በሜቴክ ላይ ከባድ የሙስና ወንጀል በመፈጸም የተጠረጠሩ ባልና ሚስት ተከሰሱ
በጥቅም በመመሳጠር የመንግሥትን ሥራ በማያመች አኳኋን በመምራት በመንግሥትና በሕዝብ ጥቅም ላይ ጉዳት በማድረስ፣ በከባድ የሙስና ወንጀል የተጠረጠሩት በብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን (ሜቴክ) እና በመከላከያ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ኃላፊ ነበሩ የተባሉ ባልና ሚስት ላይ ክስ ተመሠረተ፡፡
ክሱ የተመሠረተባቸው ተጠርጣሪዎች ከጥቅምት 30 ቀን 2011 ዓ.ም. ጀምሮ በተጠረጠሩበት ከባድ የሙስና ወንጀል በቁጥጥር ሥር ውለው በምርመራ ላይ ከሚገኙት በሜቴክ ከፍተኛ ኃላፊዎች ውስጥ አንዷ በነበሩት ሌተና ኮሎኔል ዙፋን በርሄ፣ እንዲሁም ባልተያዙትና በሜቴክ የኅብረት ማኑፋክቸሪንግና ማሽን ግንባታ ኢንዱስትሪ ዋና ሥራ አስኪያጅ በነበሩት ባለቤታቸው ሌተና ኮሎኔል ተሰማ ግደይ ናቸው፡፡ በወንጀል ድርጊቱ ተሳታፊ መሆናቸው የተገለጸውና በግል ሥራ ላይ የተሰማሩት ወ/ሮ ኬሪያ ዋስዕ የተባሉ ተጠርጣሪም በክሱ ተካተዋል፡፡
የፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ለፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 15ኛ ወንጀል ችሎት ያቀረበው ክስ እንደሚያስረዳው፣ ተከሳሾቹ የወንጀል ድርጊቱን ፈጽመዋል የተባለው የወንጀል ሕግ አንቀጽ 32 (1ሀ እና ለ) አንቀጽ 33፣ 37 እና የሙስና ወንጀሎች አዋጅ ቁጥር 881/2007 አንቀጽ 13 (1ሀ እና ሐ) እና (2) በመተላለፍ ነው፡፡
ተከሳሾቹ ከላይ የተጠቀሱትን የሕግ ድንጋጌዎች በመተላለፍ የሕዝብና የመንግሥትን ሥልጣንና ኃላፊነት ያላግባብ በመጠቀም፣ ያለ ምንም ጨረታና ዕውቅና ክሊንወሽ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር የተባለ ድርጀት ማቋቋማቸው፣ ይኼ ድርጅት የተቋቋመው በሜቴክ ሥር የሚገኘው ኅብረት ማኑፋክቸሪንግና ማሽን ግንባታ ኢንዱስትሪ ሠራተኞች ንፅህና መስጫ (ላውንደሪ) አገልግሎት ያስፈልጋል በማለት፣ በኢንዱስትሪው ዋና ሥራ አስኪያጅ ሌተና ኮሎኔል ተሰማ ግደይ የግል ፍላጎት መሆኑን ዓቃቤ ሕግ በክሱ ገልጿል፡፡
ኮሎኔሉ በግዥ መመርያው መሠረት ምንም ፍላጎት ሳይኖር በኢንዱስትሪው ውስጥ ላሉ ሠራተኞች የንፅህና አገልግሎት መስጫ እንዲገዛ ጥናት እንዲቀርብ ማስጠናታቸው በክሱ ተገልጿል፡፡ ባለሙያ ባደረገው ጥናት ኢንዱስትሪው የላውንደሪ ማሽኑን ገዝቶ አገልግሎቱን ቢሰጥ አዋጭ መሆኑንና በየሁለት ዓመቱ 991,522 ብር ጥቅም እንደሚያስገኝ፣ በቀጣይም ማሽኑ የኢንዱስትሪው ቋሚ ሀብት እንደሚሆንና የሥራ ዕድልም እንደሚፈጥር የሚያስረዳ ጥናት መቅረቡን ዓቃቤ ሕግ በክሱ ጠቅሷል፡፡ ነገር ግን የኢንዱስትሪው ዋና ሥራ አስኪያጅ ጥናቱን ውድቅ አድርገው ባለቤታቸው ሌተና ኮሎኔል ዙፋን፣ ጓደኛቸው ወ/ሮ ኬሪያንና ወንድማቸውን ባለድርሻ በማድረግ፣ ክሊንወሽ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር የተባለ ድርጅት ማቋቋማቸውን ዓቃቤ ሕግ ገልጿል፡፡ ሌሎች ድርጅቶች ሳይወዳደሩና የመወዳደሪያ ዋጋም ሳይቀርብ የመሥሪያ ቦታ፣ ኤሌክትሪክና ውኃ ኢንዱስትሪው እንዲያቀርብለት በማድረግና የድርጅቱን ማንነት የማያውቁ የኮሚቴ አባላት የውሳኔ ሐሳብ እንዲያቀርቡ ጫና በመፍጠር፣ ኮሎኔሉ ለሚመሩት የማኔጅመንት ኮሚቴ አቅርበው ማፅደቃቸውንም አክሏል፡፡ በጥናቱ ታሳቢ ከተደረገውና በውሉ ከተገለጸው የኢንዱስትሪ ማሽን አቅም በታች የሆነ የማጠቢያ ማሽን በማስቀረብና ያላግባብ ከድርጅቱ ጋር ውል በመፈጸም፣ ከጥቅምት ወር 2009 ዓ.ም. እስከ ጥቅምት ወር 2011 ዓ.ም. ድረስ 1,417,785 ብር ክፍያ መፈጸሙን ዓቃቤ ሕግ በክሱ አስፍሯል፡፡
ወ/ሮ ኬሪያ የተባሉት ተከሳሽ ክሊንወሽ የተባለው ድርጅት ምክትል ሥራ አስኪያጅ ሲሆኑ፣ ባልና ሚስት ናቸው የተባሉት ሌተና ኮሎኔሎች ጓደኛ መሆናቸውን፣ ድርጅቱን በዋናነት ያቋቋሙና በቃለ ጉባዔም የዋና ሥራ አስኪያጅነት ኃላፊነት የተሰጣቸው መሆኑንም ዓቃቤ ሕግ በክሱ ጠቁሟል፡፡ ሌተና ኮሎኔል ዙፋን በመከላከያ ዩኒቨርሲቲ ጤና ሳይንስ ኮሌጅ የሴቶች ጉዳይ ዴስክ ኃላፊ ሲሆኑ፣ ባለቤታቸው ኮሎኔል ተሰማ የኢንዱስትሪው ዋና ሥራ አስኪያጅ መሆናቸውን እያወቁ ድርጅቱ እንዲቋቋም 150,000 ብር ማዋጣታቸውንም አክሏል፡፡ በአጠቃላይ ያልተያዙት ተከሳሾችና ሌተና ኮሎኔል ዙፋን በጥቅም በመመሳጠር ሕዝብና መንግሥት የሰጣቸውን ኃላፊነት ወደ ጎን በመተው፣ የመንግሥትን ሥራ በማያመች አኳኋን በመምራት ጉዳት ማድረሳቸውን ዓቃቤ ሕግ ክሱ በዝርዝር አቅርቧል፡፡
ተከሳሾች የቀረበባቸው ክስ በችሎት ተነቦ በእስር ላይ የሚገኙት ሌተና ኮሎኔል ዙፋን ግልጽ መሆኑን ከተናገሩ በኋላ የእምነት ክህደት ቃላቸውን፣ ‹‹ድርጊቱን አልፈጸምኩም፣ ጥፋተኛም አይደለሁም›› በማለት ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ በመቀጠልም የዋስትና መብታቸው እንዲከበርላቸው ጠይቀዋል፡፡ ዓቃቤ ሕግ የተጠቀሰባቸው የወንጀል አንቀጽ ዋስትና እንደሚከለክል ገልጾ ተቃውሟል፡፡ ፍርድ ቤቱም ሕጉ ዋስትና እንደሚከለክል አረጋግጦ፣ ኮሎኔሏ ክርክራቸውን በማረሚያ ቤት ሆነው እንዲከታተሉ ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡ ያልተያዙት ተከሳሾችን የፌዴራል ፖሊስ አፈላልጎ እስከ ታኅሳስ 26 ቀን 2011 ዓ.ም. እንዲያቀርብ ትዕዛዝ በማስተላለፍ፣ የዓቃቤ ሕግ ምስክሮችን ለመስማት ለየካቲት 1 ቀን 2011 ዓ.ም. ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡
Average Rating