www.maledatimes.com የአርቲስቱ ጠላቱ ቲያትር ቤቱ በጌታቸው ታረቀኝ - MALEDA TIMES
Loading...
You are here:  Home  >  Ethiopia  >  Current Article

የአርቲስቱ ጠላቱ ቲያትር ቤቱ በጌታቸው ታረቀኝ

By   /   January 7, 2019  /   Comments Off on የአርቲስቱ ጠላቱ ቲያትር ቤቱ በጌታቸው ታረቀኝ

    Print       Email
0 0
Read Time:7 Minute, 6 Second

የአርቲስቱ ጠላቱ ቲያትር ቤቱ

የ1966ቱ አብዮት የፈጠረዉ የባሕል ምኒስቴርም ሆነ አሁን ያለዉ የቲያትር ቤቶች አደረጃጀት፤ ለአርቲስቱም ሆነ ለጥበቡ ማደግ ያበረከቱት አስዋፅኦ ብዙም የሚባልለት አይመስለኝም፡፡ ቲያትር ቤቱ በአርቲስቱ የጥበብ ሥራ፤ ኪራይ ተቀባይ ከመሆን ያለፈ፤ የዉስጥ አሰራሩን አንኳ ብዙም መቀየር ያልቻለ ደካማ ተቋም በመሆኑ፤ የመድረክ መብራት፤ አርቲስቶች የሚቀባቡት /ሜክ አፕ/ ማቅረብ የማይችል፤ መብራት አምፑል ወይ መቆጣጣሪያዉ ጠፍቶ ቲያትር ለሳምንታት የሚቋረጥበት፤ አርቲስቶች የግድግዳ ቀለም ፊታቸዉን የሚቀቡበት፤ ለመድረክ የሚያስፈልጉ ቁሶች አርቲስቶቹ ራሳቸዉ ከቤት ከጎረቤት በዉሰት የሚያመጡለት በመሆኑ አሁን በአገራችን ከተጀመረዉ ለዉጥ አንፃር ዘላቂ መፍትሄ የሚፈልግ ጉዳይ ይመስለኛል፡፡

አርቲስቱም በስራዉ ምንም ያህል ቢደክምም በቂ ጥቅም የማያገኝ በመሆኑ ደክሞ ሰርቶ ዉበቱ፤ ጉልበቱ ሲደክም ለሕክምናዉ ለቀብሩ የመዋጮ ጥሪ የማይደረግለት በጣም ጥቂቱ ነዉ፡፡ በአጠቃላይ ደመወዝ ተብሎ የሚከፈለዉ ከሚያጠፋዉ ጉልበት ጋር ተመጣጣኝ ባለመሆኑ አብዛኛዎቹ ሌላ ተጨማሪ የሌሊት ወይ የሰንበት “ከተፋ” የሚሉት በየመጠጥ ቤቶች ገንዘብ ሊያስገኝ የሚችል ነገር የዉዴታ ግዴታ የሚገቡበትና፤ በአጠቃላይ በሙያዉ መግፋት ሳይችሉ ለቀለብ ለኪራይ ብቻ ሲሉ ብቻ በማይወዱት ፊልም/ማስታወቂያ መሳተፍ እና ሌላም ክብረ-ነክ ነገሮች ዉስጥ ገብተዉ ተሰናክለዉ የቀሩት ቁጥራቸዉ ቀላል አይደለም፡፡ በየቲያትር ቤቱ የሚመደቡት የስራ ሃላፊዎችም፤ ችሎታዉና ቅንነቱ ሳያንሳቸዉ፤አሁን ባለዉ የዉስጥ አሰራር ስርአት ብዙም ለዉጥ ያመጣሉ ብሎ መጠበቁም አግባብነት ያለዉ አይመስለኝም፡፡ ለአጭር ጊዜ የቲያትር ቤት ስራ አሰኪያጅ በነበርኩበት ወቅት፤ ትልቁ ፈተኛዬ ሰራተኛዉን በሰአቱ በመስሪያ ቤቱ ማግኘት ነበር፡፡

አብዛኛዉ በሰአቱ አይመጣም፤ በሳምንት ሁለት ቀን ብቻ ታይቶ የሚጠፋም ስለነበር፤ ይሄ “ትልቅ ስርአተ-አልበኝነት” የሚመስለዉን ነገር ለመረዳት ጥቂት ጊዜ ወስዶብኝ ነበር፡፡ እህል በልቶ፤ የቤት ኪራይ ከፍሎ፤ በመድረክ በቲቪ እንደሚታዩት አምረዉ ቆንጅተዉ ለመታየት ቲያትር ቤቱ የሚሰጣቸዉ ምንዳ ጭራሽ በቂ አንዳልንዳልነበረ ስረዳዉ ግን ብዙም የምለዉ አልነበረኝም፡፡ በዳንኪራ ላይ የሚሳተፈዉ፤ የትንፋሽ መሳርያ የሚነፋዉ፤ ከበሮ ለሰአታት ስልት ሳይስት የሚመታዉ፤ መድረክ ላይ በርካታ ገፆችን በቃሉ ሸምድዶ ለዛዉን ሳይስት አዳራሹ ጥግ ድረስ ቃና ባለዉ ድምፁ ከስሜት ቀላቅሎ የሚያወርደዉ፤ የመድረክ፤ የድምፅ ቴክኒሻኖቹ…የአብዛኛዉ ደመወዝ ስሙ የማይጠራ ነዉ፡፡

በምን ገንዘብ ምን ተመግቦ ነዉ ለሰአታት መድረክ ላይ ያንን ስራ ያቀረበዉ? ልብሱስ ጌጡስ ከየት ነዉ የሚገኘዉ?፤ ያሰኛል፡፡ ለአብዛኛዉ ለሙያዉ ፍቅር ሲል የሚከፍለዉን ትልቅ መስዋዕትነት ይሁን እንጂ የተቀረነዉ ደግሞ እነሱ ተቃጥለዉ የሚያበሩትን መብራት እየሞቅን ዝም ብሎ መመልከቱም እየቆየ ፈተና መሆኑ አይቀርም፡፡ …ተመልካች ዳንኪራዉን ወዶ “ይደግም!” ብሎ ሲል፤ የስራዉ መወደድ ቢያስደስትም፤ የሚንቆረቆዉን ላባቸዉን በፍጥነት ጠራርገዉ በድጋሚ የአማረ ፈገግታ ፊታቸዉ ላይ አስቀምጠዉ ወጥተዉ ሲጫወቱ መመልከቱ አሳዛኝ የሚሆንበትም ጊዜ ነበር፡፡

ብዙም ማድረግ የምችለዉ ስላልነበረ፤ ስራዉን ሲጀምሩ እንጂ፤ ሲጨርሱ በቦታዉ መገኘት አልፈልግም ነበር፡፡ ቀኑን ሙሉ አደባባይ መሐል ለተሰማራ አርቲስት የዉሎ አበል አራት ብር መክፈሉ፤ ለድምፃዉያን ለዳንኪረኞቹ፤ ለመላዉ የመድረኩ ተሳታፊዎች በአማካኝ መቶ ሃምሳ ብር (የአሁኑ ሁለት ሺ ብር ግድም?) ብዙም ያልዘለለ ደመወዝ ከፍሎ፤ በእነሱ ጉልበትና በስራቸዉ ዉበት መወደስ እየቆየ ህሊናን የሚነካ ነገር ነበር፡፡ ዘመን አልፎ ዘመን ሲተካም፤ ቲያትር ቤቱ ራሱን ከዘመን ቴክኖሎጂ ጋር ማስኬድ ያልቻለ ደካማ ተቋም በመሆኑ ዛሬም ድረስ የመድረክ ገፅ ለመሳል የሚፈሰዉ ቀለም እና ተገጣጥሞ የሚሰፋዉ ጣቃ አቡጀዴ ጨርቅ፤ ጣዉላ ምስማሩ… ለሌላ ጉዳይ መዋል ሲችል የአርቲስቱን ድካም ጨርሶ የሚበላ አክሳሪ ተግባር/ባህል ነዉ፡፡

ቲያትሮች ለወራት ታይተዉ ደራሲዉም አዘጋጁም ተዋናዩም ሌላዉም ምንም ክፍያ ሳያገኙ ያንን አቡጀዲ፤ ጣዉላና ቀለም ወዘተ. በመክፈል ብቻ የተጠናቀቁ ቲያትሮች ቁጥራቸዉ ጥቂት የሚባል አይደለም፡፡ ስማቸዉ በሬዲዮ በቲቪ ማስታወቂያ ከጠገብነዉ በኋላ ባዶ ኪሳቸዉን መሄዳቸዉን ማን ያዉቅላቸዋል? የመድረክ ኪራይ ከፍለዉ ቲያትር የሚያሳዩትም ደፋሮች፤ ከመግቢያዉ ክፍያ እና ሌሎች ተዛማጅ ጉዳዮች ጋር በተየያያዘ ሁኔታ፤ አዳራሹ ግጥም ብሎ ካልሞላ በስተቀር ተጠቃሚዎች አይሆኑም፡፡ የመድረክ ገፅ ድባብ ለመፍጠርም ሆነ በፍጥነት ለመቀያየር ትንሽ ፕሮጀክተር ገዝቶ በመጠቀም፤ ወጪን እና የሰዉ ጉልበትን ለመቀነስ እንኳ ቲያትር ቤቱ ተነሳሽነትም ሆነ የሚያስገድደዉም አንዳችም ነገር የለዉም፡፡

ከአልባሌዉ ወጪ ቀሪ፤ ትርፍ ካለም ገሚሱ ወደ መንግስት ካዝና ይገባል፡፡ ካልሆነም የሙሉ ኪሳራዉ ከፋይ አርቲስቱ ነዉ፡፡ በአዲስ አበባ ከተማ ብቻ፤ እንደ ከተማዉ መስፋትና እንደ ነዋሪዉ ህዝብ መብዛት፤ ተጨማሪ ቲያትር ቤቶች ባለመፈጠራቸዉ፤ ወደ መድረክ በሚመጡት ስራዎች ብዛትና አሁን ያሉት ቲያትር ቤቶች ተቀብለዉ ሊያስተናግዱት በሚችሉት የፈጠራ ስራ ቁጥር ዉስንነት የተነሳ፤ ብዙ የበቁም ሆነ፤ ጀማሪ አርቲስቶች ስራቸዉን ለህዝብ ማሳየት አለመቻላቸዉ በእጅጉ የሚያሳዝን ጉዳይ ነዉ፡፡

አቅርቦት፤ ፍላጎት እና አቅም ሳይመጣጠን ሲቀርም ለማያስፈልግ ሐሜታና ቁርሾ፤ አድልኦ እና ሙስናም እንደሚያጋልጥ የታወቀ ነዉ፡፡ በቅርቡ አንድ ያስተዋልኩት ነገር ቢኖር፤ ቤተ-ክርስቲያኖች የራሳቸዉን ህንፃዎች እየሰሩ በማከራየታቸዉ፤ ከምዕመናን መዋጮ ማነስ፤ የጧፍ መብራት ወይ ቀለብ ፍለጋ ግማሽ ቀን ዱቄት/ምግብ ልመና የሚሰማሩት ቀሳዉስት እና ሌሎች አገልጋዮች፤ አሁን በኪራይ ገንዘቡ ራሳቸዉን እያስተዳደሩ ሙሉዉን ጊዜአቸዉን በመንፈሳዊ ትምህርቱ ጥራት ላይ ለማተኮር እና ለምዕመናንም በቂ መንፈሳዊ አገልግሎት ለመስጠት ጥሩ አጋጣሚ የተፈጠረላቸዉ ይመስለኛል፡፡

ቲያትር ቤቶችም በመንግስት፤ በበጎ አድራጊ ግለሰቦች፤ የደመወዝ፤ የስራ ማስኬጃ እና ሌላም ድጎማ እየተደረገላቸዉ፤ የገቢዉ ሙሉ በሙሉ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ካልተደረገ በስተቀር፤ በአርቲስቱ የግል ህይወትም ሆነ በጥበቡ ማደግ ላይ ለዉጥ ይመጣል የሚል እምነት የለኝም፡፡ አርቲስቱ ለጥበብ ባለዉ ፍቅር ምርጫዉ በመኖርና ባለመኖር፤ በመለመን እና ባለመለመን፤ ሰክሮ በማደር እና ባለመስከር መሐል መሆን የለበትም፡፡

በአጭሩ፤ ቲያትር ቤቶቹ ማህበራት መሆን ይኖርባቸዋል፡፡ /የአገር ፍቅር ማህበርም፤ የብሔራዊ ቲያትር ህንፃ ያለበትም የሱቆቹ ኪራይ የአርቲስቶቹ ነበር፤ዱሮ ሲጀመር/ አርቲስቶች በማሕበር አዳዲስ ቲያትር ቤቶችን ከከተሞች የልማት ካርታ ጋር በተያያዘ መልኩ መገንባት እንዲችሉ በቂ ድጋፍ መደረግ ይኖርበታል፡፡ ከከተማዉ ሰፍቶ፤ በክፍለ-ከተማ ሲከፋፈል ከሃምሳ አመት በፊት የተገነቡ ቲያትር ቤቶች የአርቲስቱንም የሕዝቡንም ፍላጎት በብቃት ያሟላሉ ብሎ የሚያስብ እንደማይኖር እርግጠኛ ነኝ፡፡ የቲያትር ቤቶች ግንባታ ከህዝብ ቁጥር ማደግ እና ከሚሰበሰበዉ ግብር ጋር መያያዝም ይኖርበታል፡፡ ጭራሽ እንደሌላዉ “ቢዝነስ” ለግል ባለሃብቶች የሚተዉ ስራ አይደለም፡፡ አሁን በምኖርበት አገር ያስተዋልኩት አንድ ነገር፤ ከተማዉ ሰፍቶ የእሳት አደጋ እና የፖሊስ ጥሪ አገልግሎት ከሚፈለገዉ ፍጥነት ጋር ሳይጣጣም ሲቀር፤ ዳሩ አገር አዲስ ከተማ ይሆንና ምክር ቤቱ ሲፈጠር ከራሱ የእሳት አደጋና የፖሊስ ጣቢያዎች በተጨማሪ፤ የባህል ማዕከል/ቲያትር ቤቶችም አብረዉ ለነዋሪዉ ቅርበት ለመፍጠር በአዲሱ ከተማ መዋቅር ዉስጥ ይካተታሉ፡፡

በከተማዉ የሚሰበሰበዉ ግብርም ሆነ የሙኒሲፓል ቦንድ ሽያጭም ሲታቀድ ይሄንኑ ግብ መሰረት በማድረግ ነዉ፡፡ ይህ አይነቱን አሰራር ጥበብና አርቲስቱን ወደ ህዝቡ የበለጠ ስለሚያቀርበዉ የመፍትሄ ሃሳብ ከሚያመነጩት ጋር በእኩል ያስቀምጠዋል፡፡ በእኛ አገር፤ የጥበብ ጥራት መቀነስ በተነሳ ቁጥር ከሚቀርቡት ምክንያቶች አንዱ፤ በሃያ አርቲስቶች መሰራት ያለበትን የጥብብ ስራ በሶስት ሰዉ ለማቅረብ መሞከሩና፤ ገንዘቡን ለማግኘት የማያስፈልግ “ቧልት” ከቁምነገሩ ጋር መቀላቀሉ፤ ባጠቃላይ /ሾርት ከት መፈለጉ/ ዋናዎቹ ተጠቃሾች ቢሆኑም፤ ይሄንን የፈጠረዉ የአርቲስቱ አለማወቅ አለመማር ሳይሆን፤ ሲወርድ ስዋረድ የመጣዉ የቲያትር ቤቶች የአሰራር መዋቅር መሆኑ ለማንም አይጠፋዉም፡፡ ኪሳራዉ ግን የአርቲስቶቹ ብቻ ሳይሆን የመላዉ ማህበረሰብ፤ የእኔም የእናንተም ጭምር ነዉ፡፡ የት እንዳነበብኩት ጠፋኝ እንጂ፤ “ጥሩ ጥበብ የማይቀርብበት ማህበረሰብ ጥሩነት አይኖረዉም!” ይባላል፡፡

ዛሬ ቲያትር ቤቶቹ የሚያስፈልጋቸዉ የመድረክ መብራት፤ አልባሳት፤ ሜክ አፕ፤ ወዘተ ብዙ በየኤምባሲዉ እያዞረ የሚያስለምን ወጪ ሳይሆን፤ የጥበብ ወዳጆች፤ ጥቂት በጎ-አድራጊዎች በሚያደርጉት ትንሽ መዋጮ የሚፈታ በጣም ትንሽ ችግር ነዉ፡፡ (ለአንዱ ቲያትር ቤት ከ 3000 ዶላር በማይበልጥ ወጪ ብዙዉ ችግር ይቃለላል) ይሄንን ወጪ አንድም ሰዉ ሊሸፍነዉ የሚችለዉ ይሁን እንጂ፤ ቀጣይነት እንዲኖረዉና ሌሎችንም በማሳተፍ፤ የጥበብ ጠባቂ ማህበር አባላት ለማድረግ፤ የስራዉ ተጠቃሚ አርቲስቶቹ መሆናቸዉ መረጋገጥ ይኖርበታል፡፡ አንድ አርቲስት ቢበዛ ሰላሳ አምስት አመት ድረስ የተፈጥሮ ለዛና ዉበቱ ገንዘብ ይሆነዋል፤ እድሜዉ ከሰላሳ ሲያልፍ መድረኩን ለሌሎች “ወጣቶች” ቀስ እያለ መልቀቅ ይኖርበታል፤ ጉልቱም ይደክማል፤ “ይደገም” የሚለዉ የተመልካች አድናቆት ከደስታነት ወደ ቁርጥማት ይቀየራል፡፡

በምን አቅሙ ምን በልቶ ድምፁስ አዳራሽ ጥግ ድረስ ይደርሳል?…የማስታወስ ችሎታም ከእድሜ ጋር ይቀንሳል፤ እናም ይሄ ሰዉ ወድቆ መቅረት የለበትም፡፡ በግድ ወደ እማያዉቀዉ ቅስና መግባትም አይኖርበትም፡፡ የመድረክ ስራዉ ሲጠናቀቅ ሁሉም በጊዜ እቤቱ ስለሚገባ፤ ለልጅም ለትዳር ጓደኛም ጊዜ ይኖራል፡፡ በተደረገበት ስዉር ጫና የተነሳ ከራሱ ለመሸሽ በየቀኑ በአልኮል መጠጥ ራሱን የሚጎዳና፤ ራሱን የሚጥል፤ መታከሚያ የሚለመንለት አርቲስትም የማይታይበት ዘመን ይመጣል፡፡

መልካም ስብእና ያለዉ ማህበሰብ ለመፍጠር አርቲስቱ ራሱ የመልካምነት ሞዴል መሆንም ያኔ አይገደዉም፡፡ መቼም ሁሉንም ነገር ከፈረንጅ መዉሰድ አስፈላጊ ባይሆንም፤ እዚህ በምኖርበት አገር ባለች አንዲት ቲያትር ቤት፤ አርቲስቱ የስራዉ ባለቤት መሆኑን ነዉ የተረዳሁት፡፡ የከተማዉ ምክርቤት መሰረታዊ የሆነዉን የቤት ኪራይ፤ ስራ ማስኬጃ እና ሌላም በጀት ይመድብላቸዋል፤ በጎ-አድራጊዎች በመዋጮ ይረዳሉ፤ ሃብታሞች ንብረታቸዉን ለማህበሩ በዉርስ ጭምር ይሰጣሉ፤ አርቲስቶቹም ስራቸዉን ሰርተዉ በተለያየ መድረክ ላይ ያቀርቡታል፡፡ ቋሚ መዋጮ የሚከፍሉ አባላት ሁሌም ከፊት በተያዘላቸዉ ቦታ በነፃ ገብተዉ የሚታየዉን ሁሉ ይመለከታሉ፡፡ አመቱ ሲጀመር አቅምና ጉልበት ተለክቶ ስንት ስራ በአመት ዉስጥ እንደሚቀርብ በቅድሚያ ስለሚነገርም የአመት ትኬት ለገበያ ቀርቦ በቅድሚያ ይሸጣል፡፡ ሌላዉም የተመቸዉን ብቻ በእለቱ ባለዉ ክፍት ወንበር፤ ከፍሎ ገብቶ ይመለከታል…ገንዘቡም የማሕበራቸዉ ነዉ፡፡ ጥቂት ያነጋገርኳቸዉም ሰዎች በቀን ሶስት ቲያትር የመስራት ጫና አላስተዋልኩባቸዉም፡፡

በጣም ሃብታም ባይባሉም፤ ጭራሽ “ከተፋ” የሚያስገባ አስገዳጅ ነገር ያለባቸዉ አይመስሉም፡፡ “የባሕል ምኒስቴር” የሚባልም የላቸዉ፡፡ ባሕል አጠቃላይ የሰዎች እንቅስቃሴ ጋር ተያይዞ፤ ጎጂ የተባለዉ ልማድ በመልካም እየተቀየረ፤ ስልጡን የሚረዳዳ የሚተሳሰብ፤ መልካሙን ምግባር የሚለዋወጥ ተደጋጋፊ ማህበረሰብ የሚፈጥረዉ ወግ እና ልማድ በመሆኑ እና፤ አጥር ተደርጎበት በፖሊሲ የሚተዳደር ነገር ባለመሆኑ ይመስላል ምኒስቴር የሌለዉ፡፡

ለነገሩ እኛም “ባሕል” ብለን የምንለዉ መልካምነትና መተሳሰብም፤ ከዉጭ ተፅእኖ ሙሉ በሙሉ ነፃ ይሆናል ባይባልም፤ ለአርቲስቶች ተገቢዉን ድጋፍ በማድረግ፤ ኢትዮጵያዊ የሚያደርገንን ነገር ጨርሰን እንዳናጣዉና ለልጆቻችን የምናሳልፈዉ መንፈሳዊ/ማህበራዊ ሃብት እንዲናኙልን በምንችለዉ መርዳት ይገባናል፡፡ ባሕልን የሚጠብቅ የምኒስቴር መስሪያ ቤት ካለም፤ ግቡ አርቲስቱን ነፃ ከማዉጣት የተለየ ሌላ ግብ ሊኖረዉ የሚችል አይመስለኝም፡፡ ባለፉት ስርአቶች፤ ቲያትር ቤቶች እንደ ራዲዮዉና ቲቪዉ፤ የፕሮፓጋንዳ ማሰራጫ ቦታዎች ስለነበሩና የህዝብ የመነጋገሪያ ሃሳቦችን ገድቦ መያዣ መሳሪያ ሆነዉ ሰለነበር፤ ይህ አይነቱ ሃሳብ ከመንግስት ግልበጣ ዱለታ አንፃር ቢታይ አይደንቅም ነበር፡፡ (ደራሲ በዓሉ ግርማ የተለየ ሃሳብ ይዞ በመገኘቱ ነበር ወንጀለኛ ሆኖ ያለፍርድ የተገደለዉ፡፡) ይሁን እንጂ፤ ዛሬ ምስጋና ለቴክኖሎጂ/ ለሶሻል ሚዲያዉ፤ ሰዎች በአካልም በርቀትም ተገናኝተ

ተገናኝተዉ ሃሳብ የሚለዋወጡበት መድረኮች በጣም ብዙ ስለሆኑ፤ የትኛዉም መንግስት ቲያትር ቤቶችን ሰቅዞ ስለያዘና የራሱን “አርቲስቶች” ብቻ መድረክ በመስጠት፤ የፕሮፓጋንዳዉን የበላይነት /ናሬቲቭ/ መቆጣጠርና የሃሳብ ልዉወጡን ለመገደብ የሚችልበት ዘመን ያበቃ ይመስላል፡፡

በተለይ አሁን በመንግስት የተያዘዉ የለዉጥ ሂደት፤ ቲያትር ቤቶችንም በጥልቀት በመዳሰስ፤ ጥብቡም አርቲስቶቹንም እስከዛሬ ለደረሰባቸዉ በደል ካሣ ሰጥቶ፤ ራሳቸዉን በማህበር እያደራጁ፤ ከከተማዉ ህዝብ ቁጥር ብዛትና ተደራሽነት አንፃር አዳዲስ ቲያትር ቤቶችን እንዲገነቡና በከተማ/ ክፍለ-ከተማ ምክር ቤቶቹ ጋር በማቆራኘት፤ የበጀት ድጎማዉን እያገኙ በስራቸዉ ነፃ ሆነዉ፤ ተጠቃሚ የሚሆኑበትና ጥበብንም ወደ ባለቤቱ ለመመለስ ፈጣን አማራጭ ቢፈለግ ለዉጡን የበለጠ ህዝባዊ ያደርገዋል፡፡ ጌታቸዉ ታረቀኝ ከባሕር ማዶ

Happy
Happy
0 %
Sad
Sad
0 %
Excited
Excited
0 %
Sleepy
Sleepy
0 %
Angry
Angry
0 %
Surprise
Surprise
0 %
    Print       Email
  • Published: 6 years ago on January 7, 2019
  • By:
  • Last Modified: January 26, 2019 @ 10:55 am
  • Filed Under: Ethiopia

Average Rating

5 Star
0%
4 Star
0%
3 Star
0%
2 Star
0%
1 Star
0%
<"Without the support of our readers, the Maleda Times website would not exist in its present form">

You might also like...

በሰሜን ሸዋ ዞን ኤፍራታ እና ግድም ወረዳ መከላከያ ከአማራው ማህበረሰብ እና ከፋኖ ጋር ጦርነት ገጥሟል

Read More →

This site is protected by wp-copyrightpro.com

Skip to toolbar