www.maledatimes.com የሃይማኖት መሪዎችና የአገር ሽማግሌዎች የአገሪቱ ሰላም ከምንጊዜውም በላይ አስጨንቆናል አሉ - MALEDA TIMES
Loading...
You are here:  Home  >  Ethiopia  >  Current Article

የሃይማኖት መሪዎችና የአገር ሽማግሌዎች የአገሪቱ ሰላም ከምንጊዜውም በላይ አስጨንቆናል አሉ

By   /   January 5, 2019  /   Comments Off on የሃይማኖት መሪዎችና የአገር ሽማግሌዎች የአገሪቱ ሰላም ከምንጊዜውም በላይ አስጨንቆናል አሉ

    Print       Email
0 0
Read Time:2 Minute, 41 Second

የሃይማኖት መሪዎችና የአገር ሽማግሌዎች የአገሪቱ ሰላም ከምንጊዜውም በላይ አስጨንቆናል አሉ
የሃይማኖት ተቋማት መሪዎችና የአገር ሽማግሌዎች

በኢትየጵያውያን ወንድማማቾች መካከል አለመከባበርና አለመተማመን የሚፈጥሩ ተጨባጭ ችግሮች እየታዩ ከመሆናቸውም ባለፈ፣ በአንዳንድ አካባቢዎች የእርስ በርስ ዕልቂት የሚያስከትሉ ግልጽ የወጡ ግጭቶች እየታዩ መሆኑንና ሁኔታው ከምንጊዜውም በላይ በአሁኑ ወቅት እያስጨነቃቸው እንደሆነ የሃይማኖት መሪዎችና የአገር ሽማግሌዎች ተናገሩ፡፡

የሃይማኖት መሪዎችና የአገር ሽማግሌዎች በአሁኑ ጊዜ በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች በተለይም በምዕራብና በምሥራቅ ኦሮሚያ፣ በጋምቤላ፣ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ በሶማሌ፣ በአፋር፣ በትግራይና በአማራ ክልሎች አዋሳኝ ቦታዎች እየተከሰቱ ያሉ ችግሮች አሳሳቢ መሆናቸውን አትኩረት ሰጥተው ተናግረዋል፡፡

 ሰባት የሃይማኖት ተቋማት አንድ የሆኑበት የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባዔና የአገር ሽማግሌዎች፣ ‹‹ሰላም ለሁላችን፣ በሁላችን›› በሚል መሪ ቃል ወደ ክልሎች በመሄድ ምክክር ማድረግ መጀመራቸውንና በየክልሉ ከሚገኙ ከፍተኛ አመራሮች ጋር በመገናኘት በወቅታዊ የአገሪቱ ችግሮችና መፍትሔዎች ላይ መመካከራቸውን ገልጸዋል፡፡ ‹‹ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የሚታየው ችግር በአንድነትና በሰላም ተስፋችን ላይ ሥጋት ፈጥሯል፡፡ የወገኖቻችን ጉዳይ በእጅጉ የሚያስጨንቅ ነው፡፡ በሁሉም አካባቢዎች በሚፈጠረው ግጭት የንፁሃን ደም በከንቱ እየፈሰሰ ነው፡፡ እናቶች በሐዘን ውስጥ ናቸው፡፡ በርካታ ወገኖችም በመፈናቀል ላይ ናቸው፡፡ የተፈናቀሉትም በርካታ ናቸው፡፡ ለከፋ ስቃይና እንግልትም እየተጋለጡ መሆኑ ሥጋታችንን ከፍ አድርጎታል፤›› ብለዋል በመግለጫቸው፡፡

የግጭቶች መነሻ ምክንያቶች ምንም ይሁኑ ምንም ቅድሚያ ለአገር፣ ለሰላምና ለሕዝቦች ደኅንነት በማሰብ በውይይት መፍታት ግድ እንደሚል የተናገሩት የጉባዔው አባላት፣ በየትኛውም አካባቢ የሚታይ የእርስ በርስ ግጭትና አለመረጋጋት በአፋጣኝ መቆም እንዳለበት ተማፅነዋል፡፡ የገዥው ፓርቲ አባል ድርጅቶች መሪዎች ብዙ የሥራ ጫና ቢኖርባቸውም፣ ኢትዮጵያን ሲያስተዳድሩ ግን በፍፁም ኢትዮጵያዊነት አስተሳሰብ በመገዛት፣ በመከባበር፣ በመደጋገፍና በመናበብ መሆን እንዳበት አሳስበዋል፡፡ የልዩነት ሐሳብ መኖሩ በራሱ ችግር ባይኖረውም፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የሚታዩ ምልክቶችና አዝማሚያዎች ግን ጤናማ አለመሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡ በመንግሥታት መካከል የሚታየው ልዩነት ወደ ሕዝቡ እየተጋባ፣ ሰውን በሰውነቱ ብቻ ተቀብሎና አክብሮ ይኖር የነበረው ኢትዮጵያዊ እሴት በከፍተኛ ደረጃ እየተሸረሸረ መሆኑንም አክለዋል፡፡

የአገሪቱ መሪዎች ቅድሚያ ለሕዝብ አንድነትና ደኅንነት ተጨንቀው በመካከላቸው የሚታየውን ልዩነትና ሽኩቻ ሊገቱ እንደሚገባም፣ የጉባዔው አባላትና የአገር ሽማግሌዎች በአጽንኦት ተናግረዋል፡፡ ተፎካካሪ የፖለቲካ ድርጅቶች አመራሮችም፣ የኢትዮጵያ ሰላምና አንድነት ተጠብቆ እንዲኖር፣ ሁሉን አቀፍ ይቅርታና ዕርቅ እንዲመጣ አገራዊ ኃላፊነታቸውን መወጣት እንዳለባቸውም አሳስበዋል፡፡

የሃይማኖት መሪዎቹና ሽማግሌዎቹ፣ የሕዝብም ሆኑ የግል መገናኛ ብዙኃን የሚያሠራጩትን ዘገባዎች፣ የፖለቲካ አመራሮች፣ ካድሬዎች፣ ምሁራንና ግለሰቦችም የሚያስተላልፉትን መልዕክት በጥንቃቄ መመልከት እንዳለባቸው ተናግረዋል፡፡ ምክንያቱም በተለያዩ ድረ ገጾች፣ በፌስቡክና በመገናኛ ብዙኃን የሚተላለፉት አላስፈላጊ መልዕክቶች ይዘታቸውና አቀራረባቸው አንድነትን የሚያናጉ፣ አደጋ ላይ የሚጥሉና ሕዝቡን የማይወክሉ መሆኑንም አክለዋል፡፡

የጉባዔው አባላት እንዳብራሩት፣ በምዕራብና በምሥራቅ ካለው አለመረጋጋት በተጨማሪ በደቡብ ክልል አንዳንድ አካባቢዎች ወሰን ተሻጋሪ የትራንስፖርት አገልግሎት መዘጋቱንና ዜጎች ከቦታ ቦታ መንቀሳቀስ እንዳልቻሉ ገልጸዋል፡፡ ይኼ በመሆኑም ምክንያት መድኃኒት፣ የምግብ ሸቀጣ ሸቀጦችና ሌሎች መገልገያዎች ቁሳቁሶች ነዋሪዎች እንዳያገኙ መደረጉንና ከፍተኛ ጫና እየደረሰ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡ መንገዶች በመዘጋታቸው ወላድ እናቶች፣ ጨቅላ ሕፃናት፣ ከፍተኛ ሕክምና ክትትል እያደረጉ የሚገኙ ሕሙማን ጭምር ከፍተኛ አደጋ ላይ በመሆናቸው፣ መንገዶቹ በፍጥነት እንዲከፈቱ አሳስበዋል፡፡ የፌዴራልና የክልል ሕግ አስከባሪዎች ኃላፊነታቸውን በጥንቃቄ እንዲወጡ ጠይቀዋል፡፡ ዘላቂና አስተማማኝ ሰላም እንዲኖር ሁሉም ኢትዮጵያዊ አንድ ሆኖና ተባብሮ መሥራት እንዳለበት፣ እንዲሁም ለሚቀጥሉት ሁለት ወራት የሚቆይ የፆም፣ የፀሎትና ምኅላ በማወጅ ሁሉም የኅብረተሰብ ክፍል እንደ ሃይማኖቱ ወደ ፈጣሪ እንዲለምን የሃይማኖት ተቋማት መሪዎችና የአገር ሽማግሌዎች አሳስበዋል፡፡

ከአገር ሽማግሌዎች አንዱ የሆነው ሻለቃ ኃይሌ ገብረ ሥላሴ፣ አዲስ አበባ ውስጥ መፈናቀል ስለሌለና በሰላም ስለተኖረ ሁሉም የአገሪቱ አካባቢዎች ሰላም ናቸው ማለት አይደለም ብሏል፡፡ ከ2.5 ሚሊዮን በላይ ወገኖች መፈናቀላቸውን ገልጾ፣ ይኼ ጉዳይ መንግሥትና ሕዝቡ ተረባርቦ አፋጣኝ ምላሽ ካልተሰጠው የማይመለስ አደጋ ሊያስከትል ይችላል የሚል ሥጋት እንዳለው ተናግሯል፡፡ የአገሪቱ ኢኮኖሚ በከፍተኛ አጣብቂኝ ውስጥ መግባቱን ጠቁሞ፣ እሱን የሚያሳስበው ነገሮች በዚሁ ከቀጠሉ ከስድስት ወራት በኋላ ወይም በሚቀጥለው ዓመት የኑሮ ውድነቱ እግጅ ከባድ እንደሚሆን ነው፡፡ በተያዘው በጀት ዓመት ጥሩ ሰብል የታየና የነበረ ቢሆንም፣ በተፈጠሩ አለመረጋጋቶች በአግባቡ መሰብሰብ እንዳልተቻለና ከፍተኛ ብክነት እየደረሰ መሆኑንም አስረድቷል፡፡ ጥጥ፣ ቡናና ሌሎች ሰብሎች ወቅቱን ጠብቀው የሚሰበስባቸው ባለመኖሩ እየረገፉና እየተበላሹ መሆናቸውንም አክሏል፡፡ ‹‹ውጊያ የሚገጥም ሳይሆን ጦርነትን የሚያስቀር ጀግና መንግሥት ያስፈልገናል፤›› ብሏል፡፡ 

Happy
Happy
0 %
Sad
Sad
0 %
Excited
Excited
0 %
Sleepy
Sleepy
0 %
Angry
Angry
0 %
Surprise
Surprise
0 %
    Print       Email
  • Published: 6 years ago on January 5, 2019
  • By:
  • Last Modified: January 5, 2019 @ 11:00 am
  • Filed Under: Ethiopia

Average Rating

5 Star
0%
4 Star
0%
3 Star
0%
2 Star
0%
1 Star
0%
<"Without the support of our readers, the Maleda Times website would not exist in its present form">

You might also like...

በሰሜን ሸዋ ዞን ኤፍራታ እና ግድም ወረዳ መከላከያ ከአማራው ማህበረሰብ እና ከፋኖ ጋር ጦርነት ገጥሟል

Read More →

This site is protected by wp-copyrightpro.com

Skip to toolbar