www.maledatimes.com ይድረስ የቄሮንና የጃዋርን ፍቅር በቅጡ ላልያዛችሁት ወገኖቼ! ደረሰ ትንቢቱ (ከአዲስ አበባ) - MALEDA TIMES
Loading...
You are here:  Home  >  Addis Admas  >  Current Article

ይድረስ የቄሮንና የጃዋርን ፍቅር በቅጡ ላልያዛችሁት ወገኖቼ! ደረሰ ትንቢቱ (ከአዲስ አበባ)

By   /   August 12, 2018  /   Comments Off on ይድረስ የቄሮንና የጃዋርን ፍቅር በቅጡ ላልያዛችሁት ወገኖቼ! ደረሰ ትንቢቱ (ከአዲስ አበባ)

    Print       Email
0 0
Read Time:8 Minute, 12 Second

እውነት ነው – ፍቅር ዕውር ነው፡፡ በፍቅር የታወረ ሰው ወይም ፍጡር በፍቅር ካሳወረው አካል ሌላ አያውቅም፤ ሊያውቅም አይችልም፡፡ በአማርኛ ፍቅርን ለመግለጽ የማስታውሰው ሌላ ቃል “መውደድ” ነው – በዚህ ላይ የምጨምረው ብዙም የለም፤ ስለጥላቻና ነገር ቢሆን ብዙ ቃል በታወሰኝ – ያለን ብቸኛ አንጡራ ሀብት ቂም በቀልና ጥላቻ እንዲሁም መሰዳደብ ነውና፤ ስለፍቅርና ውዴታ እናንተም ቃል ፈልጉ –  ብዙም አታገኙም፤ ስንገርም! በእንግሊዝኛ ግን ብዙ አሉ፡፡ ለምሣሌ – love, agape, infatuation, affection, passion, ….ሌሎችም ይኖራሉ፤ አሉም፡፡

ስለፍቅር ፍልስፍና ውስጥ አልገባም፡፡ እኔ አሁን የማወራው  በእንግሊዝኛው infatuation ስለሚባለውና በአማርኛ “የወረት ፍቅር” በሚል ልንገልጸው ስለምንችለው የሆይ ሆይታ ፍቅር ነው፡፡ ይህ ዓይነቱ ፍቅር መነሻው ደምባራ ስሜት እንጂ ተጨባጭ ምክንያት አይደለም፡፡ በዘር መቆላለፍ ወይም በትውልድ ሐረግ ወይም በዝምድና ወይም በጥቅም በተሳሰረ የወል ዓላማ መደጋገፍ ይመሠረትና እስከመጨረሻው የጥፋት ጥግ ድረስ አብሮ ሊያስጉዝ የሚችል የአመክንዮ ሳይሆን የግለት ቁርኝት ነው – የወረት ፍቅር፡፡ Calf’s loveም ይሉታል ፈረንጆቹ፡፡ እውነትም እናቷንና ጨሌ ሳታገኝ ውላ እንደተፈታች ጥጃ በባዶ ሜዳ የሚያስፈነጭ ስሜት ወለድ ፍቅር! ይህ ስሜታዊ ፍቅር የሚመለከትሽን ሁሉ እስከዶቃ ማሰሪያሽ እነግርሻለሁና ወረድ ብለሽ ጠብቂኝ፡-

በሚሌኒየም የተካሄደውን የልዑለ እምልዑላን ኦቦ ፊልድ ማርሻል  በፊት ድብቅ አሁን ግልጽ የኦሮሚያ ሪፓፕሊክ ፕሬዝደንት የጃዋር መሀመድን እጅግ የሚያስደምም መስተንግዶ አየሁት፡፡ የወሬየ መነሻ ቅናትም ሆነ ምቀኝነት አይደለም – በጭራሽ፡፡ ከሀገር ኅልውናና አነስ ሲልም ከፕሮቶኮል ጋር ይያያዛል፡፡ ጃዋር መሀመድ በስደት “አንተ ማነህ?” ተብሎ የማይጠየቅ ተራ ስደተኛ ያልነበረውን ያህል እዚህች ሊያርዷት ቢላዎ ሲስሉላት በምትስቅ ሀገር አቶ ለማን ጨምሮ ከፍተኛ የ“ፌዴራል”ና የክልል ባለሥልጣናት እየተሽቆጠቆጡ – ሊያውም ብዙ አስደግድጎ እጅግም ዘግይቶ ሲገባና ታዳሚዎች በታላቅ ደስታ ምድርን ቃጤ ሲያደርጉ ሳይ የሀገራችን ትንሣኤ ኩልል ብሎ ታየኝ – ከዚያማ የባንዲራው ነገር፣ የጮቤ ረገጣው ነገር፣ የዳንኪራው ነገር አይነሣ፡፡ … በአዳዲስ ባንዲራዎች አዳራሹ ደምቆ ሲታይ “አቶ መለስ የዘራው አዝመራ እንዴቱን ያህል እንደጎመራ ከመቃብሩ ቀና ብሎ ቢመለከት ምንኛ በደስታ ይፈነጥዝ!” ያስብላል፡፡ ለማንኛውም ጃዋር መሀመድ እንኳን ደስ ያለው – ከአሸባሪነት የወጣበት ሰነድ የተፈረመበት ቀለም ገና ከመድረቁ የአንዲት ገናና ሀገርን ሰንደቅ ዓላማ ባስለወጠ ሁኔታ በዚህ መልክ “በሀገሩ” ያሻውን መሥራቱ ታሪካዊ ክስተት ነው – ወያኔ ጥቁር ውሻ ይውለድ! “ለዚህ ላበቃው” ቄሮ እንኳንስ በባዶ እግር ሄዶ ለሐውልት የመሠረት ድንጋይ ማኖር ይቅርና በጭንቅላቱም ቢሄድ ሲያንሰው ነው፡፡

በነገራችን ላይ ይሄ ቄሮ ቄሮ የምትሉት ነገር ግራ እያጋባኝ መጥቶ አለ፡፡ የቄሮን ድርሻ በደምብ አውቃለሁ፡፡ ግሩም ሥራ ሠርተዋል – የኦሮሞ ወጣቶች፡፡ ነገር ግን እጅግ እየተጋነነ መጣና ድንበሩን ጣሰ፡፡ አንድ ነገር ደግሞ ድንበርን ሲጥስ የሚያስከትለው ጣጣ መኖሩ ሃቅ ነው – በቅጡ ያልተያዘ ድል ያነበርራል፤ አላግባብም ያሰክራል – በስካር ደግሞ መጃጃል አለ፡፡ የትዕቢትና ትምክህት መከሰት የመጀመሪያዎቹ በድል ስካር የመነብረር አሉታዊ ውጤቶች  ናቸው፡፡ እነዚህ ነገሮች ደግሞ መሬትን እስክንጠየፍ ድረስ በኩራት አየር ላይ እንድንንሳፈፍና ሌላውን በዐይናችን ቂጥ እንድናይ ያደርጉናል፡፡ በዚህ ሂደት የመጓዛችን ጀብድ የሌሎች ሰዎችን ትንሽም ይሁን ትልቅ አስተዋፅዖና መስዋዕትነት አሳንሰን፣ የኛን ደግሞ ምትክ የሌለው ያህል አግዝፈን እንድናይ ያስገድደናል – በኢትዮጵያ የተፈጠረውም ይሄው ነው፡፡ “በላፕቶፕ መንግሥት ገለበጥኩ” የሚለን ጉደኛው ዶንኪሾትም ከዚህ በመነጨ ልዩ የድመት ትዕቢት ተገፋፍቶ ነው፡፡ በላፕቶፕ ያን ያህል ገድል መሥራት ስለመቻሉ አላውቅም ነበር፡፡ እንግዲያውስ የኮ/ል ደመቀ ትግል፣ የጎንደርና ጎጃም ትግል፣ የቆፍጣናዎቹ የጁዬዎችና የቃሉ የደሴ ትግል፣ የማጀቴና የወልቃይቶች ትግል፣ የራያና የሌላውም ሁሉ ትግልና መስዋዕትነት ዋጋቢስ ነበር ማለት ነው – “በጨው ደንደስ በርበሬ ተወደስ” ማለት አሁን ነው ፡፡ የሆኖ ሆኖ እውነቱ ወደፊት ሲወጣ ሁሉም ማፈሩ አይቀርም፡፡ ግን ግን ፍቅርን በልክና በገደብ ማድረጉ ወደማይወጡት የስህተት አዘቅት ከመግባት ያድናል – ለነገሩ ዋናው ድሉ እንጂ የድል ሽሚያ የትም አያደርስም – ደግሞስ ምኑ ተይዞ? ገና እኮ ነው፡፡ በባዶ ሜዳ ይህን ያህል እርስ በርስ መንቆለጳጰስ አስፈላጊ አይደለም፡፡ አሁንም ልድገመው – የቄሮ ድርሻ ትልቅ ነበር – ሀገርን በአንድ ኦነጋዊ አስተሳሰብ እስከመዳመጥ ሊያደርስ ግን አይችልም፡፡ እናም እየተስተዋለ ቢኬድ ቢያንስ የዚችን ደብዳቤ ልደት ማዘግየት ይቻል ነበር፡፡ለነገሩ ሁን ያለው አይቀርምና እንዲህ የምብከነከነው በከንቱ ነው፡፡

… ዝኮነ ኮይኑ መናገር ወደምፈልገው በቶሎ ላምራና ያን ተገላግዬ ወደ ንዴቴ ልመለስ፡፡

በርካታ ትንቢቶችን አውቃለሁ – ማለቴ ሰምቻለሁ – ይህ “ትንቢትን ማወቅ” ደግሞ የወፈፌዎች አንዱ መታወቂያቸው መሆኑን በእግረ መንገድ ማስታወስ እፈልጋለሁ፡፡ ብዙዎቹ ተፈጽመዋል፡፡ ጥቂቶችና መሠረታዊ የሚባሉት ይቀራሉ፡፡ ከሚቀሩት ውስጥ መረረንም ጎመዘዘንም ኢትዮጵያ ከነሙሉ ክብሯ ወደ ዝነኛ የታሪክ ሥፍራዋ በቅርብ የመመለሷ ዜና ነው፡፡ ይህን መጠራጠር ቶማስን መሆን ነው፡፡ ክርስቶስ ለቶማስ በጦር የተወጋ ቁስሉን በጣቱ እንዲዳብስና ከሞት መነሳቱን እንዲያምን ለመጠራጠሩ ዋጋ እንዲሆንም የነካበት ጣቱ እንዲጎነዲሽ አድርጓል፡፡ ቶማስ ክርስቶስ ሲነሳ አላየምና መነሳቱን ማመን አቅቶት ነበር፡፡ እኔን በመጠራጠሩ የሚጎዳ ሰው እንደማይኖር የምገልጸው ግን በታላቅ ትህትና ነው፡፡

በገደምዳሜ የምለውን አትጠራጠሩ እያልኩ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ትነሣለች፡፡ እንደሞተች የቀረችበት አንድም ዘመን የለም፡፡ በተደጋጋሚ የሚገድሏት እንዳሉ የሚያነሷትም አሉ – ከፈጣሪ ረድኤት ጋር፡፡

የሰሞኑ ግርግር የትንሣዔዋ ብሥራት መዳረሻ መስሎኝ ተጃጅዬ ሰውንም አጃጅዬ እንደነበር ልናዘዝ፡፡ ግን ይህ የሰሞኑ ህንፍሽፍሽ ለመጨረሻው ኢትዮጵያዊ አርማጌዴዖን የሚያመቻች የመሠሪዎች የጨረባ ተዝካር መሆን አለበት፡፡ በነፈሰው የምትነፍሱና  የድርጅት አፈ ቀላጤ የሆናችሁ የሚዲያ አውታሮች ይህንን ጽሑፍ እንደማታወጡት ጠንቅቄ አውቃለሁ፡፡ እናንተን እንዲጥም ብዬ ግን እውነትን መሸፋፈን አልፈለግም፡፡ ከተለያዩ አቅጣጫዎች ያቀራሰምኩትን ሀገራዊ እውነት እናገራለሁ፡፡ የነገዎቹ የዴሞክራሲ ጠበቃዎች የዛሬዎቹ አፋኞች ደግሞ የሚጥማችሁን ሙዚቃ ብቻ እየመረጣችሁ ማዳመጣችሁን ቀጥሉ፡፡ በያለንበት ሰላሙን ያብዛልን፡፡

“ለሦስት ወር ግፋ ካለም ለሦስት ዓመት ኢትዮጵያን የእስላም ንጉሥ ይገዛታል፡፡” መባሉን ሰምቻለሁ፡፡ ያ ንጉሥ ጠ/ሚ ዶ/ር ዐቢይ አህመድ ይመስለኛል፡፡ ይህን ትንቢት እርሱም አያውቀው ይሆናል፡፡ ወይም ያውቀውም ይሆናል፡፡ የስሙ መስተካከል ከዚህ ትንቢት ጋር ይገናኝ አይገናኝ አላውቅም፡፡  ግን ይህን ትንቢት እጠብቀው ነበርና አሁን ፍጻሜው ሳይሆን አይቀርም ብዬ እገምታለሁ፡፡  ሁኔታዎች ሁሉ እያቀጣጩ ያሉት በዚያ መስመር ነውና፡፡

ከዚህ ዘመን ጋር – ከእስላሙ ንጉሥ ፍጻሜ ጋር – የሚያያዝ አንድ ነገር አለ፡፡ ያም ትልቅ ዕልቂት መኖሩ ነው፡፡ በዚያ ዕልቂት ኢትዮጵያ ውስጥ የሰው ዘር የተባለ አይተርፍም፡፡ በሩቅ የሚታይ ልብልብ ግንድ “ሰው ሳይሆን አይቀርም” ተብሎ በሰው ናፍቆት ወደዚያ ግንድ የሚሮጥበት ዘመን ይከሰታል፡፡ ከዚያ በኋላ ግን “የአንዲት ላም ወተትና የአንድ ማሣ ሰብል ላገር ይበቃል፡፡” ረድዔትና በረከትም በሀገር ይናኛል፡፡ ክፋትና ምቀኝነት ይሰደዳሉ፡፡ የሰዎች ስደት ወደ ኢትዮጵያ ይሆናል፡፡ ይህ ዘመን ሊያልፍ ሲል ሁሉም በየቤቱ ሠይፍ ይስላል፤ ጥላቻና ያን የሚከተል መገዳደል የዘመኑ ፋሽን ይሆናል፡፡ ጥላቻ ይነግሣል፤ ፍቅር ይተናል፤ እናትና ልጅ፣ ወንድምና እህት ይናቆራሉ፤ ገንዘብ ይመለካል፡፡ … ፐ! ትንቢት! የሚታየውን መናገር አሁን ትንቢት ነው?

ይህ የዶ/ር ዐቢይ ዘመን ያን ክፉ ትንቢት የሚያስቀር የመለኮት ጣልቃ ገብነት የታየበት መስሎኝ ነበር፡፡ ግን አይደለም ወይም ቢያንስ አይመስለኝም፡፡ “ሰይጣን ለብልኃቱ ከመጽሐፍ ቅዱስ ይጠቅሳል” ይባላል፡፡ እናም የዚህ ልጅ አፍ አስከፋች ማራኪ ንግግር በቁሙ ሲመለከቱት እጅግ ግሩም ነው፡፡ ለአንድ ኖቤል ቀርቶ ለ30ም ቢታጭ ከድጋፍ በስተቀር ተቃውሞ የለኝም፡፡ ይሁንና ጉድና ጅራት ከወደኋላ እንደመሆኑ የቅርብ ጊዜ ሀገራዊ ሁኔታዎች እጅግ አደገኛና የጠ/ሚኒስትሩና ቡድኑ አካሄድ ዋጮን እንደመገልበጥ ሆኖ አይቼዋለሁ፡፡ ለደኅንነቴ ዋስትና የሚሰጠኝ ቢኖር በአደባባይ ብከራከር ደስ ባለኝ፡፡ ቢጨንቀኝ ወያኔዎች ጋር ለመነጋገርና አንዳች ሀገራዊ አስተዋፅዖ ላበረክት አሰብኩና ሥራቸው ፊቴ ላይ እየተደቀነ አንገሸገሸኝ፡፡ ያም እሳት፣ ይህም ዕጥፍ ድርብ እሳት፡፡

ሀገራችን በሁለት እኩል አደገኛና እኩል ሰይጣናዊ አማራጮች መካከል ትገኛለች፡፡ አሁን ብዙው ሰው በሞቃት ንግግሮች ስለሰከረ እኔን ዕብድ የሚለው ወገን እንደሚበዛ በሚገባ አውቃለሁ፡፡ ለዚህ ነው ስጀምር ፍቅር ዕውር መሆኑን የተናገርኩት፡፡ እንደኔ ደግሞ ይህን አዲስ ለውጥ ያፈቀረ ሰው አልነበረም፡፡ እውነቱ ግን ያ አይደለም፡፡ ዐይንህ ላይ የተጋረደውን የስሜት ሞራ ግፈፍና ተመልከት!

በነገራችን ላይ ዐቢይን አሁንምና ወደፊትም አደንቃለሁ፤ ይህን ዓይነት ግለሰብ ለማግኘት ብዙ ትውልዶችን መጠበቅ እንደሚያስፈልግም እረዳለሁ፡፡ እኔ የምለው ግን ከእርሱም በላይ ስለሆነ ልዕለ-ሰብዓዊ ዕቅድና አፈጻጸሙ ነው፡፡ አትተርቡኝ፡፡ ነቢይም ሆነ ዐዋቂ አይደለሁም፡፡ ኢሕአፓን አስታውሱ፤ የምትመለምለው እንደኔ ያለውን ጀንፈልና እንደነዱሽ ሳይሆን ሲቻል ብልኁን ሳይቻል ብልጡን ነበር፡፡አንድ ኃይል – አወንታዊም ይሁን አሉታዊ – አካላዊም ይሁን መንፈሣዊ – ለሆነ ግዳጅ ከሰው ሰው ሲመርጥ የራሱ መለኪያ አለው- ከጊዜውና ከሁኔታዎች ጋር የሚሄድ ሰው ያዘጋጃል እንጅ በቀላሉ የሚንበረከክ ሰው አይመርጥም፡፡ መሬት ለነከሰ ጥልቅ ምሥጢር ላለው ዓላማ የሚመረጡ ሰዎች በብዙ መንገድ የማያሳሙ እንዲሆኑ አስፈላጊ ነው –  ለምሣሌ 33 ዲግሪ የኢሉሚናቲ ከፍተኛ ደረጃ ለመድረስ ብዙ መፍጋት አለብህ፤ እንደቁጩው የኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታ ሳይሆን ባደጉ አገሮች ጄኔራል ለመድረስ ብዙ ውጣ ውረድ እንዳለው ማለት ነው፡፡ ቀጥሎ የሚሆነውን እኮ ራሱ ዐቢይም “እኔ የምረዳውን” ያህል እንኳን ላያውቅ ይችላል፡፡ ዓለም በራሷ ከባድ ምሥጢር ናት፡፡… ዶ/ር ዐቢን ግን አሁንም ወደፊትም ከልቤ በጣም እንደምወደው መግለጽ እፈልጋለሁ፡፡ ችግሩ የችግሮቾቻችን ጥልቀት ከጣፋጭ ንግግርና ከአስለምላሚ ትክለ-ሰውነታዊ መስህብ የገዘፉ በመሆናቸው አህያን ተከልለው ለሚመጡ ጅቦች የመጋለጣችን ዕጣ የማይቀርልን መሆኑ ነው፤ ችግሩ ኢትዮጵያን ከሚጠሉ ጅቦች ኢትዮጵያን ከነጭርሱ ወደማያውቁ ድቦች የመሸጋገሪያ ምዕራፍ ላይ መገኘታችን ነው፤ ትልቁ ችግር በሲዖል ውስጥ እንኳን ጥቂት ዕረፍት ሲኖር እኛ ግን ካለምንም ዕረፍትና እፎይታ (የሦስት ወር የማገገሚያ ጊዜ እንደረፍት ካልተቆጠረ በስተቀር) ከአንዱ የስቃይ ዐውድ ወደ ሌላው መተላለፋችን ነው፡፡ የምለው ሁሉ ውሸት ቢሆን በወደድኩ – ግን አይሆንም፡፡ በምኞት የቀረ የትንቢት ፍጻሜ የለም – ምናልባት የአደጋውን መጠን መቀነስና ጊዜውን ማዛወር ይቻል እንደሆነ እንጂ፡፡ እኛም በርትተን እንጸልይ – ማን ያውቃል – አንድዬ ሊያለዝብልን ይችላል፡፡

የሚያወላዳና ለሀገር ቀርቶ ለአንድ መንደር ሥጋት ሊፈጥር የማይችል ጦር የሌለውን – በእስካሁኑ ሁኔታ ማለቴ ነው – ዳውድ ኢብሣን ለመሸምገልና ከኦነግ ጋር ለመደራደር  የአንዲት ትልቅ ሀገር የውጭ ጉዳይ ሚኒስትርና የአንድ ትልቅ ክልል ፕሬዝደንት አሥመራ ድረስ መሄዳቸው ምን ማለት ነው? ምን እየተጠነሰሰልን ይሆን? ጦር ሠራዊቱ የት እንዳለ እንኳን የማይታወቅ በጥቂት ግለሰቦች የወሬ ቱማታ ብቻ ሕይወት ያለው የሚመስልን የግማሽ ምዕተ ዓመት ዕድሜ ባዶ ድርጅት ነፍስ እንዲዘራና ባንዲራው ወይም ዓርማው  የሀገራችንን ባንዲራ ረጋግጦ መናገሻ ከተማ ውስጥ ከፍ ብሎ እንዲውለበለብ እየተደረገ ያለው በምን ምክንያት ይሆን? እንደዚያ ከሆነ ኢሕአፓንም ጦሩን አስፈትቶ ወደ ሀገር ለማምጣት ለምን አይሞክሩም? ማዕከላዊ መንግሥትን በኦነግ የመሙላቱ ሂደትስ ምን አመላካች ነው? አለ ነገር! ወያኔዎች ግን ጥቁር ውሻ ውለዱ! በናንተ ቤት ኢትዮጵያን ገድላችኋል፡፡ ኢትዮጵያን የጎዳችሁ መስሏችሁ ወደ አራት ሚሊዮን የሚገመቱ ተጋሩን ነው ልታሳርዱ የተዘጋጃችሁት – በመላዋ ኢትዮጵያ፡፡ አማራ ብቻ የሚታረድ መሰላችሁ አይደል? አማራማ ወያኔን ምሥጋን ይንሳውና መኮላሸቱንም፣ መዋረዱንም፣ መታሰሩንም ፣ መገደሉንም፣ መታረዱንም፣ መሰደዱንም፣ … ለምዶታል፡፡ እነዚህ ነገሮች ከእንግዲህ እንደብርቅ እየታዩ ኋላ ላይ ግን የሚለመዱት በወያኔ መንደር ውስጥ ነው፡፡ ያልዘሩት አይበቅልም፤ ያልተከሉት አይጠድቅም፡፡ ወዩዬ ለአማራ የዘራሽው የመከራ እንክርዳድ ላንቺም መጥቷልና ዝግጁ ሆነሽ ጠብቂ፡፡ አዎ፣ እያንዳንድሽ የወያኔ አባል ባለፉት 27 ዓመታት በተለይ በአማራው ላይ የሠራሽው ተነግሮ የማያልቅና ሊነገርም የሚዘገንን ግፍና በደል በራስሽ ወይ በልጅሽ አሊያም በዘርሽ ትከፍያታለሽ! – ያሳዝናል፡፡ በበኩሌ በዚህም ክፉኛ አዝናሁ፡፡ ስቃዩ በማንም ይድረስ በማን በሰው ስቃይ የመደሰት ባሕርይ የለኝም፡፡

በንድፈ ሃሳብ ደረጃም ቢሆን – በሃሳብ ማለቴ ነው – አማራንና ትግሬን ላስታርቅ እልና ደግሞ … ሆ… እንኳን እኔ ደካማው ፍጡር እግዚአብሔር ራሱም የሚችል ስለማይመስለኝ ሃሳቡን ወዲያው እተወዋለሁ፡፡ እንዴ – ጭካኔያቸው ጭካኔ ነው እንዴ? ይመችህ ጃዋር! በአክራሪ ጎሠኛነትህ ላይ አክራሪ ሙስሊምነት ተደርቦበት ጉድ ልናይ ነው ከእንግዲህ፡፡ ለኔ ዓይነቱማ አንድ ሣይሆን ሃምሣ ሜንጫ ነው የምታሰልፍልኝ፡፡ ገና ከአሁኑ ከሰባት በላይ አብያተ ክርስቲያን ተቃጥለዋል፤ በርካታ ካህናት ጋይተዋል፤ ብዙ ምዕመናን ተገድለዋል፤ … በዚህ አካሄዳችን ከቀጠልን በጥቂት ወራት ውስጥ ከምድረ ገፅ የመጥፋት መጥፎ ዕድል አለን፡፡ የቄራ ዐውድማው ተለቅልቋል፤ አራጆቹም ከያቅጣጫው በመጠራራት እየተሰባሰቡ ነው፡፡ ጠላታቸውንም ለይተዋል፡፡ እስኪጠናከሩና ገዢ መሬት እስኪይዙ ጥሩ የንግግር ችሎታ ያለውን ሰው መድበዋል፡፡ በኋላ ግን ይፈነግሉትና የመጨረሻውን ዙር የዕልቂት እምቢልታ ይነፋሉ፤ አዲዮስ! ወያኔዎች ጥቁር ውሻ ውለዱ!! ጥሩ ሀገር የመሥራት ዕድል እያላችሁ ጥሩ ኦሽትዊዝ ገነባችሁልን፡፡ ደግነቱ ከሞት የሚቀር የለም፡፡ (በሉ – በዚህ አጋጣሚ ፊንፊኔ ላይ አንዲት ኩሽና ቢጤ ስላለችኝ የሚገዛኝ ሰው ፈልጉልኝና እኔም በተራየ ጂጂጋ ወደሸገር ከመምጣቷ በፊት እግሬ ባመራኝ ልፈትለክ…፡፡) (ረስቼ – ያ ፀጋየ አራርሳ የሚሉት ገልቱ የወያኔና ኦነግ የፕሮፓጋንዳ ሰለባ በእንግሊዝኛ ተናገረ አሉ? እሰይ! እንኳን በንግሊዝ አፍ ተናገረ – ማንን ደስ ይበለው? ማንንስ ይክፋው? በማንነት ጥያቄ እየቃተቱ የማንም ሳይሆኑ እንደማርጀት ያለ የከፋ ችግር የለም፡፡ ኦሮሚፋን ግን በቶሎ ይማር፡፡)

ከፍ ሲል እንደጠቀስኩት ወያኔ ባሏን የጎዳች መስሏት ሰውነቷን በጋሬጣ  እንደወጋችው ሴት ናት፡፡ ወያኔ ኢትዮጵያን ያቃለለች መስሏት፣ ወያኔ “ሀገሪቱ” እያለ ስሟን እንኳን ለመጥራት ተጠይፎ ለማትወጣው የችግር አረንቋ አጋልጧት የሄደውን የቀድሞ ጠ/ሚኒስትር ሌጋሲ ለማስፈጸም ስትል…. ኤዲያ ምን አስለፈ…፡፡

 

Happy
Happy
0 %
Sad
Sad
0 %
Excited
Excited
0 %
Sleepy
Sleepy
0 %
Angry
Angry
0 %
Surprise
Surprise
0 %
    Print       Email

Average Rating

5 Star
0%
4 Star
0%
3 Star
0%
2 Star
0%
1 Star
0%
<"Without the support of our readers, the Maleda Times website would not exist in its present form">

You might also like...

Ethiopia’s Media Under Siege Amid Escalating Conflict in Amhara

Read More →

This site is protected by wp-copyrightpro.com

Skip to toolbar