www.maledatimes.com መርማሪ ፖሊስ በሜጀር ጄኔራል ክንፈ ዳኘው ላይ የተገኙ አዳዲስ ተሳትፎዎችን ይፋ አደረገ - MALEDA TIMES
Loading...
You are here:  Home  >  Ethiopia  >  Current Article

መርማሪ ፖሊስ በሜጀር ጄኔራል ክንፈ ዳኘው ላይ የተገኙ አዳዲስ ተሳትፎዎችን ይፋ አደረገ

By   /   December 24, 2018  /   Comments Off on መርማሪ ፖሊስ በሜጀር ጄኔራል ክንፈ ዳኘው ላይ የተገኙ አዳዲስ ተሳትፎዎችን ይፋ አደረገ

    Print       Email
0 0
Read Time:3 Minute, 54 Second

መርማሪ ፖሊስ በሜጀር ጄኔራል ክንፈ ዳኘው ላይ የተገኙ አዳዲስ ተሳትፎዎችን ይፋ አደረገ

በዛሬው የችሎት ውሎ መርማሪ ፖሊስ በቀድሞው የብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን ዋና ዳይሬክተር ሜጀር ጄኔራል ክንፈ ዳኘው ላይ በምርመራ ወቅት ያገኛቸውን አዲስ የወንጀል ተሳትፎዎችን ለችሎቱ በማመልከቻው አስገብቶ ችሎቱም ለተጠርጣሪውና ለችሎቱ ታዳሚዎች በንባብ አሰምቷል።

ከተጠቀሰባቸው አዳዲስ የወንጀል ግኝቶች መካከልም የሚከተሉት ይገኙበታል።

የብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን ሃይ-ቴክ ኢንዱስትሪ ሲ ኢ አይ ኢ ሲ ከተባለ የቻይና ኩባንያ ያለጨረታ፣ ያለዕቅድና የግዥ ፍላጎት፥ በቁጥር 100 የሆኑ የእግረኛ ራዳሮች በ8 ሚሊየን 581 ሺህ 92 የአሜሪካ ዶላር የግዥ ውል ስምምነት እንዲፈጸም በማድረግና ውሉን በማፅደቅ መጠርጠራቸውን፣ ሜቴክ ከሃይ ቴክ ኢንጅነሪንግ ኢንዱስትሪ ኤል አይ ቲ ከተባለ የቻይና ኩባንያ ያለጨረታ፣ ያለ እቅድና የግዥ ፍላጎት በቁጥር 100 የሆኑ የእግረኛ ራዳሮችን በ10 ሚሊየን 236 ሺህ 700 የአሜሪካ ዶላር በፈረንጆቹ 2010/11 የግዥ ውል ስምምነት እንዲፈጸም በማድረግና ውሉን በማፅደቅ የተጠረጠሩ፣ 10 የእግረኛ ራዳሮችን ብቻ የተረከቡ መሆኑና የቀሩት 90 የእግረኛ ራዳሮች የት እንዳሉ የማይታወቅ መሆኑን ጠቅሷል፤

በዚህም ከ18 ሚሊየን 817 ሺህ የአሜሪካ ዶላር በላይ የመንግስትና የህዝብ ሃብት ያለአግባብ አባክነዋል በሚል መጠርጠሩን አስረድቷል።
ከህዳሴው ግድብ የኤሌክትሮ መካኒካልና የሃይድሮሊክ ስራዎችና የተርባይኖች ግዥን በተመለከተ

ግለሰቡ የሜቴክ ዋና ዳይሬክተር በነበሩበት ወቅት የታላቁ ህዳሴ ግድብን የኤሌክትሮ መካኒካልና የሃይድሮሊክ ስራዎችን ለመስራት ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሃይል ኮርፖሬሽን ጋር በፈረንጆቹ ጥቅምት ወር 2011 በተፈረመ የ24 ቢሊየን 400 ሚሊየን 463 ሺህ 424 ብር ከ96 ሳንቲም ውል መፈራረማቸውን፣ በዚህ ስራ ሜቴክ 23 በመቶ ብቻ አከናውኖ ሳለ የውሉን 65 ነጥብ 65 በመቶ ወይም 16 ቢሊየን 790 ሚሊየን 601 ሺህ 80 ብር ከ48 ሳንቲም ላላከናወነው ስራ ክፍያ እንዲፈጸም በማድረግ የተጠረጠሩ እና ከዚህ ገንዘብ ውስጥ 7 ቢሊየን 276 ሚሊየን 408 ሺህ 897 ብር ከ60 ሳንቲም ብር የት እንደደረሰ ወይም ለምን ስራ እንዳዋሉት አይታወቅም ሲል አስረድቷል ፖሊስ።

ለግድቡ የሚሆኑት አምስት ተርባይኖች ያለ ጨረታ ከውጭ ሃገር ያገለገሉ እና የታለመለትን ሃይል ማመንጨት የማይችሉ በተጋነነ ዋጋ እንዲገዙ በማድረግ በሃገር ኢኮኖሚ ላይ ከፍተኛ ጉዳት በማድረስ የተጠረጠሩ፣ ሜቴክ ስራውን እሰራለሁ ብሎ ከተረከበ በኋላ ከህግ ውጭ ስራውን ለሌች ድርጅቶች በንዑስ ተቋራጭነት አላግባብ መስጠቱን፣ ለግድቡ የሚሆን ሲሚንቶ በመሰቦ ሲሚንቶ ፋብሪካ እንዲቀርብ የተደረገበት አግባብ ከዋጋ፣ ከጥራትና ከቦታ ርቀት አንጻር አግባብ አለመሆኑ (ጥራቱ የወረደና ግድቡ ከሚያስፈልገው ሲሚንቶ በላይ እየቀረበ ብዙ ሺህ ኩንታል ሲሚንቶ እንዲበላሽ ሆኗል)፣ ከግድቡ ስራ ጋር በተያያዘ ሜቴክ የሚፈጽማቸው የትራንስፖርት አገልግሎት ግዥዎች ላይ በርካታ ወንጀሎች መፈጸማቸውንና ከዚህ ጋር የተያያዙ በርካታ ጥቆማዎችንም አቅርቧል።

ለቢሾፍቱ አውቶሞቲቭ ኢንዱስትሪ የተፈፀመ ኮንስትራክሽን ማሽነሪዎች እንዲሁም የመኪና ኢንጅኖችን በተመለከተ

ግለሰቡ ሜቴክን በሚመሩበት ወቅት ለቢሾፍቱ አውቶሞቲቭ ኢንዱስትሪ ተብለው ከ2002 እስከ 2005 ዓ.ም ድረስ ከውጭ የተገዙ የኮንስትራክሽን ማሽነሪዎች፣ የማሽን አካላትና የመኪና ኢንጅኖች ግዥ ሲፈጸም በህጉ መሰረት የግዥ ፍላጎት ቀርቦ ጨረታ ባልወጣበትና አቅራቢው ያቀረበው ዋጋ ተወዳዳሪ የገበያ ዋጋ መሆኑ ባልተረጋገጠበት ሁኔታ እና የተጋነነ ዋጋ ከተለያዩ 13 አይነት ኩባንያዎች በጠቅላላው ከ29 በላይ ውሎች እንዲፈጸሙ በማድረግ ውሎችን በማፅደቅ በጠቅላላው ከ1 ቢሊየን ዶላር በላይ አለም አቀፍ ግዥ በመፈጸም መንግስት ከገበያ ውድድር ማግኘት የሚገባውን ጥቅም በማሳጣት መጠርጠሩን፤

ሌበኸር ወርክ ጂ ኤም ቢ ኤች ከተባለ የጀርመን ኩባንያ 6 ሚሊየን 465 ሺህ ዩሮ የሚያወጡ 3 አዳዲስና 2 ያገለገሉ ተንቀሳቃሽ ክሬኖችን እንዲሁም ከዚሁ ኩባንያ እና ሃገር ውስጥ ከሚገኝ ቢዮ ፒ ኤል ሲ ከተባለ ኩባንያ ሌሎች ሶስት ክሬኖችና ኤሌክትሮድ በ6 ሚሊየን 997 ሺህ 65 ዩሮ ከአንድ አቅራቢ በተፈጸመ ግዥ መጠርጠሩን፤

የሜቴክ ሃላፊዎችና ሰራተኞች የተቋሙንና የፌደራል መንግስቱን የግዥ ህጎች በመጣስ ዳኑቢያን ኤርክራፍት ከተባለ የሃንጋሪ ኩባንያ ያለምንም ጨረታና ውድድር በቀጥታ ግዥ quality management system implementation systems implementation phase 2 በሚል በተፈጸመ የ660 ሺህ ዶላር የአገልግሎት ግዥ መጠርጠሩን፣ የሜቴክ ሰራተኞችና ሃላፊዎች በ2004/2005 የግዥ ዘመን ምንም አይነት አለም አቀፍ ጨረታ ሳይወጣ፥ ግዥው የሚፈጸምበትን ሃገር፣ የሚገዛበትን የገንዘብ መጠን፣ ግዥው የሚፈጸምበትን ኩባንያ አስቀድሞ በመወሰን ፓወር ፕላስ ፒ ቲ ኢ ከተሰኘ የሲንጋፖር ኩባንያ የ56 ሚሊየን 943 ሺህ 800 የአሜሪካ ዶላር የኮንስትራክሽን ማሽነሪዎች ግዥ የፈጸሙና መንግስት ከገበያ ውድድር ማግኘት ይችል የነበረውን የጥራትና የገንዘብ ጥቅም በማሳጣት መጠርጠሩን፤

የሜቴክ ሰራተኞችና ሃላፊዎች በ2004/2005 የግዥ ዘመን አለም አቀፍ ጨረታ ሳይወጣ ግዥው የሚፈጸምበትን ሃገር፣ ኩባንያና የሚገዛበትን የገንዘብ መጠን አስቀድሞ በመወሰን ቴክኖ ትሬድስ ኤስ አር ኤል ከተባለ የጣሊያን ኩባንያ የ4 ሚሊየን 540 ሺህ ዩሮ ያገለገሉ ክሬኖች ግዥ በመፈጸም መንግስት ማግኘት ይችል የነበረውን የጥራትና የገንዘብ ጥቅም በማሳጣት የተጠረጠሩ፣

የትምህርት እድል አሰጣጥ ሜቴክ ከተቋሙ መመሪያ ውጭ ካሊፎርኒያ ኢንተርናሽናል ኢንስቲቲዩት ኦፍ ቴክኖሎጅ ከተባለና ህጋዊ መንገድ ለመቋቋሙ ተገቢው እውቅና ለማግኘቱ ካልተረጋገጠ ተቋምና ኢስተርን ሜዲትራንያን ዩኒቨርሲቲ ከተባለ የትምህርት ተቋም ጋር የ ፒ ኤች ዲ እና የማስተስር ትምህርት ከ60 በላይ ተማሪዎችን ለማስተማር ውል በመፈጸም ከአንድ ሚሊየን ዶላር በላይ ግልጽ ባልሆነ መንገድ ክፍያ ለተቋሙ እንዲከፈል በማድረግ የተጠረጠሩ፤

ከአዲስ አበባ ከተማ የስማርት መኪና ማቆሚያ ግንባታ ጋር በተያያዘ

የአዲስ አበባ ከተማ ትራንስፖርት ቢሮ መገናኛ እና መርካቶ አካባቢ በግል ድርጅት እንዳሰራው አይነት በከተማው ቸርችል ጎዳና አካባቢ ሶስተኛ ስማርት የመኪና መቆሚያ ለማሰራት ሲፈልግ የሜቴክ ሃላፊዎች የእኛ ተቋም ይሰራል በሚል ጠይቀው ከተፈቀደላቸው በኋላ ከመመሪያና ውል ውጭ ያለምንም ዋስትና የውሉን 70 በመቶ ቅድሚያ ክፍያ 24 ሚሊየን ብር ወስደው ስራውን ሳይሰሩና ስራውን ሮኬት ለተባለ የግል ድርጅት በንዑስ ተቋራጭነት በመስጠት ስራው ሳይሰራ ገንዘቡ ተበልቶ ቀርቷል፤ ገንዘቡ እንዲመለስ ወይም ስራው እንዲሰራ ሲጠየቅም የማስፈራራት ድርጊት ይፈጸማል በሚል እንደጠረጠራቸው ለችሎቱ በዝርዝር አስረድቷል።

ችሎቱም በቀረቡት አዳዲስ የወንጀል ግኝቶችና መርማሪ ፖሊስ በጠየቀው የ14 ቀን ተጨማሪ የማጣሪያ ጊዜ ላይ የግራ ቀኙን ለማከራከር ለነገ ታህሳስ 9 ቀን 2011 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።

በባሃሩ ይድነቃቸው

Happy
Happy
0 %
Sad
Sad
0 %
Excited
Excited
0 %
Sleepy
Sleepy
0 %
Angry
Angry
0 %
Surprise
Surprise
0 %
    Print       Email
  • Published: 6 years ago on December 24, 2018
  • By:
  • Last Modified: December 24, 2018 @ 9:52 am
  • Filed Under: Ethiopia

Average Rating

5 Star
0%
4 Star
0%
3 Star
0%
2 Star
0%
1 Star
0%
<"Without the support of our readers, the Maleda Times website would not exist in its present form">

You might also like...

በሰሜን ሸዋ ዞን ኤፍራታ እና ግድም ወረዳ መከላከያ ከአማራው ማህበረሰብ እና ከፋኖ ጋር ጦርነት ገጥሟል

Read More →

This site is protected by wp-copyrightpro.com

Skip to toolbar