[ቴዲ አትላንታ]
ጆሮ አይሰማው የለ
“ኦሮሚያን መገንጠል ከፈለግን፣ በሁለት ሳምንት መገንጠል እንችላለን፣ ማንም አያቆመንም” አቶ ጃዋር መሃመድ
“አገር የዛፍ ቅጠል አይደለም፣ ማንም ስለፈለገ ተቀንጥሶ አይወድቅም” ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ።
___________
ክላይ የተጠቀሰውን “የመገንጠል” አባባል ልብ በሉት፣ ራስን ከመቆለልና ለራስ ተራራ የሚያህል ግምት ከመስጠት የመጣ ያለበሰለ አባባል እንጂ ፣ ሌላ ምን ሊሆን ይችላል?
የዶክተር ዐቢይ ፣ ትልቁ ፈተና ከዚያው ካጠገቡ እንጂ ከሩቅ አይመጣም ብዬ ተንብያለሁ። አቶ ጃዋር መሃመድ እንደመጣለት የሚናገራቸው ነገሮች አንድምታቸው ለኔ ግልጽ አይደለም።
ለምሳሌ፦
– አቶ ጀዋር መሐመድ ባህር ዳር የሄደ ጊዜ እዚያ ያገኛቸውን ትላልቅ ሰዎች “ኦሮሚያን መጥታችሁ እንድትጎበኙ ጥሪ አቀርባለሁ” ሲል መጋበዙን በትዊተር መልክቱ ገልጿል። አቶ ጀዋር የሚመራውን “ኦ ኤም ኤን” ቢሮ መጥታችሁ ጎብኙ ማለት ይችላል፣ አንድን ክልል መጥታችሁ ጎብኙ ብሎ አንደ ክልል መሪ ወይም እንደ ሃገር መሪ (ሄድ ኦፍ ስቴት) መጋበዝ ይችላል ወይ? ይህ መገፋፋት ለማን ይጠቅማል?
– በደቡብ ክልል ባደረገው ውይይት ላይ ስለ ሲዳማ ክልል መሆን ጉዳይ ተጠይቆ የሰጠው መልስ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ከተናገሩት ወይም ተመሳሳይ ጥያቄ ተጠይቀው ከመለሱት ይቃረናል። በሄደበት ቦታ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ሃሳብ እንቅፋት ማስቀመጥ ተገቢ ነው ወይ?
– “በኢትዮጵያ ሁለት መንግስት አለ፣ አንዱ ዐቢይ ነው፣ ሌላው ቄሮ ነው” ይህን አለ የተባለው አቶ ጀዋር መሃመድ ነው። ምን ማለት ነው? ይህ ሌላውም “መንግስት ነኝ” ብሎ እንዲያስብና የፈለገውን እንዲያደርግ በር መክፈት አይደለምን? በአንድ አገር ሁለት መንግስት እንዴት ይኖራል? ይህ ንግግር በሰዎች ልብ የሚፈጥረው የመታበይ ችግር ለሚያመጣው ጣጣ ማን ሃላፊነት ይወስዳል?
– አዲስ አበባ፣ ባለው አስራር አዲስ አበባ ተብላ ነው የምትጠራው፣ የአቶ ጀዋር መሃመድ የሚዲያ ተቋም ፣ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሚባለውን ተቋም “የፊንፊኔ ዩኒቨርሲቲ” እያለ በአደባባይ ፣ ቀጥታ በሚተላለፍ ፕሮግራም ማስተዋወቅና መጥራት ምን ለማለት ነው? ሰዎች በግላቸው ፣ እንደ ግለሰብ “አዱ ገነት፣ ሽገር፣ አዲስ አበባ፣ ፊንፊኔ፣ አዱዬ…ወዘተ… “ ብለው በቤታቸው ሊጠሩ ይችላሉ፣ በአደባባይ በሚዲያ ግን እንዴት እንዲህ ይባላል? ይህ ለዶክተር ዐቢይ አስተዳደር አጉል መገዳደር ፣ አጉል መጋፋት አይሆንም?
ጀዋር መሃመድ የራሱ ዕውቀት ይኖረዋል። ነገር ግን የሚናገረውን እያንዳንዱን ነገር አስቦ ካልተናገረ ሊያደርግ የሚችለውን በጎ አስተዋጾ ያኮስሰዋል። ከጥቅሙም ጉዳቱ እያመዘነ ይሄዳል።
አነሰም በዛ፣ የጫጉላ ሽርሽሩ ጊዜ የሚያበቃበትና መጋረጃው የሚገለጥበት ጊዜ ሲደርስ እነ ዶክተር ዐቢይ የማይጋፉት ተራራ ከፊታቸው ቆሞ እንዳይጠብቃቸው በጊዜ የሚስተካከለውን በጊዜ ማስተካከል ያለባቸው ይመስለኛል።
አንድ ሰው ብፈልግ የኢትዮጵያን ግዛት እገንጥላለሁ ሲል ኢትዮጵያን ከፈለኩ እበታትናለሁ ማለቱ ነው፣ ለዚያውም በሁለት ሳምንት ! ይህ ስህተት ብቻ ሳይሆን ነውርም ነው። ሲጀመር አገርን አንድ ማድረግ አንጂ፣ አገርን መበታተን እንደ ጀግንነት አይወራም። ሲቀጥል ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዳሉት አንድ ሰው ስለፈለገ ብቻ አገር እንደ ዶሮ ላባ ወይም እንደ ዛፍ ቅጠል አይገነጣጠልም። ይህ ኢትዮጵያንም የኢትዮጵያ ህዝብንም አለማወቅ ይመስለኛል።
እንደዚህ ዓይነት ንግግር የሚመጣው ደግሞ “ለውጡ የመጣው በኔና በኔ ብቻ ነው” ብሎ ከማሰብ ነው። ይህ ደግሞ ትልቅ ስህትት ነው፣ ኢትዮጵያ ውስጥ አሁን ያለውና የሚታየው በጎ ለውጥ የመጣው ከጸሎት ጀምሮ የህይወት መስዋትነት እስከመክፈል ፣ እስር ቤት ከመግባት ጀምሮ፣ በልብ እምቢተኝነት በማመጽ እስከ ተባበረው ፣ በመላው የኢትዮጵያ ህዝብ ነው። ለውጡ የመጣው ፣ በገዳምና በመስጊድ፣ በአገር ውስጥም በውጭም ለፍትህ እምባቸውን ጭምር በረጩ ሰዎች ጸሎትም ነው። የተገኘው ለውጥ የሁሉም ፍትህ ፈላጊ ኢትዮጵያዊ የትግል ውጤት እንጂ፣ የአንድ ሰው ወይም የአንድ ቡድን ብቻ አይደለም።
በትንሹ ፣ ደሳሳ ቤቷ ለአንድ ሃብታም ፎቅ መስሪያ ተብሎ አላግባብ የፈረሰባትና ጎዳና የወደቀችው አሮጊት ያፈሰሰችው እንባም ለለውጡ ድርሻ አለው። ስንናገር እሷንም እያሰብን ይሁን።
Average Rating