ፕሮጀክቱን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይፋ ያደርጉታል ተብሏል
በጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ጠንሳሽነት የአዲስ አበባ ከተማ ገጽታ በከፍተኛ ደረጃ ይለወጣል የተባለ ግዙፍ ፕሮጀክት ተነደፈ፡፡ ይህ 29 ቢሊዮን ብር ይፈጃል የተባለው ግዙፍ ፕሮጀክት፣ በቅርብ ይፋ እንደሚደረግ የሪፖርተር ምንጮች ገልጸዋል፡፡
ፕሮጀክቱ የአዲስ አበባ ከተማን ለሁለት ከፍለው የሚፈሱ ሁለት ወንዞች ላይ ያተኮረ ነው፡፡ በሰሜን አዲስ አበባ ከእንጦጦ ተራራ በሚነሱት ባንቺ ይቀጡና ቀበና ወንዞች ተፋሰስ ዳርና ዳር 52 ኪሎ ሜትር ርዝመትና በግምት አራት ሺሕ ሔክታር መሬት የሚለማበት ፕሮጀክት እንደሚሆን ታስቧል፡፡
በዚህ ፕሮጀክት ክልል ውስጥ 15 ሺሕ ቤቶች ይነሳሉ ተብሎ ዕቅድ የተያዘ ሲሆን፣ የሚነሱ ነዋሪዎች የተሻለ ኑሮ የሚያገኙበት ዕድል ከፕሮጀክቱ ጋር እየተጠና መሆኑን መረጃዎች አመልክተዋል፡፡
በፕሮጀክቱ ድልድዮች፣ ሰው ሠራሽ ሐይቆች፣ አረንጓዴ ቦታዎችና መዝናኛ ማዕከላት፣ የውኃ ትራንስፖርትና የንግድ ማዕከላት ሲገነቡ፣ ፕሮጀክቱ የከተማውን ገጽታ በከፍተኛ ደረጃ ከመለወጥ ባሻገር ለበርካታ ወጣቶች የሥራ ዕድል እንደሚፈጥር ምንጮች ገልጸዋል፡፡
ይህ ፕሮጀክት ከመታሰቡ በፊት ተመሳሳይ የሆነ ነገር ግን አነስተኛ መጠን ያለው ፕሮጀክት ስድስት ኪሎ ዩኒቨርሲቲ አካባቢ ከሚገኘው አፍንጮ በር፣ ሸራተን ማስፋፊያ አቅራቢያ እስከሚገኘው ኦርማ ጋራዥ ድረስ ያለውን የወንዝ ተፋሰስ ለማልማት የተነደፈ ፕሮጀክት ነበር፡፡
ግዙፍ ፕሮጀክት በመጠንሰሱ ይህ የአፍንጮ በር ኦርማ ጋራዥ ፕሮጀክት እንዲቆም መደረጉን ምንጮች ገልጸዋል፡፡ በአዲሱ ፕሮጀክት የሸራተን ማስፋፊያና ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አዲስ ሕንፃ ግንባታ ታስቦ የነበረውን ሥፍራ ለማካተት መታሰቡም ተገልጿል፡፡ በአሁኑ ወቅት በሸራተን ማስፋፊያ ቦታ ላይ የሚገኘው የፌዴራል ፖሊስ ጋራዥ እንዲፈርስ እየተደረገ ሲሆን፣ የሚድሮክ የተለያዩ ቢሮዎች ሳይፈርሱ ለፕሮጀክቱ እንዲያገለግሉ መወሰኑ ታውቋል፡፡
ከዚህ በተጨማሪ አራት ኪሎ የሚገኘው ታላቁ ቤተ መንግሥት ዋናው በር ፊት ለፊት የሚገኘው የቤተ መንግሥት ጋራዥ እንዲፈርስ ተወስኗል፡፡
በእርግጥ ይህ ቦታ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሕንፃ ግንባታ የተወሰነ ቢሆንም፣ ከተፋሰስ ልማቱ ጋር አንድ ላይ እንዲለማ ሐሳብ እየቀረበ መሆኑን ምንጮች ገልጸዋል፡፡
በአዲስ አበባ ከተማ ሰባት ዋና ዋና ወንዞችና 65 ገባሮች አሉ፡፡ ሁሉም ወንዞች ከመኖርያ ቤቶች፣ ከኩባንያዎችና ከፋብሪካዎች በሚወጡ ፈሳሽና ደረቅ ቆሻሻዎች ተበክለዋል፡፡
በፕሮጀክቱ አማካይነት ወንዞቹን ወደ ነበሩበት ይዞታ ለመመለስ የሚሠራ መሆኑንና ለነዋሪዎች ጥቅም በሚውሉበት ደረጃ ይለማሉ ተብሏል፡፡
Average Rating