በቀድሞዎቹ የደኅንነትና የሜቴክ ከፍተኛ ኃላፊዎች ላይ ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ተፈቀደ
በ
በብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን (ሜቴክ) ቁርጥራጭ ብረታ ብረቶችንና ሌሎች ንብረቶችን ሰብስቦ መልሶ መጠቀም መምርያ ኃላፊ ለግዳጅ በደቡብ ሱዳን አብዬ ግዛት እያሉ በአለቃቸው መጠርጠራቸው ተነግሯቸው ወደ ኢትዮጵያ ሲመለሱ፣ ከቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ተይዘው ከታሰሩ በኋላ ፍርድ ቤት ቀረቡ፡፡
ተጠርጣሪው ኮሎኔል ካሳ ሮባ የተጠረጠሩበትን ጉዳይ የፌዴራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ቡድን እንዳስረዳው፣ የተሰጣቸውን ኃላፊነት በመጠቀም በጥቅም በመመሳጠር ሌሎች ድርጅቶች ቁርጥራጭ ብረቶች ሰብስበው እንዲያቀርቡ በማድረግ፣ በመንግሥትና በሕዝብ ላይ ከባድ የሙስና ወንጀል መፈጸማቸውን አስረድቷል፡፡ በመሆኑም ለተጨማሪ ምርመራ የ14 ቀናት ጊዜ እንዲፈቀድለት ጠይቋል፡፡
ተጠርጣሪው ፍርድ ቤት የቀረቡት ያለ ጠበቃ ቢሆንም፣ በቀጣይ ቀጠሮ ጠበቃ ይዘው እንደሚቀርቡ ተናግረው በዕለቱ በራሳቸው ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ በሜቴክ ሥር በተቋቋመ ድርጅት ውስጥ የተቆራረጡ ብረታ ብረቶችና ንብረቶች ሰብስቦ መልሶ መጠቀም ክፍል ኃላፊ መሆናቸውን አረጋግጠው፣ ሥራውን ሲያከናውኑ የነበሩት በመሥሪያ ቤቱ ግልጽ መመርያ መሠረት መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ድርጅቶች የተባሉትም ሌሎች ሳይሆኑ የመከላከያ ሠራዊት አባል የነበሩና የጦር ጉዳተኞች ሲሆኑ፣ በሠራዊቱ ውስጥ በነበሩበት ጊዜ ከብረት ሥራ ጋር ግንኙነት የነበረው ሥራ ላይ የነበሩ በመሆናቸው ተደራጅተው እንዲሠሩ መደረጋቸውንም ገልጸዋል፡፡
‹‹እኔ ወታደር ነኝ፣ የታዘዝኩትን ብቻ መፈጸም ስላለብኝ ሠርቻለሁ፡፡ ባልፈጽምስ ኖሮ . . . ›› በማለት ሥራውን ከመምራትና ከመቆጣጠር ውጪ ክፍያም ሆነ ከገንዘብ ጋር ምንም ዓይነት ግንኙነት እንደሌላቸው አስረድተዋል፡፡ ከማንም ጋር የጥቅም ግንኙነት እንደ ሌላቸው ጠቁመው፣ የጥቅም ግንኙነት ፈጥረው በመንግሥትና በሕዝብ ጥቅም ላይ ጉዳት አድርሰዋል የሚለውን የመርማሪ ቡድን ክርክር ተቃውመዋል፡፡ እስከተያዙበት ቀን ድረስ በደቡብ ሱዳን በአብዬ ግዛት ሰላም በማስከበር ሥራ ላይ እንደነበሩ የገለጹት ኮሎኔል ካሳ፣ ሜቴክን በሚመለከት በተላለፈው ዶክመንተሪ ዘጋቢ ፊልም መሠረት ‹‹ሕግ ይፈልግሃል›› ብለው አለቃቸው ነግረዋቸው እንደመጡ አስረድተዋል፡፡ መርማሪ ቡድኑ ከአገር እንደሚወጡና ሰነድ እንደሚያጠፋ በመጥቀስ ዋስትና እንዲከለከሉ መጠየቁ ተገቢ አለመሆኑን የገለጹት ተጠርጣሪው፣ አለቃቸው ሕግ እንደሚፈልጋቸው ነግረዋቸው የተመለሱት፣ በኡጋንዳ ካምፓላ አድርገውና የአንድ ዓመት ቪዛ እጃቸው ላይ ይዘው መሆኑን ተናግረዋል፡፡ መጥፋት ቢፈልጉ ወደ ፈለጉበት አገር መሄድ ይችሉ እንደነበር ጠቁመው፣ ‹‹የተወለድኩት ኢትዮጵያ ውስጥ ነው፡፡ የምሞተውም ኢትዮጵያ ውስጥ ነው፡፡ ወደ ሕግ እሄዳለሁ እንጂ ሕግን አልሸሽም፤›› ብለዋል፡፡ ማንም ሳያስገድዳቸው የአለቃቸውን ትዕዛዝ ብቻ ሰምተው ሲመጡ ቦሌ ተይዘው ቤተሰቦቻቸውን እንኳን ሳያገኙ መታሰራቸውንና ለሕግ ተገዥ እንደሆኑ ገልጸው፣ የዋስትና መብታቸው ተጠብቆላቸው በውጭ ሆነው ጉዳያቸውን እንዲከታተሉ ፍርድ ቤቱን ጠይቀዋል፡፡
ብረታ ብረትና ሌሎች ንብረቶችን ሰብስቦና መልሶ የመጠቀም ሥራን እንዲያከናውን በገንዘብ ሚኒስቴር በተላለፈ ሰርኩላር ተነግሮ የነበረው ለሜቴክ መሆኑን በመግለጽ፣ የተቃውሞ ምላሽ መስጠት የጀመረው መርማሪ ቡድኑ፣ ተጠርጣሪው ማንም ሳያዛቸው በራሳቸው ተነሳሽነት የመከላከያ ሠራዊት አባላት የነበሩ ግለሰቦችን በማደራጀት ሥራውን ሰጥተዋል ብሏል፡፡ ይኼንንም ያደረጉት ባላቸው የጥቅም ግንኙነት በመመሳጠርና ውል በመፈራረም ጭምር መሆኑንም ገልጿል፡፡
ሜቴክ እንደፈረመ በማስመሰል በርካታ ውሎችን መፈረማቸውንና ክፍያ እንዲፈጸም ማድረጋቸውንም አክሏል፡፡ ሜቴክ ራሱን የቻለ የመንግሥት የልማት ድርጅት ሆኖ እያለ፣ ከመከላከያ ጋር ለማገናኘት ጥረት ማድረግ ተገቢም እንዳልሆነ አክሏል፡፡ ገንዘብ ሚኒስቴር 46 ለሚሆኑ የመንግሥት የልማት ድርጅቶች በጻፈው ሰርኩላር እንደገለጸው፣ የቁርጥራጭ ብረቶችና ንብረቶችን ሥራ ራሱ ሜቴክ እንደሠራ መግለጹንም አስታውሷል፡፡ ነገር ግን ተጠርጣሪው ድርጅቶቹን በማቋቋምና ሥራውንም በመስጠት ክፍያ እንዲፈጸምላቸው ደብዳቤ ይጽፉ እንደነበር መርማሪ ቡድኑ አስረድቷል፡፡ ፍርድ ቤቱ ባነሳው ጥያቄ ሜቴክ ሥራውን ለሌላ ድርጅት መስጠት መቻል አለመቻሉን በሚመለከት በሰርኩላሩ ላይ መገለጽ አለመገለጹን መርማሪ ቡድኑ ተጠይቆ፣ ‹‹የሚለው ነገር የለም፤›› ብሏል፡፡
ከደቡብ ሱዳን ተነስተውና በኡጋንዳ ካምፓላ አድርገው ከመምጣታቸው አንፃር በዋስ ቢለቀቁ ስለሚኖረው ችግር መርማሪ ቡድኑ እንዲያስረዳ ፍርድ ቤቱ ጠይቆት፣ የመጡት ወንጀሉ ሳይነገራቸው ለሌላ ምክንያት መሆኑን ገልጿል፡፡ በመሆኑም ዋስትና ቢፈቀድላቸው ማስረጃ ሊያጠፉና ምስክሮችንም ሊያባብሉ እንደሚችሉ በመጠቆም ተቃውሞውን ገልጿል፡፡
ተጠርጣሪው በሰጡት ምላሽ፣ ‹‹የመጣሁት በደቡብ ሱዳን የሚገኙት አለቃዬ ሜጀር ጄኔራል ድሪባ እንደምፈልግ ነግረውኝ ነው፤›› የተፈለጉት ኃላፊ ሆነው ይሠሩበት በነበረው የቁርጥራጭ ብረታ ብረቶችን መሰብሰብና መልሶ መጠቀም ዳይሬክቶሬት በወንጀል መጠርጠራቸውን አለቃቸው ነግረዋቸው ‹‹ሂድና ጉዳይህን ፈጽም›› ብለዋቸው እንደመጡ ተናግረዋል፡፡ ማኅበራቱ በውልና ማስረጃ የተደራጁና ፈቃድ ተሰጠቷቸው የሚሠሩ በመሆኑ፣ እሳቸውም ሆኑ ሜቴክ እነሱን የማደራጀት ሥልጣን እንደሌላቸውም አስረድተው፣ ዋስትና እንዲፈቀድላቸው በድጋሚ ጠይቀዋል፡፡
የግራ ቀኙን ክርክር ያዳመጠው ፍርድ ቤቱ የተጠርጣሪውን የምርመራ መዝገብ ከተመለከተ በኋላ ለደቂቃዎች ተነጋግሮ፣ የተጠርጣሪውን ጥያቄ በማለፍ መርማሪ ቡድኑ ከጠየቀው 14 ቀናት ውስጥ ሰባት ቀናት በመፍቀድ ለታኅሳስ 17 ቀን 2011 ዓ.ም. ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡
ይህ በዚህ እንዳለ በከባድ የሰብዓዊ መብት ጥሰትና በሙስና ወንጀሎች ተጠርጥረው በእስር ላይ የሚገኙት የቀድሞ የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ምክትል ዋና ዳይሬክተርና የአገር ውስጥ ደኅንነት ኃላፊ አቶ ያሬድ ዘሪሁን ላይ፣ ፍርድ ቤት ለሦስተኛ ጊዜ ተጨማሪ የ14 ቀናት የምርመራ ጊዜ ፈቀደ፡፡
የተጠርጣሪዎቹን የተለያዩ መከራከሪያ ሐሳቦችንና ሕገ መንግሥታዊ የዋስትና ጥያቄ ውድቅ በማድረግ፣ የምርመራ ሥራውን እያከናወነ ለሚገኘው የፌዴራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ቡድን ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ የፈቀደው የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ አሥረኛ ወንጀል ችሎት ነው፡፡ ፍርድ ቤቱ ተጨማሪ የምርመራ ጊዜውን የፈቀደው፣ መርማሪ ቡድኑ ቀደም ብሎ በዋለው ችሎት በተሰጠው 14 ቀናት ውስጥ የሠራውንና የሚቀረውን የምርመራ ሒደት ካስረዳ በኋላ ነው፡፡
መርማሪ ቡድኑ በተሰጠው 14 ቀናት የምርመራ ጊዜ ውስጥ አሏቸው ስለተባሉት የተለያዩ ተሽከርካሪዎችና ንብረቶችን የሚያውቁ ግለሰቦችን መለየቱን፣ በቦሌ ክፍለ ከተማ ውስጥ አላቸው ስለተባለው መኖሪያ ቤት፣ በፊንፊኔ ዙሪያ ሰበታ ከተማ ውስጥ 500 ካሬ ሜትር ላይ ያረፈ መኖሪያ ቤት በባለቤታቸው ስም፣ በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ በራሳቸውና በባለቤታቸው ስም መኖሪያ ቤት እንዳላቸው ማረጋገጡን አስረድቷል፡፡ ማተሚያ ቤታቸውን ከገዙ ግለሰብ ጋር ያላቸውን ግንኙነት እያጣራ መሆኑን፣ በተጠረጠሩበት ከባድ የሰብዓዊ መብት ጥሰት በሚመለከት የስምንት ምስክሮችን ቃል መቀበሉንና ፒፒሎኤ ለሚባለው ድርጅታቸው ከኦሮሚያ ኅብረት ሥራ ባንክ ብድር ሲወስዱ ለመያዣነት የተጠቀሙት ምን እንደሆነ ለማወቅ እየሠራ መሆኑን አስረድቷል፡፡
አቶ ያሬድ ከገቢ በላይ በርካታ ሀብቶችን ማፍራታቸውን የሚገልጹ የሰውና የሰነድ ማስረጃዎችን እየተቀበለ መሆኑን መርማሪ ቡድኑ ለፍርድ ቤቱ ገልጾ፣ የተለያዩ ማስረጃዎች ለማግኘት ለተለያዩ የመንግሥት ተቋማት የጻፋቸውን ደብዳቤዎች ምላሽ መቀበል፣ የባለቤታቸው እናት ወ/ሮ አበበች ጉደታ የገቢ ምንጭ ምን እንደሆነ ማጣራትና በደረሰባቸው ድብደባና የተለያየ ሥቃይ የሞቱ ሰዎች የአስከሬን ምርመራ ውጤት በተፈጥሮና በደረሰባቸው ጉዳት የሚል በመሆኑ፣ የማጣራትና የመሰብሰብ ሥራ እንደሚቀረው በመግለጽ ለተጨማሪ ምርመራ 14 ቀናት እንዲፈቀድለት ጠይቋል፡፡
የተጠርጣሪ ጠበቆች ባቀረቡት የመቃወሚያ ክርክር እንደገለጹት፣ ወንጀል በባህሪው ግላዊ ነው፡፡ በመሆኑም ደንበኛቸው የሠሩት በዝርዝር ተጠቅሶ መቅረብ አለበት ብለዋል፡፡ ከታሰሩ 35 ቀናት (እስከ ታኅሳስ 10 ቀን 2011 ዓ.ም. ድረስ) ቢሆናቸውም፣ የተጠርጣሪነት ቃላቸውን መርማሪ ቡድኑ እንዳልተቀበላቸው ገልጸዋል፡፡ ተጠርጣሪው ቃላቸውን ጠበቆቻቸው ባሉበት እንዲሰጡ አመልክተው፣ በተፈቀደላቸው መሠረት ጠበቆቻቸው ከቀኑ 7፡00 ሰዓት ጀምሮ እስከ 11፡00 ሰዓት ድረስ የቆዩ ቢሆንም፣ መርማሪዎችም ሆኑ ኃላፊዎች ሳያነጋግሯቸው መቅረታቸውን አመልክተዋል፡፡ ደጋግመው ቢጠይቁም ምላሽ የሚሰጣቸው ማጣታቸውንና ይባስ ብሎ የኮምፒዩተር ጌም እየተጫወቱ ሳያነጋግሯቸው መመለሳቸው እንደተሰማቸውና አንድ ሕግን አከብራለሁ ከሚል ተቋም የማይጠበቅ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
አቶ ያሬድ በዋናነት ተጠርጥረው የታሰሩት በሰብዓዊ መብት ጥሰት ቢሆንም፣ አሁን ግን እየተመረመሩ ያሉት ከገቢያቸው በላይ ሀብት ማፍራት የሙስና ወንጀል መሆኑን ጠበቆቻቸው ተናግረዋል፡፡ መርማሪ ቡድኑ ሥራውን በዘፈቀደ እየሠራ መሆኑንና በየቀጠሮ የሚያነሳው የምርመራ ጉዳይ ተመሳሳይ መሆኑን ጠቁመው፣ መርማሪ ቡድኑ ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ የጠየቀው የባለቤታቸውን እናት ሀብት ምንጭ ለማጣራት መሆኑን ጠቁመው፣ ‹‹የእሳቸው መታሰር ከዚህ ጋር ምን ያያይዘዋል?›› በማለትም ጠይቀዋል፡፡ መርማሪ ቡድኑ በጥቅል፣ ‹‹በርካታና የተለያዩ ጥቆማዎች እየደረሰኝ ነው፤›› ማለቱ አቶ ያሬድን ይመልከታቸው ወይም አይመልከታቸው ማብራራት ባልቻሉበት ሁኔታ በመሆኑ ተቀባይነት ሊኖረው እንደማይገባ አስረድተዋል፡፡ ፍርድ ቤቱ መርማሪ ቡድኑ ሥራውን እየሠራ ስለመሆኑ የምርመራ መዝገቡን እንዲያይላቸውም ጠይቀዋል፡፡ መርማሪ ቡድኑ የተለያዩ የቤት ቁጥሮችንና ቤቶችን እያጣራ ለጊዜ ቀጠሮ መጠየቂያ የሚጠቀምባቸው ቤቶች መንግሥት የሰጣቸው በመሆኑ፣ የጠየቀው 14 ቀናት ጊዜ ተገቢ አለመሆኑን አክለዋል፡፡ የተጠርጣሪውን ቃል መርማሪ ቡድኑ ቃላቸውን ተቀብሏቸው ቢሆን ኖሮ፣ ይኼንን ሁሉ ያቀልለት እንደነበርም ተናግረዋል፡፡ መርማሪ ቡድኑ በተጠርጣሪው ላይ እያቀረበ ያለው የምርመራ ሒደት የምርመራ ማስጀመርያ እንጂ፣ በወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ሕግ ቁጥር 25 መሠረት ማስረጃ የሚሆን ነገር እንደሌለው ጠቁመዋል፡፡ በመሆኑም የመርማሪ ቡድኑ ጥያቄ ውድቅ ተደርጎ የዋስትና መብታቸው እንዲታለፍ ጠይቋል፡፡
በቂ የምርመራ መነሻ በማቅረብ ፍርድ ቤቱ አምኖበት ጊዜ ቀጠሮ እየፈቀደለት እየሠራ መሆኑንና ተጠርጣሪው ከነበሩበት የሥራ ኃላፊነት አንፃር የተጠረጠሩበት የወንጀል ድርጊት ሰፊ መሆኑን በመግለጽ፣ መርማሪ ቡድኑ የዋስትና ጥያቄውን ተቃውሞ ምላሽ ሰጥቷል፡፡ አቶ ያሬድ በከባድ የሰብዓዊ መብት ጥሰትና የሙስና ወንጀሎች ጥሰት በመጠርጠራቸው እየደረሰው ያለውን ጥቆማ በምስክሮች እያረጋገጠና እየሠራ መሆኑን ተናግሯል፡፡
አቶ ያሬድ ተሽከርካሪዎችን ገዝተው ከአዲስ አበባ ውጪ እያከራዩ መሆኑን፣ በተለያዩ ቦታዎችም ቤቶችና ሌሎች ንብረቶች እንዳሏቸው ጥቆማ እየደረሰው በመሆኑ ማጣራት ስላለበት የጠየቀው ጊዜ እንዲፈቀድለት ጠይቋል፡፡
ከግምት ውስጥ መግባት ያለበት የተጠረጠሩበት ወንጀል እንጂ የነበሩበት ኃላፊነት መሆን እንደሌለበት በመጥቀስ የአቶ ያሬድ ጠበቆች የመርማሪ ቡድኑን ምላሽ ተቃውመዋል፡፡
የግራ ቀኙን ክርክር የሰማው ፍርድ ቤቱ የምርመራ መዝገቡን በአዳር አስቀርቦ ከተመለከተ በኋላ ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡ መርማሪ ቡድኑ በተሰጠው ጊዜ ሥራውን በአግባቡ መሥራቱ መገንዘቡንና ከሥራው ውስብስብነት አንፃር የጠየቀው ተጨማሪ ጊዜ ተገቢ መሆኑን በማመኑ፣ የተጠርጣሪ ጠበቆች ያቀረቡትን የመቃወሚያ ሐሳብና የዋስትና ጥያቄ ውድቅ በማድረግ፣ የተጠየቀውን 14 ቀናት ፈቅዶ ለታኅሳስ 24 ቀን 2011 ዓ.ም. ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡
በሌላ በኩል በተጠረጠሩበት ከፍተኛ የሙስና ወንጀል ታስረው በሚገኙት በሜቴክ የቀድሞ ዋና ዳይሬክተር ሜጀር ጄኔራል ክንፈ ዳኘው ላይ ፍርድ ቤቱ ለተጨማሪ ምርመራ 14 ቀናት ፈቅዷል፡፡ የፌዴራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ቡድን ቀደም ብሎ በተፈቀደለት ጊዜ ከናፍጣ ነዳጅ ማምረቻ ፋብሪካ ግዥ፣ ከተሽከርካሪ ግዥ፣ ከአውሮፕላን ግዥ፣ ከሆቴሎች፣ ከሕንፃዎችና ከመኖሪያ ቤቶች ግዥ፣ ከቆሻሻ የጄት ነዳጅ ማምረቻ ፋብሪካ ግንባታ፣ ከታላቁ ህዳሴ ግድብ ጫካ ምንጣሮ ጋር በተያያዘ በርካታ ሥራዎችን ሠርቶ፣ ቀሪ የምርመራ ሥራዎች እንደሚቀሩትም አስረድቷል፡፡ እንዲሁም ከብድርና ከስፖንሰር ክፍያዎች፣ ከመርከቦች ግዥና ጥገና፣ ከህዳሴ ግድቡ የኤሌክትሮ ሚካኒካልና ኃይድሮሊክ ሥራዎችና ተርባይኖች ግዥ፣ ከቢሾፍቱ አውቶሞቲቭ ኢንዱስትሪ የተፈጸመ የኮንስትራክሽን ማሽነሪዎችና የመኪና ኢንጂኖች ግዥ ጋር በተያያዘም፣ በርካታ የምርመራ ሥራዎችን መሥራቱንና የቀሩትንም ሥራዎች በመግለጽ ለፍርድ ቤቱ አስረድቷል፡፡ ሊብኸር ወርክ ጂኤምቢኤች ከተባለ የጀርመን ኩባንያ 6.4 ሺሕ ዩሮ አዲስና ሁለት ያገለገሉ ተንቀሳቃሽ ክሬኖች ግዥ፣ እንዲሁም አገር ውስጥ ከሚገኝና ቢዮ ከሚባል ኩባንያ ሦስት ክሬኖችና ኤሌክትሮድ በ6.9 ሚሊዮን ዩሮ ግዥ ጋር በተያያዘም የተለያዩ ማስረጃዎችን፣ የባለሙያና የምስክርነት ቃል መቀበሉንም መርማሪ ቡድኑ ገልጿል፡፡ ቀሪ ሥራዎች እንዳሉትም አስረድቷል፡፡
የሜቴክን የግዥ ሕጎች በመጣስ ዳኑቢያን ኤርክራፍት ከተባለ የሀንጋሪ ኩባንያ የ660 ሺሕ ዶላር ኳሊቲ ማኔጅመንት ሲስተም ኢምፕሌይመንቴሽን ግዥ መፈጸሙንና የተለያዩ ሰነዶችን ሰብስቦ የተለያዩ ሥራዎች እንደሚቀሩትም አስረድቷል፡፡ እንዲሁም በ2004 እና 2005 ዓ.ም. የግዥ ዘመን ፓወር ፕላስ ሊትድ ከተባለ የሲንጋፖር ኩባንያ የ56.9 ሚሊዮን ዶላር የማሽነሪ ግዥዎች ጋር በተያያዘም ሰነዶችን መሰብሰቡንና ቀሪ ሥራዎችን እንዳሉትም ተናግሯል፡፡ በተመሳሳይ ዘመን ቴክኖ ትሬድስ ኤስአርኤል ከተባለ የጣሊያን ኩባንያ የ4.5 ሚሊዮን ዩሮ ያገለገሉ ክሬኖች ግዥ መፈጸሙን የሚያሳዩ ሰነዶችን መሰብሰቡን፣ ቀሪ ምርመራም እንደሚቀረው መርማሪ ቡድኑ ገልጿል፡፡ የአዳማ እርሻ መሣሪያዎች ማምረቻ ኢንዱስትሪ፣ የትራክተሮችና የውኃ ፓምፖች ግዥን በሚመለከት፣ የውጭ አገር የትምህርት ዕድል ያላግባብ መስጠቱን በሚመለከትና የአዲስ አበባ ከተማ ስማርት መኪና ማቆሚያ ግንባታ ግዥ ጋር በተገናኘ፣ በርካታ ሰነዶችን መሰብሰቡንና ቀሪ ሥራዎችም እንዳሉት መርማሪ ቡድኑ ለፍርድ ቤቱ አስረድቷል፡፡ ከአዲስ አበባ ከተማ አውቶብስ ግዥም ጋር በተያያዘ የተለያዩ የምርመራ ሥራዎች መሥራቱንና ቀሪ ሥራዎች እንዳሉት በማስረዳት ለተጨማሪ ምርመራ 14 ቀናት እንዲፈቀድለት ጠይቋል፡፡
የተጠርጣሪ ጠበቆች የመርማሪ ቡድኑ በየቀጠሮ የሚያቀርበው የምርመራ ሒደት ተመሳሳይ መሆኑን ገልጸው፣ 14 ቀናት ሊጠይቅ እንደማይገባ በመግለጽ ተቃውመዋል፡፡ ከግዥም ጋርም ሆነ ከሌሎች ሥራዎች ጋር በተያያዘ ውል ካገኘ መርማሪ ቡድኑ ሌላ ሰነድ ለመፈለግ በሚል ተጨማሪ ጊዜ የሚጠይቀው ተጠርጣሪን ሆን ብሎ በእስር ለማቆየት መሆኑንም ተናግረዋል፡፡
አዲስ የምርመራ ግኝት በማለት መርማሪ ቡድኑ የሚናገረው ከፍርድ ቤት ፈቃድ ሳያገኝ ያከናወነው ሥራ በመሆኑ ተቀባይነት እንደሌለውም አስረድተዋል፡፡ ማስረጃ ስለሌለውም ውድቅ እንዲደረግላቸውም ጠይቀዋል፡፡ ደንበኛቸው የዋስ መብታቸው እንዲከበርላቸውም ጠይቀዋል፡፡
የግራ ቀኙን ክርክር ያዳመጠው ፍርድ ቤቱ የምርመራ መዝገቡን በአዳር አስቀርቦ ከተመለከተ በኋላ፣ የተጠርጣሪ ጠበቆች ያቀረቡትን መቃወሚያ ክርክርና የጠየቁትን ዋስትና ውድቅ በማድረግ፣ ተጨማሪ 14 ቀናት የምርመራ ጊዜ በመፍቀድ ለታኅሳስ 22 ቀን 2011 ዓ.ም. ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡
Average Rating