡ በመለሳዊ የከፋፍለህ ግዛ መንፈስ የሚነዱ ስብሃትንና በረከትን የመሰሉ የቀን ጅቦች ሳይሆኑ ዐቢያዊ የአንድነትና የፍቅር ዜማ አቀንቃኞች ናቸው የሚያስፈልጉን አሁን፡፡ ለዚህ ፍላጎታችን እውንነት በርትተን መጸለይ አለብን፡፡ በምንችለውም ሁሉ ለውጡን መታደግ ይገባናል፡፡
ኢንጂኔር ስመኘው ከኢትዮጵያዊነቱ በስተቀር ለትግራይ ሕዝብ ምንም ማለት አይደለም፤ ለነሱ ያደረገላቸው የተለዬ ነገርም የለም፡፡ ሕወሓት ዕድሜ ልኩን እንደደከመለት ዘረኛ የአስተዳደር ዘይቤ ቢሆን ኖሮ በዚህ ሰው ሞት ትግራይና ተጋሩ ጭንቅላታቸውን ቅቤ በመቀባት እስክስታ መውረድ ነበረባቸው፡፡ እውነቱ ግን የወያኔን ልፋት መና የሚያስቀር ሆነና ትግሬው ለጎንደሬው በሀዘን ሲንገበገብ ታዘብን፡፡ እዚህ ላይ ነው ቆም ብሎ ማሰብና ጠላትንና ወዳጅን መለየት የሚገባው፡፡ እዚህ ላይ ነው በቅርቡ “ዐይጥ በበላ ዳዋ አይመታ፤ በአንድ ጠማማ እንጨት ምክንያት ደን አይጨፍጨፍ” የተባለውን የልጅ-ዐዋቂውን የጠ/ሚ ዶ/ር ዐቢይን ቁጭት አዘል ማሳሰቢያ ማስተዋል የሚገባን፡፡
(በዚህ አጋጣሚ ግን ለትግራይ ቲቪ ጋዜጠኞች የማሳስባት ትንሽዬ ነገር አለችኝ – እርሷም እያስገደዱ በሚመስል አኳኋን ተጋሩ የሌሎችን አካባቢዎች ሰላማዊ ሰልፎች “ህገ መንግሥት ተጣሰ” በሚል ሰበብ እንዲቃወሙ የሚያደርጓትን ቀሽም ትያትር እንዲተዋት ወይም እንደ እንጀራ ገመድ የምትወሰድም ከሆነ ቀነስ እንዲያደርጓት ለማሳሰብ የምሰነዝራት አስተያየት ናት፡፡ ዜጎች ፍላጎታቸውን ሲገልጡ መበረታታት እንጂ መወገዝ የለባቸውም፡፡ የለውጡ እየገዘፈ መሄድና አሸንፎ መውጣት ደግሞ የማይቀር ታሪካዊ እውነት ነውና ራስን በቶሎ ማስተካከል ተገቢ ነው፡፡)
በዚህ ሂደት ግን የሰዎች መሞት የሚጠበቅ ነው፡፡ ግድያና ሞት ደግሞ ትግልን የሚያፋፋና ይበልጥ የሚያቀጣጥል እንጂ የተጀመረን ትግል የሚያዳፍን ወይ የሚያቀዘቅዝ አይደለም፡፡ ሕወሓት ደግሞ ለዚህ ኅያው ምሥክር ነው፡፡ Some incidents, such as the attempted murder, presumably to kill the PM, carried on during the mass rally last month, and the murder of this Engineer, are altogether catalytic factors that can be taken as a blessing in disguise. The English idiom has it already; “there is no free lunch”. Though we are in shock due to the losses we happen to encounter, these sacrifices are not vain. Blood cleanses blood more than anything else. By the way I beg you not to label me as ‘cruel’; I am simply reflecting the stark truth. So let’s not dwell on what has happened, whether it’s good or bad, rather, let’s focus on what shall be happening now and as of now.
ልጃችን ስመኘው የሁላችን ልጅ መሆኑን የትግራይ ሕዝብ ጠንቅቆ ያውቃል፡፡ የሞቀ ትዳሩን ትቶ፣ ቤት ንብረቱን ዕርግፍ አድርጎ፣ ዳግም የማያገኘውን ምድራዊ ሕይወት ንቆ በበረሃ ሲቃጠል የነበረውና በመጨረሻም በዐረመኔ የሀገሩ ልጆች – እንደምገምተው – ነፍሱ ከሥጋው ልትለይ የቻለችው ለሀገሩ ኢትዮጵያ ዕድገትና ብልፅግና ሲል ነው፡፡ ስመኘው ለአማራ አላለም፤ ስመኘው ለጉሙዝ አላለም፤ ስመኘው ለኦሮሞና ትግሬ አላለም፤ ስመኘው እንደሻማ ቀልጦ መስዋዕት የሆነው ለሁሉም ነው፡፡ ለዚህ ሰው የሚደረግ ሀዘን ከኢትዮጵያ ዳር ድንበርም ቢወጣ ሲያንሰው እንጂ አይበዛበትም፡፡
…. አያችሁልኝ ግን? የአንድና የሁለት ሰዎች እውነተኛ ማንነት ተገልጦ ሲታይ ስንትና ስንት የጥላቻና የግርዶሽ ዝግንትል እንደሚገፍ ተረዳችሁልኝ? ለካንስ አልተጣላንም! ለካንስ በመካከላችን ያሉ የቀን ጅቦች ለያዩን እንጂ እኛ ውስጥ ዕምቅ ፍቅር አለ! ለካንስ እንዋደዳለን፤ እንነፋፈቃለንም፡፡ ለካንስ አጋጣሚ እየጠበቅን እንጂ አልተለያየንም፡፡ ለካንስ አንዳችን ለአንዳችን እንደቤተሰባችን አባል ኖሯል የምንተያየው፡፡ ይህን ጊዜ ያሳየን እግዚአብሔር ይመስገን፡፡
እነዚህን የቀን ጅቦች ተባብረን ጥግ ማስያዝ አለብን፡፡ ለበርካታ አሠርት ዓመታት በየጭንቅላታችን ውስጥ ያሠረጉብንን የጥላቻና የቂም በቀል ቋጠሮ ጠራርገን ማውጣትና ወደቀደመው የጋራ ኑሮ መመለስ አለብን፡፡ ከሚጥበረብሩን እውነት መሰል ውሸቶች በአፋጣኝ ወጥተን የጋራ ቤታችንን በጋራ እንጠግን፡፡ በዋናነት ታዲያ እነዚህ የቀን ጅቦች ትግራይን የመጨረሻ ምሽግ አድርገው የግመል ሌባ እንዲሆኑ መፍቀድ የለብንም፡፡ መስዋዕትነት መክፈል አለብን፡፡ “ግመል ሰርቆ አጎንብሶ መሄድ” አይቻልም፡፡ ግመሉ ስለሚታይ የሌባው ማጎንበስ አለማጎንበስ ትርጉም የለውም፡፡ የቀን ጅቦቹም ኢንጂኔሩን በጠራራ ፀሐይ እንደገደሉት ሁሉ በቀጣይም ዒላማ ያደረጓቸውን ምርጥ ዜጎቻችንን – ትግራዋዩንም ጭምር – ቢገድሉ የግድያ ሰለባው ይታወቃልና – በሞኝነታቸው የማይታወቁ ይመስላቸው ይሆናል እንጂ – ገዳዩ ከአሁን በፊትም ሆነ ከአሁን በኋላ ምሥጢር ሆኖ የሚቀር አይደለም፡፡ አሁንና ከአሁን በኋላ ማንኛውም ታዋቂና የለውጥ ደጋፊ ዜጋ – በበሽታና በሌላ የግሉ ምክንያትም እንኳን ቢሞት – ከነዚህ የቀን ጅቦች ራስ የሚወርድ አይኖርም፡፡ የሁሉም ክፉ ነገሮች ምንጭ እነሱ ናቸው፡፡
ይልቁናስ በአፄ ቴዎድሮስ ዘመን አንዲት ወንድሟ የተገደለባት አረሆ ፡-
አንድ እግር በርበሬ መንቀል አቅቷችሁ፤
አቃጥሎ ለብልቦ አንድዶ ፈጃችሁ፡፡
ብላ ያቀነቀነችውን አስታውሰን ከጥቂት እግር በርበሬዎች የማይዘሉ የጋራ ጠላቶቻችንን በጋራ ትግል ማንበርከክ ይገባናል፡፡ የተናጠል ትግል ደግሞ አንድም በቀላሉ አይሳካም አለዚያም ረጂም ጊዜና ሁለንተናዊ ወጪን ሊወስድና በውጤቱም የተጎጂዎችን ቁጥር ሊጨምር የነፃነትንም ጊዜ ሊያስረዝም ይችላል፡፡ ሥር ለሰደደው ችግራችን ትልቁ መፍትሔ የእያንዳንዳችን ወደየኅሊናችን መመለስ ነው፡፡ ጤናማ ኅሊና በኖረን ማግሥት ሀገራችን ከተጣባት አጠቃላይ ችግር ትድናለች፡፡
ለገምቢ አስተያየትና አስተምህሮ – yinegal3@gmail.com
Average Rating