www.maledatimes.com ሴፕተምበር 11 በአሜሪካ ሰማይ!!! - MALEDA TIMES
Loading...
You are here:  Home  >  Ethiopia  >  Current Article

ሴፕተምበር 11 በአሜሪካ ሰማይ!!!

By   /   September 11, 2018  /   Comments Off on ሴፕተምበር 11 በአሜሪካ ሰማይ!!!

    Print       Email
0 0
Read Time:3 Minute, 20 Second

ሴፕተምበር 11 በአሜሪካ ሰማይ!! (BEDER MOHAMMEDNUR BEDER)

የዛሬው ቀን ለታላቋ አሜሪካ ታላቅነቷን የተፈታተነ ቀን ነበረ። ሴፕተምበር 11/2001 የዛሬ አስራ ሰባት አመት ገደማ ወደ ሗላ ስንመለስ ከቀኑ 10:28 ሰአት ገደማ በአሜሪካ ምድር ተገንብተው ለሰማይ የቀረቡ መንትያ ህንፃዎቿ ንጋቱ ላይ ድብርት እና ዱካክ ተደራርቦ ያለ ወትሮው አፍዟቸዋል። የቀን ውሏቸው ጥሩ እንዳልሆነ በሚያሳብቅ ስሜት በውስጥ ያለው ድባብም ከወትሮው በገበያው ተቀዛቅዟል ። ግና ሺዎች ለሸመታ ሲሉ በ1973 በኒውዮርክ ምድር በ (1,240,000 m2) ስፋትን በያዘው ህንፃ ላይ እላይ ታች ይላሉ። ከተገነባ የ50 አመቱን ልደት ለማክበር 5 አመት ቀርቶታልና የክፍለ ዘመኑን ግማሽ አጋመስኩ ሊያስብል እና በታሪክ ማህደር ስሙን ሊያኖር ቋምጧል። በኒውዮርክ ምድር ከሌሎች ሰማይ ጠቀስ ህንፃዎች ልቆና አለቅጥ እረዝሞ በቡዳ መበላቱን አላወቀም ነበረ። የቀን ውሎውን ውሎ የምሳውን እና የሻይውን ሰአት ከዱካኩ ለማምለጥ ሲነቃቃ አንድ አስደንጋጭ ነገር ተፈፀመ።
AA 11 እና UA 175 መለያቸው የሆኑ አውሮፕላኖች የጠዋት ድብርት ሊጥለው የሚያንገዳግደውን መንትያ ህንፃ እንደ ቅቤ አቅልጠው ሊያፈርሱት አቅጣጫቸውን ወደ እርሱ አደረጉና መክነፍ ጀመሩ።

ሺዎች አሁንም የሞት ድባብ በወረሰው የገበያ ስፍራ ግብይት ላይ ናቸው። AA 77 ስያሜን የያዘው ጢያራ ደግሞ በዚያች ቅፅበት ፔንታጎንን ወደ አመድነት ለመቀየር እየነጎደ ነው። AU 97 ጢያራም ወደ ሗይት ሀውስ ተተኩሳለች ።እጅግ በተጠና ሴራ አሜሪካ ክብሯን ልታጣ ቀረበ። ከእነ ሩስያና ከበለፀጉ ሃገራት ጋር ያላትን ተፎካካሪነት ላለማጣት ስትል ለደህንነቷ እንቅልፍ የሌላት ሃያል ሃገር ዛሬ ቀኗ ሊነጠቅ ነው። እንደ ሚግ የተተኩሱት አውሮፕላኖች ያን ግዙፍ ህንፃ ከደቡብ እና ከሰሜን በመጣ ውህድ በአንድ ምት አይበገሬውን ህንፃ ሽንጡን እንደ ወረቀት ቀደው ገቡ ። ያ ሰማይ ጠቀስ ህንፃ የክፉ ቀን ምርኩዝ አልነበረውምና ከነድንጋጤው ከወገቡ ሸብረክ ብሎ እሳት እንደነካው ቅቤ በደቂቃ ውስጥ ቀልጦ ከመሬት ሺህ ነፍሶችን እንደያዘ ወደቀ።
አሜሪካ ጭንቋ ከፍ አለ ወደ ሌላ ታርጌት ያቀኑት ጢያራዎች አንዱ ከሸፈ አንደኛው መጠነኛ ስኬትን ተጎናፀፈ። ጥቃቱን አልቃኢዳ ፈፀመው የሚል ዜና በሚዲያዎች ተራገበ። በህንፃው ከነበሩ ሸማቾች 2,996 ያህሉ ያልጠበቁትን የሞት ፅዋ ተጎንጭተው ከወጡበት ቀዬያቸው ሳይመለሱ ቀሩ። 6,000 ያህል ሸማቾችም ለአካል ጉዳት ተጋለጡ። የመሰረተ ልማትና የንብረት ጉዳቷ በብር ሲሰላ አስር ቢሊዮን ዶላር ክስረት ገጥሟታል።በዚህ ያልታሰበ አደጋ ሃያሏ አሜሪካ ትርምስምሷ ወጣ ። ተቀናቃኝ ሃያላን ሃገራትም የልብና የደም ዝውውራቸው ላፍታ ቆሞ ባለማመን ስሜት ስለ ጉዳዩ እውነታ ለማወቅ ሽር ጉድ ጀመሩ። የአሜሪካ የደህንነት ቢሮ በዚህ ጥቃት 15 ወይም 19 ያህል ቁጥር ያላቸው የአልቃኢዳ አባላት እጃቸው እንዳለበት ደርሰንበታል አሉ ። ዜግነታቸውም ከሳኡዲ አረቢያ ፣ ከዩናይትድ አረብ ኢሜሬት ፣ ከግብፅ እና ከሊባኖስ ናቸው የሚል ሃሜትም ተሰማ።

የ26 አመቱ ሳኡዲያዊው ተወላጅ ኻሊድ አል- ሙሃድርና የ26 አመቱ ነዋፍ አልሃሚዚ ባልተሳካው AA 77 አውሮፕላንን ይዘው ፔንታጎንን ሊያደባዩ እንደነበረ አንዳች ማረጋገጫ አገኘን አሉ ።
ሌላው የመንትዮቹን ግብዳ ህንፃን ለማውደም የበስተሰሜኑን አቅጣጫ ይዞ የህንፃውን ሽንጥ ክፉኛ የጎመደው በዚህም እራሱን ያጠፋው የ33 አመት ወጣት ግብፃዊ መሀመድ አል-ሳይድ አታ መሆኑም ሌላ መረጃ ይፋ ወጣ። መርዋን ዩሱፍ የኢሜሬት ተወላጅ ሲሆን ከደቡብ አቅጣጫ AU 175 የተባለውን ጢያራ እንደጉድ አክንፎ ከሰሜን አቅጣጫ በሃይል የተመታውን ህንፃ በዚህም በኩል እንደ ደገመው ይፋ ሆነ። ሌላው UA 93 ጢያራን በማብረር ስኬት አልባ ጥቃት ያደረሰው ደግሞ የቤሩት ዜግነት ያለው የ26 አመቱ ወጣት ዚያድ ጀራህ ነበረ አሉ። በጨረሻም AA 77 የስኬት አልባ ጢያራን ያበረረው ሳኡዲያዊው የ29 አመት ወጣት ሃኒ ሳልህ ሁሴይን እንደነበረ ለአለም ሚዲያና ላቆቦቆቡ ጆሮዎች ሚዲያ ይፋ ሆነ ። ከዚያ የወቅቱ ፕሬዝዳንት ጆርጅ ደብሊው ቡሽ በጥቃቱ ትክን ብክን ብለው ለጋዜጠኞች በተንተባተበ እና ፍርሃት ባወየበው የሞራል ስሜት ሰጥመው አሜሪካ የሉአላዊነቷን ክብር መልሳ ለማግኘት ጉልበቷን በጠረጠረቻቸው ሃገራት ሜዳ ያበደ ጦርነት ከፍታ ልክ ልታስገባቸው እንደምትችል በቁጣ ተናገሩ። ያም ታሪካዊ ቃል ” ይህ የመስቀል ጦርነት ነው። ከእኛ ጋር ያልሆነ ከእነርሱ ነው” ብለው መግለጫ ሰጡ። ከሰአታት በሗላ ከአለም በጎረፈ ጩኸት የመስቀል ጦርነት የምትለዋን ሃረግ ፍቀው በቀረው አቋማቸው ግን እንደሚቀጥሉ ዛቱ። አገራቶች ከአሜሪካ ጋር አበሩ ።አሜሪካም የአልቃኢዳ ህዋስ አለ ወዳለችበት አፍጋኒስታን ጦሯን ልካ አፍጋኒስታንን የከሰል ምድጃዋ አደረገቻት። ከዚያ ለአሜሪካ አስጊ የተባሉ ሃገራትና መሪዎች የራቀና በጥልቅ የተቆፈረ ጉድጓድ ተምሶላቸው እንዲገቡ ተደረገ። ሳዳም ሁሴን ሙሃመድ ጋዳፊ የሴፕተምበር 11 ምት የበቀሉ ሁነኛ በግ አደረጋቸው። የሙስሊሙ አለም የተፈጠረውን ነገር አንዱን ሰበዝ ይዞ ኩርኩሙን ይቀበል ያዘ ። ያኔ የተፈጠረው የጭንቅ ገመገም ዛሬ ላይ የብዙ ሃገራቶችን ደህንነትን ይበልጥ ለማጠንከር መሰረት ሆነ። ብልጦቹ ከአደጋው ይህን ሲማሩ በፍርሃት የራዱት የአረብ ሃገራት መሪዎች ደግሞ የራሳው ጉዳይ እየጠላለፋቸው በሰልፍ ተራ በተራ መበላታቸውን ቀጥለውበታል። በሚገርም ሁኔታ በጉልበቴ የጎዱኝን እጎዳለሁ ያለችው ሃገር ዛሬ 17 የሙት አመታቸውን ስታከብር ይህን ቂም ለመበቀል የጀመረችው ጦርነት ግን አላለቀም። እስካሁን ላላሸነፈችው ፍልሚያ ያወጣችው ገንዘብ በሂሳብ ባለሙያዎች እንቅጩ ሲነገር ያስደነግጣል።
ሃያሏ አሜሪካ ለኢራቁ ለአፍጋኒስታኑ እና ለሶርያው የእርስ በእርስ ማጋጫ ያወጣችው ፍራንክ 1,5 ትሪሊዮን ነው።
ያሳትር ያረብ………

Happy
Happy
0 %
Sad
Sad
0 %
Excited
Excited
0 %
Sleepy
Sleepy
0 %
Angry
Angry
0 %
Surprise
Surprise
0 %
    Print       Email
  • Published: 6 years ago on September 11, 2018
  • By:
  • Last Modified: September 11, 2018 @ 11:51 pm
  • Filed Under: Ethiopia

Average Rating

5 Star
0%
4 Star
0%
3 Star
0%
2 Star
0%
1 Star
0%
<"Without the support of our readers, the Maleda Times website would not exist in its present form">

You might also like...

በሰሜን ሸዋ ዞን ኤፍራታ እና ግድም ወረዳ መከላከያ ከአማራው ማህበረሰብ እና ከፋኖ ጋር ጦርነት ገጥሟል

Read More →

This site is protected by wp-copyrightpro.com

Skip to toolbar