ኢንጂነር ስመኘው በቀለን ሞት አስመልክቶ ሊሰጥ የነበረው መግለጫ ለ3ኛ ጊዜ ተራዘመ
by: Zehabesha
(ዘ-ሐበሻ) የሰሌዳ ቁጥር ኮድ 3 አዲስ አበባ A 29722 በሆነው ቶዬታ ላንድ ክሩዘር መኪና ውስጥ በአዲስ አበባ አብዮት አደባባይ አካባቢ መኪናቸው ውስጥ ሞተው የተገኙት የኢንጂነር ስመኘው ሕልፈት አሁንም በአነጋጋሪነቱ በቀጠለበት ወቅት ስለ ሞታቸው ምክንያት ፌዴራል ፖሊስ እና ጠቅላይ አቃቤር ህግ ይሰጡታል የተባለው መግለጫ ዛሬም ለ3ኛ ጊዜ መራዘሙ ጉዳዩን የበለጠ እያጦዘው ሄዷል::
ረቡዕ ግንቦት 8 ቀን 2010 ዓ.ም. አሥር ሰዓት ላይ ከጸሐፊያቸውና ከሾፌራቸው ጋር ከአዲስ አበባ በስተምዕራብ 85 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምዕራብ ሸዋ ዞን አዳበርጋ ወረዳ፣ ልዩ ስሙ ረጂ በተባለ አካባቢ በሚገኘው የዳንጎቴ ሲሚንቶ ፋብሪካ አካባቢ የተገደሉት የዳንጎቴ ሲሚንቶ የኢትዮጵያ ፋብሪካ ዋና ሥራ አስኪያጅ ዲፕ ካማራ ገዳይ እና የኢንጂነሩ ገዳይ ተመሳሳይ ቡድን ነው እየተባለ በሚጠረጠርበት በአሁኑ ወቅት ፖሊስና ጠቅላይ አቃቤ ህግ ለኢንጂነር ስመኘው ሞት ይሰጡታል ተብሎ የሚጠበቀው ምክንያት ብዙዎችን ላያሳምን እንደሚችል ከሳምንት በፊት ዘ-ሐበሻ ዘግቦ ነበር:: ይህ መረጃ በዘ-ሐበሻ ከወጣ በኋላ ፖሊስና አቃቤ ህግ 3ጊዜ ስለ ኢንጂነሩ አሟሟት ሊሰጡት የነበረውን መግለጫ ሰርዘዋል::
አቃቤ ህግ እና ፌዴራል ፖሊስ ሰኔ 16 ቀን ለጠ/ሚ ዐብይ አሕመድ ድጋፍ ለመግለጽ በመስቀል አደባባይ በተጠራ ሰልፍ ላይ ስለተፈጸመው የቦምብ ጥቃት እና የአባይ ግድብ ዋና ሥራ አስኪያጅ የነበሩት ኢንጅነር ስመኘው በቀለ ሞት አስመልክቶ ዛሬ ጳጉሜ 1 ቀን 2010 ዓ.ም ሊሰጥ የነበረው መራዘሙ ይነገር እንጂ ለመቼ 4ኛ ቀጠሮ እንደተሰጠ ለማወቅ አልቻልንም::
ዶ/ር አብይ አህመድ የሰኔ አስራ ስድስቱ ፍንዳታና የኢንጂነሩ ግድያ በአስቸኳይ ተጣርቶ እንደሚነገር ቃል ገብተው ነበር:: የዳንጎቴ ሲሚንቶ ሥራ አስኪያጅ ዲፕ ካማራ, ሹፌራቸውና ጸሐፊያቸው ግድያ ጉዳይም 3 ወር ቢያልፈውም ምንም የተባለ ነገር የለም::
ወደ ስቱዲዮ እየገባን ባለንበት ወቅት በደረሰን መረጃ የኢንጂነር ስመኘው በቀለን አሟሟት እና የሰኔ 16 የቦምብ ጥቃት ምርምራን በተመለከተ ሊሰጥ የነበረው ጋዜጣዊ መግለጫ የተሰረዘው የፌደራል ጠቅላይ ዋና አቃቤ ህግ አቶ ብርሃኑ ጸጋዬ “አስቸኳይ ስራ” ስላጋጠማቸው ነው ተብሏል።
Average Rating