እሑድ ታኅሳስ 21 ቀን 2011 ዓ.ም. የሰባተኛ ዓመት ምሥረታ በዓሉንና ጠቅላላ ጉባዔውን ያከናወነው ሰማያዊ ፓርቲ ዜግነት ላይ አትኩሮት በማድረግ ለሚቋቋመው ፓርቲ ምሥረታ ይረዳ ዘንድ ራሱን በማክሰም፣ እንደ አዲስ ከሌሎች ፓርቲዎች ጋር ውህደት ለመፍጠር መወሰኑን አስታወቀ፡፡
የሰማያዊ ፓርቲ መክሰምን ውሳኔ አስመልክቶ ሰኞ ታኅሳስ 22 ቀን 2011 ዓ.ም. መግለጫ የሰጡት አመራሮቹ፣ አንድ ትልቅ አገራዊ ፓርቲ መፍጠር በማስፈለጉ ምክንያት መክሰሙን ይፋ አድርገዋል፡፡
ሰማያዊ ፓርቲ ላለፉት ሦስት ወራት ከአርበኞች ግንቦት ሰባት ለዴሞክራሲና አንድነት ንቅናቄ፣ ከኢትዮጵያውያን ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢዴፓ) እንዲሁም አቶ አንዱዓለም አራጌና አቶ ግርማ ሰይፉን ከመሳሰሉ የቀድሞ አንድነት ፓርቲ አባላት ጋር ውህደት ለመፍጠር ሲያደርጉት የነበረው ውይይት ተጠናቆ፣ ፓርቲዎች ማንነታቸውን በማክሰም በዜግነትና በማኅበራዊ ፍትሕ ላይ መሠረት ያደረገ ፓርቲ ለመመሥረት መወሰናቸው የሚታወስ ነው፡፡
ይህንን ስምምነት ተከትሎ ሰማያዊ ፓርቲ ራሱን በማክሰም አርዓያነት ማሳየት በመፈለጉ ውሳኔው መተላለፉን፣ የፓርቲው ምክትል ሊቀመንበር አቶ ጌታነህ ባልቻ ለሪፖርተር አስታውቀዋል፡፡
ጠቅላላ ጉባዔው ፓርቲውን አፍርሶ አዲሱን ፓርቲ ለመመሥረት ሥራ ለመጀመር ወስኗል ሲሉ አቶ ጌታነህ አክለው ገልጸዋል፡፡
አዲስ የሚቋቋመው ፓርቲ ከመጋቢት 30 ቀን 2011 ዓ.ም. በፊት ምሥረታውን በይፋ እንደሚያስታውቅ የገለጹት አቶ ጌታነህ፣ አሁን ያለው የብሔር ፖለቲካ እንደማያሠጋና የዜግነት ፖለቲካን በቀላሉ ሕዝቡ ውስጥ ማስረፅ ይቻላል ተብሎ እንደሚታመን ገልጸዋል፡፡
ከዚህ ቀደም ከመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ) ጋር በጋራ ለመሥራት ሰማያዊ ፓርቲ ንግግር ጀምሮ እንደነበር በማስታወስ አሁን የሁለቱ ፓርቲዎች በጋራ የመሥራት ጉዳይ ከምን ደረሰ በማለት ሪፖርተር ላቀረበላቸው ጥያቄ አቶ ጌታነህ ሲመልሱ፣ ‹‹እነሱ እንደ እኛ ቁርጠኛ መሆን አልቻሉም፡፡ እኛ አሁንም ቢሆን ፓርቲያችሁን አፍርሳችሁ ኑ ብለናል፡፡ ነገር ግን ፓርቲ ለማፍረስ ወገቤን አሉ፤›› ብለዋል፡፡
Average Rating