ጥናታዊ -ምክክር እንዲደረግ ይጠይቃል
የኢትዮጵያና የኤርትራ ድንበርን አስመልክቶ ከ16 ዓመታት በፊት በአልጀርስ የተፈጸመው ደባ በሁለት ዲክታተሮች መካከል የተደረሰ ስምምነት እንጂ፤ ሕዝቦቻችንን እንደማይወክል ከዚህ በፊት ደጋግመን ግልጽ አድርገናል። ይህ ሕዝቦቻችንን የማይወክል የ”አልጀርሱ ውል” እንዳለ አሁን በዶ/ር ዐቢይ የሚመራው መንግሥት ተግባራዊ ለማድረግ እንቅስቃሴ መጀመሩ ስንሰማ ከልብ አዝነናል። እንድንቃወምም ግድ ሆኖብናል።
ሥልጣን የተረከበው አዲሱ የኦሕዴድ ኃይል ሕወሓት/ኢሕአዴግ እስካሁን ድረስ የተጓዘበትን ፀረ-አገርና ፀረ-ሕዝብ መንገድ ቀልብሶ፣ ኢትዮጵያን ወደ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለማሸጋገር የጀመረውን ፈታኝ ትግል በጥሞና መከታተል ብቻ ሳይሆን ይበል – ግፉበትም በማለት ስናወድስ ሰንብተናል። በቅርቡ የመለስ ዜናዊ ሁለቱ ብትሮች “በክብር” ሰባብረው ማስወገዳቸውን ስናይም ዴሞክራሲያዊ ሂደቱ ያለአደናቃፊ ይበልጥ ይፋጠናል የሚል ተስፋ ማሳደራችን እውነት ነው። ሆኖም አሁን የ”አልጀርሱ ውል” አስመልክቶ የደረሱበትን ውሳኔ ስንመለከት ግን፤ የቆየውን ስሕተት እንደማረም ፈንታ፤ ያንኑ ስሕተት ደግሞ መቀስቀሱ ለምን አስፈለገ የሚል ጥያቄ እንድናነሳ አድርጎናል።
ከመጀመርያው የ”አልጀርሱ ውል” ሲጸነስ ከሕዝብ በስተጀርባ በድብቅ የተወጠነ ነበር። የኢትዮጵያ ሕዝብ አያውቀውም፣ እውቅናም ነፍጎታል። የአገር ድንበርን ያህል የሉዓላዊነት መግለጫ ወሰን፣ በዛው ላይ አያሌ ዜጎች መሥዋእት የሆኑበት የማንነት ሰንደቅ፤ እንደተራ የፖሊሲ ውሳኔ ታይቶ በአንድ ፓርቲ ወይም መንግሥታዊ አካል የሚወሰንና የሚከናወን ጉዳይ አይደለም። ትውልድ ደም የከፈለበትና ወደፊትም አስፈላጊ ሆኖ ከተገኘ እንደገና ሕዝቡ ደሙን የሚከፍልበት ቅርስ ስለሆነ ያለ ሕዝቡ ተሳትፎ ውሳኔ ላይ መድረስ የችግሩን ክብደት በውል አለማጤን ያመለክታል። በተጨማሪ በዚህ አሳሳቢ ጉዳይ ላይ ሰፊ ጥናት ያካሄዱና ጥልቅ እውቀት ያካበቱ አገር ያፈራቻቸው የታሪክ፣ የሕግ፣ የመልክዓ-ምድር፣ ወዘተ ባለሙያዎች መጠቀምም የግድ አስፈላጊ ሆኖ እያለ ከዚህ አሠራር መራቁ ሌላው ትልቁ ስሕተት ነው። ያለ እነዚህ ዐይነቶቹ አገራዊ ባለሙያዎች ተሳትፎ የተካሄደና ወደፊትም የሚካሄድ ድርድር ካለ ለአገራዊ ክስረት መዳረግ መሆኑ መገንዘብ አስፈላጊ ነው እንላለን።
የ”አልጀርሱ ውል” አሁን ከባድመ ጀምሮ እስከ ዓዲ-ኢሮብ፣ ከዛም አልፎ በባዳና በጸሮና አካባቢዎች ያለው የድንበር ጉዳይና የሕዝቦቹ መብት ጥያቄ ለአንባገነኖቹ የፖለቲካ ፍጆታ ሲባል ተድበስብሶ እንዲያልፍ በማቀዱ፤ ያኔ ከባድ ተቃውሞ እንደቀሰቀሰ ሁሉ አሁንም ከድሮው በባሰ መልኩ ተቃውሞ ቀስቅሷል። ይህ ከባድ ሕዝባዊ ተቃውሞ ጊዜ ሲረዝም ወደ ከፋ ትረምስ ሊያመራ ይችላል። ይህ አደገኛ ሁኔታ እንዳይከሰትና ሰላም እንዲሰፍን ከተፈለገ፤ ከላይ የተጠቀሰው ግልጽና ሙያዊ የችግሩን አፈታት መንገድ መከተል ፍጹም አስፈላጊ ነው።
ይህን ወሳኝ አመለካከት መሰረት በማድረግ ሥልጣን ላይ የሚገኘው የዶ/ር ዐቢይ መንግሥት የአገር ሉዓላዊነትን በሚመለከቱ ጉዳዮች ላይ የባለጉዳዩ ሕዝብ ድምፅ ማዳመጥ ብቻ ሳይሆን፤ በየረድፉ ማሳተፍም ግድ እንደሚል እያሳሰብን፣ የመጨረሻውም ውሳኔ በሕዝብና በዴሞክራሲያዊ መንገድ በተመረጠ ፓርላማ መወሰን አለበት እንላለን። በተጨማሪ ይህ አገራዊ ችግር ለዘለቄታው እልባት ያገኝ ዘንድ፤ አንድ በቅድሚያ መደረግ ያለበት ነገር አለ እንላለን። ይኸውም ባለሥልጣኑ መንግሥት ከላይ የጠቀስናቸውንና ሌሎች አግባብነት ያላቸው ባለሙያዎች ያካተተ ጥናታዊ -ምክክር(ሂሪንግ / Hearing) ሁኔታው ሳይከፋ በቶሎ እንዲካሄድ ነው።
ት.ዴ.ት. / TAND
እ.ኤ.አ. 10.06.2018
Average Rating