በሽግግር ወቅቱ ከፍተኛ የመንግሥት ባለስልጣን በነበሩት በአንጋፋው የኦሮሞ ታጋይ ኦቦ ገላሳ ዲልቦ የሚመራው ኦነግ ሃገር ቤት እንዲገባ በተደረሰው ስምምነት መሰረት ነገ ታህሳስ 20 ቀን 2011 ዓ/ም ከጧቱ 2 ሰአት አዲስ አበባ ይገባሉ።
ጃል ገላሳ ዲልቦ ወደ ኢትዮጵያ የሚሄዱት ከ26 አመታት በኋላ ሲሆን፤ በተማሪዎች ትግል ወቅት “ማነው ኢትዮጵያዊ” በሚለው ግጥማቸው የሚታወቁት ኦቦ ኢብሳ ጉተማ፣ ፕሮፌሰር መኩሪያና ሌሎች 20 የሚሆኑ ልዑካን አብረው የሚመጡ ሲሆን በገልማ ኦዳ የኦሮሞ ባህል ማዕከል ከጥዋቱ 2 ሰአት ጀምሮ አቀባበል ይደረግላቸዋል።
አቶ ገላሳ ዲልቦ በ1983 ዓ/ም የሽግግር መንግስት ሲመሰረትና ቻርተሩ ሲፀድቅ ተሳታፊ የነበሩና በወቅቱ ከነበሩት የኦነግ አመራርና የፖለቲካ ቢሮ አባላት ከነበሩት ሌንጮ ለታ፣ ጣሃ አብዲ፣ ዶ/ር ታደሰ ኤባ፣ ዲማ ኖጎ፣ ዱጋሳ በከኮ፣ ቡሩይሶ ቦሩ፣ ነዲ ገመዳ፣ ጉተማ ሀዋስ፣ አቶምሳ ዲማ፣ ኩምሳ ገዳ፣ ቢያ ጀበል፣ ዳውድ ኢብሳ፣ አባጫላ ለታ፣ ቦባሳ ገዳ፣ ቁብሳ ሰባ፣ ቱጂ ረጋሳ፣ ደምሴ ከበደ፣ አባቢያ አባጆብር፣ ዘገዬ አስፋው፣ ኢብሳ ጉተማ፣ መኮንን ገላን፣ አቢዩ ገለታና አህመድ ሑሴን አንዱ ነበሩ።
አቶ ገላሳ በተለይ የሚታወቁት በ1984 ዓ/ም እሳቸው የመሩት የኦነግ አመራሮች ቡድን የአርሲና ባሌ አባ ገዳዎችና የሀገር ሽማግሌዎች የሰጡትን ምክር ሳይቀበል ቀርቷል በሚል ነው።
ጉዳዩ እንዲህ ነበር:
በ1984 ዓ.ም በኦቦ ገላሳ ዲልቦ የሚመራ ከፍተኛ የኦነግ አመራሮችን የያዘ ቡድን ወደ አርሲና ባሌ ይጓዛል፤ የጉዞው ዋና አላማም አባ ገዳዎችንና ታላላቅ የሀገር ሽማግሌዎችን ምክር ለመቀበል በሚል ነበር። የኦነግ አመራር “ከሽግግር መንግስቱ ልንወጣ አስበናል ኢህአዴግን ጫካ ገብተን ለመፋለም ቆርጠናል ምን ትመክሩናላችሁ?” ብለው ነበር ምክር የጠየቁት። ምክር የተጠየቁት አባገዳዎችና ሽማግሌዎችም የኦነግን አካሄድ በጥብቅ ተቃውመው በተለይም “ደርግን ደምስሶ በከፍተኛ የአሸናፊነት ስነ ልቦና ላይ ከሚገኘዉ የኢህአዴግ ሰራዊት ጋር መዋጋት አደገኛ ይሆናል” ብለው መከሩ።
የኦነግ አመራሮች ምክር ሊጠይቋቸው በሄዱት አባ ገዳዎችና ሽማግሌዎች ላይ አላግጠው አዲስ አበባ በመመለስ ብረት መወልወል ጀመሩ። ኦነግ በዚያው አመት ይካሄድ ከነበረው የቀበሌና የወረዳ ምርጫ ራሱን ማግለሉን አሳወቀ ትንሽ ሰንብቶም ከሽግግር መንግስቱ መውጣቱን አወጀ። በርካታ ወጣት ምሁራንን ጨምሮ ገበሬዎች የመንግስት ሰራተኞች የዩኒቨርስቲና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎች የኦሮሞ ነፃነት ሰራዊትን መቀላቀል ጀመሩ። ራሱን ለትጥቅ ትግል ያዘጋኘዉ ኦነግ በሌላ በኩል ደግሞ ለድርድር ከኢህአዴግ ጋር ተቀመጠ፤ አደራዳሪ ደግሞ ሻዕቢያ ሆነ…..በድርድሩና በድርድሩ አካሄድ ክህደት የተፈፀመበት ኦነግ ከፍተኛ ውድቀት ዉስጥ ገባ(ዝርዝሩ ይቅር)። ኦነግ ከፍተኛ ውድቀት ከደረሰበት በኋላ በአንዳንድ የኦሮሚያ ዞኖች መጠነኛ የደፈጣ ውጊያዎችን ማድረጉ አልቀረም፤ በእርግጥ ብዙ የሚወራለት አይነትና ብዙም ውጤታማ አልነበረም።
ኦነግ ከሽግግር መንግስቱ ከወጣባት እለት ጀምሮ የኦሮሞ ህዝብ አበሳ ተጠናክሮ ቀጠለ። ከወያኔ ግድያና እስር ያመለጡና ከሃገር እንዲወጡ መለስ ዜናዊ የፈቀደላቸው የግንባሩ አመራሮች ከሃገር ውጭ ሆነው ትግላቸውን ቀጠሉ።
በአብዛኛው የኦሮሞ ህዝብ ዘንድ ከፍተኛ ቦታ ያለው ኦነግ የደጋፊ ሃብታም ቢሆንም የአመራሩ ፖለቲካዊ አመራር ቁመናና ያለው ህዝባዊ ድጋፍ አይመጣጠንም የሚሉ በርካቶች ናቸው። እንደማስረጃ የሚጠቀሰውም አንድ የነበረውና ግዙፉ ኦነግ በአሁኑ ጊዜ ወደ አምስት ኦነግነት መቀየሩን ያነሳሉ። እነዚህም:
- በአቶ ዳውድ ኢብሳ የሚመራው ኦነግ፤
- በአቶ ገላሳ ዲልቦ የሚመራው ኦነግ፤
- የተወሃደ ኦነግ ተብሎ የሚጠራው፤
- የኦሮሚያ ነፃነት ግንባር በጄኔራል ከማል ገልቹ የሚመራ፤
- የኦሮሚያ ነፃነት ኃይልች አንድነት (ULFO) ናቸው።
እነዚህ አምስቱ ኦነጎች ተመሳሳይ የሆነ የትግል ስልት፣ ዓላማም ሆነ የመጨረሻ ግብ ያላቸው መሆኑ መከፋፈላቸው ከምን የሚመነጭ ነው የሚለውን ማወቅ አዳጋች ነው።
ከግንባሩ ቀደምት መስራቾችና አመራሮች መካከል እንደነ ሌንጮ ለታ፣ ዲማ ነጎ፣ በያን አሶባና ሌሎች የኦሮሞ ስመጥር ታጋዮች የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኦዴግ) የሚል አቋቁመዋል።
በአቶ ገላሳ ዲልቦ የሚመራው ኦነግ አመራሮች በጀርመን ፍራንክፈርት ከውጭ ጉዳይ ሚንስትር ወርቅነህ ገበየሁና፣ ከቀድሞው የኦህዴድና የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ፕሬዚዳንት ከነበሩት ከወቅቱ በጀርመን የኢትዮጵያ አምባሳደር ኩማ ሚደቅሳ ጋር የተወያዩ ሲሆን፤ በመርህ ደረጃ ስምምነት ላይ የደረሱና ቀጣይ ውይይታቸውን በሀገር ውስጥ ለማካሄድ መስማማታቸው ታውቋል።
Average Rating