www.maledatimes.com ቤተ ክርስቲያን: የጅግጅጋውን የጭካኔና የዐመፅ ድርጊት አወገዘች! ለሟቾች ጸሎተ ፍትሐት እንዲደረግና መንግሥትም የነፍስ አድን ሥራ እንዲሠራ አሳሰበች - MALEDA TIMES
Loading...
You are here:  Home  >  Ethiopia  >  Current Article

ቤተ ክርስቲያን: የጅግጅጋውን የጭካኔና የዐመፅ ድርጊት አወገዘች! ለሟቾች ጸሎተ ፍትሐት እንዲደረግና መንግሥትም የነፍስ አድን ሥራ እንዲሠራ አሳሰበች

By   /   August 6, 2018  /   Comments Off on ቤተ ክርስቲያን: የጅግጅጋውን የጭካኔና የዐመፅ ድርጊት አወገዘች! ለሟቾች ጸሎተ ፍትሐት እንዲደረግና መንግሥትም የነፍስ አድን ሥራ እንዲሠራ አሳሰበች

    Print       Email
0 0
Read Time:2 Minute, 37 Second

IMG_20180806_160513

  • በጾመ ፍልሰታ ለማርያም ሱባኤ፣ በኹሉም ገዳማት እና አድባራት ጸሎተ ምሕላ ይደረግ፤
  • የሀገርና የወገን ፍቅርና ስሜት የተለየው፣ መወገዝ ያለበት የዐመፅና የጭካኔ ተግባር ነው፤
  • መጠፋፋቱ ወደ ከፋ ኹኔታ ሳይሸጋገር እንዲገታ ኹሉም ባለድርሻ መረባረብ ይጠበቅበታል፤
  • በረኀብ፣ በጽምና በእርዛት ለሚሠቃዩ ካህናትና ምእመናን መንግሥት ፈጥኖ ይድረስላቸው፤
  • የክልልና የዞን መስተዳድር አካላት፣ሕገ መንግሥታዊ ግዴታቸውን በብቃት ሊወጡ ይገባል፤
  • ቤተ ክርስቲያን፥በማረጋጋት፣ በማጽናናትና በማስታረቅ ሥራ የመፍትሔው አካል ትኾናለች፤

†††

pat exco jigjiga attack

ከኢትዮጰያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የተሰጠ መግለጫ

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን፣ በረዥም የታሪክ ጉዞዋ፣ ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያውያንን ኹሉ በእኩልነት ስታገለግል የኖረች እናት ቤተ ክርስቲያን ናት፤ አሁንም አገልግሎቷን ከመፈጸም የተገታችበት ጊዜ የለም፡፡

ሀገራችን ኢትዮጵያ፣ የብዙ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ሀገር ብትኾንም፣ ሕዝቦቿ በሃይማኖት፣ በጎሣና በቋንቋ ሳይለያዩ፣ ሀገርን የሚወር ነፃነትን የሚገፍ ጠላት ሲነሣ አንድነቱን አጠናክሮ ኹሉም ኢትዮጵያዊ ደሙን አፍስሶ አጥንቱን ከስክሶ የሀገሩን ነፃነት ሲያስከብር ኖሮአል፡፡

በተለይም የክርስትናና የእስልምና እምነት ተከታዮች፣ በወንድማማችነት ተሳስበው የኖሩት፣ አንዱ የሌላውን እምነትና ሥርዐት ሳይነካ ከኢትዮጵያዊነት ስሜት በመነጨ መተሳሰብና እውነተኛ ፍቅር ነው፡፡

ይኹን እንጅ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ፣ ሕግና መንግሥት ባለበት ሀገር፣ በአንዳንድ የክልልና የዞን መስተዳድሮች፥ በባሌ ጎባ፣ በጣና በለስ፣ በኦሮምያ ክልል አሁን ሰሞኑን ደግሞ በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልልና በአንዳንድ አካባቢዎች፣ በተለያየ ምክንያት በሚፈጠር የእርስ በርስ ግጭት መነሻነት፣ በአርኣያ እግዚአብሔር የተፈጠረ፣ በቅዱስ ረድኤቱ የከበረ፤ ሕያዊት፣ ነባቢት ነፍስ የተዋሐደችው፤ ፍጹም አእምሮና ዕውቀት የተሰጠው የሰው ነፍስ እየጠፋ እናያለን፤ ይልቁንም በሱማሌ ክልል 7 አብያተ ክርስቲያናት ተቃጥለዋል፤ ካህናት ተገድለዋል፤ ንብረት ተዘርፎአል፡፡

ዛሬ በመላ ሀገራችን ከመሀል ኢትዮጵያ እስከ ጠረፍ ዳርቻ ባሉት የመስተዳድር ዞኖች፥ ሰላም፣ ፍቅር፣ አንድነት፣ መከባበርና መቻቻል፤ እየተደማመጡና እየተባበሩ መሥራት በበለጠ እንዲዳብርና እንዲሰፍን የአመራር መርሕ በስፋትና በጥልቀት እየተሰጠ ባለበት በአሁኑ ወቅት፣ ለሚተላለፈው መመሪያና የሰላም መልእክት ትኩረት ባለመስጠት፣ የሀገርና የወገን ፍቅርና ስሜት የተለየው የጭካኔን ሥራ መሥራትከኢትዮጵያውያን ዜጎች የሚጠበቅ ተግባር ኾኖ አላገኘነውም፡፡

ይህ መወገዝ ያለበት የዐመፅ ተግባር፣ አብረው በኖሩ ወንድማማቾች መካከል የፈጠረው ግጭት፣ አለመግባባትና መቃቃር፤ በዚህም ሳቢያ እየተካሔደ ያለው መጠፋፋት፣ እየሰፋና እያደገ ወደ ሌላ የከፋ ኹኔታ ከመሸጋገሩ በፊት ከወዲሁ ታስቦበት ተፋጥኖ ይገታ ዘንድ የባለድርሻ አካላት ኹሉ መረባረብ ይጠበቅባቸዋል፡፡

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንም፣ የተፈጠረው ችግር ተወግዶ የተሟላ ሰላምና መረጋጋት እውን እስከሚኾን ድረስ፣ የመፍትሔው አካል በመኾን የሚቻላትን ኹሉ በመፈጸምና በማስፈጸም ያለባትን ሀገራዊ ግዴታና ሓላፊነት በተግባር ማረጋገጥ ይጠበቅባታል፡፡

IMG_20180806_160403

የሀገሪቱንና የቤተ ክርስቲያኒቱን ሰላምና መረጋጋት በሚጎዳ መንገድ የሚንቀሳቀሱ ግለሰቦች ሁሉ፣ፈጥነው እንዲስተካከሉ፣ ከእግዚአብሔር ሕግ አኳያ ምክርና ትምህርት በመለገስና በማስተላለፍ ዓላማዋና ዐይነተኛው ተግባርዋ እንደኾነም ማስገንዘብ ይኖርባታል፡፡

ስለዚህ ሰላምና መረጋጋት የሚመነጨው ከቤተሰብና ከኅብረተሰብ ስለኾነ፡-

  • ወላጆች ልጆቻቸውን እንዲመክሩ፣ እንዲገሥጹና እንዲያስተምሩ ያስፈልጋል፤

  • ኅብረተሰቡም፥ በዘር፣ በሃይማኖትና በጎሣ ሳይለያይ፣ በሀገራችን በአንዳንድ አካባቢ እየታየና እየተሰማ ካለው መጥፎ እንቅስቃሴ ራሱን እንዲገታና እንዲቆጣጠር፤

  • ካህናትና ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያንም፣ የመልካም ሥነ ምግባር መሠረት በኾነችው ሀገራችን ላይ ችግር በተከሠተበት አካባቢ እየተገኙ ትምህርተ ወንጌል እየሰጡ የማረጋጋት፣ የማጽናናትና የማስታረቅ ሥራ እንዲሠሩ፤

  • ይህን አላስፈላጊ ግጭት፣ እግዚአብሔር ከሀገራችንና ከሕዝባችን እንዲያርቅልን፣ ጾመ ፍልሰታ ለማርያምን ምክንያት በማድረግ በኹሉም ገዳማትና አድባራት ጸሎተ ምሕላ እንዲደረግ

  • በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል፣ በጅጅጋ፣ በጎዴና በሌሎችም ከተሞች በደረሰው አሠቃቂ ግድያና ዝርፊያ ምክንያት በየመጠለያው፥ በረኀብ፣ በጽምና በእርዛት ለሚሠቃዩ ካህናት ምእመናን፣ መንግሥት ፈጥኖ እንዲደርስላቸውና የነፍስ አድን ሥራ እንዲሠራበአጽንኦት እናሳስባለን፡፡

  • ለሞቱት ወገኖቻችንም፣ በመላ ገዳማትና አድባራት ጸሎተ ፍትሐት እንዲደረግ፤

  • በችግሩ ዙሪያ የሚገኙ የክልልና የዞን መስተዳድር አካላትም፣ የገላጋይ ያለህ የሚል ሮሮ እስከሚሰማ ሳይጠብቁ፣ በሕገ መንግሥቱ የተቀመጠውን ድንጋጌ በማክበርና በማስከበር፣ ከሕዝብና ከመንግሥት የተረከቡትን ሓላፊነት በብቃት እንዲወጡበቤተ ክርስቲያን ስም አደራ እያልን ይህን መልእክት እናስተላልፋለን፡፡

ኅልፈተ ሕይወት ያጋጠማቸውን ወገኖቻችንን፥ እግዚአብሔር በመንግሥቱ እንዲቀበልልን፤ ያዘኑትን እንዲያጽናናልን፤ የተጎዱትን በምሕረቱ እንዲጎበኝልን፤ ዘላቂ ሰላምም እንዲሰጠን እንጸልያለን፡፡

 

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

አባ ማትያስ ቀዳማዊ

ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ

ሊቀ ጳጳስ ዘአኵስም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት

ሐምሌ 30 ቀን 2010 ዓ.ም.

አዲስ አበባ

Happy
Happy
0 %
Sad
Sad
0 %
Excited
Excited
0 %
Sleepy
Sleepy
0 %
Angry
Angry
0 %
Surprise
Surprise
0 %
    Print       Email

Average Rating

5 Star
0%
4 Star
0%
3 Star
0%
2 Star
0%
1 Star
0%
<"Without the support of our readers, the Maleda Times website would not exist in its present form">

You might also like...

በሰሜን ሸዋ ዞን ኤፍራታ እና ግድም ወረዳ መከላከያ ከአማራው ማህበረሰብ እና ከፋኖ ጋር ጦርነት ገጥሟል

Read More →

This site is protected by wp-copyrightpro.com

Skip to toolbar