የአትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር
አዲስ አበባ
ክቡር ሆይ!
ትላንት፣ ግንቦት 28 ቀን 2010 ዓ.ም. የኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሜቴ በቁልፍ የአኮኖሚ ተግባር የተሰማሩና እስካሁን በመንግሥት ቁጥጥር ስር ያሉ አገልግሎት ሰጪና አምራች ድርጅቶች በከፊል ወይም ሙሉ በሙሉ ለግል ባለሀብቶች እንዲሸጡ መወሰኑን ተረድቻለሁ። በተለይም የኢትዮጵያ አየር መንገድና የባቡር አገልግሎት ለሽያጭ እንዲቀርቡ መወሰኑ ከፍተኛ ኀዘንና ድንጋጤ ፈጥሮብኛል።
ክቡር ጠቅላይ ሚኒሰትር፣
ከሁለት ወራት በፊት የኢሕአዴግ ሊቀመንበርና የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው ከተመረጡ በኋላ በሚያራምዱት የአንድነት፣ የፍቅር፣ የልማት፣ የዴሞክራሲና የሕግ የበላይነት ኢትዮጵያዊ ራእይ በአገራችን በኢትዮጵያ ለረጅም ዘመናት ታይቶ የማያውቅ የሰላም፣ የፍቅርና የተስፋ መንፈስ ቀስቅሰዋል። አንዳንዶቻችን ኢሕአዴግ እንደ ድርጅትና እንደ መንግሥት ባለፉት 27 ዓመታት በሕዝብና በአገር ላይ የፈጸመው በደል ሳያግደን ከጎንዎ ተሰልፈናል። ይሁን እንጂ፣ ይህ አሁን የተገለጠው የኢሕአዴግ ውሳኔ የአገርንና የሕዝብን ዘላቂ ጥቅም ከፍተኛ ጉዳት ላይ የሚጥል መሆኑን በአክብሮት ልገልጥልዎ እወዳለሁ።
የሕዝብ ንብረት የሆኑ አገልግሎት ሰጭና አምራች ድርጅቶችን ወደ ግል ንብረትነት ለማዛወር የተወሰነው የአገሪቱን ፈጣንና ተከታታይ እድገት ለማገዝ መሆኑ ተገልጧል። ይህ ምክንያት ለስኳር አምራች ድርጅቶችና ለኢትዮ ቴሌኮም ይሠራ ይሆናል። የኢትዮጵያ አየር መንገድን እና ባቡርን በሚመለከት ግን የሚያስከትለው ጥቅምን ሳይሆን ከፍተኛ ጉዳትን ነው።
በ1938 ዓ.ም. የተቋቋመው የኢትዮጵያ አየር መንገድ በአገልግሎቱ ብቃትና ጥራት በአፍሪካ ተወዳዳሪ የሌለው፣ በዓለም ዙሪያ ታዋቂነትን ያተረፈ ድርጅት። በዓለም ዙሪያ ያሉ ትላልቅ የግልና የመንግሥት አየር መንገዶች እየከሰሩ በሚዘጉበት ወቅት በአትራፊነት የዘለቀ ብሔራዊ ቅርስ ነው። በሙሉ ቀርቶ በከፈልም ቢሆን ለግል ባለንብረቶች የሚሸጥበት አንዳች አሳማኝ ምክንያት የለም። አላማው ይበልጥ እድገት ማስቻል ከሆነ የግል ባለሀብቶች ሌላ ተፎካካሪ አየር መንገድ አቋቁመው ገበያውን እንዲቀላቀሉ መምከር እንጂ፤ ይህንን የመሰለ ሁለት ትውልድ መሥዋዕት ከፍሎ ያበለጸገውን አትራፊ ስመ-ጥር ተቋም ለግል ባለሀብቶች መሸጥ ታሪካዊ ስህተት ይሆናል።
ባቡርን በሚመለከት የበርካታ አውሮፓ አገሮች ልምድ የሚያሳየው ባቡር ሙሉ ለሙሉ ወይም ከ80 በመቶ በላይ የአክስዮን ድርሻው በሕዝብ ንብረትነት የተያዘ ነው። ከነዚህ መሀል ሆላንድ፣ ስዊድን፣ ጀርመን፣ ፈረንሳይ፣ ጣልያን፣ ቤልጂግ የመሳሰሉት ይገኙበታል።
በአንጻሩ በ1985 ዓ.ም. በሥልጣን ላይ የነበረው የእንግሊዝ ወግ አጥባቂ መንግሥት፣ በፖለቲካ ምክንያት፣ የሕዝብ ንብረት የነበረውን የእንግሊዝ ባቡር ለግል ባለንብረቶች ከሸጠው በኋላ እስካሁን ራሱን መቻል አቅቶት በኪሳራ ላይ ይገኛል። በመሆኑም በየዓመቱ ከእንግሊዝ መንግሥት በቢልዮን ዶላር የሚቆጠር ድጎማ ለግል ባለንብረቶቹ ይሰጣል። የባቡር አገልግሎት ጥራት ከአውሮፓ አገሮች ጋር ሲወዳደር የእንግሊዝ ከተጠቀሱት አገሮች ሁሉ ዝቅተኛ ነው። ባቡር ለመሳፈር የእንግሊዝ ሕዝብ የሚከፍለው ዋጋ ግን፤ ከአውሮፓ አገሮች ጋር ሲወዳደር እስከ 40 በመቶ ከፍ ያለ ነው። በነዚህና ሌሎች ተያያዥ ምክንያቶች ተቃዋሚው የእንግሊዝ ሠራተኞች ፓርቲ ባቡርን መልሼ እወርስና የሕዝብ ንብረት አደርጋለሁ ሲል ለሕዝብ ቃል ገብቷል።
ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር፣
ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅምና ለዘላቂው ሕዝባዊ ጥቅም ሲባል፣ ጫናው ከየትም ይምጣ ከየት፣ እነዚህን የመሳሰሉ ብሔራዊ ተቋሞች ለሽያጭ ሊቀርቡ አይገባም።
አትዮጵያ ለዘላለም ትኑር!
አበራ የማነ አብ፣ ብሩሴል፣ ቤልጅግ ግንቦት ፳፱ ቀን ፳፻፲ ዓ.ም. (ጁን 6, 2018 እ.ኤ.አ.)
Average Rating