በጠቅላይ ዐቃቤ ሀግ ከ1934-2010 ዓ.ም ድረስ ያሉትን የተጠቃለሉ ህጎች እና በፌዴራል ሰነዶች ማረጋገጫ ኤጀንሲ ኦንላይን አገልግሎት መስጠት የሚያስችል ሶፍትዌር ተመረቀ፡፡
ታህሳስ 19 ቀን 2011 ዓ.ም በጠቅላይ ዐቃቤ ህግ መሰብሰብያ አዳራሽ የተለያዩ የሚድያ አካላትና የሁለቱም ተቋማት ኃላፊዎች በተገኙበት በጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ከ1934 – 2010 ዓ.ም ያሉትን የተጠቃለሉ ህጎች፣ አዋጆች እና ደንቦች እንዲሁም የሰበር ሰሚ ውሳኔዎች ያካተተ በኦንላይንም (online) ሆነ በኦፍላይን (off line) የሚሰራ ሶፍትዌር ያስመረቀ ሲሆን የፌዴራል ሰነዶች ማረጋገጫ ኤጀንሲ አገልግሎቱን በቀላሉ ማከናወን የሚያስችል ሶፍትዌር አስመርቋል፡፡
ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ አቶ ብርሃኑ ጸጋዬ በተቋሙ የተሰራውን በኦንላይንም ሆነ በኦፍላይን መጠቀም ስለሚያስችለው ሶፍትዌር ማብራሪያ ሲሰጡ ካሁን ቀደም ህጎችን ለማግኘት አስቸጋሪ ከመሆኑም በላይ የተሻሩና በስራ ላይ ያሉትን በመለየት ወቅታዊ የሆኑ መረጃዎችን ተደራሽ ለማድረግ አዳጋች እንደነበር በመግለጽ ተቋሙ አሰራሩን በማዘመን ውጤታማና ጥራቱን የጠበቀ፣ ፈጣን የሆነ አገልግሎት፣ ማንኛውም የህብረተሰብ ክፍል ባለበት ቦታ ሆኖ መጠቀም የሚያስችል፣ ህብረተሰቡ ስለህግ ያለውን እውቀት የሚያሳድግበት፣ ህግ አውጪው የሚያወጣቸውን ህጎችና የሰበር ውሳኔዎችን በቀላሉና በጥራት ለማግኘት የሚያስችል የመረጃ ቋት መዘጋጀቱን በመጠቆም ይህ ተግባር ሀገራችን የተጀመረውን የለውጥ ጎዳና ለመደገፍ የሚያስችል መሆኑንም አውስተዋል፡፡
በመሆኑም http://fag.gov.et/laws/ የሚለውን ድረገጽ search በማድረግ የጠቅላይ ዐቃቤ ህግ የመረጃ ቋትን ማግኘት የሚቻል ሲሆን www.dara.gov.et የሚለውን ሊንክ search በማድረግ ደግሞ የሰነዶች ማረጋገጫን መረጃዎች ማግኘት እንደሚቻልም አብራርተዋል፡፡
በመቀጠልም የሰነዶች ማረጋገጫ ምዝገባ ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ መረሳ ገ/ዮሃንስ እንደገለጹት ተቋሙ የተሰጠው ሀላፊነት ሰነዶችን አረጋግጦ መመዝገብ እንደመሆኑ መጠን የዚህን አይነት አገልግሎት ለማግኘት የሚፈልጉ ተገልጋዮች አገልግሎቱን ለማግኘት በርካታ ውጣ ውረዶችን የሚያሳልፉ መሆኑን ገልጸው የተገልጋዬችን እንግልት ለመቀነስ በሚያስችል መልኩ አሰራርን ዘመናዊ በማድረግና ተገልጋዮች በኦንላይን (online) በቀላሉ በመሙላት መጠቀም የሚያስችል፣ ፈጣን፣ የመረጃ ደህንነትን የሚስጠብቅ፣ የስራ ጥራትን የሚጨምር፣ ሰነዶችን በቀላሉ ለማግኘት በሚያስችል መልኩ የተዘጋጀ ሶፍትዌር መሆኑን በመጠቆም ሁሉንም አይነት ውክልናዎች፣ የሚንቀሳቀሱና የማይንቀሳቀሱ ንብረቶች፣ የሽያጭ ውሎች፣ የስጦታ ውሎች፣ ውክልናን መሻሪያና ውልን ቀሪ ለማድረግ የሚያስችል ሶፍትዌር መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በመጨረሻም ጠቅላይ ዐቃቤ ህጉ እነዚህን ህጎች የሚፈልግ ማንኛውም አካል ያለምንም የኢንተርኔት አክሰስም ማግኘት ስለሚያስችል የፍትህ አካላትም ሆነ ከፍተኛ የትምርት ተቋማት እንዲሁም በህግ ዙሪያ ጥናት ለሚያደርጉ ሰፊ የመረጃ ምንጭ ሊሆን እንደሚችል አብራርተዋል፡፡ እንዲሁም በፌዴራል የሰነዶች ማረጋገጫና ምዝገባ ኤጀንሲ በኩል የተዘጋጀው ኦንላይን የሚሰራው ሶፍትዌር ተገልጋይ ጉዳዩን ባለበት አካባቢ ሆኖ ያለምንም ወጪ በቀላሉ የሚያስፈጽምበት በመሆኑ የተገልጋይን ጊዜና ገንዘብ በመቆጠብ ብሎም አላስፈላጊ መጭበርበርን በመቀነስ በኩል የጎላ ሚና እንዳለው ገልጸዋል፡፡
በጠቅላይ ዐቃቤ ሀግ ከ1934-2010 ዓ.ም ድረስ ያሉትን የተጠቃለሉ ህጎች እና በፌዴራል ሰነዶች ማረጋገጫ ኤጀንሲ ኦንላይን አገልግሎት መስጠት የሚያስችል ሶፍትዌር ተመረቀ፡፡
Read Time:1 Minute, 43 Second
- Published: 6 years ago on December 29, 2018
- By: maleda times
- Last Modified: December 29, 2018 @ 10:34 am
- Filed Under: Ethiopia
Average Rating