www.maledatimes.com ‹‹ጦብላሕታ›› – ቀዳሚዋ የኢትዮጵያ ሥነ ጽሑፍ? - MALEDA TIMES
Loading...
You are here:  Home  >  Addis Admas  >  Current Article

‹‹ጦብላሕታ›› – ቀዳሚዋ የኢትዮጵያ ሥነ ጽሑፍ?

By   /   November 10, 2018  /   Comments Off on ‹‹ጦብላሕታ›› – ቀዳሚዋ የኢትዮጵያ ሥነ ጽሑፍ?

    Print       Email
0 0
Read Time:6 Minute, 10 Second

  1. ‹‹ጦብላሕታ›› – ቀዳሚዋ የኢትዮጵያ ሥነ ጽሑፍ?

‹‹ጦብላሕታ›› - ቀዳሚዋ የኢትዮጵያ ሥነ ጽሑፍ?
ከ123 ዓመት በፊት የታተመው የጉዞ ማስታወሻ

ኪንና ባህል

‹‹ጦብላሕታ›› – ቀዳሚዋ የኢትዮጵያ ሥነ ጽሑፍ?

31 October 2018ሔኖክ ያሬድ

ኢትዮጵያውያን ከራቀው ዘመን አንስቶ በየዓረፍተ ዘመኑ ወደ መካከለኛ ምሥራቅና አውሮፓ ቅዱሳት ሥፍራዎችን ለመሳለም፣ እንዲሁም ለመጎብኘት ይጓዙ እንደነበር ይታወቃል፡፡ በተለይ ወደ ኢየሩሳሌም (እሥራኤል) ሆነ ወደ ሮም (ጣሊያን) በካይሮ (ግብፅ) በኩል የማቅናታቸው ሰበብ ጉዞው በመርከብ በመሆኑ ነው፡፡

በ15ኛ ምዕት ዓመት በተለይ ወደ ሮም ካቀኑት ሊቃውንት መካከል ለአውሮፓ ምሁራን ስለኢትዮጵያ ባህልና ቋንቋ ያስተምሩ ያሳውቁ እንደነበር ይወሳል፡፡ የሃይማኖትና የሰዋስው መጻሕፍት እንዲሁም መዝገበ ቃላት ከውጭ ምሁራን ጋር ሆነው ሲያሳትሙ፣ ከአገራቸው ባህር ማዶ እስከዘለቁበት እንዲሁም ስለ አውሮፓው ኑሮአቸው መጻሕፍት ያሳተሙ ስለመኖራቸው አይታወቅም፡፡

ይሁን እንጂ በ19ኛው ምዕት ሮም ጎራ ያሉት ደብተራ ፍሥሐ ጊዮርጊስ ዐቢየዝጊ የጉዞ ማስታወሻ በማሳተም ረገድ ቀዳሚ ተጠቃሽ ናቸው፡፡ ‹‹ጦብላሕታ ብዛዕባ ወሬ መንገዲ እንካብ ጦቢያ ንኢጣሊያ›› የሚል ረዥም ርዕስ ያለው መጽሐፉን ወደ አማርኛ በተረጎሙትና መግቢያም በጻፉለት ዶ/ር ኃይሉ ሃብቱ አገላለጽ ጉዞ፡- ከጦብያ ወደ ኢጣሊያ ይሰኛል፡፡ ከመቶ ሃያ ሦስት ዓመት በኋላ ለሦስተኛ ጊዜ በቅርቡ ታትማ ለአደባባይ ውላለች፡፡

‹‹ይህቺ መጽሐፍ እንደ ጉዞ ዘጋቢ መጽሐፍነት ብቻ ሳይሆን፣ እንደ ሥነ ጽሑፍም በማንኛውም የኢትዮጵያ ቋንቋ ከመጀመሪያዎቹ አንዷ ናት፤›› ይላሉ፡፡ ስለቀዳሚነቷ ጣሊያናዊው ተመራማሪ ላንፍራንኮ ሪቺም፣ ‹‹ጦብላሕታ ከመላው ዘመናዊ የኢትዮጵያ ሥነ ጽሑፍ ቀዳሚዋ ናት (በትግርኛም ቢሆን በአማርኛ)›› በማለትም ገልጸውታል፡፡

ይህች አጠር ያለች ግን ባለ ረጅም ርዕስ ጽሑፍ ፍስሓ ጊዮርጊስ በክረምት ወራት (በአውሮፓውያን ዘንድ የበጋ ወራት) በ1890 ዓ.ም. ከምፅዋ ወደ ናፖሊ በመርከብ ከናፖሊ ወደ ሮማ ደግሞ በ‹‹ሠረገላ ጢስ›› [ባቡር] ስላደረጉት ጉዞ የምትተርክ፣ እንዲሁም በውስጧ ጉዞው ያሳደረባቸውን ስሜትና አጠቃላይ ትዝብቶቻቸውን እንዳካተተች ተገልጿል፡፡

የተነሱበት ቀን ማለትም ሰኞ ይሁን ረቡዕ ወይንም ሐሙስ ወዘተ አይግለፁ እንጂ፣ ወሩንና ዕለቱን ሰዓቱን ግን በውል ገልጸውታል፡፡ ‹‹በሐምሌ ልደታ በስምንት ሰዓት ከምፅዋ ወደ ጣሊያን ጉዞ ጀመርን፡፡››

ከምፅዋ እስከ ናፖሊ በጠቅላላ ዐሥር ቀን ሲፈጅባቸው በይቀጥላልም በናፖሊና በቸካኖ ከተማ አምሰት ቀን ከቆዩ በኋላ በሁለተኛ ሳምንታቸው ሮም ገብተዋል፡፡

እንደ ዶ/ር ኃይሉ አገላለጽ፣ ፍስሓ ጊዮርጊስ ለትግርኛ ሥነ ጽሑፍ የመጀመሪያውን የመሠረት ድንጋይ የተከሉ ናቸው፡፡ ጽሑፎቻቸውም በጥልቀት ሊጠኑ ስለሚገባ ለመፃእያን ተመራማሪዎች ተገቢ ዓውደ ጥናት መሆናቸው አይቀሬ ነው፡፡

​​​​‹‹ጦብላሕታ›› - ቀዳሚዋ የኢትዮጵያ ሥነ ጽሑፍ?
ዶ/ር ኃይሉ ሃብቱ

የፍስሓ ጊዮርጊስ የሕይወት ታሪክ

ፍስሓ ጊዮርጊስ ትውልድ አገራቸው የሓ ነው፡፡ የአገሬው ሰዎች የሓ ‹‹ዓዲ ዓርባዕተ ዙፋን›› (የዓራት ዙፋን አገር) ተብላ ትጠራ እንደነበር ቢናገሩም፣ በዘመን ሚዛን ለታሪክ ቀረብ የሚሉት ፍስሓ ጊዮርጊስ ግን የሓ ‹‹ዓዲ ክልተ ዙፋን›› (የሁለት ዙፋን አገር) ትባል ነበር ይላሉ፡፡

የተወለዱት በ1868 ዓ.ም. በስንኩሑና፣ የሓ ሲሆን፣ የሞቱት ደግሞ በ1931 ዓ.ም. በ63 ዓመታቸው ዓዲ ዜኑ በምትባል በሠራዬ በምትገኝ አንድ የኤርትራ መንደር ውስጥ ነው፡፡ እንደ ዶ/ር ኃይሉ ማብራሪያ መጀመሪያ ግዕዝ ተምረው፣ ከዚያም ገና አገር ቤት ሳሉ ፈረንሣይኛን አውቀው፣ ዓረብኛንም ጀምረው ነበር፡፡ ወደ ጣሊያን ጉዞ ሲጀምሩ ገና የሃያ ሁለት ዓመት ጎበዝ ብቻ ነበሩ፡፡

ከአገራቸው ከመውጣታቸው በፊት ብዙ ዓመታት የሚወስደውን የግዕዝ ትምህርት አጠናቀው ነበር፡፡ በተጨማሪም ጣሊያን ከመሄዳቸው በፊት የፈረንሣይኛ ቋንቋን እየተማሩና እያጠኑ እንደነበርና በቋንቋውም መግባባት ይችሉ እንደነበር፣ ከጉዞ ትረካቸው ጽሑፍ መረዳት ይቻላል፡፡ ‹‹አንድ ሰርጀንት ጊዜ ሲያገኝ ሁልጊዜ ከኔ ጋር በፈረንሣይኛ ይጫወት ነበር፡፡››

አውሮፓ ከመሄዳቸው በፊት በመጠኑ ዓረብኛም ያውቁ ነበር ብሎ ደፍሮ መናገር እንደሚቻል ዶ/ር ኃይሉ ያመላከቱበትና ከጽሑፋቸው የወሰዱት የሚከተለውን ነው፡፡

‹‹ከኔ በቀር ሌላ ጦብያዊ አልነበረም፡፡ ሆኖም አንድ ሻንቅላ 19 ዓመት የሚያህል ላንድ ጌታ ተቀጥሮ መጥቶ ነበር፡፡ ጣሊያንኛ መናገር ትንሽ ይችል ስለነበር ከወታደሮቹ ጋር ይጫወት ነበር፡፡ ከኔ ጋር ደግሞ አንዳንዴ በዓረብኛ ይናገር ነበር፡፡››

በጣሊያን ስንት ዓመት እንደተቀመጡ ለጊዜው የሚታወቅ ነገር የለም፡፡

ስለ ጽሑፋቸው ትችት፡- አካሄዱና ይዘቱ

ጣሊያን አገር ደርሰው፣ ከጥቂት ዓመታት በኋላ ይህችን ጽሑፋቸውን ሲያዘጋጁ፣ የጣሊያን ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ውስጥ ይሠሩ ነበር፡፡ ራሳቸው እንደገለጹት በመሥሪያ ቤቱ ዓይነ ቁራኛ ሥር ነበሩ፡፡ ስለዚህም ጽሑፋቸውን ሲነበብ ይህን ግምት ውስጥ በማስገባት መሆን አለበት፡፡ በጥገኝነት በሚኖሩበት መሥሪያ ቤትና አገር ውስጥ ሆኖ በቀጥታ መተቸት፣ መዝለፍ፣ ወይም መንቀፍ አይመችም፡፡ ስለዚህም ጽሑፋቸው ‹‹እንደ ወረደ›› መነበብ የለበትም ይላሉ ዶ/ር ኃይሉ፡፡ በዕድገታቸውና በትምህርታቸው ግዕዝ ጠገብ ናቸውና ምናልባት አንዳንድ ሐሳቦቻቸውን ሸፈን ባለና ቅኔ አዘል በሆነ መንገድ እየገለጹ ይሆንን? ብሎ መገመት ጠቃሚ ይሆናል፡፡ ጣሊያኖቹን ለማስደሰት ይመስል አገሪቷ ‹‹ገነት ትመስላለች›› ይበሉ እንጂ በዳኘው ምላስ አስመስለውም በአገሪቱ ‹‹ጠባብ የዘረኛ አስተያየት የነገሠበት›› እንደሆነም ይነግሩናል፡፡ ብዙ ጣሊያኖች ጥቁሮችን ‹‹ሰው – በላ›› እያሉ ያጥላሉና ያዋርዱ እንደነበር ጨረፍ አድርገው ያልፉታል፡፡

በአውሮፓ ሥልጣኔ ተደንቀው፣ አገራቸውን ከአውሮፓ ጋር በማነፃፀር ዝቅ አድርገው የሚያዩን ሰዎች ገና ‹‹ቀዩንና ነጩን›› ያልለዩ ናቸው ብለው ይነቅፏቸዋል፡፡ ለአገራቸው እንደዚህ ዓይነት ዝቅተኛ አስተያየት ስላላቸው ሰዎች በአባ ዘካርያስ አስመስለው እንደዚህ ብለው ይተቻሉ፡፡

‹‹(አባ ዘካርያስ) ፕሮፓጋንዳ ትምህርት ቤት አስር ዓመት ተቀመጡ፣ ላቲን፣ ግሪክ፣ ዕብራይስጥ፣ ጣሊያንኛ፣ ፈረንሣይኛ እዚያ ተማሩ፡፡ ቄስ ሲሆኑ፣ ታዘው ወደ አቡነ ያዕቆብ ወደ ጦብያ ተመለሱ፡፡ እኚህ ሰው እንኳንስ ስለ አገሩ ተጠጋቢነት ሊናገሩ እንዲያውም እንደ አዝማሪ እያወደሱት ሞቱ፡፡››

ፍስሓ ጊዮርጊስ ኢትዮጵያን በተመለከተ በጠቅላላው ስለ አውሮፓውያን ተመራማሪዎች የነበራቸው አስተያየት ግን አሉታዊ ነው፡፡ ኤድዋርዶ ግሌዘር የሚባለው ጀርመናዊ ምሁር ‹‹የኢትዮጵያ ሕዝቦች ከዓረብ ምድር የፈለሱ ናቸው›› ብሎ በሰፊው ያራምድ የነበረውን አመለካከት በሚከተለው መንገድ ‹‹ታሪኽ ኢትዮጵያ›› በተሰኘው መጽሐፋቸው ይነቅፉታል፡፡

‹‹ስለ ሐበሻ ነገድና ስም፣ ኤድዋርዶ ግሌዘር ብዙ ነገር ተናግረዋል፡፡ ይሁን እንጂ ለኢትዮጵያዊ ሰው አንዳችም ስሜት ሊሰጠው አይችልም፡፡ ይህ ሊቅ . . . ዓረብ አገር ሐበሻ የሚል ስም በጥንት ጽሑፎች አገኘና . . . እኒህ ያሁኑ ጦብያውያን በሐድራሞትና በፆማን መካከል ከምትገኘው ማህራ ከምትባል አገር የመጡ ናቸው፤ የጥንቱ የጠዋቱ ነዋሪዎች አይደሉም ይላል፡፡ . . . ስለሌላው ራሱ ይጨነቅበት፣ አንነቅፍም፣ አናመሰግንም፡፡ ግዕዝ ማለት ስደተኞች ማለት ነው ያለው ግን ስሕተት ነው፡፡ ግዕዝስ ባለ አርነት፣ አውራ መዠመርያ ማለት ነው፡፡ በገዓዝን፣ ጐዐዝን፣ ገዐዝን መካከል ያለን ልዩነት ማወቅ ያስፈልጋል፡፡ የጦብያ ሰው ትውልድህ የዓረብ ትውልድ ነው ብትለው የሱ ስላልሆነ ብቻ ወይ በመጥላት ወይ በመናቅ ሳይሆን፣ ሰውነቱን ይቀፈዋል፡፡ . . . የዓረቦች ታሪክ ግን ምንም እንኳን ፍጹም ግልጽ ባይሆንም እነዚህ ኢትዮጵያውያን የዓረብን በር እየተሻገሩ ቤቶች ያንጹ እርሻም ያካሂዱ እንደነበር ያሳያል እንጂ፤ ከዓረብ አገር ወደ ሳባ ማለትም ወደ ኢትዮጵያ እንደተሻገሩ አያሳይም፡፡

ገና  በእንጭጩ ፍስሓ ጊዮርጊስ የተቃወሙት የእነኤድዋርዶ ግሌዘር አስተሳሰብ ግን ስለ ኢትዮጵያ ሕዝብና ስለ ኢትዮጵያ ሥልጣኔ ምንጭና መበቆል ተቀባይነት የተቸረው የማዕዘን ደንጊያ ሆኖ ለብዙ ጊዜ መቆየቱን ያስታወሱት ዶ/ር ኃይሉ፣ ጣሊያናዊው ኮንቲ ሮሲኒና ሌሎች የአውሮፓ ሊቃውንትም የኤድዋርዶ ግሌዘርን  አሳብ እያስፋፉ፣ የኢትዮጵያ ምሁሮችም በተራቸው እያራገቡትና እንደ ገደል ማሚቶ እያስተጋቡት እንደ ነበር ሳይገልጹ አላለፉም፡፡

የፍስሓ ጊዮርጊስ ጽሑፎች ዕጣ ፈንታ

ፍስሓ ጊዮርጊስ ከጻፏቸው ብዙ ጽሑፎች ውስጥ በሕይወት ዘመናቸው ለኅትመት የበቁት ግን ጦብላሕታን ጨምሮ ሦስት ብቻ ናቸው፡፡ ከመቶ ዓመታት ገደማ በኋላ ያን በእጅ ጽሑፍ የተዉትን ‹‹ታሪኽ ኢትዮጵያ›› የሚለውን መጽሐፋቸውን ዶ/ር ያዕቆብ በየነ ፎቶ ኮፒ አድርገው ወደ ጣሊያንኛም ተርጉመው በ1987 ዓ.ም. በናፖሊ አሳትመውታል፡፡

ሦስተኛው ከዓረብኛ የተቀዳ የቀደምት ዓረቦች ትውፊትና ከጣሊያንኛ የተገለበጠ የግብፆች ታሪክ በ1890 ዓ.ም. በሮማ በትግርኛ የታተመ ነው፡፡ ‹‹አለቃ ዘወልድ›› በሚል የብዕር ስም ፊተኛዪቱና ኋላኛዪቱ ኢትዮጵያ የሚል መጽሐፍ በ1891 ዓ.ም. አሳትመዋል፡፡  

ዶ/ር ኃይሉ በኢትዮጵያ ጥናት መጽሔት በጻፉት ሐተታ ትዝብታቸውን እንዲህ ገልጸውታል፡፡ ከሁለተኛው የጣሊያን ወረራ ማለትም ከ1928 ዓ.ም. በፊት ስለነበሩ ደራስያን፣ ለምሳሌ ስለ እነአለቃ ታየ፣ አፈወርቅ ገብረየሱስ፣ ገብረ ሕይወት ባይከዳኝ ወዘተ ብዙ ጊዜ ይነሳል፣ ይጻፋልም፡፡ ፍስሓ ጊዮርጊስ ግን ስማቸው ሆነ ጽሑፎቻቸው እጅግም ተነስተው አያውቁም፡፡ ይሁን እንጂ ሁለት ደራስያን አንስተዋቸዋል፡፡ እነሱም አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌና ተአምራት አማኑኤል ናቸው፡፡ ስለ ማንነታቸው አይናገሩ እንጂ፣ ተአምራት አማኑኤል ስለ አንዲት ጽሑፋቸው የሚከተለውን አስተያየት ሰጥተዋል፡፡

‹‹የተወለደበትንና የሞተበትን ዘመን ለማወቅ ያልተቻለ አለቃ ዘወልድ በ1891 (1899) ዓ.ም. አቅራቢያ ‹‹ፊተኛዪቱና ኋለኛዪቱ ኢትዮጵያ ብሎ ሠይሞ ከዚህ በፊት በግዕዝና በአማርኛ ታሪክ ከጻፉት ደራሲዎቻችን በተለየ አስተያየት ስለ ኢትዮጵያ ሁኔታ ጽፏል፡፡››

ቀደም ሲል፣ አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌም ተመሳሳይ አስተያየት ሰጥተው ነበር፡፡ የፍስሓ ጊዮርጊስን ማንነት ሲገልፁ ‹‹ትግሬው ፍስሓዬ›› ይሉዋቸዋል፡፡ ኅሩይ ወልደ ሥላሴም ቢሆኑ፣ ስለ ግዕዝና አማርኛ መጻሕፍት ባቀረቡት ዝርዝር ላይ የፍስሓ ጊዮርጊስን ጽሑፍ አካተዋል፡፡

ተአምራት አማኑኤል ሆኑ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ ስለ ፍስሓ ጊዮርጊስ ጽሑፍ የሚሉት ነገር ቢኖር፣ ጸሐፊው ስለ ኢትዮጵያ ታሪክ ያላቸው አስተያየት ከመደበኛ ገለጻ የተለየ መሆኑን ነው፡፡ አስተያየታቸው አዲስና ደፋር ነው፡፡ የአውሮፓ ሊቃውንት ስለ ኢትዮጵያ ታሪክና ሥልጣኔ አመጣጥ ከሚያቀርቡት አስተያየት እጅግ የተለየ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብም ሆነ ሥልጣኔ አገር በቀል ነው፡፡ ከባህር ማዶ ከዓረብያ የመጣ አይደለም ብለው ሽንጣቸውን ገትረው ይከራከራሉ፡፡ ይህና ይህን መሰል አቋማቸው ይሆንን ከኢትዮጵያ ደራስያን ታሪክ መዝገብ እንዲረሱ ያደረጋቸው? ያሉት ዶ/ር ኃይሉ፣ እንግዲያስ ይህ ዝንጋዔ ቀርቶ፣ ሌላው ቢቀር ይህች ትንሽ ጽሑፋቸው ለአንባብያን ትድረስ በሚል ዓላማ እነሆ ከ123 ዓመት በኋላ እንደገና ታትማ እንድትቀርብ ተደርጋለች ይላሉ፡፡

በትግርኛ የታተመችውም ጦብላሕታ ራሳቸው ፍስሓ ጊዮርጊስ በመቅድማቸው እንደተናገሩት ጽሑፉን እንዲጽፉ ያበረታቷቸው ጣሊያናዊ ፕሮፌሰር ፍራንቼስኮ ጋሊና ነበሩ፡፡ ትግርኛ ማስተማሪያ እንዲሆን በማለት፡፡ በትግራይም ማለፊያ ማስተማሪያ በሆነ ነበር፤ የትግራይ ክልል ትምህርት ቢሮ ማስተማሪያ ይሁን ብሎ ቢወሰን ኖሮ በማለት ዶ/ር ኃይሉ አጽንዖት ሰጥተው ጥሪ ያቀርባሉ፡፡

Happy
Happy
0 %
Sad
Sad
0 %
Excited
Excited
0 %
Sleepy
Sleepy
0 %
Angry
Angry
0 %
Surprise
Surprise
0 %
    Print       Email

Average Rating

5 Star
0%
4 Star
0%
3 Star
0%
2 Star
0%
1 Star
0%
<"Without the support of our readers, the Maleda Times website would not exist in its present form">

You might also like...

Ethiopia’s Media Under Siege Amid Escalating Conflict in Amhara

Read More →

This site is protected by wp-copyrightpro.com

Skip to toolbar