የኦነግ ሠራዊት ራሱን እንዲከላከል መታዘዙን ሊቀመንበሩ አስታወቁ
ኦዴፓ በኦሮሚያ በሚንቀሳቀሱ የጥፋት ኃይሎች ላይ ማንኛውም ዓይነት ዕርምጃ ይወሰዳል አለዮ
የኦነግ ሠራዊት ራሱን እንዲከላከል መታዘዙን ሊቀመንበሩ አስታወቁ
በኦሮሚያ በሚንቀሳቀሱ የጥፋት ኃይሎች ላይ ማንኛውም ዓይነት ዕርምጃ እንዲወሰድ መወሰኑን፣ ክልሉን የሚያስተዳድረው የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኦዴፓ) አስታወቀ።
የኦዴፓ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ አስቸኳይ ስብሰባውን ሐሙስ ታኅሳስ 11 ቀን 2011 ዓ.ም. በማካሄድ፣ የክልሉን ሰላም ለመጠበቅ ሲባል ማንኛውም ዓይነት አስፈላጊ ዕርምጃ እንዲወሰድ መወሰኑን ባወጣው መግለጫ አስታውቋል። ኦዴፓ እንዳስታወቀው አገሪቱን ሲዘርፉ፣ ሕዝብ ሲያሰቃዩ የነበሩና ከሥልጣን የተባረሩ ኃይሎች ከሕዝቡ በዘረፉት ገንዘብ ተላላኪዎችን በመግዛት ኦሮሚያንና ኦሮሞን የጦርነት አውድማ ለማድረግ እየሠሩ መሆኑን ጠቁሟል።
በዚህ ደባ ውስጥ በሰላማዊ መንገድ ትልግ ለማድረግ የገቡትን ቃል አፍርሰውና ለኦሮሞ ሕዝብ የሚያደርጉትን ትግል ክደው፣ መጠቀሚያ የሆኑ የኦሮሞ ሕዝብ ወገኖች መኖራቸውን አመልክቷል።
ኦዴፓ ለሰላም ቅድሚያ በመስጠት እያሳየ ያለውን ትዕግሥት እንደ ፍራቻ በመመልከት የሕዝቡ ሰላም እንዲደፈርስ፣ ሕዝቡ በሰላም ወጥቶ እንዳይገባና ሥጋት እንዲሰማው፣ የማኅበረሰቡን ችግሮች የሚቀርፉ ፕሮጀክቶች እንዲቆሙ፣ እንዲሁም ለሕዝቡ የተገባው ቃል እንዳይሳካ የውስጥና የውጭ የጥፋት ኃይሎች ኦሮሞ አገር መምራት አይችልም በሚል ጋብቻ ፈጽመው ሴራ በመሸረብ ሌት ተቀን እየሠሩ መሆኑን አስታውቋል።
አሁን የተገኘው ድል በአፈሙዝ፣ እርስ በእርስ በመደነቃቀፍና ለጠላት መሣሪያ በመሆን እንዳልሆነ፣ ይልቁንም የፖለቲካ ለውጡ የተገኘው በትዕግሥትና በበሰለ የኦሮሞነት ፍልስፍና እንዲሁም በመደማመጥና አንድነት መሆኑን፣ ዛሬም ቢሆን ይህን መንገድ ከማጠናከር ውጪ እርስ በእርስ የመታኮስ መንገድ አንዱ አንዱን ይሰብር ይሆናል እንጂ ወደ ቀጣይ ምዕራፍ እንደማያሸጋግር ጠቁሟል።
የኦዴፓ እምነት ይህ ቢሆንም ጠላቶች ለሸረቡት ሴራ በቂ ዕውቀት በሌለው በሰላማዊ የኦሮሞ ሕዝብ ላይ ጭካኔ በተሞላበት የሽብር ጥቃት በፈንጂ ሕይወታቸውን መቀጠፉን፣ ሴቶች መደፈራቸውን፣ ንብረት እየወደመና የሕዝቡ የመንቀሳቀስ መብት እየተገደበ መሆኑን አመልክቷል። ሰላም ይቅደም በማለት ሲሠሩ የነበሩ የኦዴፓ አመራሮችና የሕዝብ ጋሻ የሆነው የኦሮሚያ ፖሊስ አባላትም በአሰቃቂ ሁኔታ ሕይወታቸው እያለፈ መሆኑን አስታውቋል።
በመሆኑም በተቀናጀ መንገድ ሴራ የሚሸርቡትን አክሽፎ የሕዝቡን ሰላም ለማረጋገጥ ማንኛውንም ዓይነት ዕርምጃ ለመውሰድ መወሰኑን በይፋ ገልጿል።
የሕግ የበላይነትን ማረጋገጥ የመንግሥት ግዴታ መሆኑን ያስታወሰው መግለጫው፣ በዚሁ መሠረት በኦዴፓ የሚመራው የኦሮሚያ ክልል መንግሥት ወንጀል የሚፈጽሙና እንዲፈጸም ሁኔታ የሚያመቻቹ አካላትን በአስቸኳይ በማደን ለሕግ እንዲያቀርብ አቅጣጫ ማስቀመጡን አስታውቋል።
የክልሉ መንግሥት ጥፋተኞችን ለሕግ ለማቅረብ ዕርምጃ በሚወስድበት ወቅትም የኦሮሞ ሕዝብ፣ ወጣቶች፣ ምሁራንና የአገር ሽማግሌዎች ከጎኑ እንዲሆኑም የኦዴፓ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ጥሪውን አቅርቧል።
በተያያዘ ዜና የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) የኦዴፓን መግለጫ ተከትሎ ለዚህ ምላሽ የሚመስል መግለጫ ዓርብ ታኅሳስ 12 ቀን 2011 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ሰጥቷል።
መግለጫውን የሰጡት የግንባሩ ሊቀመንበር አቶ ዳውድ ኢብሳ እንደተናገሩት፣ በአሁኑ ወቅት የሚታየውን የመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች እንቅስቃሴን በማጤን የኦነግ ሠራዊት በማንም ላይ ጥቃት እንዳይፈጽም፣ ነገር ግን ራሱን እንዲከላከል ታዟል።
‹‹በዛሬው ዕለት ከፍተኛ የሆነ የመንግሥት ሠራዊት በሰላሌ፣ በባሌ፣ በጉጂና በወለጋ ተገቢ ያልሆነ እንቅስቃሴ ማካሄድ ጀምሯል፤›› ያሉት ሊቀመንበሩ፣ ‹‹ሠራዊታችን ጥቃት አይፈጽምም፣ ራሱን ግን እንዲከላከል ትዕዛዝ ተሰጥቶታል፤›› ብለዋል፡፡
ኦነግ ከኤርትራ ወደ አገር ቤት ሲመለስ ከመንግሥት ጋር ስምምነቶችን በመፈጸም ቢሆንም መንግሥት ስምምነቶችን እንዳላከበረ ተናግረዋል። የኦነግ ሠራዊት በተለያዩ የመንግሥት የፀጥታ መዋቅሮች ውስጥ እንዲቀላቀል ስምምነት እንደነበር፣ ነገር ግን ይህ አለመፈጸሙን አስታውቀዋል፡፡ ወደ አርሲ አርዳይታ ካምፕ የገቡ የኦነግ ሠራዊት አባላት የተያዙበት አግባብ የተሃድሶ ሳይሆን የእስር ዓይነት እንደሆነ የተናገሩት አቶ ዳውድ፣ የኦነግ አመራሮች በካምፕ የሚገኙትን ወታደሮቹን ለመጎብኘት እንዳልቻለ ገልጸዋል።
የኦሮሚያ ክልልና የፌዴራል መንግሥት ሰላምን ለማስፈን ቁርጠኛ ከሆኑ ኦነግ በሰላም ዙሪያ ለመወያየት ዝግጁ መሆናቸውንም አስታውቀዋል።
Average Rating