www.maledatimes.com ፌዴራል ፖሊስ ስለታገዱት የሪል ስቴት ኩባንያዎች መረጃዎች እንዲላኩለት ጠየቀ - MALEDA TIMES
Loading...
You are here:  Home  >  Ethiopia  >  Current Article

ፌዴራል ፖሊስ ስለታገዱት የሪል ስቴት ኩባንያዎች መረጃዎች እንዲላኩለት ጠየቀ

By   /   December 23, 2018  /   Comments Off on ፌዴራል ፖሊስ ስለታገዱት የሪል ስቴት ኩባንያዎች መረጃዎች እንዲላኩለት ጠየቀ

    Print       Email
0 0
Read Time:2 Minute, 9 Second

የታገዱ የሪል ስቴት ኩባንያዎች የሚካሄድባቸው ምርመራ በፍጥነት እንዲጠናቀቅ ጠየቁ

በ28 የሪል ስቴት ኩባንያዎች ላይ ታኅሳስ 8 ቀን 2011 ዓ.ም. ከወጣው ዕግድ በኋላ፣ ፌዴራል ፖሊስ በኩባንያዎቹ ላይ የአዲስ አበባ ከተማ ክፍላተ ከተሞችን መረጃዎች ጠየቀ፡፡

ፌዴራል ፖሊስ ለአሥሩም ክፍላተ ከተሞች የመሬት ባንክና ማስተላለፍ ጽሕፈት ቤቶች፣ እንዲሁም ለይዞታ አስተዳደር የሽግግር ጊዜ አገልግሎት ዴስክ በጻፈው ደብዳቤ ተቋማቱ ኩባንያዎቹን በተመለከተ መረጃዎች እንዲልኩ ጠይቋል፡፡

ፌዴራል ፖሊስ በጻፈው ደብዳቤ በከባድ የሰብዓዊ መብት ጥሰትና የሙስና ወንጀል በተጠረጠሩ ግለሰቦች ላይ የምርመራ ሥራ እያከናወነ መሆኑን አስታውሷል፡፡

ከዚሁ ምርመራ ጋር በተያያዘ ቢሮው ለሥራው ይረዳ ዘንድ ተቋማቱ የሪል ስቴት ኩባንያዎቹን መረጃዎች እንዲልኩ ጠይቋል፡፡

ፌዴራል ፖሊስ የጠየቃቸው መረጃዎች የኩባንያዎቹ ባለቤቶች እነማን እንደሆኑ፣ ኩባንያዎቹ የመሬት ሊዝ የከፈሉበት ሰነድ፣ ቤት ገንብተው ያስተላለፉላቸው ግለሰቦች ዝርዝርና የተላለፈበትን ዋጋ የያዙ ሰነዶች፣ እንዲሁም ሌሎች ተያያዥ ሰነዶች እንዲላኩለት ጠይቋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ ፌዴራል ፖሊስ በተሻሻለው የፀረ ሙስና ልዩ የሥነ ሥርዓትና የማስረጃ ሕግ አዋጅ ቁጥር 434/97 አንቀጽ 8(4) (በአዋጅ ቁጥር 882/2007 አንቀጽ 5 እንደተሻሻለው) መሠረት ታግዶ፣ ሕንፃዎቹ በማን ስም እንደሚገኙና የቦታዎቹን አሰጣጥ ሕጋዊነት፣ እንዲሁም ቦታዎቹ ከተጠርጣሪ ግለሰብ ወደ ሦስተኛ ወገን ተላልፈው ከሆነ ለእነ ማንና እንዴት እንደተላለፈ ተጣርቶ ከአስፈላጊው ሰነድ ጋር እንዲላኩለት ጠይቋል፡፡

ፌዴራል ፖሊስ በተሻሻለው የፀረ ሙስና ኮሚሽን ማቋቋሚያ አዋጅ ቁጥር 433/97 አንቀጽ 26 ንዑስ አንቀጽ 3 እና 4 መሠረት መረጃ መጠየቁን አስታውቆ፣ ተቋማቱ ጉዳዩ በፍርድ ቤት ቀጠሮ ላይ የሚገኝ መሆኑን በመገንዘብ ማስረጃዎችን በተቻለ ፍጥነት እንዲልኩ አሳስቧል፡፡ 

የሪል ስቴት ኩባንያዎች መታገድ ከተሰማ በኋላ የሪል ስቴት ገበያ ከመቀዛቀዝ አልፎ በደንበኞች ላይ ድንጋጤ መፍጠሩ ታውቋል፡፡

ሪፖርተር ያነጋገራቸው የሪል ስቴት ኩባንያዎች እንደሚሉት፣ የሪል ስቴት ዘርፍ ለበርካታ ጊዜያት በተለያዩ ምክንያቶች ቀውስ ውስጥ የቆየ እንደመሆኑ የሥጋት ቀጣና ነው፡፡

በአዲስ አበባ በተለይ ከ1996 ዓ.ም. ወዲህ በርካታ ኩባንያዎች በሪል ስቴት ዘርፍ ተሰማርተዋል፡፡ ዘርፉ በየጊዜው የተለያዩ ችግሮች የሚገጥሙት በመሆኑ የተረጋጋ መሆን ባለመቻሉ መንግሥት ለጉዳዩ ትኩረት እንዲሰጥ ኩባንያዎቹ ጠይቀዋል፡፡    

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምንም ዓይነት አገልግሎት እንዳያገኙ ታኅሳስ 8 ቀን 2011 ዓ.ም. ያገዳቸው 28 የሪል ስቴት ኩባንያዎች፣ በመታገዳቸው ምክንያት የገበያ መናጋት መፈጠሩን በመጥቀስ አስተዳደሩ የጀመረውን ማጣራት ባስቀመጠው ቀነ ገደብ እንዲያጠናቅቅም ጠይቀዋል፡፡

በብዙ ፈተናዎች ውስጥ አልፎ አንፃራዊ መረጋጋት ታይቶበት የቆየው የሪል ስቴት ዘርፍ፣ ባለፈው ሳምንት ከወጣው የ28 ሪል ስቴት ኩባንያዎች ዕግድ በኋላ በድጋሚ ቀውስ ውስጥ መግባቱን የኩባንያዎቹ ኃላፊዎች ተናግረዋል፡፡

ለሪፖርተር አስተያየታቸውን የገለጹ የሪል ስቴት ኩባንያ ኃላፊዎች እንደሚሉት፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሕገወጥነትን ለመዋጋት የሚወስደውን ዕርምጃ ይደግፋሉ፡፡ ነገር ግን የማጣራት ሒደቱ በፍጥነት ተቋጭቶ ውጤቱ ይፋ እንዲደረግ ይፈልጋሉ፡፡

ምክንያታቸውን ሲገልጹም በአሁኑ ወቅት የሪል ስቴት ኩባንያዎች የገነቧቸውን ቤቶች ለደንበኞች በማስተላለፍ ሒደት ላይ የሚገኙ በመሆኑ፣ በዚህ ወር መጨረሻ ለሚከበረው የገና በዓል በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ወደ አገራቸው ስለሚመጡና ባንኮች ደግሞ የቤት ግዥ ፋይናንስ እንደሚያቀርቡ የገለጹ ስለሆነ ለሪል ስቴት ቤቶች የተሻለ የገበያ ወቅት በመሆኑ ነው ብለዋል፡፡

የማጣራት ሒደቱ በፍጥነት አልቆ ሕጋዊና ሕገወጡ ተለይቶ ዘርፉ በፍጥነት ከቀውስ መውጣት አለበት በማለት፣ የሪል ስቴት ኩባንያዎች የማጣራት ሒደቱ እንዲፋጠን ጠይቀዋል፡፡ 

Happy
Happy
0 %
Sad
Sad
0 %
Excited
Excited
0 %
Sleepy
Sleepy
0 %
Angry
Angry
0 %
Surprise
Surprise
0 %
    Print       Email
  • Published: 6 years ago on December 23, 2018
  • By:
  • Last Modified: December 23, 2018 @ 2:59 pm
  • Filed Under: Ethiopia

Average Rating

5 Star
0%
4 Star
0%
3 Star
0%
2 Star
0%
1 Star
0%
<"Without the support of our readers, the Maleda Times website would not exist in its present form">

You might also like...

በሰሜን ሸዋ ዞን ኤፍራታ እና ግድም ወረዳ መከላከያ ከአማራው ማህበረሰብ እና ከፋኖ ጋር ጦርነት ገጥሟል

Read More →

This site is protected by wp-copyrightpro.com

Skip to toolbar