- ጠንካራ ተቆጣጣሪ ባለሥልጣን ካልተቋቋመ ፕራይቬታይዜሽን አደጋ ሊያስከትል እንደሚችል ተገለጸ
ከ300 በላይ የሚሆኑ ሕገወጥ የቴሌኮም አገልግሎት ሰጪዎች በተለያዩ ክልሎች በመንቀሳቀስ፣ ኢትዮ ቴሌኮምን ከፍተኛ መጠን ያለው የውጭ ምንዛሪ እያሳጡት እንደሆነ ተገለጸ፡፡
ሐሙስ ታኅሳስ 11 ቀን 2011 ዓ.ም. በጽሕፈት ቤታቸው መግለጫ የሰጡት የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ሥራ አስፈጻሚ ወ/ሪት ፍሬሕይወት ታምሩ፣ በአዲስ አበባና በተለያዩ ክልሎች በማጭበርበር ድርጊት የተሰማሩ ግለሰቦች ኢትዮ ቴሌኮምን ብቻ ሳይሆን በአገር ላይ ከፍተኛ ጉዳት እያደረሱ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ ግለሰቦቹ በርካታ ሲም ቦክሶችን በተለያየ መንገድ ወደ አገር በማስገባት ከውጭ የሚደረጉ ጥሪዎችን በኢትዮ ቴሌኮም መሠረተ ልማት ጠልፈው ለደንበኞች በማስተላለፍ፣ ከውጭ ኩባንያዎች የአገልግሎት ክፍያ እንደሚሰበስቡ ወ/ሪት ፍሬሕይወት አስረድተዋል፡፡
‹‹መንግሥት የሚያውቀው አንድ ሕጋዊ ቴሌኮም ኦፕሬተር ብቻ መኖሩን ነው፡፡ ነገር ግን ከውጭ የሚመጡ ጥሪዎች ከ300 በላይ በሚሆኑ ሕገወጥ ኦፕሬተሮች እየተስተናገዱ ነው፤›› ያሉት ወ/ሪት ፍሬሕይወት፣ አንዱ ሲም ቦክስ ከ1,000 በላይ ሲም ካርዶች እንደሚይዝ ገልጸው፣ ግለሰቦች በሐሰተኛ መታወቂያ ሲም ካርድ እንደሚገዙ፣ አንዳንድ ግለሰቦች ከአሥር እስከ 15 መታወቂያ ይዘው ሲም ካርድ እንደሚገዙ ተናግረዋል፡፡
‹‹አገሩ በሲም ቦክስ ተሞልቷል፤›› ያሉት ወ/ሪት ፍሬሕይወት፣ ኢትዮ ቴሌኮም በቅርቡ የመከታተያ መሣሪያ መግዛቱን ጠቁመው ሕገወጥ ኦፕሬተሮቹ የሚንቀሳቀሱባቸውን አካባቢዎች መለየት መቻሉን ገልጸዋል፡፡ ‹‹አብዛኛዎቹ ሲም ቦክሶች በተወሰኑ ግለሰቦች የተያዙ እንደሆነ ለማወቅ ችለናል፡፡ ከጅማ ስናባርራቸው ወደ ድሬዳዋ ይሄዳሉ፡፡ ከእነዚህ ሲም ቦክሶች በስተጀርባ የተወሰኑ ኩባንያዎችና ግለሰቦች በሕገወጥ መንገድ ሀብት እያከማቹ እንደሆነ አውቀናል፡፡ እነዚህ ግለሰቦች ለአገር ደኅንነት አሥጊ ናቸው፤›› ብለዋል፡፡ መንግሥት ከፍተኛ መዋዕለ ንዋይ ባፈሰሰበት የቴሌኮም መሠረተ ልማት ተጠቃሚ እንዳይሆን መደረጉን ተናግረዋል፡፡
በየወሩ በአማካይ ከኢትዮጵያ ወደ ውጭ 4.7 ሚሊዮን ጥሪዎች ሲደረጉ፣ ከተለያዩ አገሮች 23 ሚሊዮን ጥሪዎች ወደ ኢትዮጵያ እንደሚደረጉ ታውቋል፡፡
ለሕገወጥ የቴሌኮም አገልግሎት መስፋፋት የተለያዩ ምክንያቶች ተጠቅሰዋል፡፡ ኢትዮ ቴሌኮም ለዓለም አቀፍ ሥራ ትኩረት አለመስጠቱ፣ የውጭ ጥሪዎች ለመቀበል የሚያስከፍለው ክፍያም ከፍተኛ መሆን፣ የዓለም አቀፍ ጥሪ ዋጋ በየጊዜው አለመከለሱና በሕገወጥ ቴሌኮም አገልግሎት የተሰማሩ ግለሰቦችን ተከታትሎ ለሕግ የማቅረብ ሥራ በበቂ መጠን አለመከናወን እንደ ድክመት ተዘርዝረዋል፡፡
ይሁን እንጂ የሕገወጥ ቴሌኮም አገልግሎት መስፋፋት ተጠያቂው ኢትዮ ቴሌኮም ብቻ እንዳልሆነ ወ/ሪት ፍሬሕይወት አስረድተዋል፡፡ ይህ ሁሉ ሲም ቦክስ ወደ አገር ሊገባ የቻለው የገቢዎች ሚኒስቴር ሥራውን በአግባቡ ባለመሥራቱ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ ‹‹ፖሊስ፣ ደኅንነት፣ ገቢዎች ሚኒስቴርና ሌሎች የሕግ አካላት በሙሉ ኃላፊነታቸውን ባለመወጣታቸው ነው፤›› ብለዋል፡፡
ኢትዮ ቴሌኮም የውጭ ጥሪዎችን በማስተናገድ ያገኝ የነበረው ገቢ ባለፉት ሰባት ዓመታት እያሽቆለቆለ መሆኑ ተገልጿል፡፡ ቀደም ሲል ከገቢው ሃያ በመቶ የሚሆነውን የሚሰበስበው የውጭ ጥሪ በመቀበል ከሚሰጠው አገልግሎት የነበረ ቢሆንም፣ እየተስፋፋ በመጣው የቴሌኮም ማጭበርበር ምክንያት ወደ አምስት በመቶ እንደወረደ ታውቋል፡፡
የቴሌኮም ኢንዱስትሪ በፍጥነት የሚለዋወጥ ቢሆንም ኢትዮ ቴሌኮም ዓለም አቀፍ ገበያውን እየተከታተለ የዋጋ ማሻሻያዎችን ቶሎ ቶሎ እንደማይከልስ ዋና ሥራ አስፈጻሚዋ ተናግረዋል፡፡ ‹‹ለውጭ ጥሪ መቀበያ የምናስከፍለው ዋጋ መጨረሻ የተከለሰው እ.ኤ.አ. በ2013 ሲሆን፣ ላለፉት ስድስት ዓመታት ማሻሻያ ሳናደርግ ቆይተናል፡፡ በቅርቡ የዋጋ ክለሳ ካደረግን በኋላ በምናስተናግደው ጥሪ ላይ ከፍተኛ ለውጥ ዓይተናል፤›› ብለዋል፡፡ ኢትዮ ቴሌኮም በቀን በአማካይ 500,000 ደቂቃ የውጭ ጥሪ ይቀበል እንደነበር ገልጸው፣ የዋጋ ማሻሻያ ከተደረገ በኋላ በቀን በአማካይ 800,000 ደቂቃ በመቀበል ላይ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
ከውጭ የሚቀበለው ጥሪ በ40 በመቶ እንደጨመረ የገለጹት ወ/ሮ ፍሬሕይወት፣ ከዓለም አቀፍ ጥሪ የሚገኘውን ገቢ በ60 በመቶ ለማሳደግ እንደታቀደ ተናግረዋል፡፡
አሜሪካ፣ አውሮፓ፣ መካከለኛው ምሥራቅና ደቡብ አፍሪካ ኢትዮጵያውያን በብዛት የሚኖሩባቸው በመሆናቸው፣ በርካታ ጥሪዎች ከእነዚህ አካባቢዎች እንደሚመነጩ ታውቋል፡፡ ኢትዮ ቴለኮም የውጭ ምንዛሪ ገቢውን ለማሻሻል ዓለም አቀፍ ቢዝነስ ክፍል ማዋቀሩንና ተጠሪነቱ ለዋና ሥራ አስፈጻሚ እንደሆነ ተገልጿል፡፡ ኃላፊና ባለሙያዎች ለአዲሱ የዓለም አቀፍ ቢዝነስ ክፍል እንደተመደቡለት ወ/ሪት ፍሬሕይወት ተናግረዋል፡፡
ዓለም አቀፍ ሥራውን ለማጠናከርም በዓለም አቀፍ ጥሪዎች ላይ ከአሥር እስከ አርባ በመቶ የሚደርስ የዋጋ ቅናሽ ያደረገ መሆኑን፣ በአጭር የጽሑፍ መልዕክት ላይ የ51 በመቶ ቅናሽ እንዳደረገ አስታውቋል፡፡
ኢትዮ ቴሌኮም ከደንበኞች ያልሰበሰበው 800 ሚሊዮን ብር የአገልግሎት ክፍያ እንዳለው አስታውቋል፡፡ ግለሰቦችና ኮርፖሬት ደንበኞች ለተጠቀሙበት የስልክና የኢንተርኔት ብሮድባንድ አገልግሎት ያልፈጸሙት 800 ሚሊዮን ብር ዕዳ እንዳለ ወ/ሪት ፍሬሕይወት ገልጸው፣ ‹‹ጉዳዩን እየመረመርን ነው፡፡ ችግሩ ከእነሱ ነው ወይስ ከእኛ የሚለውን እያጠናን ነው፤›› ብለዋል፡፡
በተያያዘ ዜና ኢትዮ ቴሌኮም ለረዥም ጊዜ ተዘግተው የቆዩ የሞባይል ቁጥሮች በድጋሚ ለሽያጭ ማቅረብ መጀመሩን አስታውቋል፡፡ እንደ ዋና ሥራ አስፈጻሚዋ ገለጻ ከሁለት እስከ ሰባት ዓመታት አገልግሎት ሳይሰጡ የቆዩ 18 ሚሊዮን የሞባይል ቁጥሮች ጥቅም ላይ ለማዋል እንቅስቃሴ ተጀምሯል፡፡
‹‹የሞባይል መስመር የፈቃድ ክፍያ የምንፈጽምበት ሀብት ስለሆነ በአግባቡ ልንጠቀምበት ይገባል፡፡ ከሁለት ዓመት በላይ ምንም ዓይነት ጥሪ ያላስተናገዱ የሞባይል ቁጥሮች ከታኅሳስ 12 ቀን 2011 ዓ.ም. ጀምሮ በመዝጋት እንደ አዲስ ለደንበኞች ለሽያጭ ማቅረብ ጀምረናል፤›› ብለዋል፡፡
ፕራይቬታይዜሽንን አስመልክቶ የተጠየቁት ወ/ሪት ፍሬሕይወት፣ የኢትዮ ቴሌኮም ፕራይቬታይዜሸን በዋነኛነት የሚያስተባብረው የገንዘብ ሚኒስቴር ቢሆንም ኢትዮ ቴሌኮም እንደ ዋነኛ ተዋናይ በቅድመ ዝግጅቱ ላይ በንቃት በመሳተፍ ላይ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
የተሳካ የቴሌኮም ዘርፍ ትራንስፎርሜሽን ለማካሄድ ጠንካራ የሆነ፣ የቴክኖሎጂ ዕውቀትና የገንዘብ አቅም ያለው ተቆጣጣሪ ባለሥልጣን ማቋቋም ወሳኝ መሆኑን የገለጹት ወ/ሪት ፍሬሕወት፣ በአሁኑ ወቅት ብቃት ያለው ተቆጣጣሪ ባለሥልጣን አለ ብለው እንደማያምኑ አስረድተዋል፡፡ ‹‹ዛሬ አንድ ኦፕሬተር ብቻ ስላለ የተቆጣጣሪ ባለሥልጣን አስፈላጊነት ብዙ ላይታይ ይችላል፡፡ ነገ ሁለት ሦስት ኦፕሬተሮች ሲኖሩ ብዙ ችግር ሊፈጠር ይችላል፡፡ ጠንካራ ተቆጣጣሪ ባለሥልጣን ሳይቋቋም ወደ ፕራይቬታይዜሽን መግባት አደጋ ሊያስከትል ይችላል፡፡ የቴሌኮም ትራንፎርሜሽን የተሳካላቸው አገሮች እንዳሉ ሁሉ ያልተሳካላቸውም አሉ፤›› ያሉት ወ/ሪት ፍሬሕይወት፣ መንግሥት አዲስ የኮሙዩኒኬሽን አዋጅ በማዘጋጀት ላይ መሆኑንና ኢትዮ ቴሌኮምም እንደ ዋነኛ ተዋናይ የበኩሉን አስተዋጽኦ በማድረግ ላይ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ አዋጁ የቴሌኮምና ብሮድካስቲንግ ዘርፎችን አንድ ላይ አካቶ የያዘ እንደሆነ ለማወቅ ተችሏል፡፡
የቅድመ ፕራይቬታይዜሸን ሥራው በመልካም ሒደት ላይ እንደሚገኝ ገልጸው፣ አንዳንድ ግለሰቦች ሥራውን እንደተጠናቀቀ በማስመሰል ኩባንያዎች ኢትዮ ቴሌኮምን ሊገዙት እንደሆነ የሚገልጽ የሐሰት ዜና በማሠራጨት ላይ እንደሆኑ ጠቁመዋል፡፡
‹‹እከሌ የተባለው ኩባንያ ኢትዮ ቴሌኮምን ሊወስደው ነው እያሉ የሐሰት ዜና በማሠራጨት የተጠመዱ ደላሎች አሉ፡፡ የመንግሥት ዓላማ ኢትዮ ቴሌኮምን አድቅቆ ሌላ አፕሬተር ማምጣት አይደለም፡፡ በፍፁም እንደሱ አይሆንም፡፡ ቢገባን ኢትዮ ቴሌኮም ከፍተኛ ገንዘብ የፈሰሰበት የኢትዮጵያ ሕዝብ ሀብት ነው፡፡ መንግሥት ማየት የሚፈልገው የተጠናከረና ተወዳዳሪ የሆነ ኢትዮ ቴለኮምን ነው እንጂ፣ እሱን አጥፍቶ ሌላ አገልግሎት ሰጪ ማምጣት አይደለም፤›› ያሉት ወ/ሪት ፍሬሕይወት፣ ኢትዮ ቴሌኮምን ከገበያ ለማስወጣት በተለያዩ ኃይሎች አሻጥር እየተሠራ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ ‹‹አንዳንድ ዓለም አቀፍ ግንኙነቶችን በመዝጋት ኢትዮ ቴሌኮም አልቻለም ይዘጋ እያሉ የሚሟገቱ አሉ፡፡ አንዳንዱ ስለታሪፍ ሲወራ ኢትዮ ቴሌኮም ይሸጥ፣ ይዘጋ ይላል፡፡ ይህ በዕውቀት ላይ ያልተመረኮዘ አስተያየት ነው፡፡ ለራሳችን ስንል በዕውቀት ላይ የተመረኮዘ አስተያየት ብንሰጥ ጥሩ ነው፡፡ ኢትዮ ቴሌኮም ተወዳዳሪ፣ ብቁና ደንብኞቹን ማርካት የሚችል አገልግሎት ሰጪ ተቋም እንዲሆን የምንችለውን ሁሉ ጥረት እናደርጋለን፤›› ብለዋል፡፡
የኢትዮ ቴሌኮም ዓላማ ገቢውን በማሳደግ ለመንግሥት ከፍተኛ የገቢ ድርሻና ግብር በመከፈል መንግሥት ለሚያካሂዳቸው ሌሎች የልማት ፕሮጀክቶች የበኩሉን አስተዋጽኦ ማድረግ እንደሆነ ገልጸው፣ በአንዳንድ ቡድኖች የድርጅቱን እሴት በማንኳሰስ ሌሎች አገልግሎት ሰጪዎችን ለማስገባት የሚደረገው ጥረት ገቢ አይደለም ብለዋል፡፡Facebook
Average Rating