የኢትዮጵያ አየር መንገድ ራዕይ 2025 የዕድገት መርሐ ግብር ተግባራዊ ማድረግ ከጀመረ እ.ኤ.አ. 2011 ጀምሮ፣ በየዓመቱ ከ20 እስከ 30 በመቶ በማደግ ላይ እንደሆነ አስታወቀ፡፡ ዋና ሥራ አስፈጻሚው አቶ ተወልደ ገብረ ማርያም፣ አየር መንገድ የአገሪቱን ሰንደቅ ዓላማ ተሸክሞ የሚበር የአገር አምባሳደር ነው ብለዋል፡፡
ሐሙስ ኅዳር 13 ቀን 2011 ዓ.ም. በአቪዬሽን አካዴሚ መግለጫ የሰጡት የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከፍተኛ የማኔጅመንት አባላት አየር መንገዱ ባለፉት ስምንት ዓመታት ፈጣን ዕድገት በማስመዝገብ ላይ መሆኑን ገልጸው፣ በራዕይ 2025 ላይ የተቀመጡትን አብዛኞቹን ግቦች በማሳካት ላይ እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡
አቶ ተወልደ አየር መንገዱ በአውሮፕላኖች ብዛትና በበረራ መዳረሻዎች የተቀመጡትን ግቦች ከዕቅዱ ዘመን ሰባት ዓመት ቀደም ብሎ ማሳካት መቻሉን ገልጸው፣ በአቪዬሽን አካዴሚው ላይ 100 ሚሊዮን ዶላር ወጪ በማድረግ ሰፊ የማስፋፊያ ሥራ መከናወኑን፣ ዘመናዊ የምግብ ማደራጃ፣ የአውሮፕላን ጥገና ሐንጋሮች መገንባታቸውን አስታውሰዋል፡፡ በራዕይ 2025 የተቀመጡ ግቦችን ማሳካት በመቻሉ ዕቅዱን በመከለስ ራዕይ 2030 በመዘጋጀት ላይ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
አየር መንገዱ በተቀመጠው ዕቅድ መሠረት ዘጠኝ የትርፍ ማዕከላት ያሉት የአቪዬሽን ቡድን መሥርቷል፡፡ ዓለም አቀፍ አየር መንገድ፣ የአገር ውስጥና ክልላዊ አየር መንገድ፣ ካርጎ፣ ኬተሪንግ፣ ጥገና ማዕከል፣ አቪዬሽን አካዴሚ፣ ግራውንድ ሃንድሊግ፣ የኢትዮጵያ ኤርፖርቶች፣ ሆቴልና የጉዞ አገልግሎት ዘርፍ ናቸው፡፡ የኤሮስፔስ ማምረቻ ተቋም ለመመሥረት በእንቅስቃሴ ላይ ይገኛል፡፡
አየር መንገዱ በ65 ሚሊዮን ዶላር ወጪ ያስገነባው ባለአምስት ኮከብ ሆቴል በኅዳር ወር ማብቂያ እንደሚያስመርቅ ተገልጿል፡፡ ዓለም አቀፍ ደረጃቸውን የጠበቁ 372 የመኝታ ክፍሎች፣ ዘመናዊ ምግብ ቤቶችና የስብሰባ አዳራሾች ያሉት ሆቴሉ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸውን የቻይና ቱሪስቶች ለመሳብ እየተዘጋጀ እንደሆነ ተነግሯል፡፡ ሆቴሉ ከአፍሪካ ትልቁ የቻይና ምግብ ቤት እንደሚኖረው ታውቋል፡፡ አየር መንገዱ 637 መኝታ ክፍሎች ያሉት ሁለተኛ ሆቴል ግንባታ መጀመሩ፣ እንዲሁም ሁለተኛው ምዕራፍ ሲጠናቀቅ ከ1,000 በላይ የመኝታ ክፍሎች የሚኖሩት በመሆኑ ግዙፍ የስብሰባ ማዕከል እንደሚሆን ተነግሯል፡፡
የተለያዩ ክልላዊ መናኸሪያዎችን ለማቋቋም በታቀደው መሠረት በቶጎና በማላዊ በሽርክና አየር መንገዶች ማቋቋሙን ያስታወሱት አቶ ተወልደ በሞዛምቢክ፣ በዛምቢያ፣ በቻድና በጊኒ አዳዲስ አየር መንገዶች ለማቋቋም ስምምነቶች ተፈርሞ እንቅስቃሴ እንደተጀመረ አስረድተዋል፡፡ ማኔጅመንቱና ሠራተኛው ጠንክረው በመሥራታቸው አየር መንገዱ ከአፍሪካ ቀዳሚ ለመሆን እንደቻለ ጠቁመዋል፡፡
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና የሒሳብ ሹም አቶ መሠረት ቢተው አየር መንገዱ ጠንካራ የፋይናንስ አቋም እንዳለው ገልጸዋል፡፡ አየር መንገዱ በሚበደርበት ወቅት ግልጽ ዓለም አቀፍ ጨረታ በማውጣት ባንኮችን አወዳድሮ እንደሚበደር የገለጹት አቶ መሠረት፣ ብድሩንም በአግባቡ በመክፈል ላይ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ የብድር መጠኑን የተጠየቁት አቶ መሠረት 2.4 ቢሊዮን ዶላር እንዳለበት ገልጸዋል፡፡
አቶ ተወልደ አየር መንገዱ ሲበደር የመንግሥት ዋስትና እንደማይጠይቅ፣ ራሱን ችሎ እንደሚበደርና ብድሩን ራሱ ሠርቶ በመክፈል ላይ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡ አየር መንገዱ ብድሩን ለአውሮፕላኖች ግዥና ለመሠረተ ልማት ግንባታዎች እንደሚያውለው ገልጸው፣ ይህንንም በተገቢው የአዋጭነት ጥናት ላይ ተመርኩዞ የሚሠራ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡
አየር መንገዱን በተመለከተ በማኅበራዊ ሚዲያዎች ላይ ስለሚወጡ ጽሑፎች ተጠይቀው በሰጡት ምላሽ፣ ከአየር መንገዱ የለቀቁና የሥነ ሥርዓት ዕርምጃ የተወሰደባቸው አንዳንድ ሠራተኞች ራሳቸውን ደብቀው በማኅበራዊ ሚዲያዎች ላይ ዘመቻ መክፈታቸውን ተናግረዋል፡፡ አንዳንዶችም ከፍተኛ ጥፋት ፈጽመው ከሥራ ሲታገዱ በራሳቸው ፈቃድ ጥለው የሄዱ የቀድሞ ሠራተኞች፣ ምንም እንዳላጠፉና እንደተበደሉ ሲናገሩ በቴሌቪዥን መመልከታቸውን ተናግረዋል፡፡
አየር መንገዱ ጥብቅ የሆነ የሥራ ሥነ ሥርዓት ያለበት ቤት በመሆኑ ጫናውን ለመቋቋም ያልቻሉ አንዳንድ ሠራተኞች ቅሬታ እንደሚያሰሙ ገልጸዋል፡፡ በተለይም ከሌሎች መሥሪያ ቤቶች የመጡ አዲስ ሠራተኞች ጥብቅ የሆነ አሠራር ለመላመድ እንደሚቸገሩ ገልጸዋል፡፡ ‹‹እኛ የምንወዳደረው እንደ ኤምሬትስና ሲንጋፖር ካሉ ግዙፍ አየር መንገዶች ጋር ነው፡፡ የሲንጋፖር አየር መንገድ የአንድ ሠራተኛ ምርታማነት በዓመት 675,000 ዶላር ነው፡፡ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ሠራተኛ ምርታማነት 375,000 ዶላር ነው፡፡ ምርታማነትን ለማሳደግ በምናደርገው ጥረት አንዳንድ ሠራተኞች ጋር ቅሬታ መፍጠሩ አይቀርም፤›› ብለዋል፡፡
የአየር መንገዱ ቺፍ ኦፕሬቲንግ ኦፊሰር አቶ መስፍን ጣሰው በቴሌቪዥን ቅሬታ ሲያቀርቡ የተመለከቷቸው ሁለት የቀድሞ ቴክኒሺያኖች አንድ ቦይንግ 737 አውሮፕላን ጠግነው ሲያበቁ የተጠቀሙበትን መሣሪያዎች አውሮፕላኑ ውስጥ በመተው፣ ያልሠሩትን እንደሠሩ ሪፖርት በማድረግ በአውሮፕላኑ ላይ ከፍተኛ የደኅንነት ሥጋት በመፍጠራቸው ከሥራቸው እንዲታገዱ መደረጉን ተናግረዋል፡፡ በዚህም ምክንያት የአውሮፓ የሲቪል አቪዬሽን ኅብረት የኢትዮጵያ አየር መንገድ የደኅንነት ሥጋት አለበት፣ የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን በአየር መንገዱ ላይ በቂ ቁጥጥር አያደርግም በማለት ከፍተኛ ችግር ተፈጥሮ እንደነበር ገልጸው፣ ችግሩን ለመፍታት ከሁለት ዓመት በላይ እንደፈጀ አስታውቀዋል፡፡ ከሥራ የታገዱት ቴክኒሽያኖች በራሳቸው መንገድ ከአገር እንደወጡ ተናግረዋል፡፡
የሰው ኃይል አስተዳደር ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ መሳይ ሽፈራው የኢትዮጵያ አየር መንገድ በሰው ኃይል ልማት ላይ ሰፊ ሥራ በማከናወን ላይ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ ባለፉት ሰባት ዓመታት ከ8,000 በላይ ሠራተኞች መቅጠሩን የተናገሩት አቶ መሳይ፣ ለሠራተኞች የተለያዩ ሥልጠናዎች እንደሚሰጡ ገልጸው አየር መንገዱ የራሱ የሆነ የቅሬታ አፈታት ሥርዓት እንዳለው ተናግረዋል፡፡ ሠራተኞች ቅሬታቸውን እስከ በላይ አለቆች ድረስ የሚያቀርቡበት አሠራር እንዳለ ገልጸዋል፡፡
የአውሮፕላኖችን ግዥ አስመልክቶ ማብራሪያ የሰጡት የፍሊት ፕላኒንግ ዳይሬክተር አቶ ዳንኤል አበበ፣ በአየር መንገዱ ውስጥ እንደ ዋዛ የሚገዛ ዕቃ እንደሌለ ተናግረዋል፡፡ የአውሮፕላን ግዥ ሲፈጸም ከፍላይት ኦፕሬሽን፣ ከጥገና ክፍልና ከደንበኞች አገልግሎት የተወጣጡ ከፍተኛ ባለሙያዎች የሚሳተፉበት ጥልቅ ጥናት እንደሚካሄድ የገለጹት አቶ ዳንኤል፣ አውሮፕላኑ አየር መንገዱ ለሚፈልገው ተልዕኮ ብቁ መሆኑ ሲረጋገጥ ብቻ ግዥ እንደሚፈጸም አስረድተዋል፡፡
የኩባንያው ሠራተኞች የብሔር ተዋጽኦን አስመልክቶ ለቀረበላቸው ጥያቄ ምላሽ የሰጡት አቶ ተወልደ፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዓለም አቀፍ ኩባንያ በመሆኑ ከአገር ውስጥ ብቻ ሳይሆን የውጭም ዜጎች በመቅጠር ላይ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡ ‹‹እንግሊዝኛ የማይናገሩ መንገደኞቻችን በራሳቸው ቋንቋ የሚያስተናግዷቸው የአገራቸውን ሰዎች እያሠለጠንን በመቅጠር ላይ ነን፡፡ ቻይናውያንና ፈረንሣይኛ ተናጋሪ የሆኑ የምዕራብ አፍሪካ የበረራ አስተናጋጆች ቀጥረናል፤›› ያሉት አቶ ተወልደ፣ በአገር ውስጥ የሥራ ዕድሉ ለሁሉም ክልል ክፍት እንደሆነ አስረድተዋል፡፡ ‹‹የቅጥር ሥርዓታችንን ተደራሽ ለማድረግ በሁሉም ክልሎች በመሄድ በመመልመል ላይ ነን፡፡ ነገር ግን በብቃት መመዘኛዎች ላይ አስተያየት አናደርግም፤›› ብለዋል፡፡
የፍላይት ኦፕሬሽን ምክትል ፕሬዚዳንት ካፒቴን ዮሐንስ ኃይለ ማርያም በበኩላቸው፣ የበረራ ሥራ ከደኅንነት አንፃር ከፍተኛ ጥንቃቄ የሚደረግበት ሙያ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ ‹‹የበረራ ሥራ ስህተት ተፈጽሞ የማረም ዕድል የሚገኝበት አይደለም፡፡ ለበረራ ትምህርት ተማሪዎች በምንመለምልበት ወቅት ከፍተኛ ጥንቃቄ እናደርጋለን፡፡ ሥልጠናውም በጥንቃቄ የሚካሄድ ነው፡፡ እያንዳንዱ ፓይለት ከእኔ ጀምሮ በየሦስት ወሩ የምሥለ በረራና የጤና ምርመራ ያደርጋል፡፡ አንዳንዱ አብራሪ ፈተናውን ማለፍ ሲያቅተው ችግሩን በሌሎች ሰዎች ላይ ለማላከክ ይሞክራል፤›› ብለዋል፡፡
አቶ ተወልደ የአየር መንገዱ ማኔጅመንት አባላት ኩባንያውን በኃላፊነት ለተወሰነ ጊዜ እንዲመሩ የተቀመጡ በመሆናቸው፣ ለመጪው ትውልድ የተሳካላት አየር መንገድ ማስተላለፍ እንደሚፈልጉ ተናግረዋል፡፡ ‹‹እኛ በኃላፊነት የምንቆየው ለተወሰነ ጊዜ ነው፡፡ ይህ አየር መንገድ የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ ተሸክሞ በመላው ዓለም የሚበር፣ የአገር አምባሳደርና የሁሉም ኢትዮጵያዊያን ንብረት ነው፤›› ብለዋል፡፡
Average Rating