ድርጅቶቹ ይፋ ተደርገዋል
ገቢዎች ሚኒስቴር ባደረገው ድንገተኛ ፍተሻ፣ በሐሰተኛ ደረሰኝና ያለ ደረሰኝ ግብይት ሲፈጽሙ የደረሰባቸውን 35 ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ሥር አውሎ ምርመራ መጀመሩን አስታወቀ፡፡
ሚኒስቴሩ ትልልቅ ድርጅቶች ሆነው አነስተኛ ሽያጭ በሚያስመዘግቡ፣ ሳይከራከሩ ኪሳራ በሚያሳውቁ፣ ምንም ሽያጭ እንዳላካሄዱ በሚያሳውቁና ተመላሽ የሚጠይቁ ላይ ጥናት ካደረገ በኋላ በ15 ድርጅቶችና 18 ቦታዎች ላይ ባደረገው ድንገተኛ ፍተሻ፣ ተጠርጣሪዎቹ ያለ ደረሰኝ ሲሸጡ እጅ ከፍንጅ እንደያዛቸው አስታውቋል፡፡
በሚኒስቴሩ የሕግ ማስከበር ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ዘመዴ ተፈራ ዓርብ ኅዳር 14 ቀን 2011 ዓ.ም. እንደተናገሩት፣ መሥሪያ ቤታቸው ከላይ የተጠቀሱትን ምክንያቶች መሠረት አድርጎ ጥናት አካሂዷል፡፡ በተደረገው ጥናት በአስመጪና በላኪነት የንግድ ዘርፍ ተሰማርተው የሚገኙና ዓመታዊ የገበያ ልውውጣቸው (Transaction) ከ100 ሚሊዮን ብር በላይ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በቁጥጥር ሥር የዋሉ ተርጣሪዎች በሽያጭ ሥራ ላይ የተሰማሩና በድርጅቶቹ ውስጥ በሥራ አስኪያጅነት የሚሠሩ መሆናቸውንም አስረድተዋል፡፡
ያለ ደረሰኝ ግብይት ሲፈጽሙ ከተደረሰባቸው ድርጅቶች መካከል በተለያዩ ቦታዎች አራት ቅርንጫፎች ያሉትና በአምራችነት የሥራ ዘርፍ የተሰማራው ምሥራቅ ፒኤልሲ፣ ከውበት ዕቃ ንግድ ቬልቬት ፒኤልሲ፣ ባዝራ ፈረስ ሌዘር ላኪ፣ በመጠጥ ማከፋፈልና የቤት ዕቃዎች የተሰማራው ቢኤምኤች አጠቃላይ ንግድ፣ ከሕንፃ መሣሪያዎች በላከ ትሬዲንግ ፒኤልሲ፣ ድናሪም ትሬዲንግ ፒኤልሲ፣ ከኤሌክትሮኒክስ ዕቃዎች ደሚር ትሬዲንግ አገልግሎት ሰጪዎች ጆቢራ ካፌ፣ አሰብ ሆቴልና ሌሎችም ድርጅቶች መሆናቸውን ሚኒስትር ዴኤታው አስታውቀዋል፡፡
ሚኒስቴሩ ድንገተኛና ተከታታይ ፍተሻ ማድረጉን እንደሚቀጥልም ተናግረዋል፡፡ ኅብረተሰቡ ለሚገዛው ዕቃ ደረሰኝ የመጠየቅ መብት እንዳለው አውቆ፣ ከካሽ ሬጂስተር ወይም በእጅ ጽሑፍ የሚገለጽ ደረሰኝ በመቀበል፣ ሕገወጦችን ማስተማርና አገራዊ ልማትን መታደግ እንዳለበትም ጠቁመዋል፡፡
ቀደም ሲል በሐሰተኛ ደረሰኝ ግብይት የሚፈጽሙ 124 ድርጅቶች እንደተደረሰባቸው ይፋ መደረጉንና ግብረ መልሱም መልካም እንደነበረ የተናገሩት አቶ ዘመዴ፣ በታክስ አስተዳደር አዋጅ ቁጥር 983/2008 ድንጋጌ መሠረት ደረሰኝ መስጠት ግዴታ መሆኑን አስታውሰዋል፡፡
ያለ ደረሰኝ መገበያየት በአዋጁ አንቀጽ (108) ድንጋጌ መሠረት 50,000 ብር የገንዘብ ቅጣትና በአንቀጽ 120(1) መሠረት ደረሰኝ አለመስጠትና በንዑስ አንቀጽ (4) ድንጋጌ መሠረት ደግሞ ያለ ደረሰኝ መገበያየት፣ በወንጀል ተጠያቂ እንደሚያደርግ አስታውቀዋል፡፡ ጉዳቱ ከባድና ለአገርም አደገኛ በመሆኑ ዜጎች ሥራቸውን በሕግና በጥንቃቄ እንዲሠሩ አሳስበዋል፡፡
Average Rating