Reyot – ርዕዮት
ይመኑኝ ጠቅላይ ሚኒስትር፤ ክልላዊ አስተዳደርን ከብሄር ጋር የደባለቀው ህገመንግስቱ እንጂ ዜጎች አይደሉም፡፡
ቴዎድሮስ ጸጋዬ
ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር፣ የኢህአዴግን ጉባኤ ሲከፍቱ ያደረጉትን ንግግር ሰማሁ፡፡ በመልካም ቃላትና አረፍተነገሮች በጎ መንፈስ በሀገራችን ለማስፈን ያደረጉትን ሙከራ ተመልክቻለሁ፡፡ እሰየው፡፡ ነገር ግን፣ ክልላዊ አስተዳደርን ከብሄር ጋር አናምታታ ብለው ማለትዎን አየሁና ድምጼን ላሰማ ተነሳሁ፡፡
እውነት እውነት እልዎታለሁ፡፡ ይህንን ክልላዊ አስተዳደርን ከብሄር የመቀላቀል ቅሌት የሰራው የድርጅትዎ ግራ ርዕዮትና ከዝያ የተወለደው ህገመንግስት ነው፡፡
1) ገና ሲጀምር የህገመንግስቱ ተዋዋዮችና ቃልኪዳን አሳሪዎች አድርጎ የጠቀሳቸው ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችንና ህዝቦችን ብቻ አይደለምን; እነኚህ አካላት ስንት ህዝብ ሲያካትቱ፣ ምን አይነት ስነልቡና ሲኖራቸውና እንዴት ሲሰፍሩ ይህን “ብሄር
“ “ብሄረሰብ” ወይም “ህዝብ” የሚል ስያሜ እንደሚያገኙ እራሱ ህገመንግስቱ ባያውቀውም፡፡ ነገር ግን ስላቁ ይገባናል፡፡ ህገመንግስቱ ብሄር፣ ብሄረሰብ ወይም ህዝብ ሲል የህገመንግስቱ ፈጣሪ የሆነው ኢህአዴግ እራሱን፣ ብሄራዊ ድርጅቶቹንና አጋር አሻንጉሊቶቹን እንዲሁም በኋላ ለስልጣኑ ሲያሰጉት ከአገር ያባረራቸውን ጽንፈኛ ተገንጣይ ቡድኖችን መሆኑ አይጠፋንም፡፡
2) ይህ ህገመንግስት ከብሄር በቀርስ ሌላ ማንነት ያውቃልን? አንድ ዜጋ በአፍ መፍቻ ቋንቋው መማር መዳኘቱ ሰብአዊ መብቱ እንጂ ከመንግስት የሚሰጠው ልዩ ስጦታ እንዳይደለ አምናለሁ፡፡ ነገር ግን በኢትዮጵያችን ያለው ማንነት የብሄር ብቻ ይመስል ህገመንግስቱን፣ አስተዳደራዊ መዋቅሩን፣ ፖለቲካውን፣ የትምህርት ስርዐቱን ወዘተ በብሄርና ብሄር ብቻ እንዲቃኝ መደረጉ የህወሀትና የኦነግ ይቅር የማይባል ጥፋት ነው፡፡
3) በዚሁ የመከራ ህገመንግስት አንቀጽ 8 ላይ ሉአላውያን ወይም የራሳቸው ሉአላዊነት ያላቸው ስለመሆናቸው የተደነገገው ካለእነኚህ ብሄር፣ ብሄረሰብና ህዝብ በቀር ሌላ ስለማን ነው? ታድያ ከዚህ ህገመንግስት በላይ አገራዊ አንድነትን የሚያፈርስና ኢትዮጵያን ከአንዲት የተዋሃደች አገርነት ወደጥቃቅን አገራት ክምችት የቀየረ ተወቃሽ ከየት ይመጣል?
4) ከዚህ ለዜጎች ሳይሆን ለብሄሮች… ሉአላዊነት ከሚያጎናጽፍ ግራ ህገመንግስትና አንቀጽ ማህጸንም ለየብሄሩ መገንጠልን የሚፈቅድ አንቀጽ ተወልዶ በህገመንግስቱ ሰፍሮ እንደሚገኝ መቼም ይዘነጋዎታል ተብሎ ሊታመን አይችልም፡፡ ይህም፣ የአገር ህልውና ስግብግብና ጽንፈኛ በሆኑ እኩይ ተጽእኖ አሳዳሪ የዘውግ ፖለቲከኞች እጅ የወደቀ እንዲመስል አድርጎታል፡፡ ሀገር፣ እንዳትነጣጠል ሆና የተዋሃደች ሳትሆን ማንም “ደበረኝ” ሲል ጥሏት የሚወጣ ገርበብ ተደርጋ የተተወች ደሳሳ ቤት እንድትሆን የተደረገው በዚህ ህገመንግስትነው፡፡ ስለዚህም ክልላዊ አስተዳደርን ከብሄር ማንነት እንዳይለይ አድርጎ የዘረጋውና ከብሄር ማንነት በላይ ለሌሎች ማንነቶች አይኑ የታወረው ይህ ህገመንግስት ነውና ጣትዎን እዚህ አሜሪካ መጥተው በጎበኙን ጊዜ “ባይሻሻል እመርጣለሁ” ባሉት ህገመንግስት ላይ ብቻ ይቀስሩ፡፡
5) ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር፣ ብዙ ጊዜ ስለዜጎች በአገራቸው ያሻቸው ቦታ ተንቀሳቅሶ፣ ሰርቶና ሀብት አፍርቶ የመኖር መብት ሲናገሩ እሰማለሁ፡፡ ይገርምዎታል፤ እኔ በዚህ ሃሳብዎ አልስማማም፡፡ ምክንያቱም፣ ተንቀሳቅሶና ሰርቶ ሀብት አፍርቶ የመኖር መብትማ የማናቸውም የመኖርያ ፈቃድ ያገኙ ስደተኞች እንጂ የዜጎች መብት አይደለም፡፡ የዜጎች መብት ከዚህ በእጅጉ ይልቃል፡፡ የዜጎች መብትማ የአገር ባለቤትነት መብት ነው፡፡ አንድ ኢትዮጵያዊ ከአንዱ ወደሌላው የአገሩ ግዛት ሲንቀሳቀስ እየተሰደደ አይደለምና ያለው መብት ተንቀሳቅሶ ሰርቶና ሀብት አፍርቶ በመኖር ብቻ መገለጡ ዜግነትን ያሳንሳል፡፡ ይህም በአንድ ኢትዮጵያዊና ከደቡብ ሱዳን ወይም ከኤርትራ ወይም ከሌላ ስፍራ በመጣ ስደተኛ ተጠላይ መሀል ያለውን የመብት ልዩነት የሚያጠፋ ነው፡፡ ታድያ በተለያየ ጊዜ ዜጎችን ማፈናቀል እንደማይገባ ሲናገሩ “የጎሮቤት አገራትን ስደተኞች እንኳ እንቀበል የለ” አይነት ንግግር ሲያደርጉ ልቤን ቅር ይለዋል፡፡ የዜጎች መብት ከዜግነታቸው እንጂ እዚያ በተሳሳተ ርዕዮትና ትርክት ቀድመው እንደሰፈሩ ከሚያምኑ ቡድኖች ቸርነት ሊመነጭ አይችልምና፡፡ ዜግነት ከገዛ አገር ጋ ያለ ልዩ ቃልኪዳንና ውድ ቁርኝት ነውና እንደአንድ ኢትዮጵያዊ በገዛ አገሬ ያለኝ መብት ከስደተኞች ጋር መነጻጸሩን ወይም መስተካከሉን ልቤ አይፈቅደውም፡፡ በሰው አገርም በእኔው አገርም ስደተኛ ሆኜ እንዴት እችለዋለሁ? ሆኖም፣ ይህም ጠማማ እይታ ከምን እንደመነጨ ያውቃሉ? ከዚህ ጭንጋፍና አገር አፍራሽ ህገመንግስት፡፡ የዚህ ህገመንግስት ውላጆች የሆኑት የየክልሎቹ ህገመንግስቶችም በየክልሉ ያሉ ህዝቦችን ነባርና መጤ ብለው የሚከፍሉ፣ ነባር ለሚሏቸው ደግሞ በዝያ ክልል መሬትም ሆነ ሀብት ላይ ሌላው ዜጋ የሌለውን የልዩ ባለቤትነት መብት የሚሰጡ ሆኑ፡፡ ይኼ፣ ሰሞኑን ያየነው “አዲስአበባ የእኔ ብቻ ናት፣ ሌሎቻችሁ ነዋሪዎች እንጂ ዜጎች አይደላችሁም” የሚል የኦሮሞ ድርጅቶች ዳንኪራም አንዱ ምንጭ የዚህ ህገመንግስት ነጣጣይ መንፈስ ነው፡፡ ልብ ይበሉ ጠቅላይ ሚኒስትር፣ የእነኚህ ድርጅቶች አስነዋሪ አዋጅ ህገመንግስታዊ ነው አላልኩም፡፡ የማወራው ግን ህገመንግስቱ በሀገሪቱ ስላረበበው የ“እኔ ብቻ” መንፈስ ነው፡፡ ስለዚህም ባለፉት 3 አስርት አመታት ገደማ በመላ አገሪቱ በዜጎች ላይ የሚደርሰው መፈናቀልና የአገር ውስጥ ስደት እዚህም እዝያም ባሉ ግለሰቦች ስህተት የተከተለ ሳይሆን፣ ህገመንግስት ሰራሽ፣ መዋቅር ሰራሽና ስርአት ወለድ ነው፡፡ መፍትሄውም የህገመንግስት፣ የመዋቅርና የስርአት ለውጥ ነው፡፡
6) እስኪ ያስቡት ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር፣ በአንድ “የራሴን ቋንቋ ብቻ እናገራለሁ” በሚልና ከሌሎች ኢትዮጵያውያን ወገኖቹ ጋር የሚግባባበትን አማርኛ ቋንቋን ባለመማር ለብሄሩ መብት አስተዋጽኦ የሚያደርግ የሚመስለውን ምስኪን ወጣት ያስቡት፡፡ ይህ ወጣት፣ ሌሎች ወገኖቹን እንዳይገነዘብና ወገኖቹም እርሱን እንዳይገነዘቡት በቋንቋ ግድግዳ ተለይቶ፣ ብሄር ባለው ቢሮክራሲ ተነጥሎ፣ ብሄር ባለው ባንዲራ ተከልሎ፣ በከፋፋይ ትምህርት ተጋርዶ በየት በኩል ኢትዮጵያ በልቡ ሰሌዳ ትጻፍ? ይህንን የቋንቋ፣ የመዋቅር፣ የቢሮክራሲ፣ የትምህርት ስርአት፣ የባንዲራ፣ የፕሮፖጋንዳና የህግ አጥር ተሻግሮ በምን አቅሙ ወደኢትዮጵያዊነት ይደግ? እንዴት ብሎ ኢትዮጵያ ሰገነት ላይ ይውጣ? ይህ ወጣት፣ የሰው ልጅ ታሪክ በአጼ ምኒሊክ የተጀመረ ይመስል፣ ዳግማዊ አጼ ምኒሊክና አባታችን አዳም ቢምታቱበት እንዴት እንፍረድበት? ይህ ስርአታዊና መዋቅራዊ ህመም ነውና በባህል ትውውቅ መድረኮችና በአገርህን እወቅ ክበባት አይፈወስም፡፡
ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር፣ ሀገራችንን በውስጥ መፈናቀል ባለፉት አመታት በጦርነት አፈር ድሜ ከምትበላው ከሶርያ እንኳ እንድትበልጥ ምክንያት የሆነው፣ የአንድ አገር ዜጎችን በማያቋርጥ የእለትተእለት ሽኩቻ ውስጥ የዘፈቀን፣ ህይወቱን በእኛ ልዩነት ላይ የመሰረተውና የጋራ የኖሩ ኢትዮጵያዊ እሴቶቻችንን ይበልጥ እንዳናበለጽግ ገደል ሆኖ የነጣጠለን ይኸው ህገመንግስትና አስተዳደራዊ መዋቅር ነው፡፡ እመሀላችን ሆኖ ግጭት የሚያቀጣጥለው፣ ልዩነት የሚያባብሰው፣ የአገርን ወደፊት የሚያጨልመው፣ አንድነታችንን ቀስ በቀስ በልቶ እዚህ ያደረሰን የታቀፍነው እሳት ይኸው በንግግርዎ ያልጠቀሱት፣ በለውጥ አጀንዳዎም ስፍራ ያልሰጡት የዘር መዋቅርና ህገመንግስት ተብዬ ነው፡፡ ዙርያ ዙርያውን አይሂዱ፡፡ ሸረሪቷ ሳለች እለት እለት ድሩን መጥረግ ምን ይረባል ብለው? ዝሆኑ ችግር ሊድጠን በደረስንበት፣ ስለዚህ ዋና ጭብጥ ሳያነሱ፣ እኛን ዜጎችዎን ስለግብረገብና ሞራል ሲሰብኩን ቢውሉ ምን ይፈይዳል? ያጣነው ስር ተከል መሰረታዊ ለውጥ እንጂ የግለሰቦች በጎ ፈቃድ አይደለም፡፡ ግለሰብ በስልጣኑ ሲባልግ ወይም በስነምግባር ሲጎድፍ በስርአትና በተቋም ያርቁታል፡፡ ስርአትና መዋቅር ሲጎድፍስ?
እውነት እውነት እልዎታለሁ፤ ይህንን ግልጽ ችግር የማያምንና ለዚህ መፍትሄ የማይሻ፣ ስለዚህም መከራ ሰነድ “ህገመንግስት”ና ይኸው ስለወለደው የዘር መዋቅር መለወጥ የማይወያይ ጉባኤ ለኢትዮጵያ መዳንን ሊያስገኝ ከቶ አይችልም፡፡
አመሰግናለሁ፡፡
ሰላምዎ ይብዛ፡፡
Average Rating