www.maledatimes.com የስደተኛው የሃገር ቤት ጉዞ፤ አርቲስት አለምፀሀይ ወዳጆ ወደ ሀገሯ ልትገባ ነው!! አበባየሁ ታደሰ - MALEDA TIMES
Loading...
You are here:  Home  >  Addis Admas  >  Current Article

የስደተኛው የሃገር ቤት ጉዞ፤ አርቲስት አለምፀሀይ ወዳጆ ወደ ሀገሯ ልትገባ ነው!! አበባየሁ ታደሰ

By   /   August 19, 2018  /   Comments Off on የስደተኛው የሃገር ቤት ጉዞ፤ አርቲስት አለምፀሀይ ወዳጆ ወደ ሀገሯ ልትገባ ነው!! አበባየሁ ታደሰ

    Print       Email
0 0
Read Time:3 Minute, 56 Second
Image may contain: 1 person, smiling, text

አርቲስት አለምፀሀይ ወዳጆ ወደ ሀገሯ ልትገባ ነው!!
የአስራ ዘጠኝ መቶ ሰማንያ ሶስቱ ግንቦት ሀያ ማክሰኞ ሊውል አራት ቀን ቀደም ብሎ አርብ ግንቦት አስራ ስድስት፤ ከለውጡ ጥቂት ቀደም ብሎ፤
ገና ብሶት የወለደው ሰራዊት የደርግን
ራዲዬ ጣቢያ ሳይቆጣጠር፤
ገና ታጋዮቹ ከእንጦጦ ተራራ ላይ ሆነው
ወይ አዲስ አበባ ወይ አራዳ ሆይ
አንቺ ጋር ለመድረስ ስንቱን ገበርን ወይ
እያሉ ተደመው ሳይጨርሱ፤ ገና አዲስ አበባ በግንቦት ሀያ ሰባቱ ፍንዳታ ሳትረበሽ፤ ገና ገና ግንቦት ሀያ ከሌሎቹ ሃያዎች የተለየ ቀን ሳይሆን፤ ገና አሁን የሆነው ሁሉ ለመሆን ከመጀመሩ አስቀድሞ ተወዳጇ አርቲስት አለምፀሀይ ወዳጆ በእለተ አርብ ሀገሯን ለቃ ወጣች። የዛሬ ሀያ ሰባት አመት።
ሀያ ሰባት አመት አንድ የተወለደ ህፃን አድጎ ተምሮ ተመርቆ ትዳር ይዞ ራሱን የሚተካበት አመት ወይም አንድ ወጣትነቱን የጨረሰ ጎልምሶ፤ ሸምግሎ፤ ጡረታ ወጥቶ እቤቱ የሚቀመጥበት የግዜ ርዝመት ነው። አለምፀሀይ ወዳጆ በዘመኗ ገናና የሆነ ስሟን እንደያዘች እና ለሀገሯ ብዙ መስራት የሚያስችላት ብቃት እያላት ነው በነባራዊ ሁኔታዎች አስገዳጅነት ወደ ምድረ አሜሪካ የተጓዘችው። የመንግስት ለውጡም በሂደት ትናንት እና ዛሬ፤ እኛና እነሱ እያለ መከፋፈልና መቧደን ስላበዛ ተመልሶ ወደ ሀገር የመግባት ተስፋዋ እየጠፋ የምትወደው የብሔራዊ ትያትር መድረክ እየራቀ የተወለደችበትና ያደገችበት ሀገርና ህዝብ ህልም እየሆነባት ኑሮዋ በውጭው አለም እንዲሆን ተገደደ።
እንደዛሬው፤ ትወና እንደ ቡና ጠጡ ድንገት ጎራ የሚባልበት ሙያ ሳይሆን በተሰጥኦ እና በችሎታ በሚፈተንበት፤ ከዛም ባለፈ ነጥሮ ለመውጣት የየእለት ስራና ትጋት በሚያስፈልግበት ሰአት ሀገራችን ያፈራቻትና የደከመችባት ድንቅ ባለሙያችን ናት አርቲስት አለምፀሀይ ወዳጆ። ‘ኢትዮጵያ’ ብላ በጥላሁን፤ ‘ሰላም’ ብላ በመሀሙድ ‘ቁመትሽ ሎጋ ነው’ ብላ በሙሉቀን በሌሎችም ታዋቂና ዝነኛ ዘፋኞች ብቅ ብላ ፍቅራችንን፣ ምኞታችንን፣ ህልማችንን፣ ተስፋችንን በጠቅላላው እኛዊ ስሜታችንን የተጋራችልን ድንቅ ገጣሚም ናት አለምፀሀይ
ዛሬ ዛሬ ተቋማት በሙያና በልምድ ማነስ በሚዋዥቁበት ሰአት እንደ እሷ አይነቱ በባህል ሚኒስቴርነት ደረጃ ቢቀመጥ እንኳን ትርጉም ያለው ስራ መስራት የሚችል፤ ትጋቱንና ጥንካሬውን በጣይቱ ባህል ማእከል ያሳየ፤ ገና በወጣትነቱ በሀገር እና በአፍሪካ ደረጃ የደራሲያን ማህበር መምራት የቻለ ባለሙያ እያለን ሳንጠቀምበት ዘመን ማለፉ የሚቆጭ ነው። በተለይም እንደ ዋሽንግተን ዲሲ አይነት በፖለቲካ ልዩነት፤ በሀይማኖቱ መከፋፈል፤ በትውልዱ አለመከባበር፤ መግባባት ጠፍቶ መደነቋቆር በዝቶበት በነበረበት ከተማ ለአመታት ሁሉን እንደ አመሉ ችሎና አቻችሎ፤ ገፋ ባለ ግዜም ዘለፋና የስሜተኞችን አንደበት ታግሶ ሙያውን እያንቀሳቀሱ መኖር ቀላል አልነበረም። እውነት ለመናገር ስለሷ መመስከር የምችልበት አጋጣሚዎች ለአመታት ስፈልግ ወደ ሀገር የመግባቷን ዜና ስሰማ ከዚህ የተሻለ ወቅት የለም ብዬ ነው ጥቂት ስለእሷነቷ ለማለት የፈለኩት።
የዛሬ አስራ ሁለት አመት አካባቢ ኦክላንድ ካሊፎርኒያ ላይ በተደረገ የትያትር ፕሮግራም ተጋባዥ ሆና መጥታ እኔም በውጭው አለም የተውኔት አምሮቴን ለመወጣት መዳከር በጀመርኩበት አመታት ላይ ነበር ለመጀመሪያ ግዜ የተገናኘነው። በእለቱ ፕሮግራማችንን ማቅረብ ብንችልም ተቀራርቦ ለመተዋወቅና ለማውራት እድለኛ አልነበርኩም። የዛን እለት አለምፀሀይ ከዲሲ ወደ ሳንፍራንሲስኮ በምትበርበት ሰአት ኒው ዮርክ ላይ ታዋቂው ባለቅኔ ሎሬት ፀጋዬ ገ/መድህን ህይወቱ አልፎ ነበርና በተፈጠረው ያልተጠበቀ ሁኔታ ከባድ ሀዘን ውስጥ በመግባቷ ወድያውኑ ተመልሳ ለመሄድ ተገደደች። ይሁን እንጂ በቀጣይ ግዜያቶች አብሮ የመስራቱ ሁኔታ ተመቻችቶና በጣይቱ ማእከል በመታቀፍ ለአመታት የዘለቀ እስካሁንም ያልተቋረጠ ስራ በመላው አሜሪካ ካናዳና አውሮፓ ለማቅረብ ችለናል። በበረዶ ተጉዘናል፤ በፀሀይና በዝናብ ተመተናል፤ ከአንድ ሺህ በላይ ሰው ታድሞ ተውነናል፤ ከአስር ሰው በታች ሆኖብንም መድረክ ክቡር በመሆኑ ዝግጅታችንን አቅርበናል። የተዋናይ ልብስ ኤርፖርት ዘግይቶብን ልብስ እየተዋዋስን ሰርተናል፤ ተዋናይ ቀርቶብን በኢንፕሮቫይዜሽን ተረዳድተን አሳልፈናል። መብራት ተቋርጦ በስልክ ብርሀንና በሻማ ለመጨረስ ተገደናል፤ ከዲሲ አምስት ሰአት ተጉዘን ተውኔት አቅርበን እንደገና አምስት ሰአት ተመልሰን ዲሲ ገብተናል (ሾፌሯ አለምፀሀይ ነበረች)፤ ከምንም በበለጠ በተለይም በአውሮፓ ጉዞ የአለምፀሀይን የግሩፕ መሪነት በሚገርም ሁኔታ ተረድተናል። ቁጣዋን፤ ሳቅዋን፤ ፍቅሯን፤ ጠንካራነቷን፤ ብልህነቷን፣ ቆራጥነቷን አስተውለናል።
አለምፀሀይ ጠንካራ መሪ፣ የማትነጥፍ ገጣሚ እና የማትሰለች ተዋናይ በተለይም ለትያትር ሙያ የተፈጠረች እንስት ናት። ተፈጥሮ የሰጣትን ተሰጥኦ ከትምህርት እና ንባብ ጋር በማዋሀድ እራሷን በየግዜው ዝግጁ የምታደርግ ስትሆን የመፃፍ፣ የማዘጋጀት፣ በጠቅላላው የመምራት ብቃቷ ሙሉ ያደርጋታል። አለምፀሀይን ከአነስተኛ ጭውውት ጀምሮ እስከ ሼክስፒሩ ማክቤዝ ድረስ በውጭው አለም እራሷን የፈተነች ሲሆን በተለይም የራሷን ያክል የምትወዳት እና ህልሟም አድርጋ የያዘቻችን ጣይቱን መተወን ፍላጎቷም ብቃቷም ደስታዋም እንደሆነ ምስክር ነኝ።
“እኛ እባብን የምናጫውተው መርዙን ካስተፋነው በኋላ ነው” ስትል ቀልብ ትስባለች። “ጦርነቱን ብትፈልግ ነገ አድርገው . . . . .የኔ ሴትነትና ያንተ ወንድነት የሚለየው እዚህ ሚኒሊክ ቤተመንግስት ሳይሆን እዛው ጦርነቱ ቦታ ላይ ነው” ብላ በጣልያኑ ላይ ስትገሰልና ስትፎክር እያስመሰለች ሳይሆን ሆና እየተቆጣች፣ ቀጠሮ እየሰጠች፣ ስለሀገሯ እየተቆረቆረች፤ ሀገሯም ደርሳበት የነበረውን የሞራል ልእልና እያስተማረች ነበር፡፡
ከዚህ ውጭ ዓለም በማህበራዊ ግንኙነቷ ጎበዝ እና ለሌላው ትምህርት ልትሆን የምትገባ ናት። በሰፊው ስራዎቿ ማህከል የታመመ መጠየቅ፤ የወለደን መመልከት፤ ልደት መድረስ፤ ሀዘን ማስተዛዘን፤ የተጣላ ማስታረቅ የማይቀሩ ተግባራቶቿ ናቸው። በሁለት ሺህ አስራ ሁለት ጥቅምት ላይ የመጀመሪያ ልጄን ሳገኝ አንድ አመሻሽ ላይ ቴዎድሮስ ለገሰን እና ትግስት ንጋቱን ይዛ እኔና ባለቤቴን ሰርፕራይዝ ያደረገችንን በህይወት እያለሁ አልረሳውም። የዛን እለት ደንዝዤ መቅረቴ ጓደኞቼ ቴድና ቲጂ እስከዛሬ ይስቁበታል። በእርግጥም ያን ቀን ከሰርፕራይዙም በላይ ለኔ አለምፀሀይን በአመነችበትና በወደደችው ጉዳይ ምን ያህል ጥግ ድረስ መሄድ እንደምትችል የተረዳሁበት እለት ነበር።
ዓለም እንኳን እግዚአብሔር አምላክ፤ የድንግል ማርያም ልጅ እየሱስ ክርስቶስ በህይወት እና በጤና እያለሽ ሀገርሽን እና ህዝብሽን ለማየት ተስፋ ለሰንቅሽበት ዘመን አደረሰሽ። ምኞትሽን፣ ፍላጎትሽን እና ሆድ መባስሽን በቅርበት ሆኜ አየው ስለነበር ላንቺ ወደ ሀገር መመለስ ማለት ምን ማለት እንደሆነ እረዳለሁ። እናትን የምታክል ግዙፍ ነገር፣ አባትን ያክል ጥላ፣ ውድ ባለቤትን የመሰለ ትከሻ ማጣት ብሎም በመጨረሻዋ ሰአት በአካል ተገኝቶ መቅበር አለመቻል ከባድ ነገር ነው።
በሀገር ቤት ቆይታሽ ደስተኛ እንደምትሆኚ በመተማመን ጓደኞቻችን እና የጥበብ አባላቱ ካንቺ ጋር ጥሩ ሙያዊና ቤተሰባዊ ቆይታ ይኖራቸዋል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ። ቦን ቮዬጅ መልካም መንገድ።
እግዚአብሔር ኢትዮጵያንና ህዝቦቿን ይባርክ።
አበባየሁ ታደሰ

Happy
Happy
0 %
Sad
Sad
0 %
Excited
Excited
0 %
Sleepy
Sleepy
0 %
Angry
Angry
0 %
Surprise
Surprise
0 %
    Print       Email

Average Rating

5 Star
0%
4 Star
0%
3 Star
0%
2 Star
0%
1 Star
0%
<"Without the support of our readers, the Maleda Times website would not exist in its present form">

You might also like...

Ethiopia’s Media Under Siege Amid Escalating Conflict in Amhara

Read More →

This site is protected by wp-copyrightpro.com

Skip to toolbar