በኦሮሚያ ክልል በጉጂ ዞን የተለያየ አካባቢ እንዲሁም በደቡብ ክልል ጌዲኦ ዞንና በሃዋሳ በሲዳማና በወላይታ ብሔረሰብ መካከል ተፈጥረው የነበሩ ግጭቶችን በተመለከተ ምርመራ አከናውኖ ሪፖርት ያጠናቀረው የሰብአዊ መብቶች ጉባኤ (ሰመጉ)፤ በእነዚህ ግጭቶች በጠቅላላው 207 ሰዎች መገደላቸውንና አንድ ሚሊዮን ያህል ዜጎች መፈናቀላቸውን አረጋግጫለሁ ብሏል፡፡
በጌዲኦ ዞን ከሚያዚያ 25 ቀን 2010 እስከ ሚያዚያ 28 ቀን 2010 ዓ.ም በብሔር ተኮር ግጭት 8 ሰዎች መገደላቸውን የጠቆመው ሪፖርቱ፤ከእነዚህም አራቱ የአንድ ቤተሰብ አባላት ማለትም ባልና ሚስት ከሁለት ልጆቻቸው ጋር የተገደሉበት መሆኑን አመልክቷል፡፡ ሰመጉ በዚሁ በጌዲኦ ዞን በተለያዩ ወረዳዎች ማለትም በገደብ፣ በኮቸሬ፣ በ7/ጨሎ እና በወናሳ ወረዳዎች ተጨማሪ 74 ሰዎች መገደላቸውን የጌዲኦ ዞን ፖሊስ መምሪያን መረጃ ዋቢ አድርጎ በሪፖርቱ አጠናቅሯል፡፡
በምዕራብ ጉጂ ዞን በጉጂና በጌዲኦ ብሔረሰብ መካከል በተፈጠረው ግጭት ደግሞ ከሚያዚያ 3 ቀን 2010 እስከ ሚያዚያ 6 ቀን 2010 ዓ.ም ድረስ ባሉት ቀናት ብቻ 103 ሰዎች መገደላቸውን የምዕራብ ጉጂ ዞን አስተዳደር ጽ/ቤት መረጃን ዋቢ አድርጎ በሪፖርቱ አመላክቷል፡፡
በሃዋሳ ከተማ ከጨንበላላ በአል ጋር ተያይዞ ሰኔ 5 ቀን 2010 ዓ.ም በሲዳማ ብሔር ተወላጆች በአካባቢው በሚኖሩ የወላይታ ተወላጆች ላይ በተፈፀመ ጥቃት 22 ሰዎች የሞቱ ሲሆን ሁሉም ሟቾች ወንዶች መሆናቸው ተጠቁሟል፡፡ በእነዚህ ሶስት አካባቢ ግጭቶች ከ100 በላይ ሰዎች ለከፍተኛ የአካል ጉዳት መዳረጋቸውንና ከ8 መቶ ሺህ በላይ መፈናቀላቸውን፣ ከ20 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት የግለሰቦችና የመንግስት ንብረት መውደሙ በሪፖርቱ ተመልክቷል፡፡
በአጠቃላይ በዞኖቹ የተፈጠረውን ግጭትና የሰብአዊ መብት ጥሰት ለማስቆም የፌደራል፣ የክልል፣ የዞንና ወረዳ የመንግስት አካላትና የፀጥታ መዋቅሮች፣ ግጭቱን ለመከላከል በወቅቱ ያደረጉት ጥረት እንደሌለም ሰመጉ በሪፖርት ግኝቱ አመልክቷል፡፡ በአንዳንድ አካባቢዎች ደግሞ የአስተዳደር አካላትና የፀጥታ ኃይሎች በግጭቱ ላይ እጃቸው እንዳለበት ከተጎጂዎች መረዳቱን ያመለከተው ሰመጉ፤በእነዚህ አካላት ላይ እስካሁን የህግ ማስከበር ስራ እየተሰራ አይደለም ብሏል፡፡
በእነዚህ ግጭቶች ህገ ወጥ ግድያና የአካል ጉዳት ለደረሰባቸው ተጎጂ ቤተሰቦች ካሳ እንዲከፈል፣ አጥፊዎች ለህግ እንዲቀርቡ፣ መሰል ግጭቶችና ጥቃቶች እንዳይደገሙ ያሳሰበው ሰመጉ፤ ብሄር ተኮር ግጭቶችን የሚያነሳሱ ቅስቀሳዎችን በመከታተል፣ መንግስት አፋጣኝ እርምጃዎችን እንዲወስድ አስገንዝቧል፡፡
በጌዲኦ፣ አዋሣ እና በጉጂ አካባቢ ግጭቶች 207 ሰዎች ተገድለዋል
Read Time:1 Minute, 27 Second
- Published: 6 years ago on January 7, 2019
- By: maleda times
- Last Modified: January 7, 2019 @ 4:24 pm
- Filed Under: Ethiopia
Average Rating