www.maledatimes.com ይብፃህ ብውሽጥን ብደጌን ዘለኹም ተጋሩ (መግቢያው ብቻ ትግርኛ….) - MALEDA TIMES
Loading...
You are here:  Home  >  Ethiopia  >  Current Article

ይብፃህ ብውሽጥን ብደጌን ዘለኹም ተጋሩ (መግቢያው ብቻ ትግርኛ….)

By   /   August 14, 2018  /   Comments Off on ይብፃህ ብውሽጥን ብደጌን ዘለኹም ተጋሩ (መግቢያው ብቻ ትግርኛ….)

    Print       Email
0 0
Read Time:10 Minute, 13 Second

(ካብ ይነጋል በላቸው – አዲስ አበባ)

እዚኣ ደብዳቤይ ብዝፈልጣ ንእሽተይ ትግርኛ ቋንቋ እንተጸሓፍኩዋ ቃህ’ምበለኒ፡፡ እንተኮይኑ ግና ብዙሓት ሕዝብታት ኢትዮጵያ ስለምንታይ ከምዝዛረብ ምእንቲ ክርድኡ ወይ ከኣ ክፍልጡ ስለዝደሊ በአማሃርኛ ክቅጽል መሪፀ፡፡ ትግርኛን አምሃርኛን ቋንቋታት ካብ ሃደ ምንጪ ከምዝወፅዑ ኸምዘይንፈልጥ፣ ብባህሊን ብሃይማኖትን ብሥነ ልቦናዊ ቀመርን ብማኅበራዊ ሕይወትን ዝአምሰሉ መሠረታዊ አነባብሮን ተጋሩ ምስአኅዋቶም አምሃሩ “ተመሳሳሊ” ካብዝብሃል አገላለፃ በዝበለጸ ሃደ ምኋኖም ምሥጢር ዘይምኋኑ ኸምዘይንፈልጥ  ስለምንታይ እዚ ሁሉ እግርግርን፣ ህንፍሽፍሽን፣ ፅልኢን፣ ምቅትታልን በዚኦም ክልቲኧን ሕዝብታት ኢትዮጵያ ከምዘወረዶም  ናይ ዕድመ ለኸ ህንቅል ህንቅሊተይ ምኋኑ በዚ አጋጣሚዚ ክገልጽ ይደሊ፡፡ ሠናይ ንባብ፡-

 

ውድ ወንድሞቼና እህቶቼ ተጋሩ!

 

አሁን የምንገኝበት ወቅት እጅግ አሳሳቢ ነው፡፡ እንደትግራዋይም እንደኢትዮጵያዊም በአንዲት ሉዓላዊት ሀገር በሰላም ለመኖር ያለን ብቸኛ አማራጭ በዚህች አጭር መልእክቴ የማነሳቸውን አንዳንድ ጉዳዮች ከልብ ማጤንና ሰፊውን የጥፋት መንገድ ትቶ ወደ መልካሙ ጠባብ መንገድ በቶሎ መግባት መሆኑን አምናለሁ፡፡ ይህ አስተያየቴ በብዙዎች ተደጋግሞ የሚጠቀስ ምክረ-ሃሳብ እንጂ የኔ ብቻ እንዳልሆነም መጠቆም እፈልጋለሁ፡፡ “ምክር የድሃ ነበርሽ – ማን ቢሰማሽ” እንዳይሆንብኝም እጸልያለሁ፡፡

በአማርኛ “ፍርዱን ነው!” የሚል ግሩም አባባል አለ፡፡ እንደዚህ የሚባለው አንድ ሰው ብዙ እየተበደለና እየተገፋ ቆይቶ በበዳዩ ላይ አንዳች እርምጃ ሲወስድ ነው፡፡ እንዲህ የሚለው ወገንም አንድም በዳዩ ራሱ ወይም የውጪ ታዛቢ ነው፡፡ “እገሌ እኮ እገሌን እንዲህ አደረገው!” መባልን ስንሰማ አፀፋ መላሹ ላይ የተደረገው ግፍና በደል እውነትም ከትግስት በላይ ከሆነ ታዛቢ ሳይቀር “አዎ፣ ፍርዱን ነው፡፡ እንዲያውም ማድረግ ካለበት በጣም ትንሹን ነው ያደረገው፤ በጣም ተበድሎ ነበር…” የሚል ሕዝባዊ ፍርድና አስተያየት ይሰጣል፡፡ እዚህ ላይ “ልክ ነው / ልክ አይደለም” ሌላ ነገር ነው፡፡ የተበደለ ወገን ዝንታለሙን እንደተበደለ እንደማይኖር ግን ማሳያ ነው፡፡ ይህን ማኅበራዊ የፍትህ ብያኔ ለምን እንዳመጣሁት በጥቂቱ ማስረዳት ይኖርብኛል፡፡

በበረሃ 17 እና በመንግሥትነት 27 በጥቅሉ ላለፉት 44 ዓመታት ሕወሓት  በተጋሩ ስም ኢትዮጵያን ሲያደማና ሲያቆስል ለመቆየቱ የወቅቱ የከረረ ሕዝባዊ ዐመፅና እንደብጉንጅ በየአካባቢው የሚፈነዳው የተቃውሞ እንቅስቃሴ  ምሥክሮች ናቸው፡፡ ሕወሓት በኢትዮጵያና በትግራይ መሀል – በእናትና ልጅ መሀል ማለትም ይቻላል – የገነባው የብረት ግምብ እጅግ ጠንካራ መሆኑን ለመረዳት ከ90 ሚሊዮን በላይ የሚገመት ሕዝብ በአንድነት “ሕወሓት ሆይ አጉራህ ጠናን! የዛሬን ተወን፤ በወንድ ልጅ አምላክ ይሁንብህ  ለዛሬ እንኳን በፍቅር ስለፍቅር ተሸነፍልን” እያለ እሹሩሩ ቢለው ሊለሳለስ አለመቻሉን ማስታወስ ነው፡፡

የሕወሓት ዋናው ደጀን የትግራይ ሕዝብ ነው – ምንም ዓይነት ጥናት አያሻውም፡፡ ሁለተኛው ደጀኑ ከኢትዮጵያ ሀገራዊ ካዝናና ከሕዝብ የዘረፈው ሀብት ንብረትና ተቆጥሮ የማይዘለቅ ገንዘብ ነው፡፡ ተጋሩ አመዛዛኝ አእምሮ አላቸውና የሕወሓትን የጥፋት ጉዞ በመገንዘብ ራሳቸውን ከዚህ የጥፋት ጉዞ ሊያርቁ እንደሚችሉ ይገመታል፤ ይታመናልም፡፡ ገንዘቡ ግን አእምሮ ስለሌለው ለሕወሓት በሚታዘዙ አንጎል የሌላቸው ብኩን ሰዎች እጅ እየገባ ትልቅ ውድመት እያስከተለ ነው፡፡ ገንዘብና የጦር መሣሪያ በብልኆችና በጀግኖች እጅ ካልሆነ በስተቀር በደናቁርት እጅ ከገባ መዘዙ ብዙ ነው፡፡ በአሁኑ ሰዓት ለምሣሌ የሕወሓት አባላትና ደጋፊ የሆኑ ትግሬዎች እያደረሱት ካለው የጥፋት ተልእኮ ይልቅ ኅሊናቸውን ለገንዘብ የሸጡ አማራና ኦሮሞን ጨምሮ የሌሎች ዘውጎች አባላት እያደረሱት የሚገኘው ጥፋት እንደሚበልጥ ወይም ቢያንስ ሊተናነስ እንደማይችል መገመት አይከብድም፡፡ “ገንዘብ የተጫነች አህያ የማትደረምሰው ምሽግ የለም” እንደሚባለው በገንዘብ ፍቅር ያበዱ ዜጎች – ከየትኛውም ጎሣና ነገድ – የሕወሓትን ሀገርን የማናወጥና ለውጡን የማጨናገፍ ተልእኮ ለማሣካት በሁሉም የዘመቻ ዓይነት ጦርነት ከፍተው ከመቶ ሚሊዮን ሕዝብ ጋር ተፋጠዋል፡፡ ይህ ሌት ከቀን የሚጧጧፍ ሁለገብ ዘመቻ አንዳንድ መረጃዎች እንደሚጠቅሱት በ50 እና በ100 ሺዎች የሚገመቱ የሳይበር ጦርነት ተዋጊዎችን ይጨምራል፡፡  “ጦር ከፈታው ወሬ የፈታው” እንዲሉ ነውና እነዚህ ዕንቅልፍ-አልባ የበሬ-ወለደ ጦረኞች ሕዝባችንን ክፉኛ እየተፈታተኑት ይገኛሉ፡፡ መንግሥትና ጤናማ ናቸው የሚባሉ ሚዲያዎችም እየተከታተሉ ቢያንስ የማረጋጊያ ማስተባበያ እንኳን መስጠት አልቻሉም፡፡ በዚህ ምክንያት የለውጡ ጠላቶችና ደጋፊዎች ማንና ማን እንደሆኑና እንዳልሆኑ ለማወቅ ተቸግረናል፡፡ እየጠራ መሄድ ያለበት ነገር ይበልጥ እየደፈረሰ መገኘቱ ሀገራችንን ወደማትወጣው አዘቅት እንዳይከታት ፍራቻ አለ፡፡ የዝምታ አዙሪቱን ካልገፈፍነው ትልቅ አደጋ ውስጥ ነን፡፡

ነገሩን በጥሞና ስናጤነው “ላታመልጠኝ አታሩጠኝ” ወይም “ የጭንቅላት ሥጋ መብሰሉ ለማይቀረው እንጨት ይፈጃል” እንዲሉ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ አምርሯል፡፡ ያመረረውም በሕወሓት በደረሰበት ግፍና በደል ነው፡፡ ይህን ግፍና በደል መሸከም የማይችልበት ደረጃ ላይ በመድረሱ ከዳር እዳር ሆ ብሎ ተነስቷል፡፡ ዕድሜ ለጠ/ሚ ዶ/ር ዐቢይ ብዙ ውድመት ሊደርስ ሲል ድንገት ሳናስበው በተከሰተ መለኮታዊ የሚመስል ጣልቃ ገብነት ሳቢያ ክፉዎችን ብቻ ሊያስደስት ይችል የነበረው ሦርያዊ ክስተት ባጭሩ ሊቀጭ ችሏል – ይህ “በአጭር ተቀጨ” የተባለ አደገኛ ክስተት ካገረሸ ግን መቆሚያ እንደሌለው በተለይ ተጋሩ መገንዘብ ይኖርባቸዋል፡፡ ምክንያቱም ተጋሩን ምሽግ አድርጎ ሤራና ተንኮል እየጎነጎነ የሚገኘው ሕወሓት የሚያመጣው ዳፋ በቀላሉ የማይበርድና ወርድና ስፋቱም ከወዲሁ የማይታወቅ ነውና፡፡ ልብ እናድርግ – አይበልብንና ተወርዋሪ ኮከብ ኢትዮጵያ ላይ ወድቆ በከፊል ወይም አብዛኛውን ክፍል ቢያጠፋ ተጠያቂው ሕወሓት ከመሆን አይዘልም – እንኳንስ በብዙ ገንዘብ ክፍያ ወንጀለኞችን እየላከ እዚህና እዚያ ቦምብ ማፈንዳትና ጎሣን ከጎሣ ማጣላት ይቅርና፡፡ የሀገራችን የአሁን ውድመት ዋና መንስዔ ሕወሓት ነው፡፡

ተጋሩ በአንድ ነገር መስማማት አለባቸው፡፡ በሕወሓት የተገደሉና የተበደሉ ተጋሩ የሉም ማለት ሣይሆን ሕወሓት ኢትዮጵያን በድሏል፤ ሕዝቧንም አዋርዷል፡፡ እርግጥ ነው – በሕወሓት ምክንያት ሀገራችን ያገኘችው መልካም ነገር መኖሩ አይካድም፤ ጥፋቱ ሸፈነብኝ እንጂ እኔም ከነዚህ ነገሮች ጥቂቶቹን መጥቀስ አያቅተኝም፡፡ ዋናው ግን የሕወሓት ከይቅርታ በላይ የሆነ ሀገራዊ ውድመት በአሥርና በሃያም ሣይሆን በመቶዎች ዓመታትም የሚስተካከል አለመሆኑ ነው፡፡ ሕወሓት በዕኩይ ምግባሩ እንዳልነበር ያደረገው አካልን ወይም ሥጋን ብቻ ሣይሆን ኅሊናንም፣ ሞራልንም፣ ሰብኣዊነትንም፣ ባህልንም፣ ወግና ሥርዓትንም፣ ሃይማኖትንም … በጥቅሉ ብዙ ትውልድን ጭምር ነው በቁሙ የገደለው፡፡ የሕወሓት አጥፊነት “እነእገሌን አኮላሸ፣ እነእገሌን በሥውር ገደለ፣ እገሌ ላይ ኢሞራላዊ ነገር ፈጸመ…” በሚል ብቻ በቀላሉ የሚገለጽ አይደለም – ይህኛውም ዘግናኝ የታሪክ ጠባሳችን መሆኑ እንዳለ ሆኖ፡፡ የሀብት ዝርፊያና የታሪክ ብረዛውም በጊዜ ሂደት ይስተካከላል፡፡ ትልቁ የሕወሓት ጥፋት እንግዲህ ሀገራችንን በሁሉም ረገድ በሺዎች ለሚቆጠሩ ዓመታት ወደ ኋላ ማሽቀንጠሩ ነው፡፡ ሀገራችን በዓለም ፊት ምናልባትም ለመጀመሪያ ጊዜ የውርደት ካባ የለበሰችው በወያኔዎች ነው፡፡ ለዚህ ሁሉ ጥፋቱም ቁጥር አንድ ተባባሪና አለሁህ ባይ ለብረት ትግሉ ዋና ግብኣት ከመሆን ጀምሮ የትግራይ ሕዝብ መሆኑ ቢደብቁት የማይደበቅ አሳዛኝ እውነት ነው፡፡ በመጠኑ አብራራለሁ፡፡

ትግራይ ውስጥ የሚኖር ትግራዋይ እኔ ከምጠቅሰው የሕወሓት ጥፋት “የለሁበትም” ብሎ እጁን ሊታጠብ ይችል ይሆናል፡፡ የማጣራት ሥራ የምንገባበት ጊዜ አይደለምና ወደዚያ መግባት አይገባም፡፡ ነገር ግን ስለትግሬዎችና ሕወሓት ጥብቅ ግንኙነት የመሀል አገሩ ሕዝብ የሚያውቀው ብዙ ነገር አለ – ምሥጢር ያልሆነ፡፡ አብነት መጥቀስ ይቻላል፡፡ ከ83ዓ.ም ወዲህ ያለችን ኢትዮጵያ በፌዴራል የውሸት ሥርዓት ስም ወያኔዎች ምን ሲያደርጉ እንደነበር አውቆ ኅሊናውን ላልሳተ ትግራዋይ ግልጽ ነው፡፡ ሌሎች በገዛ ሀገራቸው ግዞተኛና የስቃይ ሰለባ ሲሆኑ በሕወሓት ሥር የተኮለኮሉ ሞልቃቃ ተጋሩ ግን ሽንጥና ዳቢቱን እያማረጡ የሚምነሸነሹ  ከነሱም ተርፎ ለቻይና፣ ለህንድና ለፓኪስታን ቱጃሮች የሚያድሉ አንደኛ ደረጃ ዜጎች ነበሩ፡፡ ኢንቬስትመንቱንና የመንግሥት የልማት አውታሮችን ግንባታ ሙሉ በሙሉ በሚባል ሁኔታ ተጋሩ ተቆጣጥረው ሊያውም በውድ ዋጋና ጥራቱ በተጓደለ አሠራር የሚዘባነኑባቸው ለሌሎች ግን በፍጹም የማይፈቀዱ ነበሩ፡፡ ነባር ነዋሪዎችን በመፍጀትና በማፈናቀል ወይም ወደነሱው ባህልና ቋንቋ እንዲለወጡ በማስገደድ የአጎራባች ክልሎችን ለም መሬቶች ነጥቀዋል፡፡ የሀገሪቱን የመረጃ ቋት ወደ ትግራይ እስከማዛወርና አየር ኃይልን ነቃቅሎ ትግራይ ላይ እስከመትከል የደረሰ ድፍረትና ዕብሪት ለመቶ ሚሊዮኑ ሕዝብ በግልጽ አሳይተዋል፤  ጄኔሬተሮችን፣ የሕክምና ማቴሪያሎችንና የዳቦ መጋገሪያ ማሽኖችን ጨምሮ ብዙ የሀገር ዕቃዎችን ከያሉበት ነቃቅለው ከመሀል አገር ወደ ትግራይ አጓጉዘዋል፡፡ ንቀታቸውና በዱባ ጥጋብ እየፈነጠዙ የማይታሰብን ነገር በተግባር ማሳየታቸው እነዚህን ወያኔዎች በሰው ልጅ ታሪክ አንደኛ ያደርጋቸዋል፡፡

በሌላም በኩል የሠራተኞችን ቅጥር በሚመለከት ብዙ መናገር ይቻላል፡፡ አየር መንገድ የተሞላው በተጋሩ ነው፤ የቴሌ፣ የባንክ፣ የሜቴክ፣ የመከላከያ፣ የፖሊስ፣ የደኅንነት፣ የመብራት ኃይል – የሁሉም የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ማለት ይቻላል – ማኔጅመንትና ቁልፍ ቁልፍ ቦታዎች የተያዙት በትግሬ ነው (`ነበር` ወደሚለው ደረጃ ገና አልደረስንም አይደል?)፡፡ ንግዱ፣ የሕንፃ ግንባታው፣ የፕሮጀክት ሥራው፣ ጨረታው፣ ወዘተ. ሁሉ የተያዘው በትግሬ ወይም ትግሬ ሊቆጣጠረው በሚችል የመሀል አገር እንደራሴና ሆድ-አምላኩ ምስለኔ ነው፡፡ እያንዳንዱ የፌዴራልና የክልል እንቅስቃሴ በትግሬዎች ራዳር ውስጥ እንደነበር የአደባባይ ምሥጢር ነው፡፡ በምለው ሁሉ “የዐዋጁን በጆሮ” እንደምባል አውቃለሁ፡፡ ይህን ሁሉ የሕወሓት መረን የለቀቀ ተግባር ትግሬዎች አያውቁም ነበር  ብሎ ማሰብና ከዚህም ባለፈ ትግሬዎችና ሕወሓቶች ይለያያሉ ብሎ ማመን አስቸጋሪ ነው፡፡ ይህን ሁሉ ወያኔያዊ የሀብትና የሥልጣን ቁጥጥር ካለትግሬዎች ማሰብ ከተቻለ እርግጥ ነው ሕወሓትና ተጋሩ ይለያያሉ፡፡ ለአብነት በቦሌ አየር መንገድ ካሉት ሠራተኞች መካከል ስምንትና ዘጠኝ ሺው ትግሬ ነው መባልን ስንሰማና በሌሎች  መሥሪያ ቤቶች ደግሞ ሊኖር የሚችለውን የትግሬ ሠራተኛ ከሌሎች ጎሣዎች ጋር ያላቸውን ተመጣጥኖኣዊ ብዛት በምናባችን ስንገምት ወያኔ ያለ ትግሬ እገዛና ድጋፍ ምንም ማለት እንዳልሆነ – መረዳት ከፈለግን – መረዳት አያቅተንም፤ እዚህ ላይ የተጋሩን የሕዝብ ብዛት መቶኛ ስሌት ማወቅም ተገቢ ነው – ከኢትዮጵያ ሕዝብ ብዛት 6% ብቻ! በዚህ በሕወሓትና ሕወሓታውያን ሱቅ እንደገባ ሕጻን ሁሉንም ለኔ ባይነት ካላፈርን ሀፍረትን ከናካቴው አናውቅም ማለት ነው፡፡ ፍርድ ለራስ ነውና ዐይናችንን ጨፍነን ይህን አስቀያሚ የታሪክ አጋጣሚ በኅሊናችን እናስበው፡፡ ከዚያም “በርግጥ ወያኔ ያለተጋሩ ሕይወት አለው/የለውም?” ብለን እናስብ፡፡  በተጋሩና በሌላው ሕዝብ መሀል ጥቁር መጋረጃ የዘረጋ ይህን የታሪክ ስብራት ለመጠገን ነው እንግዲህ ሁላችንም መጣር ያለብን – መሸፋፈንንና አጉል ይሉኝታን ትተን፡፡

“ለምን አንጻራዊ የበላይነቴ ይቀራል?” በሚል የሚያኮርፍና በሌሎች ወንድምና እህቶቹ ከእሥራት መውጣት የሚቀየም ትግራዋይ ካለ ራሱን ይመርምር፡፡ ሌላው ወገኑ የሚለው “እንድኖር ይፈቀድልኝ! ሰብኣዊና የዜግነት መብቴ ይከበር፤ እኔም እንደ እናንተ ኢትዮጵያዊ ነኝ” ነው፡፡ …. ሁሉንም ቢያወሩት አያልቅም፡፡ እንግዲህ እንዲህ እናድርግ፡– የችግሩን መኖር ማመን፣ ለተፈጠሩ ችግሮች ይቅርታ መጠየቅ ያለበት ወገን ተበዳይን ይቅርታ መጠየቅ፣ ግፎችና በደሎች እንዳይደገሙና ከትውልድ ወደ ትውልድ እንዳይወረሱም ጥንቃቄ በተሞላበት ሁኔታ ሁሉም ወገን የየራሱን የቤት ሥራ መሥራት፣ የተበደለን መካስ፣ የተዘረፈን መመለስ፣ ለሆነው መጥፎ ነገር ሁሉ ከልብ መጸጸትና እንዳይደገም በቁርጠኝነት መወሰን፣ ለተሻለ የጋራ ኑሮ መጣር …. ወቅቱ የሚጠይቀው ግዳጅ መሆኑን መገንዘብ፡፡ ከዚያ ውጪ ያለው እንቶ ፈንቶ የደቂቃዎችን ኅልውና ወደ ሰዓታት ይለውጥ እንደሆነ እንጂ ሣምንታትን ወደ ዓመታት ቀይሮ ለ27 ዓመታት የዘለቀውን የሰቆቃ አገዛዝ ቋሚ አያደርገውም፡፡ ነፍስ እንወቅ፤ እንንቃ፤ ከምንኖርበት የምናብ ዓለም እንውጣ…፡፡ “እኔስ እንደነሱ ብሆን ኖሮ?” የሚል ጥያቄ በአእምሯችን ያቃጭል፡፡ ነግ በኔንም እንወቅ፡፡ ያስቀመጡት አይጠፋምና ለሌላ ዙር ግፍና በደል መዘጋጀቱን እንተው፡፡

… ስለዚህ ለ27 ዓመታት ሲረገጥና ሲበደል፣ ሲሰደድና በገዛ ሀገሩ የበይ ተመልካች ሲሆን የከረመ ሕዝብ አሁን የግፍ ቋቱ ሞልቶ በአልሞት ባይ ተጋዳይ ወያኔን ከጫንቃው ሊያወርድ ቢነሳ ተጋሩ ሊቆጡ አይገባም፡፡ እንዲያውም “ፍርዱን ነው” ብለው ሊያዝኑለትና ከተነፈገው የሀገር በረከትና ሲሳይ የድርሻውን እንዲቋደስ አብረው ሊታገሉለት ይገባል፡፡ ከዚያም በተጓዳኝ በሕወሓት ይደርስበት የነበረው ስቃይና እንግልት፣ እሥራትና ግርፋት፣ ሞትና ደብዛ መጥፋት በአስቸኳይ እንዲቆም ተጋሩ ብዙ መሥራት ይገባቸዋል፡፡ “እኔ አላጠፋሁም፤ ከደሙ ንጹሕ ነኝ!” የሚለው ጲላጦሳዊ አነጋገር ደግሞ የትም አያደርስም፡፡ በአዳም ኃጢኣት እኛ ሁሉ አሁን ድረስ መከራ እየተቀበልን የመሆናችን ምሥጢር በሕወሓት ሳቢያ ተጋሩና ትግራይ ወደፊት አሣር  ሊገጥማቸው እንደሚችል ጠቋሚ ነውና የግል ንጽሕና የወል መርገምትን እንደማይከላ(እንደማያስወግድ) ልንረዳ ይገባል፡፡

…. ልቦለድም ቢሆን ከፍቅር እስከ መቃብር አንድ ነገር አስታወስኩ፡፡ ፊታውራሪዎች መሸሻና አሰጌ ሊፋለሙ ሲሉ የአንድ ደብር ካህናት ታቦት አውጥተው በመለማመን ፍልሚያውን አስቀርተዋል፡፡ የትግራይ ጳጳሣትና ሌሎች ካህናትና ፓትርያርኮችም ያንኑ የተቀደሰ ተግባር አሁን በገሃዱ ዓለም እንዲደግሙት ማሳሰብ እልጋለሁ፡፡ ትግራይ ውስጥ የመሸገው ኃይል ምን እየመከረ እንደሆነ  በግልጽ እያየን ነው፡፡ እነዚህ በልተው ጠጥተውና ገድለው የማይረኩ ብቻ ሣይሆኑ ኢትዮጵያን አጥፍተውና በታሪክ ተሳልቀው የማይረኩ አዛውንት እኛ እንዴት ሆነን ከምድረ ገጽ እንደምንጠፋላቸው ለመረዳት በሚቸግር ሁኔታ ከዚህም በባሰ ብን ብለን እንድንጠፋላቸው እያሤሩ ናቸው፡፡ ይህንን ህልማቸውን እውን ለማድረግም ከኛው ዘርፈው ያከማቹትን ቁጥር የማይገልጸው ገንዘብ እየበተኑ ነው፡፡ በዚህ ድርጊታቸው ለውጡን በተወሰነ ደረጃ ሊያጠይሙትና የትኩረት አቅጣጫን በማዛነፍ ኃይልንና ገንዘብን አላግባብ ያባክኑ ወርቃማ ጊዜያችንንም ይሻሙብን እንደሆነ እንጂ የኢትዮጵያውያንን የለውጥ መንፈስ ሊያስቀሩት እንደማይችሉ ተጋሩ ተገንዝበው እነዚህን እንደውሻ ያበዱ ዜጎች ሃይ ሊሉዋቸው ይገባል፡፡ ተጋሩ በራሳቸው ተነሳሽነት ይህን ማድረግ ያለባቸው ጦስ ጥምቡሳቸው ለትግራይም የሚተርፍ በመሆኑ ነው፡፡ እነሱን ያሳወረ የጥቅም፣ የሥልጣንና የቂም በቀል ሱስ በተለይ ትግራይን በአጠቃላይ ደግሞ ኢትዮጵያን ይዞ መቀመቅ እንዳይወርድ ያሰጋል፡፡ ሚዲያዎች እያሉ እንነጋገር፤ መንግሥት ሳይፈርስ እንወያይ፤ በአንዳንድ ቦታዎች የሚታዩ ሥርዓተ አልበኝነት የሠፈነባቸው ግብታዊ እርምጃዎች ሳያጥለቀልቁን ይሄኔዜ እንምከር፡፡ የከረፋንና የገለማን የዘረኝነት አካሄድ ተመልሶ እንዳያጨራርሰን ጥንቃቄ ይደረግ፡፡ ዝም ያላችሁ ተናገሩ፡፡

የሰሞኑ ሁኔታ አሳሳቢ ነው፡፡ ከኢትዮ-ሶማሌ  እስከ ሻሸመኔ የዘለቀው የሁከት ድርጊት የት እንደሚያቆም አይታወቅም፡፡ በሀገር ላይ የነገሠው ድባብ አስጠሊታ ነው፡፡ በየማኅዲያው የሚታዬውና የሚነበበው አብዛኛው ኃላፊነት የሚጎድለው ነገር ሁሉ ጠያቂና ተጠያቂ የለም እንጂ እጅግ አደገኛ ነው፡፡ ይህች ወቅት ለኢትዮጵያ ሰሙነ ህማማት ናት፡፡ በሰሜን የሚነፍሰው ነፋስ እጅግ ሞቃታማ በመሆኑ በተለይ ጆሮን ያግላል፡፡ ጊዜው ትልቅ ሰው የሚፈለግበት ወቅት ነው፡፡ የሰው ልጆችን በእኩል ዐይን የሚያየውንና ለሁሉም ሲል በመስቀል ተቸንክሮ የሞተውን የክርስቶስን ሥጋ ወደሙ  ከሚፈትቱ ታላላቅ ተጋሩ የሃይማኖት አባቶች አንደበት “የአማራ ፓትርያርክ ስም በክልላችን በሚደረጉ ቅዳሤዎች መነሣት የለበትም”  የሚል አሣፋሪ ንግግር እየሰማን ነው፡፡ እረኛው እንዲህ ከሆነ በግና ፍየሉ እንዴት እንደሚሆን መገመት አይከብድም፡፡ እግዚአብሔር ይሁነን እንጂ እየጠፋን ነን፡፡

ተጋሩ ቆም ብለው የሚያስቡበት ጊዜ አሁን ነው፡፡ አንዳንዴ ምርጫዎች አስቸጋሪ ይሆኑና ፈተና ውስጥ የምንወድቅበት ጊዜ አለ፡፡ የሌሎች ኢትዮጵያውያን ምርጫ የመኖርና ያለመኖር ግዴታ የደቀነባቸው ምርጫ ነው፡፡ ከመኖር ውጪ ሌላ አማራጭ ስለሌላቸው ከሕወሓት የጭቆና ቀምበር ተላቀው በነፃነት መኖር የሚያስችላቸውን ብቸኛ መንገድ ተከትለዋል፡፡ ተጋሩ ደግሞ ከሕወሓትና ከሌሎች ኢትዮጵያውያን ጋር ተባብሮና ተከባብሮ መኖር ከሚሉት ሁለት ምርጫዎች ጋር ተፋጠዋል፡፡ በዚያ ላይ የዘመናት የወያኔ ቅስቀሳና ፕሮፓጋንዳ አለ – አይናቅም፡፡ ከባድ ምርጫዎች ናቸው፡፡ ይህን ቢሉ ችግር አለው –  ያን ቢሉም ችግር አለው፡፡ ሁለቱም ምርጫዎች እሳትን ያስከትላሉ፡፡ ተጋሩ የሚበጃቸውን በአፋጣኝ መምረጥ አለባቸው፡፡ እንደኔ ግምት ግን ነገ ከሚጠፋ ውድብ ይልቅ መቼም የማትጠፋውን ኢትዮጵያን እንደሚመርጡ አልጠራጠርም፡፡ ቸር ያሰማን፡፡

ተጋሩ “ኢትዮጵያውያን ወንድምና እህቶቻችን በርግጥም በሕወሓት ተበድለዋል፤ ይህንን ችግራቸውንም ተረድተን ልናግዛቸው ይገባናል” ማለት ይጠበቅባቸዋል፡፡ የተወሰኑ ተጋሩ ባለፈላቸው አብዛኛውና በግዞትና በትግራይ የሚኖረው ሕዝብ በታሪክና በትውልዶች ውግዘት መቀጣት የለበትም፡፡ ከምሁራንና ከአባቶች የተመረጡ ነገር ዐዋቂዎች ከሌሎች ክልሎች ተመሳሳይ ሰዎች ጋር ግንኙነት በመፍጠር ክረቱን ማለዘብ፣ የተሳሳተን መመለስና የተበላሸን ለማተስካከል መሞከር አለባቸው፡፡ የትግራይ ምሁራንና የክልሉ ተቃዋሚ ኃይላት በፊት ይቃወሙት ከነበረው ኃይል ጋር ተደርበው ትዝብት ውስጥ ለሚከት ከፋፋይ ተግባር ከመጣደፍ ይልቅ ቆም ብለው ያስቡና ለሁሉም ሕዝብ ወደሚጠቅም አጀንዳ ቢገቡ ይመረጣል፡፡ የትግራይ ምሁራን የትግራይ ብቻ አይደሉም – የኦሮሞ ምሁራን ለኦሮሞ ብቻ እንዳልሆኑት፡፡ ወደኋላ ማሰብ ይቅር፡፡ መማር ዐይንን መግለጥ እንጂ መታወር አይደለም፡፡ እልህና ቂም በቀል የትም አያደርስም፡፡ እኛ አባቶች ያጠፋነው ጥፋት ይበቃል፤ ቀጣዩ ትውልድ በኛ አበሳ መቀጣት የለበትም፡፡

ጦር መስበቅና መገዳደል የሕይወት ብርሃንን (‹karma›ን) እያጠቆረ ለበለጠ ቆሻሻ ስብዕና ይዳርጋል እንጂ ልዕለ-ኅሊና ስብዕናን (‹Over-self›ን) አያሳድግም፡፡ ከዚያ አቅጣጫ መቶ ሺህ ጦር ቢሰለፍ፣ ከዚህ አቅጣጫ መቶ ሺህ ጦር ቢሰለፍ ድምሩ ዜሮ መሆኑን መረዳት ተገቢ ነው – ሊጠፋፉ ነውና ቀጠሯቸው፡፡ በመዋጋት ማጣት እንጂ ማግኘት የለም – ተገኘ ቢባልም በአንደኛው ኪሣራ የሚገኝ ትርፍ ዞሮ ዞሮ ለሚዘገይ ኪሣራ የሚዳርግ ያው ኪሣራ ነው፡፡ ምክንያቱም “ነገ” የሚባል የትርፍና ኪሣራ ማወራረጃ የታሪክ ማሽን አለና፡፡ ትንሽ የማሰብ ጉዳይ እንጂ ይህ ዘመን ላለለት ከሚጣላበት ይልቅ ቢፋቀርበት ያተርፋል፡፡

የሚሰማኝን አልኩ፤ አልኩ ለማለት እንጂ የታሪክን ጎማ ወደፊትም ሆነ ወደኋላ ማሽከርከር የማይሣነው የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር ነው ሁሉን ነገር የሚያስተካክለው፡፡ ለሀገራችን ሰላምንና ፍቅርን አብዝቶ ይስጠን፡፡ ከሚያስጨንቅ ነገርም ይሠውረን፡፡ ዕንቅልፍ አጥው ሰላማችንን ለማደፍረስ የሚተጉ ወገኖቻችንን ወደ አቅላቸው ይመልስልን፡፡ yinegal3@gmail.com

Happy
Happy
0 %
Sad
Sad
0 %
Excited
Excited
0 %
Sleepy
Sleepy
0 %
Angry
Angry
0 %
Surprise
Surprise
0 %
    Print       Email

Average Rating

5 Star
0%
4 Star
0%
3 Star
0%
2 Star
0%
1 Star
0%
<"Without the support of our readers, the Maleda Times website would not exist in its present form">

You might also like...

በሰሜን ሸዋ ዞን ኤፍራታ እና ግድም ወረዳ መከላከያ ከአማራው ማህበረሰብ እና ከፋኖ ጋር ጦርነት ገጥሟል

Read More →

This site is protected by wp-copyrightpro.com

Skip to toolbar