አብይ ለማ……አንዷለም እስክንድር! በደረጄ ደስታ
ስልኩን ሀሎ ካልኩ በኋላ “እስክንድር የት ነህ?” አልኩት።
“እዚህ ታክሲ እየጠበቅኩ ነኝ።” አለኝ።
የአዲስ አበባው የታክሲ ሰልፍ ብዛት በዋሽንግተን ዓይን አንድ አነስተኛ የተቃውሞ ሰልፍ ይወጣዋል። የሰው ብዛት ያስደነግጣል። እስክንድር ነጋ እዚያ መሃል ቆሞ ታክሲ ሲጠብቅ አሰብኩት። እኔ እምልህ ሰዎች አያስቸግሩህም? አልኩት ታዋቂ ሰውነቱን በማስታወስ። አይ እዚያ እናንተ ጋ ዋሽንግተን ነው እንጂኮ እዚህ ማንም አያውቀኝም። በዚያ ላይ ሰው ኑሮውን ስለሚያሳድድ ግድ የለውም” አለኝ። መቸም እስክንድር ከልቡ ትሁት ነው። አብረን በሆንበት ሰዓት ሁሉ እሱን እማያውቅ አብረን ፎቶ እንነሳ እማይል አላገኘሁም። ግን ምርጫ የለውም። አሁን የሱ ሀሳብ መኪና ሳይሆን ቢሮ ከፍቶ ጋዜጣና የድረ ገጽ ቴሌቪዥን መጀመር ነው። ቢራቸውን ሄጄ ጎበኘሁ። “ድል ለዲሞክራሲ!” እምትለዋን አስይዤ ያነሳሁት እዚያች አዲሷ ቢሯቸው ውስጥ ሆኖ ነው። ሁለት ወይም ሶስት እምትሆን ጠረጲዛ እምታስዘረጋ ባለ አንድ ክፍል ትንሽዬ ቢሮ አራት ኪሎ አካባቢ ከሚገኝ አንድ ፎቅ ላይ ተከራይተዋል። ከነ ተመስገን ደሳለኝ ጋር ሆነው ወደጋዜጠኝነት ሥራቸው ለመመለስ ያሰቡት እዚህ ሆነው እንደሆነ ነገረኝ። መቸም ጽናታቸው ይገርማል። ከዓይን ያውጣቸው እሚባሉት እነ አብይ እና ለማ መገርሣ እንዳሉት ሁሉ እዚህም በሌላው መንገድ ካይን ያውጣችሁ እሚባሉ ጽኑ ሰዎች አየሁ። መንገዳቸው ቢለይም አገራቸው ኢትዮጵያ ናት። ኢትዮጵያም ልጆችዋን ከያሉበት እየጠራች ነው። ጽናት በሚፈተንበት አዲስ አበባ ያልተሰበሰበ የለም። ጨዋታው ሲጀመር ሁሉም እየታየ ይመጣል።
አዲስ አበባ ስገባ ሟቹን ደራሲ ስብሐት ገ/እግዚአብሔርን አስቤው ነበር። ጎድሎ ጠበቀኝ። ኢህአዴግ አዲስ አበባ የገባ ሰሞን በጨዋታ መካከል “እኔ እምልህ ኢህዴግን እንዴት አየኸው ታዲያ?” ብዬው ነበር ። እንደዚህ አለኝ ጋሽ ስብሐት፣ “ …አየህ እስካሁን ቆንጆ መጥተዋል። አሁን አዲስ አበባ ገብተዋል። አዲስ አበባ ደግሞ ትልቅ ብሰበሳ አለ። ይህን ብሰብሳ አሸንፈው ከወጡ በቃ እውነትም አሸናፊዎች ናቸው…”
“ታዲያ ይህን ብሰበሳ እሚያሸንፉ ይመስልሃል?” አልኩት። “እሱን አብረን ነዋ እምናየው ! “ አለኝ ፍርጥም ብሎ።
ደራሲው “ብስበሳ” ሲል ሥልጣኑ ቁንጣኑ፣ ዝናው፣ ሙስናው ብልግናው አፈናው…ማለቱ መሆኑን ሳይዘረዝርልኝ ተግባብተናል። አሁንም መቸም የሄደውም ወይም የመጣው፣ ያው ኢህአዴግ ራሱ ቢሆንም፣ አዲስ መንግሥት መስሎ የቲም ለማው ኢህአዴግ ከአሮጌው ተገንጥሎ፣ ከህዝብ ተቀላቅሎ ይገኛል። ዘፋኙ “አዲስ ንጉሥ እንጂ ለውጥ መቼ መጣ?” ቢልም ነገሩስ ለለውጡማ ለውጥ አለ ያልመጣውስ አዲስ ንጉሥ ይሆናል ብሎ መጫወት ይቻላል። “አዲስ ለውጥ እንጂ አዲስ ንጉሥ መቼ መጣ?” ተብሎ አይዘፈን ነገር መከራ ነው። እና አዲሶቹ ኢህአዴጎች ይህን የአዲስ አበባ ብስበሳ አልፈው እናያቸው ይሆን?
ለነገሩ ለውጥ ስለመኖር አለመኖሩ እየተከራከሩ ገና ያልተደመሩ፣ “አሁንስ ቢሆን ምን ተይዞ ጉዞ ?” እያሉ የዴሞክራሲ ጥያቄና የነጻነት ትግልን እሚዘምሩ ዜጎች አሉ። ስም የሌላቸውን ቤት ይቁጠረውና ስም ካላቸው ውስጥ እነ እስክንድር ነጋን እነ አንዷለም አራጌን ማንሳት ይቻላል። ለአዲስነቱማ አዲስ ንጉሥ ነው ብለው እሚሟገቱ በመጣውና እያዩት ባሉት ለውጥ የተደሰቱም ሚሊዮኖች ናቸው። በየመኪናዎቻቸው በየታክሲውና በየቦታው የጠቅላይ ሚኒስትር አብይንና የአቶ ለማ መገርሣን ፎቶ ለጥፈው ከሚዞሩት አንስተው፣ ኢሳያስ አፈወርቂናን የመንግሥቱ ኃ/ማርያምን ምስሎች ሳይቀር የለጠፉ በርካቶች መሆናቸው ሲወራ የከረመ ነው። አገር በነጻነት ማውራት መጀመሩ፣ ሽኩሹክታው ቀርቶ አዳሜ ድምጹን እንደመጥምቁ ዮሐንስ ከፍ አድርጎ ያለስጋት መናገሩ ግን እሚታይ ነው። እዚህም እዚያም እሚውለበለበው የባንዲራ ዓይነት ራሱ ብዙ ነው። በዚሁ ከቀጠለ ሴቶቻችን የጸጉር ሻሾቻቸውን ሳይቀር እየፈቱ እንደ አንድ ባንዲራ ይመዝገብልን ሳይሉ እሚቀሩ አይመስለኝም።
ይህን ሁሉ እያስተዋልኩና እየተገረምኩ ከአራት ኪሎው ቱሪስት ሆቴል ብቻዬን ተቀምጫለሁ። እለቱ ኢንጂነር ስመኘው የተቀበሩበት እለት ሲሆን ኃይለኛ ዝናብ ጥሎ እስኪያባራ ትንሽ ትልቁ ከሆቴሉ በረንዳና ታዛ ተጠልሎ ነበር። መብራት ጠፍቶ ቤቱ ጨለምለም ብሏል። የሰውም አንደበት ከመብራቱ ጋር የሄደ ይመስል ዝምታ ሰፍኖ ሁሉም ከደጅ ከሚጥለው ዝናብ ላይ አይኑን ጥሎ ይታያል። ከታክሲ እየወረዱ ወይም ካሉበት እየመጡ መንገድ አቋርጠውና ሮጠው እየገቡ እሚጠለሉ ሰዎች ይታያሉ። በዚህ ጊዜ አንድ እማውቀው ሰው ዝናብ ውስጥ እየሮጠ ወደ ሆቴሉ ሲመጣ አየሁት። አንዷለም አራጌ ነበር። አያውቀኝም። ምናልባት የቀጠረው ሰው ኖሮት ይሆናል። ገና ወደ በረንዳው እንደዘለለ ከውስጥ ተስፈንጥሬ “አንዷለም! አንዷለም!” ብዬ ጠራሁት። ዞር ብሎ አይቶኝ ወደኔ መጣና ተጨባበጥን። ደረጀ እባላለሁ አልኩት። ትኩር ብሎ አይቶኝ እኔም እማውቅህ ይመስለኛል አለኝ። ትሁት ለመሆን ነው እንጂ አያውቀኝም። ግድ የለህም አታውቀኝም ብዬው እስከንድርን ቀጥሬው እየጠበቅኩ መሆኔን ነገርኩት። እንዴ እኔንም እዚሁ ቀጥሮኝ ነበር አልመጣም እንዴ አለኝ። እየመጣ መሆኑን ነገርኩት። በል እንግዲህ እስከዚያ እኛ እንድናወራ ፈልጎ ይሆናል ብሎኝ ቦታ ቀይረን ከቡና ቤቱ ጭር ወዳለው ምግብ ቤት እንድንሄድ መራኝ። እዚያ ሰዎች ያስቸግሩናል ብሎኝ ጥግ ይዘን ተቀመጥን። አንዷለም አራጌን በዚህ መንገድ አገኘዋለሁ ብዬ አልጠበቅኩም። የከሰለው ፊቱ ድኖ ተመልሷል። አሁን ደህና ሆነኻል አልኩት። ፈገግ ብሎ ዝም አለ። ዝምታው ያሰምጣል። ማንም ያላስተዋወቀን ሁለት ሰዎች ተገናኝተናል። እኔ ስለሱ ብዙ ማወቅ ብቻ ሳይሆን በጋዜጣም ስዘግብ ስጽፈው ኖሬያለሁ። ዛሬ ግን ለውጡ እሱን ከሥር ቤት አውጥቶ እኔን ወደ አገርቤት አምጥቶ አንድ ላይ “ደምሮ” አገናኝቶናል። “መደመር” በዚያ መልኩ ከሆነ ሰዎች ከየተሰደዱበት ከየታሰሩበትና እንደ ኤርትራ አገር ሆነው ተነጥለው ከተራራቁበት እየመጡ ተገናኝተዋል። ድምር በዚያ መልኩ ከሆነ አልተመደመርኩም ማለት እንዴት ይሆናል? መደመር የፖለቲካ አንድነትና የአመለካከት ውህደት ከሆነ ግን ሌላ ጉዳይ ነው። እነ አንዷለም እሱን ማለታቸው መሰለኝ።
ኋላ ላይ እነ እስክንድርና ናትናኤል መኮንን ተጨመሩና ቁጥራችን በርከት አለ። በፖለቲካው ያልተደመሩበትን ምክንያት እየዘረዘሩ ጥያቄያቸውንና ትግላቸውን በሰላማዊ መንገድ እንደሚገፉበት እየተናገሩ በሚያከራክረው ላይ ተከራከርን በሚያነጋግረው ተነጋገርንበት። ክእስክንድር ጋር እንኳ ያው በተደጋጋሚ ቀናት ተገናኝተን እንዲሁም ዋሽንግተንም ላይ አውርተንበት ስለነበር ነገሩ አዲስ አልሆነብኝም። ነጥቦችን ወደፊት እምናነሳው ሆኖ ለአሁን ግን የሀሳብ ልዩነት ተከብሮ እውነት በጩኸትና በሁከት ሳይሆን በክርክር ነጥሮ እየወጣ አገር የፍቅርን ጽዋ ቢጠጣ ማለፊያ ነው። ነገር ሁሉ – ይውደም ብያለሁ ይውደም! ይቅደም ብያለሁ ይቅደም! ሳይባል ጥያቄዎችና ክርክሮች በወጉ እየቀረቡ፣ እሚያሸንፈው እያሸነፈ፣ የተሸነፈው ወደ ሚቀጥለው ጥያቄ እያለፈ ቢሄድ መታደል ነበር። “እኔ እምፈልገው ከህሊናዬ ጋር አስተቃቅፎ እሚያስተኛኝ ነገር ብቻ ነው” ዓይነት አገላለጽ የተጠቀመው አንዷለም የሱ ጥያቄ እሚመለሰው እሱና ህሊናው ሲታረቁ መሆኑን ብቻ ገልጾልኛል። እስርና መከራን የተጋሩት እነዚህ ቆራጦች አገሪቱ ልትከለው ስለሚገባት የፖለቲካ መስመርም እሚጋሩት ሀሳብ ያላቸው ይመስለኛል።
ያው ተደጋግሞ እንደተገለጸው ከቡድን ይልቅ የግለሰብን ነጻነትን ስለሚያጎላው የሊብራል ዴሞክራሲ፣ ስለ ብሔራዊ እርቅ፣ የደቡብ አፍሪካውን ልምድና ሞዴልነትን ስለመከተል፣ ስለ ሽግግር መንግሥት አስፈላጊነት ስለዴሞክራሲ ሁሉን አቀፍ መፍትሄ ሰጭነት የመሳሰሉት ነጥቦቻቸው መከራክሪያዎቻቸው ናቸው። እነዚህ ነጥቦች ያስፈልጋሉ አያስፈልጉም እየተባሉ በደፈናው እሚነሱ እሚጣሉ ሳይሆኑ በቂ መድረክ ተሰጥቷቸው ሊያከራክሩ እሚችሉ ሊሆኑ ይችላሉ። በጠላትነትና በወዳጅነት ሳይፈርጁ እሚወሰደው ተወስዶላቸው እሚጣለውም ሊጣልላቸው እሚገቡም ሊሆኑ ይችላሉ። ትናንት ያሸበሩ ሀሳቦች ዛሬ ከተወደዱ፣ ሀሳቦችን ከጊዜ አሻግሮና ተሻግሮ ማየቱ ሳይጠቅም አይቀርም። በተወሳሰበ ሁኔታ ውስጥ ያሉትን አዲሶቹ የኢትዮጵያ መሪዎችም ያለባቸውን የውስጥና የውጭ ፈተናዎችንም የአገር ፈተናዎች አድርጎ አብሮ ማየቱም ከዜጎች እሚጠበቅ ዜግነት መሆኑንም ማስተዋሉ አይከፋም። ዋናው ነገር እርቅና መደመር ያለ መዋቅራዊ ለውጥ ዋጋ እንደማይኖረው ሁሉ መዋቅራዊ ለውጡንም ለማምጣት እርቅና መደመር የበኩላቸውን አስተዋጾ ያላቸው መሆኑን ማወቁም ጠቃሚ ይመስለኛል። እነስክንድር ለቆሙለት የግለሰብ ነጻነት ግን አለመቆም አልችልም። ምክንያቱም እኔ ቡድን ሳልሆን ግለሰብ ነኝ። እነ እስክንድርም ግለሰቦች ናቸው። ቡድን እያስፈራራ ግለሰብ እየፈራ እሚኖርባት አገር እንዳይኖረን በየግላችን መጣር ይኖርብናል። አንድ አብይ እሚባል ግለሰብ እንኳ ከኢህአዴግ በልጦ እየሰራ ያለውን ያየ በግለሰብ አይደራደርም። አብዩ ነገር ግለሰቡን አብይ እና የቡድኑን (ኢህአዴጉን) አብይ መለየቱ ላይ ይመስለኛል። ምርጫው እንኳ ቢያስቸግረን ሚዛኑን መሳት አይኖርብንም።
(ፎቶ ላይ እሚታዩት እስክንድር አንዷለም ናትናኤልና የአንዷለም ወንድም ናቸው)
Average Rating