በዛሬው ዕለት ከጋሞ ጎፋ ዞን አስተዳደር ማዕከል ፣ ከ9 ወረዳዎች እና አርባምንጭ ከተማ አስተዳደር የመንግሥት ስራ ኃላፊዎች ፣ የሕዝብ ተወካዮች ፣ የሀገር ሽማግሌዎች እና ወጣቶች በመገኘት የተፈናቀሉ ወገኖችን ጄነራል ዊንጌት ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ ፣ መድኃኔአለም መሰናዶ ት/ቤት ፣ አስኮ ቃሌ 1ኛ ደረጃ ት/ቤት ፣ አስኮ ፊ/ ሀብተጊዮርጊስ መጀመሪያ ደረጃ ት/ቤት ፣ አስኮ ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት ፣ ፊሊጶስ የመጀመሪያ ደረጃ ት/ቤት እና በሌሎች ት/ቤቶች ያሉ የተፈናቀሉ የጋሞ ተወላጆችን ጎብኝተዋል ።

ተፈናቃዮችን በጠየቁበት ወቅት የዞኑ አስተዳዳሪ አቶ እሳያስ እንድሪያስ እንደገለፁት የጋሞ ብሔር ትጉህ ሠራተኛ ፣ የሰው የማይነካ እና ለበቀል የማይነሳሳ ባህሉን አክባሪ ሕዝብ መሆኑን ጠቅሰው በዚህ ሕዝብ ላይ ኢ- ሰብዓዊ ድርጊት የፈፀሙ አካላት ለሕግ ቀርበው ውሳኔ እንዲያገኙ ለመንግሥት ጥሪ አቅርበዋል ።
የዞኑ አስተዳደር ፣ 9ኙ የጋሞ አካባቢ ወረዳዎች እና የዞኑ ልማት ማህበር የ5 ሚሊዮን ብር ድጋፍ ማድረጋቸውን አቶ እሳያስ ገልፀዋል ።
የጋሞ ሀገር ሽማግሌዎችም በብሔሩ ባህል መሠረት ጋሞ እርጥብ ሣር ነጭቶ ፀብን ወደ ሠላም ጥልን ወደ እርቅ የሚለውጥ ኩሩ ባህል ያለው በመሆኑ ወጣቶች በስሜት ተነሳስተው ወዳልተፈለገ ግጭት ውስጥ እንዳይገቡ አሳስበዋል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች እና ወጣቶች ከተጎጂዎች ጎን ሆነው ላደረጉት በጎነት ምስጋና አቅርበዋል ።
ሚዲያዎችም በዜጎች ላይ የደረሰውን ጉዳት እና የሚደርሰውን ችግር እውነታውን በመዘገብ እነዚህ ወገኖች የሚረዱበትን ሁኔታ እንዲያመቻቹ ጥሪ ቀርቦላቸዋል፡፡
Average Rating