Maleda Times Media Group
ታምሩ ጽጌ
ሰኔ 16 ቀን 2010 ዓ.ም. በመስቀል አደባባይ በተፈጸመው የቦምብ ጥቃት የተጠረጠሩ አምስት ግለሰቦች የሽብርተኝነት ክስ ተመሠረተባቸው፡፡
በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ተረኛ ወንጀል ችሎት ዓርብ መስከረም 18 ቀን 2011 ዓ.ም. ክሱን ያቀረበው ዓቃቤ ሕግ፣ የቦምብ ጥቃቱ የተፈጸመው ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ለመግደል መሆኑን በክሱ አስታውቋል፡፡
በቦምብ ጥቃቱ ክስ የተመሠረተባቸው ተጠርጣሪዎች አቶ ጌቱ ግርማ፣ አቶ ብርሃኑ ጃፋር፣ አቶ ጥላሁን ጌታቸው፣ አቶ ባህሩ ቶሎሳና አቶ ደሳለኝ ተስፋዬ ናቸው፡፡
ዓቃቤ ሕግ ለፍርድ ቤቱ ባቀረበው ክስ እንደገለጸው፣ ተከሳሾቹ በጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ ላይ ግድያ ለመፈጸም ያነሳሳቸው በእሳቸው የሚመራ መንግሥት መኖር ስለሌለበት ነው፡፡ የአገሪቱ መንግሥት መመራት ያለበት ቀድሞ በተመሠረተው የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) ነው የሚል ዓላማ ተከሳሾቹ እንዳላቸው ዓቃቤ ሕግ በመሠረተው ክስ ጠቁሟል፡፡
በተጨማሪም ጠቅላይ ሚኒስትሩ በኦሮሞ ሕዝብ ዘንድ ተቀባይነት የላቸውም በማለትም፣ ተጠርጣሪዎቹ ለግድያ መነሳሳታቸውን ዓቃቤ ሕግ አስታውቋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአሜሪካ ኮንግረስ የፀደቀውን ኤችአር 128 ለማስፈጸምና በስመ ሕዝበኝነት የራሳቸውን ዓላማ የሚያራምዱ መሆናቸውን፣ በዚህም ምክንያት የኦሮሞን ሕዝብ ፍላጎት ስለማያስፈጽሙ ተጠርጣሪዎቹ ጥቃቱን ለመፈጸም መነሳሳታቸቸውን ዓቃቤ ሕግ በክሱ አክሏል፡፡
የሰኔ 16 ቀን 2010 ዓ.ም. የመስቀል አደባባይ የወንጀል ድርጊት ያቀነባበረችው በኬንያ ናይሮቢ የምትገኝ ገነት ታምሩ (ቶለሺ ታምሩ) የምትባል መሆኗን፣ ዓቃቤ ሕግ በክሱ አመልክቷል፡፡
በመስቀል አደባባይ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ድጋፍና ምሥጋና በተደረገ ሥነ ሥርዓት ላይ በተፈጸመ የቦምብ ጥቃት ሁለት ግለሰቦች ሲሞቱ፣ ከ150 በላይ ጉዳት እንደደረሰባቸው ይታወሳል፡፡
Average Rating